በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን በልብህና በአእምሮህ ፈልገው

አምላክን በልብህና በአእምሮህ ፈልገው

አምላክን በልብህና በአእምሮህ ፈልገው

እውነተኛ ክርስትና አምላክን የሚያስደስት እምነት ለመገንባት ልባችንንና አእምሮአችንን እንድንጠቀም ያበረታታናል።

እንዲያውም የክርስትና መሥራች የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክን ‘በፍጹም ልባችንና ነፍሳችን’ ብቻ ሳይሆን “በፍጹም ሐሳባችን” ወይም በማሰብ ኃይላችን እንድንወደው አስተምሯል። (ማቴዎስ 22:​37) አዎን፣ የማገናዘብ ችሎታችን በአምልኳችን ውስጥ ወሳኝ ሚና መጫወት ይኖርበታል።

ኢየሱስ አድማጮቹ በትምህርቱ ላይ እንዲያሰላስሉ ሲጋብዝ ብዙውን ጊዜ “ምን ይመስላችኋል?” በማለት ይጠይቅ ነበር። (ማቴዎስ 17:25፤ 18:​12፤ 21:28፤ 22:42) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጴጥሮስ የክርስቲያን ባልደረቦቹን ‘የማሰብ ችሎታ ለማነቃቃት’ ሲል ደብዳቤ ጽፎላቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:​1, 2 NW ) በርካታ የስብከት ጉዞዎችን ያደረገው ሐዋርያው ጳውሎስም ክርስቲያኖች “የማገናዘብ ችሎታቸውን” እንዲጠቀሙና ‘በጎና ደስ የሚያሰኘው ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ለራሳቸው ፈትነው እንዲያውቁ’ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። (ሮሜ 12:​1, 2 NW ) ክርስቲያኖች አምላክን የሚያስደስትና በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በተሳካ መንገድ ለመወጣት የሚያስችል እምነት መገንባት የሚችሉት እምነታቸውን ይህን በመሰለ ጥንቃቄ የተሞላበት መንገድ ከመረመሩ ብቻ ነው።​—⁠ዕብራውያን 11:​1, 6

የጥንት ክርስቲያን ወንጌላውያን ሌሎች ይህን የመሰለውን እምነት እንዲገነቡ ለመርዳት ‘ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ያመራምሯቸውና ማስረጃ እያቀረቡ ያስረዷቸው’ ነበር። (ሥራ 17:​1-3 NW ) እንዲህ ዓይነቱ ምክንያታዊ አቀራረብ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ ገፋፍቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ቤርያ በተባለች የመቄዶንያ ከተማ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች “ነገሩ [ጳውሎስና ጓደኞቹ ያስተማሯቸው ነገር] እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን [የአምላክን] በሙሉ ፈቃድ [“በጉጉት፣” NW ] ተቀበሉ።” (ሥራ 17:​11) እዚህ ጥቅስ ላይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ሁለት ነጥቦች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ የቤርያ ሰዎች ለአምላክ ቃል ጉጉት ነበራቸው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሰሙትን ሁሉ እንዲያው በጭፍን ከመቀበል ይልቅ ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥንቃቄ መርምረዋል። ክርስቲያን ሚስዮናዊ የሆነው ሉቃስ የቤርያን ሰዎች “ልበ ሰፊዎች” ብሎ በመጥራት ለዚህ ዝንባሌያቸው በአክብሮት አመስግኗቸዋል። አንተስ በመንፈሳዊ ጉዳዮች ረገድ ይህን የመሰለውን የልበ ሰፊነት ባሕርይ ታሳያለህ?

አእምሮና ልብ ተቀናጅተው ይሠራሉ

ቀደም ሲል እንደተገለጸው እውነተኛ አምልኮ ከአእምሮና ከልብ ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው። (ማርቆስ 12:​30) በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰውንና የተሳሳተ ቀለም የቀባውን ቀለም ቀቢ አስታውስ። የባለቤቱን መመሪያ በጥንቃቄ አዳምጦ ቢሆን ኖሮ ልቡን ሙሉ በሙሉ በሥራው ላይ ሊያደርግና ባለቤቱን የሚያስደስት ሥራ መሥራት ይችል ነበር። አምልኮታችንንም በተመለከተ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

