በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ነቅታችሁ ኑሩ፣ በድፍረት ወደፊት ግፉ!

ነቅታችሁ ኑሩ፣ በድፍረት ወደፊት ግፉ!

ነቅታችሁ ኑሩ፣ በድፍረት ወደፊት ግፉ!

ልዩ የሆኑ ስብሰባዎችን በተመለከተ የቀረበ ሪፖርት

‘በሚያስጨንቅ ዘመን’ ውስጥ እንደምንኖር ማን ሊክድ ይችላል? የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችን “በመጨረሻው ቀን” ውስጥ መኖር ከሚያስከትላቸው ጫናዎች ነፃ አያደርገንም። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) ሆኖም ሰዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እንገነዘባለን። በዓለም ላይ የሚታዩ ክስተቶች ምን ትርጉም እንዳላቸው አያውቁም። ማጽናኛና ተስፋ ያስፈልጋቸዋል። ሰዎችን በመርዳት ረገድ ያለብን ዋነኛ ኃላፊነት ምንድን ነው?

ስለ ተቋቋመው የአምላክ መንግሥት ምሥራቹን የማካፈል ከአምላክ የተሰጠ ተልዕኮ ተቀብለናል። (ማቴዎስ 24:​14) የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ ይህ ሰማያዊ መንግሥት መሆኑን ሰዎች ማወቅ አለባቸው። ሆኖም መልእክታችን ሁልጊዜ ጥሩ ምላሽ ያገኛል ማለት አይደለም። በአንዳንድ አገሮች ሥራችን የታገደ ከመሆኑም በላይ ወንድሞቻችን ይሰደዳሉ። ይሁን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም። በይሖዋ ላይ ሙሉ ትምክህት በመጣል ምሥራቹን ያለማሰለስ በማወጅ ነቅተን ለመኖርና በድፍረት ወደፊት መግፋታችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።​—⁠ሥራ 5:​42

ይህ ቁርጥ ውሳኔ ጥቅምት 2001 በተካሄዱ ልዩ ስብሰባዎች ላይ በግልጽ ታይቷል። ቅዳሜ፣ ጥቅምት 6 የፔንሲልቬንያ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ዓመታዊ ስብሰባ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በጀርሲ ሲቲ ኒው ጀርሲ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዶ ነበር። a በቀጣዩ ቀን በአራት ቦታዎች ላይ ይኸውም ሦስት በዩናይትድ ስቴትስ አንድ ደግሞ በካናዳ ተጨማሪ ስብሰባዎች ተካሂደው ነበር። b

የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነው የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር ሳሙኤል ኤፍ ኸርድ ዓመታዊው ስብሰባ ላይ ባቀረበው የመክፈቻ ንግግር መዝሙር 92:​1, 4ን ጠቅሶ “አመስጋኝ መሆን እንፈልጋለን” ሲል ተናገረ። በእርግጥም ከዓለም ዙሪያ የተገኙ አምስት ሪፖርቶች አመስጋኝ የምንሆንባቸውን ምክንያቶች አሳይተዋል።

ከዓለም ዙሪያ የተገኙ ሪፖርቶች

ወንድም አልፍሬድ ክዋቺ ቀድሞ የወርቅ ጠረፍ ተብላ በምትጠራው በጋና የስብከቱ ሥራ ስላሳየው እድገት በማስመልከት ሪፖርት አቅርቧል። በዚህች አገር ሥራችን ለበርካታ ዓመታት ታግዶ ነበር። ሰዎች “ሥራችሁ የታገደው ለምንድን ነው? ምን አደረጋችሁ?” እያሉ ይጠይቁን ነበር። ይህም ምሥክርነቱን ለመስጠት የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍትልን ነበር ሲል ወንድም ክዋቺ ተናገረ። እገዳው በ1991 ሲነሳ በጋና 34, 421 የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። በነሐሴ 2001 አጠቃላይ ቁጥሩ 68, 152 የደረሰ ሲሆን ይህም 98 በመቶ ጭማሪ መሆኑ ነው። አሥር ሺህ መቀመጫዎች ያሉት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለመሥራት የተያዘው ዕቅድ በሂደት ላይ ይገኛል። በጋና የሚኖሩ መንፈሳዊ ወንድሞቻችን ሃይማኖታዊ ነፃነታቸውን በተሻለ መንገድ እየተጠቀሙበት እንዳለ ግልጽ ነው።

