በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለአሁንም ሆነ ለዘላለም መተማመኛ ማግኘት

ለአሁንም ሆነ ለዘላለም መተማመኛ ማግኘት

ለአሁንም ሆነ ለዘላለም መተማመኛ ማግኘት

መተማመኛ የሚሆን ነገር ማግኘት ይህን ያክል አስቸጋሪ የሆነውና ቢገኝም እንኳ ዘለቄታ የማይኖረው ለምንድን ነው? ምናልባት የተማመንበት ነገር ሊደረስበት የማይችል ከዚያ ይልቅ በምናባችን ፈጥረን የምንመኘው ነገር ስለሆነ ይሆን? እንዲህ ያለው ከንቱ ምኞት በሕልም ዓለም መኖር ተብሎ ሊጠራ ይችላል።

ምናብ፣ አእምሮ መከራና ጭንቀት ከሞላው ከገሃዱ ዓለም በመሸሽ በሕልም ዓለም ፍስሃ ወደሞላበት ውብና ሰላማዊ ወደሆነ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ በገሃዱ ዓለም ያሉት ችግሮች በሕልም ዓለም ውስጥ የሚዋኘውን ሰው ያባንኑትና እውነታውን እንዲጋፈጥ በማድረግ የደህንነት ስሜቱን ያጠፉበታል።

እስቲ ሰዎች መተማመኛ ይሆነኛል ብለው የሚያስቡትን አንዱን መስክ ይኸውም የመኖሪያ አካባቢን እንመልከት። ለምሳሌ ያህል ትልቅ ከተማ ተስፋ የሚጣልበት፣ ደስ የሚል ሕይወት የሚመራበት፣ ገንዘብ የሚታፈስበት፣ የተንደላቀቀ የመኖሪያ ቤቶች የሚገኙበት መስሎ ይታይ ይሆናል። አዎን፣ ይህ ዘላቂ የሆነ አስተማማኝ ሕይወት የሚያስገኝ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ሕልም እውን ሊሆን ይችላልን?

የመኖሪያ አካባቢ —⁠ትልቅ ከተማ ወይስ ትልቅ ሕልም?

በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች የሚነገሩ ማስታወቂያዎች የትልቅ ከተማን ኑሮ ማራኪ አድርገው በማቅረብ ወደዚያ የመሄድን ፍላጎት ያነሳሳሉ። እንደዚህ ያለውን ማስታወቂያ የሚያዘጋጁ ድርጅቶች ይህን የሚያደርጉት ለአንተ ኑሮ አስበው ሳይሆን ለራሳቸው ገበያ ሲሉ ነው። በገሃዱ ዓለም ያሉትን ችግሮች በመደበቅ የተደላደለ ኑሮን የሚያሳዩ ማስታወቂያዎችን ያቀርባሉ። በዚህ መንገድ ዋስትና ያለውን ሕይወት እነርሱ ከሚያስተዋውቁት ሸቀጥና ከትልቅ ከተማ ኑሮ ጋር ለማያያዝ ይሞክራሉ።