ኢየሱስ “እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስ እና በእውነት ያመልኩታል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:​23 NW ) ሐዋርያው ጳውሎስም እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “እኛ ደግሞ . . . የፈቃዱ [“ትክክለኛ፣” NW ] እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን፣ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ . . . በእግዚአብሔርም [“ትክክለኛ፣” NW ] እውቀት እያደጋችሁ፣ . . . በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን።” (ቆላስይስ 1:​9-12) ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ‘የሚያመልኩትን ስለሚያውቁ’ እንዲህ ያለው “ትክክለኛ እውቀት” ልባቸውንና ነፍሳቸውን ሙሉ በሙሉ በአምልኳቸው ላይ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።​—⁠ዮሐንስ 4:​22 NW

በዚህም ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች ሕፃናትንም ሆነ ቅዱሳን ጽሑፎችን ያላጠኑ ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎችን አያጠምቁም። ኢየሱስ ተከታዮቹን “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት አዝዟቸዋል። (ማቴዎስ 28:​19, 20) ቅን ልብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አምልኮን በተመለከተ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ትክክለኛ ውሳኔ ሊያደርጉ የሚችሉት ስለ አምላክ ፈቃድ ትክክለኛ እውቀት ሲያገኙ ብቻ ነው። አንተም እንዲህ ያለውን ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት ጥረት እያደረግህ ነው?

የጌታን ጸሎት ትርጉም መረዳት

ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በማግኘትና ቁንጽል የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በመያዝ መካከል ያለውን ልዩነት ለመገንዘብ እንድንችል በማቴዎስ 6:​9-13 ላይ የሚገኘውን በተለምዶ አባታችን ሆይ ወይም የጌታ ጸሎት በመባል የሚታወቀውን ዘገባ እንመልከት።

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የኢየሱስን የናሙና ጸሎት ዘወትር በየቤተ ክርስቲያኖቻቸው ይደግሙታል። ይሁን እንጂ ትርጉሙን በተለይ ደግሞ ስለ አምላክ ስምና መንግሥት የሚገልጸውን የመጀመሪያ ክፍል የሚረዱት ስንቶቹ ናቸው? እነዚህ ነጥቦች በጣም አስፈላጊ ከመሆናቸው የተነሣ ኢየሱስ በጸሎቱ መጀመሪያ ላይ ጠቅሷቸዋል።

ጸሎቱ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” በማለት ይጀምራል። ኢየሱስ የአምላክ ስም እንዲቀደስ መጸለይ እንደሚገባ መጠቆሙን አስተውል። ይህ በብዙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ ቢያንስ ሁለት ጥያቄዎችን ያስነሳል:- የመጀመሪያው የአምላክ ስም ማን ነው? የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ስሙ መቀደስ ያስፈለገው ለምንድን ነው? የሚል ነው።

የመጀመሪያው ጥያቄ መልስ በመጽሐፍ ቅዱስ በኩረ ጽሑፍ ውስጥ ከ7, 000 በሚበልጡ ቦታዎች ላይ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል አንደኛው “ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ በምድር ሁሉ ላይ አንተ ብቻ ልዑል እንደሆንህ ሰዎች ሁሉ ይወቁ” በሚለው በመዝሙር 83:​18 [NW ] ላይ ይገኛል። ይሖዋ የተባለውን መለኮታዊ ስም አስመልክቶ ዘጸአት 3:​15 “ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው፣ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው” ይላል። a ታዲያ የንጽሕናና የቅድስና ተምሳሌት የሆነው የአምላክ ስም መቀደስ ያስፈለገው ለምንድን ነው? ይህ የሆነበት ምክንያት ስሙ ገና ከሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ አንስቶ ስድብና ነቀፋ ስለደረሰበት ነው።

አዳምና ሔዋን ከተከለከለው ፍሬ ከበሉ እንደሚሞቱ አምላክ ነግሯቸው ነበር። (ዘፍጥረት 2:​17) ሰይጣን ደግሞ “ሞትን አትሞቱም” በማለት አምላክን በድፍረት ተቃወመ። በዚህ መንገድ አምላክን ውሸታም በማለት ከሰሰው። ይሁንና ሰይጣን በዚህ ብቻ አላበቃም። አምላክ በጣም ውድ የሆነ እውቀት ከልክሏችኋል ብሎ ለሔዋን በመናገር በአምላክ ስም ላይ ተጨማሪ ስድብ ሰነዘረ። “ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።” ይህ እንዴት ያለ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው!​—⁠ዘፍጥረት 3:​4, 5