በአየርላንድ የፖለቲካ አለመረጋጋት ቢኖርም እንኳ ወንድሞቻችን በአገልግሎት በትጋት እየተካፈሉ ሲሆን ገለልተኛ አቋማቸውም አክብሮት አትርፎላቸዋል። የቅርንጫፍ ኮሚቴ ሰብሳቢው ፒተር አንድሪውስ አየርላንድ በ6 ወረዳዎች የተከፋፈሉ 115 ጉባኤዎች እንዳሏት ተናግሯል። ወንድም አንድሪውስ ትምህርት ቤት ውስጥ በመመስከር ረገድ ደፋር የሆነውን የአሥር ዓመቱን የሊዓምን ተሞክሮ ተናገረ። ሊዓም የይሖዋ ምሥክሮች ያዘጋጁትን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ 25 ለሚሆኑ የክፍሉ ተማሪዎችና ለአስተማሪው አበረከተላቸው። ሊዓም መጠመቅ እንደሚፈልግ ሲናገር አንድ ሰው ገና ልጅ መሆኑን ገለጸለት። ሊዓም “ወሳኙ ነገር ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር እንጂ ዕድሜዬ አይደለም” ሲል መለሰለት። “መጠመቄ ይሖዋን ምን ያህል እንደምወደው ያሳያል።” ሊዓም ሚስዮናዊ የመሆን ግብ አለው።

በ1968 ቬኔዙዌላ 5, 400 የምሥራቹ አስፋፊዎች ነበሯት። አሁን ግን ከ88, 000 በላይ አስፋፊዎች መኖራቸውን የቅርንጫፍ ኮሚቴ ሰብሳቢው ስቴፋን ጆሐንሰን ገለጸ። እንዲሁም በ2001 የመታሰቢያው በዓል ላይ ከ296, 000 በላይ ሰዎች የተገኙ መሆኑ ከፍተኛ እድገት ሊኖር እንደሚችል ይጠቁማል። በታኅሣሥ 1999 የጣለው ከባድ ዝናብ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ በግምት 50, 000 የሚያህሉ ሰዎችን ለሞት የዳረገ የጭቃ ጎርፍ አስከትሎ ነበር። አንድ የመንግሥት አዳራሽ በጭቃ ከመሞላቱ የተነሳ ኮርኒሱን ሊነካ የቀረው ግማሽ ሜትር ብቻ ነበር። አንድ ሰው ያለው አማራጭ አዳራሹን ጥሎ መሄድ መሆኑን ሲናገር ወንድሞች “ይህማ የማይሆን ነገር ነው! የመንግሥት አዳራሻችን እስከሆነ ድረስ በዚህ ጊዜ ጥለነው መሄድ አንፈልግም” ሲሉ መለሱ። ብዙ ቶን የሚመዝን ጭቃ፣ ድንጋይና ሌሎች ፍርስራሾችን ጠርገው በማውጣት የመንግሥት አዳራሹን መጠገን ጀመሩ። ሕንፃው በአዲስ መልክ የተገነባ ሲሆን ወንድሞች አደጋው ከመድረሱ በፊት ከነበረው ይልቅ አሁን ይበልጥ ማራኪ እንደሆነ ተናግረዋል!

የቅርንጫፍ ኮሚቴ ሰብሳቢው ወንድም ዴንተን ሆፕኪንሰን ፊሊፒንስ ውስጥ 87 ቋንቋዎችና ቀበሌኛዎች እንዳሉ ተናገረ። ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ሙሉው የቅዱሳን ጽሑፎች የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ሴብዋኖ፣ ኢሎኮ እና ታጋሎግ በሚባሉ የአገሪቱ ሦስት ዋና ዋና ቋንቋዎች ተተርጉሞ ወጥቷል። ወንድም ሆፕኪንሰን የይሖዋ ምሥክሮች ያዘጋጁትን ጉድ ኒውስ​—⁠ቱ ሜክ ዩ ሃፒ የተባለውን መጽሐፍ ስላነበበ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ተሞክሮ ተናገረ። ይህ ልጅ ከቅርንጫፍ ቢሮው ያገኛቸውን ሌሎች ጽሑፎችም አንብቧል። ሆኖም ቤተሰቦቹ ተቃወሙት። ከዓመታት በኋላ የሕክምና ተማሪ በነበረበት ወቅት ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ በመጻፍ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠኑት ጥያቄ አቀረበ። በ1996 ተጠምቆ ብዙም ሳይቆይ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመረ። በአሁኑ ጊዜ ከሚስቱ ጋር በቅርንጫፍ ቢሮው ያገለግላል።

‘ፖርቶ ሪኮ “ምሥክሮች በመላክ” ንግድ ተሠማርታለች’ ሲል የቅርንጫፍ ኮሚቴ ሰብሳቢው ሮናልድ ፓርኪን ገለጸ። በደሴቲቱ ወደ 25, 000 ገደማ አስፋፊዎች ያሉ ሲሆን ቁጥሩ ለዓመታት ንቅንቅ ሳይል ቆይቷል። ለምን? ፖርቶ ሪኮ በየዓመቱ በግምት ወደ 1, 000 ገደማ አስፋፊዎችን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ “የምትልክ” በመሆኑ ነው። ብዙዎቹ ወደዚያ የሚሄዱት ኑሯቸውን ለማሻሻል ብለው ነው። ወንድም ፓርኪን የሉኬሚያ ታማሚ የሆነውን ሉዊስ የተባለ የ17 ዓመት ምሥክር በተመለከተ ትልቅ ግምት የሚሰጠው የፍርድ ቤት ውሳኔ መተላለፉን ተናገረ። ሉዊስ ደም አልወስድም በማለቱ ምክንያት ጉዳዩ ፍርድ ቤት ቀረበ። ዳኛዋ እሱን በግል ማነጋገር ስለፈለጉ ሆስፒታል ድረስ መጡ። ሉዊስ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው:- “ከባድ ወንጀል ብፈጽም እንደ ዐዋቂ ተቆጥሬ የምዳኝ ከሆነ አምላክን መታዘዝ ስፈልግ ግን እንደ ልጅ የምታየው ለምንድን ነው?” ዳኛዋ የበሰለ ልጅ እንደሆነና ለራሱ መወሰን እንደሚችል አምነው ተቀበሉ።