እስቲ የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት። የአንዲት የምዕራብ አፍሪካ ዋና ከተማ ባለ ሥልጣናት ማጨስ በብዙ ልፋት የተገኘን ገንዘብ ቃል በቃል ከማቃጠል በምንም እንደማይለይ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳዩ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን ሰቀሉ። ሲጋራ ማጨስ አደገኛ መሆኑን ዜጎቻቸውን ለማስጠንቀቅ ከሚጠቀሙበት ዘመቻ መካከል ይህ አንዱ መንገድ ነበር። ሲጋራ አምራች ኩባንያዎችና ሻጮች በበኩላቸው የሰዎችን ቀልብ የሚስቡ ደስተኛና ስኬታማ ሕይወት የሚመሩ አጫሾችን የሚያሳይ የማስታወቂያ ሰሌዳ ሰቀሉ። ከዚህም በተጨማሪ አንድ ሲጋራ አምራች ኩባንያ አንዳንድ ሠራተኞቹ ምርጥ ልብስ እንዲለብሱና የቤዝቦል ተጫዋቾች የሚያደርጉት ዓይነት ቄንጠኛ ቆብ እንዲያጠልቁ በማድረግ በመንገድ ላይ የሚያገኙትን ወጣት ሁሉ “ሞክረው” እያሉ በማበረታታት ሲጋራ እንዲያድሉ አደረገ። ከእነዚህ ወጣቶች መካከል ብዙዎቹ ከገጠራማ መንደሮች የመጡና ግብዣው ለማጥመጃነት የተዘጋጀ የማስታወቂያ ዘዴ መሆኑን ለይተው የማያውቁ ገራገሮች ናቸው። የኋላ ኋላ ኃይለኛ አጫሾች ሆኑ። የገጠር ወጣቶች ወደ ትልቅ ከተማ የመጡት ለራሳቸው አልፎላቸው ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ወይም ደህና ገንዘብ ለማጠራቀም ነበር። ሆኖም ለተሻለ ዓላማ ሊያውሉት የሚችሉትን አብዛኛውን ገንዘብ ያለአግባብ ያጠፉታል።

በትልቅ ከተማ ስኬታማ ሕይወት ይገኛል በማለት ወሬ የሚነዙት ነጋዴዎች ብቻ አይደሉም። ወደ ትልቅ ከተማ ሄደው ወደ ትውልድ መንደራቸው መመለስ ያሳፈራቸው ሰዎችም ተመሳሳይ ወሬ ሊያናፍሱ ይችላሉ። ያልተሳካላቸው መሆኑ እንዲታወቅባቸው ስለማይፈልጉ በከተማ ውስጥ ሃብትና ስኬት እንዳገኙ በማስመሰል በጉራ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ኑሯቸውን ላየው ከትውልድ መንደራቸው ምንም የተሻሻለ ነገር የለውም። እንደ አብዛኛው የከተማ ነዋሪ ሁሉ እነርሱም የገንዘብ ችግር አለባቸው።

በትልቅ ከተማ ውስጥ ይሉኝታ በሌላቸው ሰዎች ወጥመድ በቀላሉ የሚወድቁት ቢያልፍልን ብለው የሚመጡ የገጠር ሰዎች ናቸው። ለምን? በአብዛኛው የቅርብ ወዳጅ ለመመሥረት በቂ ጊዜ ስላላገኙና ከቤተሰባቸውም ርቀው ስለሚኖሩ ነው። ስለሆነም በፍቅረ ነዋይ ከተያዘው የከተማ ኑሮ ስውር ወጥመድ እንዲጠነቀቁ የሚረዳቸው መካሪ የላቸውም።

ዦዝዌ ሲጋራ እንዲያጨስ ለቀረበለት ማባበያ አልተሸነፈም። ከዚህም በተጨማሪ የከተማ ኑሮ የሚጠይቃቸውን ነገሮች አሟልቶ መኖር እንደማይችል ተገነዘበ። በእርሱ በኩል ከከተማ ያተረፈው ነገር ቢኖር እውን ሊሆን ያልቻለ ትልቅ ሕልም ብቻ ነው። ከተማ በመኖር እውነተኛ መተማመኛ ማግኘት እንደማይችል ተገነዘበ፤ ለእርሱ የሚሆን ቦታ ሆኖ አላገኘውም። የባዶነት፣ የበታችነትና የሽንፈት ስሜት ተሰማው። በመጨረሻ ኩራቱን ዋጥ አድርጎ ወደ ትውልድ ቀዬው ተመለሰ።

መሳለቂያ እሆናለሁ ብሎ ፈርቶ ነበር። በተቃራኒው ግን ቤተሰቦቹና እውነተኛ ጓደኞቹ እጃቸውን ዘርግተው ተቀበሉት። ሞቅ ያለ መንፈስ ላለው ቤተሰቡ፣ መውጪያ መግቢያውን ለሚያውቀው መንደሩና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ወዳጆቹ ላሳዩት ፍቅር ምስጋና ይግባውና ብዙም ሳይቆይ የብዙዎች ሕልም ቅዠት ሆኖ በቀረበት በትልቅ ከተማ ውስጥ ከተሰማው በእጅጉ የሚበልጥ ደህንነት ተሰምቶታል። የሚያስገርመው ደግሞ ከአባቱ ጋር በእርሻ ውስጥ ጠንክሮ መሥራቱ ከተማ ቆይቶ ቢሆን ኖሮ ያገኘው ከነበረው የተጣራ ገቢ የሚበልጥ ገንዘብ ለእርሱም ሆነ ለቤተሰቡ አስገኝቶለታል።

ገንዘብ​—⁠ዋነኛው ችግር ምንድን ነው?

ገንዘብ መተማመኛ ሊሆንልህ ይችላልን? በካናዳ የምትኖረው ሊዝ “ወጣት በነበርኩበት ጊዜ ገንዘብ ከጭንቀት ነጻ ያደርጋል ብዬ አስብ ነበር” በማለት ተናግራለች። ደህና ገንዘብ ካለው ከአንድ ሰው ፍቅር ይይዛትና ብዙም ሳይቆይ ተጋቡ። አሁንስ ከጭንቀት ነጻ ሆና መኖር ችላ ይሆን? ሊዝ በመቀጠል እንዲህ ትላለች:- “ያገባሁ ጊዜ አንድ ቆንጆ ቤትና ሁለት መኪናዎች ነበሩን። ደግሞም ያለን ገንዘብ በቁሳዊ ነገሮች፣ በጉዞና በመዝናኛ ረገድ ዓለም በሚያቀርባቸው ነገሮች ሁሉ የመደሰት ነፃነት ሰጥቶን ነበር። የሚያስገርመው ግን እንደዚያም ሆኖ ስለ ገንዘብ እጨነቅ ነበር።” ይህ ለምን እንደሆነ ስታብራራ:- “ብዙ ያጣነው ነገር ነበር። ብዙ ባለህ መጠን የዚያኑ ያህል ለአደጋ የተጋለጥህ እንደሆነ ይሰማሃል። ገንዘብ ከጭንቀትም ሆነ ከስጋት ነጻ አያደርግም” ብላለች።

መተማመኛ ይሆነኛል የምትለው በቂ ገንዘብ እንደሌለህ ሆኖ ከተሰማህ ‘ዋነኛው ችግር ምንድን ነው? የገንዘብ እጥረት ነው ወይስ የገንዘብ አያያዝ ችሎታ ማጣት?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ሊዝ የድሮ ሕይወቷን መለስ ብላ በማስታወስ እንዲህ ትላለች:- “ትንሽ ልጅ በነበርኩበት ጊዜ ለቤተሰባችን ችግር ዋነኛው መንስዔ የገንዘብ አያያዝ ችሎታ ማጣት መሆኑን አሁን ተረድቼዋለሁ። እቃ በዱቤ እንወስድ ስለነበር ዕዳ አያጣንም ነበር። ይህ ደግሞ ጭንቀት አስከትሎብናል።”

ይሁን እንጂ ዛሬ ሊዝ እና ባለቤትዋ ያላቸው ገንዘብ አነስተኛ ቢሆንም ከምንጊዜውም የበለጠ የመተማመን ስሜት ይሰማቸዋል። የአምላክን ቃል እውነት ሲማሩ ስለ ገንዘብ የሚነገሩ የማባበያ ወሬዎችን መስማት አቁመው “የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል፣ ከመከራም ሥጋት ያርፋል” የሚሉትን ቃላት ጨምሮ የአምላክን ጥበብ ማዳመጥ ጀመሩ። (ምሳሌ 1:​33) ባንክ የተቀመጠ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ሊሰጥ ከሚችለው የበለጠ ሕይወታቸው ትርጉም እንዲኖረው ፈለጉ። አሁን ሊዝ እና ባለቤትዋ ርቆ በሚገኝ አንድ አገር ውስጥ ሚስዮናውያን ሆነው በማገልገል ይሖዋ አምላክ በቅርቡ እውነተኛ ዓለም አቀፍ ዋስትና ያለው ሕይወት እንደሚያመጣ ሃብታም ድሃ ሳይሉ ሁሉንም ሰዎች በማስተማር ላይ ይገኛሉ። ይህ ሥራ ከተሻለ ዓላማና ከላቁ መሠረታዊ ሥርዓቶች ካልሆነ በስተቀር ከሃብት ሊመነጭ የማይችል ጥልቅ እርካታና መረጋጋት ያስገኛል።

ይህን መሠረታዊ እውነት አስታውስ:- በአምላክ ዘንድ ባለጠጋ መሆን ቁሳዊ ሃብት ከማካበት በእጅጉ የሚበልጥ ዋጋ አለው። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ጎላ ተደርጎ የተገለጸው ቁሳዊ ሃብት ማካበት ሳይሆን መለኮታዊውን ፈቃድ በእምነት ያለማቋረጥ በማድረግ በይሖዋ ፊት ጥሩ አቋም መያዝ ነው። ክርስቶስ ኢየሱስ ‘በአምላክ ዘንድ ባለ ጠጋ’ በመሆን ‘በሰማይ መዝገብ’ እንድንሰበስብ ማበረታቻ ሰጥቶናል።​—⁠ሉቃስ 12:​21, 33

የኑሮ ደረጃ​—⁠ሩጫው የት ለመድረስ ነው?

በኅብረተሰቡ ውስጥ ከፍ ያለ የኑሮ ደረጃ ላይ መድረስ ዋስትና ያለው ሕይወት ያስገኛል በሚል ስሜት ተሸንፈህ ከሆነ ‘እውነተኛ ዋስትና ያለው ሕይወት የሚመሩት በየትኛው ደረጃ ላይ የሚገኙት ሰዎች ናቸው? እዚህ ቦታ ላይ ለመድረስ ምን ያህል ደረጃ መውጣት ይኖርብኛል?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ያገኘኸው ስኬታማ የሆነ ሥራ የተሳሳተ የመተማመን ስሜት እንዲሰማህ በማድረግ ወደ ብስጭት አልፎ ተርፎም ለውድቀት ሊዳርግህ ይችላል።

የሰዎች እውነተኛ ተሞክሮ እንደሚያሳየው በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም ማትረፍ በሰው ዘንድ ጥሩ ስም ማትረፍ ሊያስገኝ ከሚችለው በእጅጉ የሚበልጥ የመተማመን ስሜት ያስገኛል። ለሰዎች የዘላለም ሕይወት መስጠት የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። ይህ በማኅበረሰቡ ውስጥ ባለ የማንነት መግለጫ መዝገብ ላይ ሳይሆን በአምላክ የሕይወት መጽሐፍ ላይ ስማችንን መጻፍ ይጨምራል።​—⁠ዘጸአት 32:​32፤ ራእይ 3:​5

ምኞትን ወደ ጎን ገሸሽ ብታደርግ አሁን ስላለህበት ሁኔታ ለራስህ የምትሰጠው ግምት ምንድን ነው? ከወደፊቱ ጊዜስ ምን ትጠብቃለህ? ሁሉም ነገር ያለው ማንም ሰው የለም። ሁኔታው “ሕይወት ይህ ወይም ያ እንጂ ይህ እና ያ ሊሆን እንደማይችል መማር ነበረብኝ” በማለት አንድ አስተዋይ ክርስቲያን እንዳስቀመጠው ነው። እስቲ ለአንድ አፍታ ቆም በልና “በቤኒን የተነገረ” የሚለውን ሣጥን አንብብ።

አሁን ደግሞ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ስጥ:- በሕይወቴ ውስጥ ዋነኛ ግብ አድርጌ የያዝኩት ነገር ምንድን ነው? እዚያ ደረጃ ላይ ለመድረስ ከሁሉ የተሻለው ቀጥተኛ መንገድ የትኛው ነው? ምናልባት ከልብ የምፈልገውና በቀላሉ ሊገኝ የሚችለውን ነገር እምብዛም ባልተወሳሰበ መንገድ ማግኘት ስችል ረጅምና አደገኛ በሆነ መንገድ ለማግኘት ሙከራ እያደረግኩ ይሆን?