አዳምና ሔዋን ከተከለከለው ዛፍ በመብላት ከሰይጣን ጎን መሰለፋቸውን አሳዩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አብዛኛው የሰው ዘር የአምላክን የጽድቅ መሥፈርቶች በመጣስ አውቆም ይሁን ሳያውቅ በስሙ ላይ ተጨማሪ ስድብ እንዲከመር አድርጓል። (1 ዮሐንስ 5:​19) ሰዎች ለሚደርስባቸው መከራ አምላክን ተጠያቂ በማድረግ ይሰድቡታል። መከራው የደረሰባቸው በራሳቸው ጥፋት ቢሆንም እንኳ እንዲህ ከማድረግ አይቆጠቡም። ምሳሌ 19:​3 [አ.መ.ት ] “ሰው በራሱ ተላላነት ሕይወቱን ያበላሻል፤ በልቡ ግን እግዚአብሔርን ያማርራል” በማለት ይናገራል። አባቱን ከልቡ ይወድድ የነበረው ኢየሱስ ስሙ እንዲቀደስ የጸለየው ለምን እንደሆነ አሁን አስተዋልክ?

“መንግሥትህ ትምጣ”

ኢየሱስ የአምላክ ስም እንዲቀደስ ከጸለየ በኋላ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” በማለት ተናገረ። (ማቴዎስ 6:​10) ይህንን ዘገባ በተመለከተ “የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?” “የዚህ መንግሥት መምጣትስ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ከመፈጸሙ ጋር ምን ግንኙነት አለው?” ብለን እንጠይቅ ይሆናል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መንግሥት” የሚለው ቃል “ንጉሣዊ አገዛዝ” የሚል መሠረታዊ ትርጉም አለው። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው የአምላክ መንግሥት እርሱ በመረጠው ንጉሥ የሚመራ አምላካዊ አገዛዝን ወይም መስተዳድርን ያመለክታል። ይህ ንጉሥ “የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ” ከተባለለትና ትንሣኤ ካገኘው ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። (ራእይ 19:​16፤ ዳንኤል 7:​13, 14) ነቢዩ ዳንኤል በኢየሱስ ክርስቶስ የሚተዳደረውን የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት አስመልክቶ የሚከተለውን ብሏል:- “በእነዚያም ነገሥታት [አሁን በሚገዙት ሰብዓዊ መንግሥታት] ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።”​—⁠ዳንኤል 2:​44

አዎን፣ የአምላክ መንግሥት ክፋትን ከምድረ ገጽ ጠራርጎ ካጠፋ በኋላ ምድርን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር “ለዘላለም” ይገዛል። ይሖዋ ሰይጣንና ኃጢአተኛ የሰው ልጆች በስሙ ላይ የከመሩትን ስድብ የሚያስወግደውና ስሙን የሚያስቀድሰው በዚህ መንግሥት አማካኝነት ይሆናል።​—⁠ሕዝቅኤል 36:​23

እንደ ሌሎቹ መንግሥታት ሁሉ የአምላክ መንግሥትም ተገዢዎች አሉት። እነዚህ እነማን ናቸው? መጽ​ሐፍ ቅዱስ “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል” በማለት መልሱን ይሰጣል። (መዝሙር 37:​11) በተመሳሳይም ኢየሱስ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና” በማለት ተናግሯል። በእርግጥም እነዚህ ሰዎች ለሕይወት የሚያበቃ ትክክለኛ የአምላክ እውቀት አላቸው።​—⁠ማቴዎስ 5:​5፤ ዮሐንስ 17:​3

ምድር አምላክን በሚወዱና እርስ በእርሳቸው በሚዋደዱ ገርና የዋህ ሰዎች ስትሞላ በዓይነ ሕሊናህ መመልከት ትችላለህ? (1 ዮሐንስ 4:​7, 8) ኢየሱስ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ሲል እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ እንዲሰፍን መጸለዩ ነበር። ኢየሱስ ተከታዮቹ በዚህ መንገድ እንዲጸልዩ ያስተማራቸው ለምን እንደሆነ ተረዳህ? ከሁሉም በላይ ደግሞ የዚህ ጸሎት ፍጻሜ አንተን በግል የሚነካህ እንዴት እንደሆነስ አስተዋልክ?