ራቅ ካሉ አገሮች የመጡ ሪፖርቶች ከቀረቡ በኋላ የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ሃሮልድ ኮርከርን ለረጅም ዓመታት ይሖዋን ላገለገሉ አራት ወንድሞች ቃለ ምልልስ አደረገላቸው። አርተር ቦኖ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት 51 ዓመታት ያሳለፈ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በኢኳዶር ቅርንጫፍ ኮሚቴ በማገልገል ላይ ይገኛል። አንጄሎ ካታንዛሮ በአብዛኛው ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ 59 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አሳልፏል። በ1953 ከጊልያድ ትምህርት ቤት የተመረቀው ሪቻርድ አብራሃምሰን ወደ ብሩክሊን ቤቴል ከመምጣቱ በፊት ዴንማርክ ውስጥ ለ26 ዓመታት ሥራውን በበላይ ተመልካችነት የመምራት መብት አግኝቷል። በመጨረሻም ከ96 ዓመት አዛውንቱ ከኬሪ ደብልዩ ባርበር ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ በመስማታቸው ሁሉም ተደስተው ነበር። በ1921 የተጠመቀው ወንድም ባርበር በሙሉ ጊዜ አገልግሎት 78 ዓመታት ያሳለፈ ሲሆን ከ1978 አንስቶ የአስተዳደር አካል አባል ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል።

ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮች

በዓመታዊው ስብሰባ ላይ አመራማሪ የሆኑ በርካታ ንግግሮች ቀርበው ነበር። ወንድም ሮበርት ደብልዩ ዎለን “ለስሙ የተመረጠ ሕዝብ” በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ። እኛ ለአምላክ ስም የተመረጥን ሕዝብ ነን፤ ከ230 በሚበልጡ አገሮችም ውስጥ እንገኛለን። ይሖዋ “የወደፊት ጊዜና ተስፋ” ሰጥቶናል። (ኤርምያስ 29:​11 NW ) ማጽናኛና ማበረታቻ የያዘውን አስደሳች መልእክት ለሌሎች በማካፈል የአምላክን መንግሥት ማስፋፋታችንን መቀጠል ይኖርብናል። (ኢሳይያስ 61:​1) ወንድም ዎለን “የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን ከምንጠራበት ስም ጋር በሚስማማ መንገድ በየቀኑ መመላለሳችንን እንቀጥል” በማለት ደመደመ።​—⁠ኢሳይያስ 43:​10

የፕሮግራሙ የመጨረሻ ክፍል ሦስት የአስተዳደር አካል አባላት ያቀረቡት ሲምፖዚየም ነበር። ሲምፖዚየሙ “ነቅቶ ለመኖር፣ ጸንቶ ለመቆምና እየጎለበቱ ለመሄድ ጊዜው አሁን ነው” የሚል ርዕስ ነበረው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 16:​13 NW

በመጀመሪያ ወንድም ስቲቨን ሌት “በዚህ በመጨረሻ ሰዓት ነቅታችሁ ኑሩ” በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ። ወንድም ሌት አካላዊ እንቅልፍ በረከት ነው ሲል ገለጸ። ኃይላችንን ያድስልናል። መንፈሳዊ እንቅልፍ ግን አንዳች ጥቅም የለውም። (1 ተሰሎንቄ 5:​6) ታዲያ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን መኖር የምንችለው እንዴት ነው? ወንድም ሌት ሦስት መንፈሳዊ “እንክብሎችን” ዘረዘረ:- (1) የጌታ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ። (1 ቆሮንቶስ 15:​58) (2) ለመንፈሳዊ ፍላጎታችሁ ንቁ ሁኑ። (ማቴዎስ 5:​3 NW ) (3) በጥበብ መመላለስ ትችሉ ዘንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክርን በደስታ ተቀበሉ።​—⁠ምሳሌ 13:​20

ወንድም ቴዎዶር ጃራዝ “በፈተና ሥር ጸንታችሁ ቁሙ” በሚል ርዕስ ቀስቃሽ ንግግር አቀረበ። ወንድም ጃራዝ ራእይ 3:​10ን ጠቅሶ “‘የፈተናው ሰዓት’ ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ አቀረበ። ይህ ፈተና የሚመጣው በዚህ በምንኖርበት “በጌታ ቀን” ውስጥ ነው። (ራእይ 1:​10) ይህ ፈተና የምንደግፈው የተቋቋመውን የአምላክን መንግሥት ነው ወይስ የሰይጣንን ክፉ የነገሮች ሥርዓት በሚለው አንገብጋቢ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ነው። ይህ የፈተና ሰዓት እስኪያልፍ ድረስ ፈተናዎች ወይም ችግሮች ይገጥሙናል ብለን እንጠብቃለን። ለይሖዋና ለድርጅቱ ታማኝ ሆነን እንቀጥላለን? ወንድም ጃራዝ ‘እንዲህ ዓይነቱን ታማኝነት በግለሰብ ደረጃ ማሳየት ይኖርብናል’ ሲል ጠቀሰ።

በመጨረሻም ወንድም ጆን ኢ ባር “እንደ መንፈሳዊ ሰው ጎልብቱ” በሚል ጭብጥ ንግግር አቀረበ። ሉቃስ 13:​23-25ን በመጥቀስ “በጠበበው በር ለመግባት” መጋደል እንዳለብን ተናገረ። ብዙዎች በመንፈሳዊ ለመጎልበት ትጋት ስለሚያንሳቸው ይወድቃሉ። የጎለመስን ክርስቲያኖች ለመሆን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ተግባራዊ ማድረግን መማር አለብን። ወንድም ባር እንዲህ ሲል በጥብቅ አሳስቧል:- “(1) ይሖዋን በአንደኛ ደረጃ ማስቀደማችንን የምንቀጥልበት፤ (2) በመንፈሳዊ የምንጎለብትበት፤ እንዲሁም (3) የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም የምንጋደልበት ጊዜ አሁን ነው ብትባሉ እንደምትስማሙ እርግጠኛ ነኝ። በዚህ መንገድ ማብቂያ ወደሌለው አስደሳች ሕይወት በሚመራው በጠበበው በር መግባት እንችላለን።”

ዓመታዊው ስብሰባ ወደ መደምደሚያው እየተቃረበ ሲመጣ፣ የ2002 የአገልግሎት ዓመት የዓመት ጥቅስ ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ ገና መልስ አላገኘም ነበር። በሚቀጥለው ቀን የዚህ ጥያቄ መልስ ተሰጠ።

ተጨማሪ ስብሰባ

እሁድ ጠዋት ተጨማሪው የስብሰባ ፕሮግራም የሚጀምርበትን ጊዜ ሁሉም በከፍተኛ ጉጉት ይጠባበቁ ነበር። ፕሮግራሙ የሳምንቱ የመጠበቂያ ግንብ ትምህርት ፍሬ ሐሳቦች በክለሣ መልክ ከቀረበ በኋላ የዓመታዊው ስብሰባ አንዳንድ ጎላ ያሉ ነጥቦች በአጭሩ ቀረቡ። ቀጥሎም “ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” በሚለው የ2002 የዓመት ጥቅስ ላይ የቀረበውን ንግግር በመስማታቸው ተደስተዋል። (ማቴዎስ 11:​28) ንግግሩ ጥቂት ቆይቶ በታኅሣሥ 15, 2001 የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ ታትመው በወጡት የጥናት ርዕሶች ላይ የተመሠረተ ነበር።

ከዚያ በመቀጠል በነሐሴ 2001 በፈረንሳይና በኢጣሊያ በተካሄዱት “የአምላክ ቃል አስተማሪዎች” ልዩ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የተገኙ አንዳንድ ልዑካን የነኳቸውን ነጥቦች ተናገሩ። c በመጨረሻም ከብሩክሊን ቤቴል የመጡ ጎብኚ ተናጋሪዎች ያቀረቧቸው የመጨረሻዎቹ ሁለት ንግግሮች የዕለቱ ፕሮግራም ዓበይት ገጽታዎች ነበሩ።

የመጀመሪያው ንግግር “በእነዚህ አስጨናቂ ቀናት በልበ ሙሉነት በይሖዋ መታመን” የሚል ርዕስ ነበረው። ተናጋሪው የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች አብራርቷል:- (1) የአምላክ ሕዝቦች ምንጊዜም በሙሉ ልብ በይሖዋ መታመን አስፈልጓቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም ድፍረትና እምነት ያሳዩ የበርካታ ሰዎችን ምሳሌ ይዟል። (ዕብራውያን 11:​1–12:​3) (2) ይሖዋ ሙሉ በሙሉ በእሱ እንድንታመን የሚያስችል አሳማኝ መሠረት ጥሎልናል። ሥራውና ቃሉ ለአገልጋዮቹ እንደሚያስብና ፈጽሞ እንደማይረሳቸው ዋስትና ይሰጣሉ። (ዕብራውያን 6:​10) (3) በተለይ በዛሬው ጊዜ ድፍረትና እምነት አስፈላጊ ናቸው። ኢየሱስ እንደተነበየው ‘የጥላቻ’ ዒላማ ሆነናል። (ማቴዎስ 24:​9) መጽናት እንድንችል መንፈሱ እንዳለን ትምክህት በማሳደር በአምላክ ቃል መደገፍና ምሥራቹን ማወጃችንን ለመቀጠል ድፍረት ያስፈልገናል። (4) በአሁኑ ጊዜም ተቃውሞ እንደሚደርስብን የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ። ተናጋሪው ወንድሞቻችን በአርማንያ፣ በፈረንሳይ፣ በጆርጂያ፣ በካዛክስታን፣ በሩሲያ እና በተርከሜኒስታን በጽናት ያሳለፏቸውን ፈተናዎች ሲገልጽ ሁሉም በጥልቅ ተነክተዋል። በእርግጥም በይሖዋ ላይ ድፍረትና ትምክህት እንዳለን የምናሳይበት ጊዜ አሁን ነው!

የመጨረሻው ተናጋሪ ያብራራው ጭብጥ “ከይሖዋ ድርጅት ጋር አንድ ሆነን ወደፊት መግፋት” የሚል ነበር። ንግግሩ በርካታ ወቅታዊ ነጥቦችን አካትቷል። (1) የይሖዋ ሕዝቦች ወደፊት የሚያደርጉት ግስጋሴ በሰፊው ተስተውሏል። የስብከት ሥራችንና የአውራጃ ስብሰባዎቻችን የሌሎችን ትኩረት ይስባሉ። (2) ይሖዋ አንድነት ያለው ድርጅት አቋቁሟል። ኢየሱስ በ29 እዘአ በመንፈስ ቅዱስ የተቀባበት ዓላማ ‘ሁሉንም’ ማለትም ሰማያዊ ውርሻ ያላቸውንም ሆነ ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን አንድነት ባለው የአምላክ ቤተሰብ ውስጥ ለመጠቅለል ነው። (ኤፌሶን 1:​8-10) (3) የአውራጃ ስብሰባዎች ዓለም አቀፋዊ አንድነት እንዳለን በሚገባ የሚያሳዩ ናቸው። ባለፈው ነሐሴ በፈረንሳይና በኢጣሊያ በተደረጉት ልዩ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ይህ በግልጽ ታይቷል። (4) በፈረንሳይና በኢጣሊያ ቀስቃሽ የአቋም መግለጫ ተላልፏል። ተናጋሪው ከዚህ ቀስቃሽ የአቋም መግለጫ ውስጥ የተወሰኑ ነጥቦችን ቀንጨብ አድርጎ አቀረበ። የአቋም መግለጫው ሙሉ ቃል ከታች ይገኛል።

የመጨረሻው ንግግር መደምደሚያ ላይ ጎብኚ ተናጋሪው የአስተዳደር አካሉ ያዘጋጀውን ልብ የሚነካ ማስታወቂያ አነበበ። ማስታወቂያው በከፊል እንዲህ ይላል:- “በዓለም ላይ የሚደርሱ ክስተቶች ምን መልክ እንደሚይዙ በማስተዋል ነቅተን የምንኖርበትና የምንተጋበት ጊዜ አሁን ነው። . . . የአስተዳደር አካሉ ለእናንተም ሆነ ለመላው የአምላክ ሕዝብ ያለውን ፍቅራዊ አሳቢነት ልንገልጽላችሁ እንወዳለን። የእሱን ፈቃድ በሙሉ ነፍሳችሁ ስትፈጽሙ አትረፍርፎ እንዲባርካችሁ እንመኛለን።” በሁሉም ቦታ የሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች በእነዚህ አስጨናቂ ቀናት ነቅተው ለመኖርና አንድነት ካለው የይሖዋ ድርጅት ጋር በቆራጥነት ወደፊት ለመራመድ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የዓመታዊው ስብሰባ ፕሮግራም ወደ ሌሎች በርካታ ቦታዎች በኤሌትሮኒክስ መሣሪያዎች አማካኝነት ስለተላለፈ አጠቃላዩ የተሰብሳቢዎች ቁጥር 13, 757 ሊደርስ ችሏል።

b ተጨማሪ ስብሰባዎች የተካሄዱት በካሊፎርኒያ ሎንግ ቢች፣ በሚሺጋን ፖንቲያክ፣ በኒው ዮርክ ዩኒየንዴል እና በኦንታሪዮ ሃሚልተን ነበር። በኤሌትሮኒክስ መሣሪያዎች የተገናኙትን ሌሎች ቦታዎች ጨምሮ አጠቃላዩ የተሰብሳቢዎች ቁጥር 117, 885 ነበር።

c ፈረንሳይ ውስጥ በፓሪስ፣ ቦርዶ እና ሊዮን ሦስት ልዩ የአውራጃ ስብሰባዎች ተደርገው ነበር። በኢጣሊያ በድምሩ ዘጠኝ የአውራጃ ስብሰባዎች በተመሳሳይ ቀናት የተካሄዱ ሲሆን ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡ ልዑካን ሮምና ሚላን በተደረጉት ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ተመድበው ነበር።