ኢየሱስ ቁሳዊ ነገሮች ያላቸውን አንጻራዊ ጠቀሜታ መንፈሳዊ ነገሮች ካላቸው ጠቀሜታ ጋር በማወዳደር ምክር ከሰጠ በኋላ ዓይንህ “ቀና” ይሁን በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:​22 NW ) በሕይወት ውስጥ ዋነኞቹ ነገሮች በአምላክ ስምና በመንግሥቱ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መንፈሳዊ እሴቶች መሆናቸውን በግልጽ ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:​9, 10) ሌሎች ነገሮች ከዚያ ያነሰ ጠቀሜታ ያላቸው ወይም ከትኩረት አድማሳችን ውጪ ናቸው።

ዛሬ ያሉ ብዙ ካሜራዎች ሩቅም ሆነ ቅርብ ባሉ ነገሮች ላይ ራሳቸው በራሳቸው ማነጣጠር ይችላሉ። አንተም እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ አለህ? የምታየው ነገር ሁሉ ጠቃሚ፣ ተፈላጊና በአንድ ዓይነት ምኞት በቀላሉ ሊገኝ እንደሚችል ሆኖ ይሰማሃልን? እንዲህ ያለው ችግር በከፊል ቢኖርብህ እንኳ የምታየው ነገር ሁሉ ትኩረትህን ሊስብና ለክርስቲያኖች በጣም አስፈላጊ ከሆነው ምስል ይኸውም ከመንግሥቱ በቀላሉ ዞር ሊያደርግህ ይችላል። ኢየሱስ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” በማለት ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።​—⁠ማቴዎስ 6:​33

ለአሁንም ሆነ ለዘላለም መተማመኛ ማግኘት

ሁላችንም ብንሆን ለራሳችንም ሆነ ለምንወዳቸው ሰዎች የተሻለ ነገር እንመኝ ይሆናል። ይሁን እንጂ ፍጹም አለመሆናችን፣ ፍጽምና በጎደለው ዓለም ውስጥ የምንኖር መሆናችንና የምንኖርበት የሕይወት ዘመን አጭር መሆኑ እናገኘዋለን ብለን ተስፋ በምናደርጋቸው ነገሮች ላይ ገደብ እንድናበጅ ያስገድደናል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት እንዲህ በማለት ጽፏል:- “እኔም ተመለስሁ፣ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፣ ሰልፍም ለኃያላን፣ እንጀራም ለጠቢባን፣ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፣ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል።”​—⁠መክብብ 9:​11

አንዳንድ ጊዜ አሰልቺ በሆነ የሕይወት እሽክርክሪት ውስጥ እንገባና ማንነታችንንና እውነተኛ ደህንነት እንዳገኘን እንዲሰማን ምን እንደሚያስፈልገን እንዘነጋለን። እስቲ የሚከተሉትን ጥበብ የተሞላባቸውን ጥንታዊ ቃላት ልብ በል:- “ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም፤ ባለጠግነትንም የሚወድድ ትርፉን አይጠግብም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። እጅግ ወይም ጥቂት ቢበላ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው የባለጠጋ ጥጋብ ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል።” (መክብብ 5:​10, 12) አዎን መተማመኛ አድርገህ የምትመለከተው ምንን ነው?

