በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዕድሜያቸው እንዳይማሩ አላገዳቸውም

ዕድሜያቸው እንዳይማሩ አላገዳቸውም

ዕድሜያቸው እንዳይማሩ አላገዳቸውም

ክሴንያ የተወለዱት በ1897 ነው። ሦስት ሴቶችና አንድ ወንድ ልጅ፣ 15 የልጅ ልጆች እንዲሁም 25 የልጅ ልጅ ልጆች አሏቸው። ሕይወታቸውን ሙሉ ወላጆቻቸው እንዲያደርጉ ያስተማሯቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ወደ ሞስኮ የመጡት በጦርነት ከታመሰችው አብኮስ የተባለች በጥቁር ባህርና በኮከሰስ መካከል የምትገኝ ሪፑብሊክ ተሰድደው ቢሆንም በሕይወታቸው በተለይም ከወላጆቼ የወረስኩት እምነት ብለው በሚጠሩት ሃይማኖታቸው ረክተው ይኖሩ ነበር።

በ1993 የክሴንያ ሴት ልጅ ሜሪ የይሖዋ ምሥክር ትሆናለች። ሜሪ ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለክሴንያ ትነግራቸው ጀመር፤ ክሴንያ ግን ሊያዳምጧት አልፈለጉም። “በዚህ ዕድሜዬ አዲስ ነገር መማር አልችልም” ይሏት ነበር።

ያም ሆኖ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑት የቤተሰባቸው አባላት ማለትም ሴት ልጃቸው ሜሪ፣ የልጅ ልጃቸው ሚስት ሎንዳ እና የልጅ ልጅ ልጆቻቸው ናና እና ዛዛ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግሯቸው ነበር። በ1999 አንድ ምሽት ላይ ያነበቡላቸው ጥቅስ ልባቸውን ነካው። ጥቅሱ ኢየሱስ የጌታ እራትን ሲያቋቁም ለታማኝ ሐዋርያቱ የተናገራቸውን ቀስቃሽ ቃላት የያዘ ነበር። (ሉቃስ 22:19, 20) ክሴንያ፣ በዚያ ምሽት በ102 ዓመታቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ወሰኑ።

ክሴንያ እንዲህ ይላሉ:- “ለ102 ዓመታት ከኖርኩ በኋላ በመጨረሻ የሕይወትን ዓላማ ተረዳሁ። አሁን ድንቅና አፍቃሪ የሆነውን አምላካችንን ይሖዋን ከማገልገል የተሻለ ምንም ነገር እንደሌለ ተገንዝቤያለሁ። አሁንም ንቁና ጤናማ ነኝ። መነጽር ሳላደርግ ማንበብ እንዲሁም ከቤተሰቤ ጋር እንደልቤ መጫወት እችላለሁ።”

ክሴንያ ኅዳር 5, 2000 ተጠመቁ። እንዲህ ይላሉ:- “ይሖዋን በፍቅር ተገፋፍቼ ለማገልገል ሕይወቴን ሰጥቼዋለሁ። በቤቴ አቅራቢያ ባለው የአውቶቡስ ማቆሚያ ተቀምጬ መጽሔቶችንና ትራክቶችን አበረክታለሁ። ብዙውን ጊዜ ዘመዶቼ ሊጠይቁኝ ይመጣሉ፤ እኔም ደስ እያለኝ ስለ ይሖዋ እውነቱን አካፍላቸዋለሁ።”

ክሴንያ ‘ሥጋቸው እንደ ሕፃን ሥጋ የሚለመልምበትንና ወደ ጉብዝናቸው ዘመን የሚመለሱበትን’ ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። (ኢዮብ 33:25) ከመቶ ዓመት በላይ የሆናቸው ሴት የሕይወትን ዓላማ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለመማር ዕድሜያቸው ካላገዳቸው አንተስ?