[በገጽ 29-31 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የአቋም መግለጫ

በነሐሴ 2001 በፈረንሳይና በኢጣሊያ “የአምላክ ቃል አስተማሪዎች” የተባለ ልዩ የአውራጃ ስብሰባዎች ተደርገው ነበር። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ቀስቃሽ የአቋም መግለጫ ወጥቷል። የአቋም መግለጫው ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል።

“በዚህ ‘የአምላክ ቃል አስተማሪዎች’ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኘን የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ እጅግ ጠቃሚ ትምህርት ቀስመናል። የዚህ ትምህርት ምንጭ ማን እንደሆነ በግልጽ ታውቋል። ትምህርቱ ከሰዎች የተገኘ አይደለም። ትምህርቱ የመጣው በጥንት ዘመን የኖረው ነቢዩ ኢሳይያስ ‘ታላቅ አስተማሪያችን’ ሲል ከገለጸው አካል ነው። (ኢሳይያስ 30:​20 NW ) ኢሳይያስ 48:​17 ላይ የሚገኘውን የይሖዋን ማሳሰቢያ ልብ በሉ:- ‘እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW ] ነኝ።’ ይሖዋ ይህን የሚያከናውነው እንዴት ነው? ዋነኛው መንገድ በዓለም ላይ በሰፊው በተተረጎመውና በተሰራጨው መጽሐፍ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ሲሆን እዚያም ላይ ‘የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ጠቃሚ ነው’ ተብሎ በማያሻማ መንገድ ተነግሮናል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​16

“በዛሬው ጊዜ የሰው ዘር ይህን የመሰለ ጠቃሚ ትምህርት የግድ ያስፈልገዋል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ተለዋዋጭና ግራ የሚያጋባ የሆነውን የዚህን ዓለም ሁኔታ ስንመለከት አስተዋይ የሆኑ ሰዎች ምን ይገነዘባሉ? በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በዓለም የትምህርት ተቋማት ገብተው ከፍተኛ ትምህርት ያገኙ ቢሆንም እውነተኛ ዋጋ ያላቸውን ነገሮች አለመረዳትና ትክክልና ስህተት በሆኑ ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት መለየት አለመቻል በአስከፊ ሁኔታ ይታያል። (ኢሳይያስ 5:​20, 21) የመጽሐፍ ቅዱስ መሃይምነት በእጅጉ ተስፋፍቷል። ቴክኖሎጂ በኮምፒውተር አማካኝነት ከፍተኛ መጠን ያለው መረጃ ቢያቀርብም የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? በጊዜያችን የሚታዩትን ክስተቶች መረዳት ያለብን እንዴት ነው? የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ አስተማማኝ ተስፋ አለ? ሰላምና ደኅንነት እውን የሚሆንበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? እንደሚሉት ያሉት አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ የሚገኙት ከየት ነው? በተጨማሪም በቤተ መጻሕፍት መደርደሪያዎች ላይ ቃል በቃል ሰዎች የደረሱባቸውን እያንዳንዱን ግኝቶች የሚዳስሱ በርካታ ጥራዝ ያላቸው የማጣቀሻ ጽሑፎች ይገኛሉ። ሆኖም የሰው ልጆች በፊት የፈጸሟቸውን ስህተቶች አሁንም ይደግማሉ። ወንጀል በጣም ተስፋፍቷል። ከዚህ በፊት ተወግደዋል ተብለው ይታሰቡ የነበሩ አንዳንድ በሽታዎች በድጋሚ እየተከሰቱ ሲሆን እንደ ኤድስ ያሉ ሌሎች በሽታዎች ደግሞ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጩ ናቸው። የቤተሰብ ሕይወት በአስደንጋጭ ሁኔታ እየፈራረሰ ነው። ብክለት ምድርን እያበላሸ ነው። ሽብርና ከፍተኛ እልቂት የሚያስከትሉ መሣሪያዎች ሰላምንና ደኅንነትን አደጋ ላይ ጥለዋል። መፍትሔ ያልተገኘላቸው ችግሮች እየተበራከቱ መጥተዋል። በዚህ አስጨናቂ ዘመን ሰዎችን በመርዳት ረገድ ያለን ተገቢ ድርሻ ምንድን ነው? የሰው ልጅ የደረሰበትን መከራ መንስኤ የሚያሳውቅና በአሁን ጊዜ የተሻለ ሕይወት እንዴት እንደሚገኝ ብቻ ሳይሆን ወደፊት አስደሳችና እርግጠኛ ተስፋ እንዳለ የሚገልጽ ትምህርት ይኖራል?