በዛሬው ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቅዱሳን ጽሑፎችን እየመረመሩ ነው

ኢየሱስ መጪውን የአምላክ መንግሥት የሚያውጅ መንፈሳዊ የትምህርት ዘመቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚካሄድ አስቀድሞ ተናግሯል። እንዲህ አለ:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው [የዚህ ዓለም ወይም የነገሮች ሥርዓት መጨረሻ] ይመጣል።”​—⁠ማቴዎስ 24:​14

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወደ ስድስት ሚልዮን የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ይህንን ምሥራች ለጎረቤቶቻቸው በመንገር ላይ ናቸው። የማገናዘብ ችሎታህን ተጠቅመህ ‘ቅዱሳን ጽሑፎችን በመመርመር’ ስለ አምላክና ስለ መንግሥቱ ተጨማሪ እውቀት እንድታገኝ ይጋብዙሃል። እንዲህ ማድረግህ እምነትህን ከማጠንከሩም በላይ ‘ውኃ ባሕርን እንደሚከድን እግዚአብሔርን በማወቅ በምትሞላው’ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የሚኖረውን ሕይወት ስታስብ ልብህ በደስታ እንዲሞላ ያደርጋል።​—⁠ኢሳይያስ 11:​6-9

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንዳንድ ምሁራን “ይሖዋ” በሚለው ስም ፋንታ “ያህዌህ” የሚለውን መጠቀም ይመርጣሉ። ሆኖም አብዛኞቹ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የአምላክን ስም ጨርሶ ከትርጉሞቻቸው በማውጣት “ጌታ” እና “አምላክ” በሚሉት የማዕረግ ስሞች ተክተውታል። የአምላክን ስም በተመለከተ ጥልቅ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም የተባለውን ብሮሹር ተመልከት።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ታላቁን አስተማሪ ኮርጅ

ኢየሱስ አብዛኛውን ጊዜ ሲያስተምር በአንድ በተወሰነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕስ ላይ ያተኩር ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ከትንሣኤው በኋላ በእርሱ ሞት ምክንያት ግራ ተጋብተው ለነበሩ ሁለት ደቀ መዛሙርት እርሱ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ገልጾላቸዋል። ሉቃስ 24:​27 “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጎመላቸው” በማለት ይናገራል።

ኢየሱስ ‘ስለ እርሱ’ ማለትም ስለ መሲሁ የሚናገር አንድ ርዕስ እንደመረጠና በውይይቱ መሃል ‘ከመጻሕፍት ሁሉ’ እንደጠቀሰ ልብ በል። በሌላ አባባል ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የመንፈሳዊውን እውነት ምሳሌ እንዲረዱ ለማድረግ ከጉዳዩ ጋር አግባብነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ተገጣጥመው አንድ ቅርጽ እንደሚሠሩ ቁርጥራጮች አንድ ላይ አስቀምጧቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 1:​13) ይህም ደቀ መዛሙርቱ ተጨማሪ እውቀት እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ ስሜታቸው በጥልቅ እንዲነካም አድርጓል። ዘገባው “እርስ በርሳቸውም:- በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን? ተባባሉ” በማለት ይነግረናል።​—⁠ሉቃስ 24:​32

የይሖዋ ምሥክሮች በአገልግሎታቸው የኢየሱስን የማስተማሪያ ዘዴዎች ለመኮረጅ ይጥራሉ። ዋነኞቹ የማስተማሪያ መሣሪያዎቻቸው አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለው ብሮሹርና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው መጽሐፍ ናቸው። እነዚህ የማስተማሪያ ጽሑፎች ማራኪ የሆኑ በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሶች ይዘዋል። ከእነዚህም ውስጥ “እውነተኛው አምላክ ማን ነው?” “አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ?” “እውነተኛውን ሃይማኖት ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?” “የምንኖረው በመጨረሻው ቀን ነው!” እና “አምላክን የሚያስከብር ቤተሰብ መመሥረት” የሚሉት ይገኙበታል። እያንዳንዱ ርዕስ በርካታ ጥቅሶች ይዟል።

እነዚህንና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮችን የሚመለከት ነጻ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግልህ የምትፈልግ ከሆነ በአካባቢህ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች ማነጋገርም ሆነ በዚህ መጽሔት ገጽ 2 ላይ ወደሚገኘው አድራሻ መጻፍ ትችላለህ።

[ሥዕል]

በተወሰኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሶች ላይ በማተኮር የተማሪህን ልብ ለመንካት ጣር

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስ የናሙና ጸሎት ትርጉም ምን እንደሆነ ታውቃለህ?

“በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ . . .”

“[መሲሐዊ] መንግሥትህ ትምጣ . . .”

“ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን”