በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነት በማገናዘብ ችሎታ ላይ መመሥረት አለበትን?

እምነት በማገናዘብ ችሎታ ላይ መመሥረት አለበትን?

እምነት በማገናዘብ ችሎታ ላይ መመሥረት አለበትን?

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኝ የአንድ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ዲን “መመራመር ስለማይፈልጉ ብቻ አንድን ሃይማኖት በጭፍን የሚከተሉ በጣም ብዙ ሃይማኖተኛ ሰዎች አሉ” በማለት ጽፈዋል። አክለውም “ሁሉንም ነገር ‘ሳያገናዝቡ ያላንዳች ማስረጃ’ ይቀበላሉ” ብለዋል።

ይህም ሃይማኖት እንዳላቸው የሚናገሩ አብዛኞቹ ሰዎች የሚያምኑትን ነገር ለምን እንደሚያምኑበት ለማወቅም ሆነ እምነታቸው ትክክለኛ መሠረት ይኑረው አይኑረው ለመመርመር ብዙም ግድ እንደሌላቸው ይጠቁማል። ሃይማኖት ብዙዎች ለማንሳት የማይፈልጉት ርዕሰ ጉዳይ መሆኑ ምንም አያስደንቅም።

የሚያሳዝነው ሃይማኖታዊ ምስሎችን እንደመጠቀምና ጸሎትን በቃል እን​ደመድገም ያሉ ልማዶችም ቢሆኑ የማ​ገናዘብ ችሎታን መጠቀም የሚጠይቁ አይደሉም። በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ሃይማኖት ማለት ከእነዚህ ልማዶች ጋር ተዳምሮ ድንቅ የምህንድስና ጥበብ ከተንጸባረቀባቸው ሕንጻዎች፣ በተለያዩ ሥዕሎች ካሸበረቁ መስታወቶችና ስሜት ከሚያነሳሱ ሙዚቃዎች ያለፈ ትርጉም የለውም ለማለት ይቻላል። አንዳንድ ቤተ ክርስቲያኖች እምነታችን የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው ይበሉ እንጂ ‘በኢየሱስ እመን ትድናለህ’ የሚለው መልእክታቸው መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ የማጥናትን አስፈላጊነት አያበረታታም። ሌሎች ደግሞ ማኅበራዊ አሊያም ፖለቲካዊ ወንጌል ወደ መስበክ ዞር ይላሉ። ታዲያ የዚህ ሁሉ ውጤት ምንድን ነው?

አንድ የሃይማኖት ጸሐፊ በሰሜን አሜሪካ ያለውን ሁኔታ ሲገልጹ “ክርስትና . . . ተዳክሟል። ተከታዮቹም ስለ እምነታቸው በቂ እውቀት የላቸውም” ብለዋል። አንድ የሕዝብ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስን “የመጽሐፍ ቅዱስ መሃይማን አገር” ብለው እስከ መግለጽ ደርሰዋል። እውነቱን ለመናገር እነዚህ አስተያየቶች ክርስቲያን ነን በሚሉ በሌሎች አገሮችም ይሠራሉ። በተመሳሳይም ከክርስትና ውጭ ያሉ ብዙ ሃይማኖቶች መመራመርን አያበረታቱም። ይልቁንም አበክረው የሚያበረታቱት ዝማሬዎችን፣ ልማዳዊ የጸሎት ሥነ ሥርዓቶችን እንዲሁም ምክንያታዊና ገንቢ አስተሳሰብ ሳይሆን ምሥጢራዊነት የሚንጸባረቅባቸውን የተለያዩ የማሰላሰል ልማዶች ነው።

ይሁን እንጂ የሃይማኖታቸው ትክክለኛነት ወይም እውነተኛነት ብዙም የማያሳስባቸው እነዚሁ ሰዎች ብዙውን ጊዜ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ሌሎች ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ያጤኗቸዋል። አንድ ቀን ቆሻሻ መጣያ የሚወድቅ መኪና ለመግዛት ከፍተኛ ምርምር የሚያካሂድ ሰው ሃይማኖቱን በተመለከተ ‘ለወላጆቼ ጥሩ ከነበረ ለእኔም ጥሩ ነው’ ብሎ ሲናገር ብትሰማው በሁኔታው አትገረምም?

አምላክን ከልባችን ማስደሰት የምንፈልግ ከሆነ ስለ እርሱ የምናምነውን ነገር ትክክለኛነት በቁም ነገር ማሰብ አይኖርብንም? ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ትክክለኛ እውቀት ሳይኖራቸው ለእግዚአብሔር ይቀኑ’ ስለነበሩ አንዳንድ የዘመኑ ሃይማኖታዊ ሰዎች ጽፏል። (ሮሜ 10:​2) እንደነዚህ ያሉት ሰዎች የባለቤቱን መመሪያ በትክክል ሳያዳምጥ ቤቱን የተሳሳተ ቀለም ለመቀባት ከሚጥር ቀለም ቀቢ ጋር ይመሳሰላሉ። ቀለም ቀቢው በሥራው ሊደሰት ቢችልም እንኳ ሥራው በባለቤቱ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል?

እውነተኛ አምልኮን በተመለከተ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ [“የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ፣” NW ] በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው” በማለት መልሱን ይሰጣል። (1 ጢሞቴዎስ 2:​3, 4) አንዳንዶች ዛሬ ካሉት ብዙ ሃይማኖቶች አንጻር እንዲህ ያለውን ትክክለኛ እውቀት ማግኘት አይቻልም ብለው ያስቡ ይሆናል። ግን እስቲ አስበው፣ የአምላክ ፈቃድ ሰዎች ሁሉ ትክክለኛውን የእውነት እውቀት እንዲያገኙ ከሆነ አምላክ ሆን ብሎ ይህንን እውቀት የሚደብቅባቸው ይመስልሃል? “[አምላክን] ብትፈልገው ታገኘዋለህ” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል መሠረት እንደዚያ አያደርግም።​—⁠1 ዜና መዋዕል 28:​9

ታዲያ አምላክ በቅን ልቦና ተነሳስተው ለሚፈልጉት ራሱን የሚገልጠው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ መልሱን ይሰጣል።