“‘ሄደን አሕዛብን ሁሉ ክርስቶስ ያዘዘውን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማርን ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ’ ቅዱስ ጽሑፋዊ ተልዕኮ ተሰጥቶናል። (ማቴዎስ 28:​19, 20) ይህ ተልዕኮ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ ከተነሣ በኋላ በሰማይና በምድር ሥልጣን ሲሰጠው ያስተላለፈው ትእዛዝ ነው። ተልዕኮው ሰዎች ከተሠማሩበት ከማንኛውም የሥራ መስክ የላቀ ነው። ከአምላክ አመለካከት አንጻር ለጽድቅ በተራቡ ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎቶች ላይ የሚያተኩረው ተልዕኳችን ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል። ይህን ተልዕኮ በቁም ነገር እንድንይዘው የሚያደርግ አጥጋቢ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት አለን።

“ይህም እንዲህ ዓይነቱን ሥራ በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ እንድንሰጠው ያደርገናል። ሥራውን የሚያስተጓጉሉ በርካታ ተጽዕኖዎች፣ እንቅፋቶች እንዲሁም ከሃይማኖታዊም ሆነ ከፖለቲካዊ ቡድኖች ይህን ዓለም አቀፋዊ የማስተማር መርሐ ግብር እድገት ለመግታት የታቀዱ ተቃውሞዎች ቢሰነዘሩም በአምላክ በረከትና እርዳታ ሥራው መፈጸሙ አይቀርም። ይህ ሥራ ማደጉን እንደሚቀጥልና ታላቅ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ትምክህትና እምነት አለን። ይህን ያህል እርግጠኞች የሆንነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ እስኪደርስ ድረስ አምላክ የሰጠንን አገልግሎት ስናከናውን ከእኛ ጋር እንደሚሆን ቃል ስለገባልን ነው።

“በሥቃይ ላይ የሚገኘው የሰው ዘር ፍጻሜውን የሚያገኝበት ጊዜ ተቃርቧል። መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የአሁኑ ተልዕኳችን ፍጻሜውን ማግኘት አለበት። በመሆኑም እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ለማድረግ ወስነናል:-

“አንደኛ:- ራሳችንን ለአምላክ የወሰንን አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የመንግሥቱን ጥቅሞች በሕይወታችን ውስጥ ለማስቀደምና በመንፈሳዊ ማደጋችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። ከዚህም የተነሳ መዝሙር 143:​10 ላይ ‘አንተ አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ’ ከሚሉት ቃላት ጋር የሚስማማ ጸሎት እናቀርባለን። ይህም በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ፣ የግል ጥናትና ምርምር ለማድረግ ትጉ ተማሪዎች መሆንን ይጠይቅብናል። እድገታችን በሰው ሁሉ ፊት ግልጽ ሆኖ እንዲታይ በጉባኤ ስብሰባዎች፣ ወረዳው ውስጥ በሚደረጉ ትልልቅ ስብሰባዎች እንዲሁም በአውራጃ፣ በአገር አቀፍና በብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ከሚቀርበው ቲኦክራሲያዊ ትምህርት የተሟላ ጥቅም ለማግኘት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​15፤ ዕብራውያን 10:​23-25

“ሁለተኛ:- አምላክ እንዲያስተምረን ከፈለግን ከእሱ ገበታ ብቻ እንመገባለን እንዲሁም የአጋንንትን አሳሳች ትምህርቶች በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠንን ማስጠንቀቂያ በጥብቅ እንከተላለን። (1 ቆሮንቶስ 10:​21፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:​1) ሃይማኖታዊ ውሸቶችን፣ ከንቱ ትምህርቶችን፣ አሳፋሪ የሆኑ የፆታ ብልግናዎችን፣ እንደ ወረርሽኝ የተስፋፉ ወሲባዊ ስዕሎችን፣ የረከሰ መዝናኛን እንዲሁም ‘ከጤናማ ትምህርት የማይስማማ’ ማንኛውንም ነገር ጨምሮ ጎጂ ነገሮችን ለማስወገድ ልዩ ጥንቃቄ እናደርጋለን። (ሮሜ 1:​26, 27፤ 1 ቆሮንቶስ 3:​19, 20፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:​3፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:​13) ጤናማ የሆነውን ትምህርት ለማስተማር ብቃት ላላቸው ‘ስጦታ ለሆኑ ወንዶች’ ካለን አክብሮት የተነሳ የሚያደርጉትን ጥረት ከልብ የምናደንቅ ከመሆኑም በላይ የአምላክ ቃል የያዘውን ንጹሕና ጽድቅ ያለበትን የሥነ ምግባርም ሆነ መንፈሳዊ የአቋም ደረጃዎችን በመደገፍ ከእነሱ ጋር በሙሉ ልባችን እንተባበራለን።​—⁠ኤፌሶን 4:​7, 8, 11, 12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:​12, 13፤ ቲቶ 1:​9

“ሦስተኛ:- ክርስቲያን ወላጆች እንደመሆናችን መጠን ልጆቻችንን በቃል ብቻ ሳይሆን ምሳሌ በመሆንም ለማስተማር በሙሉ ልባችን ጥረት እናደርጋለን። በአንደኛ ደረጃ የሚያሳስበን ጉዳይ ልጆቻችንን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ‘መዳን የሚገኝበትን ጥበብ የሚሰጧቸውን ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲያውቁ’ መርዳት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​15) ልጆቻችንን በይሖዋ ምክርና ተግሣጽ ማሳደጋችን ‘መልካም እንደሚሆንላቸውና ዕድሜያቸው በምድር ላይ እንደሚረዝም’ የተገባላቸውን መለኮታዊ የተስፋ ቃል እንዲያገኙ ከሁሉ የተሻለ አጋጣሚ እንደሚሰጣቸው ሁልጊዜ እናስታውሳለን።​—⁠ኤፌሶን 6:​1-4

“አራተኛ:- ጭንቀቶች ወይም ከባድ ችግሮች ሲያጋጥሙን ‘አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም’ እንደሚጠብቀን በተሰጠን ዋስትና መሠረት በመጀመሪያ ደረጃ ‘በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችንን እናስታውቃለን።’ (ፊልጵስዩስ 4:​6, 7) በክርስቶስ ቀንበር ሥር መሆናችን ዕረፍት ይሰጠናል። አምላክ እንደሚያስብልን ስለምናውቅ የሚያስጨንቁንን ነገሮች በእሱ ላይ ከመጣል ወደኋላ አንልም።​—⁠ማቴዎስ 11:​28-30፤ 1 ጴጥሮስ 5:​6, 7

“አምስተኛ:- ይሖዋ የቃሉ አስተማሪዎች እንድንሆን ለሰጠን መብት ካለን አመስጋኝነት የተነሳ ‘የእውነትን ቃል በቅንነት ለመናገር’ እና ‘አገልግሎታችንን ለመፈጸም’ ጥረታችንን እናድሳለን። (2 ጢሞቴዎስ 2:​15፤ 4:​5) ይህ ሥራ የሚያካትተውን ነገር ጠንቅቀን ስለምንረዳ የሚገባቸውን ሰዎች ፈልጎ ለማግኘትና የተዘራውን ዘር ለመኮትኮት ልባዊ ፍላጎት አለን። ከዚህም በላይ ተጨማሪ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ በመምራት የማስተማር ችሎታችንን እናሻሽላለን። ይህ ‘ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ’ ፍላጎት ካለው ከአምላክ ፈቃድ ጋር ይበልጥ እንድንስማማ ያስችለናል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 2:​3, 4

“ስድስተኛ:- ባለፈው መቶ ዘመንም ሆነ በዚህ መቶ ዘመን እንደታየው የይሖዋ ምሥክሮች በበርካታ አገሮች ውስጥ ልዩ ልዩ ዓይነት ተቃውሞና ስደት ደርሶባቸዋል። ሆኖም ይሖዋ ከእኛ ጋር መሆኑን አስመስክሯል። (ሮሜ 8:​31) አስተማማኝ የሆነው ቃሉ የመንግሥቱን ስብከትና የማስተማር ሥራችንን ለማደናቀፍ፣ ለማቀዝቀዝ ወይም ለማስቆም ‘በእኛ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ’ እንደማይከናወን አረጋግጦልናል። (ኢሳይያስ 54:​17) ቢመችም ባይመችም እውነትን መናገራችንን አናቆምም። የስብከቱንና የማስተማር ተልዕኳችንን በጥድፊያ ስሜት ለማከናወን ቆርጠናል። (2 ጢሞቴዎስ 4:​1, 2 NW ) ዓላማችን ለሰዎች ሁሉ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በተቻለ መጠን በተሟላ ሁኔታ መስበክ ነው። በመሆኑም ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ስለሚያስችለው ዝግጅት ቀጣይነት ያለው የመማር አጋጣሚ ይኖራቸዋል። አንድነት ያለን የአምላክ ቃል አስተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን የታላቁ አስተማሪያችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ለመከተልና አምላካዊ ባሕርያቱን ለማንጸባረቅ ወስነናል። ይህን ሁሉ የምናደርገው ታላቅ አስተማሪያችንና ሕይወት ሰጪያችን ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ክብርና ውዳሴ ለማምጣት ነው።

“በዚህ ስብሰባ ላይ የተገኛችሁ በሙሉ ይህን መግለጫ የምትደግፉ ከሆነ እባካችሁ አዎን! በማለት ምላሽ ስጡ።”

የአቋም መግለጫው የመደምደሚያ ጥያቄ በፈረንሳይ በተካሄዱ ሦስት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ለተገኙ 160, 000 ሰዎች እንዲሁም በኢጣሊያ በዘጠኝ የመሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ ለተገኙ 289, 000 ሰዎች ሲቀርብ ልዑካኑ በሚናገሯቸው በተለያዩ ቋንቋዎች እንደ ነጎድጓድ በሚያስተጋባ ድምፅ “አዎን” የሚል መልስ ተሰጠ።