አንተም እንደ ዦዝዌ እውን ሊሆን በማይችል የሕልም ዓለም ውስጥ የምትኖር ከሆነ ዕቅድህን መለወጥ ትችላለህ? የዦዝዌ ቤተሰቦችና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ጓደኞቹ እንዳደረጉት ከልብ የሚወዱህ ሰዎች ድጋፍ ያደርጉልሃል። ጉልበትህን ያላግባብ ከሚበዘብዙህ ሰዎች ጋር በከተማ ውስጥ ከመኖር ይልቅ በትንሿ መንደርህ ውስጥ ይህ ነው የማይባል ደህንነት ማግኘት ትችላለህ።

እንደ ሊዝ እና ባለቤትዋ ሁሉ አንተም በድሎት የምትኖር ከሆነ ሃብታምም ሆኑ ድሃ ሰዎች እውነተኛ ዋስትና ያለው ሕይወት ምንጭ ስለሆነው ስለ አምላክ መንግሥት እንዲያውቁ ለመርዳት የሚያስችልህን ተጨማሪ ጊዜና ጉልበት ለማግኘት በአኗኗርህ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ትችል ይሆን?

የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ለመድረስ ወይም የሥራ እድገት ለማግኘት በመጣጣር ላይ የምትገኝ ከሆነ ለዚያ ያነሳሳህ ውስጣዊ ግፊት ምን እንደሆነ ለማወቅ በሃቀኝነት ራስህን መርምር። እርግጥ ነው፣ የግል ምቾትህ በሕይወትህ ውስጥ ደስታን ይጨምርልህ ይሆናል። ሆኖም ትኩረትህን ዘላቂ ደህንነት ለማግኘት እውነተኛ ምንጭ በሆነው በአምላክ መንግሥት ላይ ማሳረፍ ትችላለህ? “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” የሚሉትን የኢየሱስን ቃላት አስታውስ። (ሥራ 20:​35) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች የምትሳተፍ ከሆነ መልሶ የሚክስ ዋስትና ያለው ሕይወት ታገኛለህ።

በይሖዋና በመንግሥቱ ላይ ሙሉ በሙሉ የሚታመኑ ሰዎች አሁን ስጋት የሌለበት አስደሳች ሕይወት ይመራሉ፤ ወደፊት ደግሞ የተሟላ ደህንነት ለማግኘት ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ። መዝሙራዊው “ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ፤ በቀኜ ነውና አልታወክም። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው ምላሴም ሐሴት አደረገች፤ ሥጋዬ ደግሞ በተስፋ ታድራለች” በማለት ተናግሯል።​—⁠መዝሙር 16:​8, 9

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በቤኒን የተነገረ

ይህ ታሪክ ለበርካታ ጊዜያት በተለያዩ መንገዶች ሲነገር ቆይቷል። በቅርቡ በምዕራብ አፍሪካ በአንዲት የቤኒን መንደር ለረዥም ዓመት የኖሩ አንድ ሰው ለአንዳንድ ወጣቶች ይህን ታሪክ እንደሚከተለው ሲሉ አጫውተዋቸው ነበር:-

አንድ ዓሣ አጥማጅ በታንኳ ወደ ቤቱ ሲመለስ ለሥራ ጉዳይ ወደዚች ታዳጊ አገር ከመጣ ከአንድ ኤክስፐርት ጋር ይገናኛል። ኤክስፐርቱ ለምን ቶሎ እንደተመለሰ ዓሣ አጥማጁን ይጠይቀዋል። ብዙ መቆየት ይችል እንደነበረ ሆኖም ለቤተሰቡ የሚበቃውን ያህል ስላጠመደ እንደተመለሰ ይነግረዋል።

“ታዲያ ከዚህ በኋላ ምን ስትሠራ ትውላለህ?” ሲል ኤክስፐርቱ ይጠይቀዋል።

ዓሣ አጥማጁ “ለትንሽ ጊዜ ዓሣ አጠምዳለሁ። ከልጆቼ ጋር እጫወታለሁ። የፀሐዩ ሙቀት ሲበረታ ሁላችንም ጥቂት እንተኛለን። ሲመሽ አንድ ላይ ሆነን እራት እንበላለን። በኋላም ከጓደኞቼ ጋር ተሰባስበን እየዘፈንን እንጨፍራለን። እንዲሁም . . .።”

ኤክስፐርቱ በመሃል ያቋርጠውና “ተመልከት፣ እኔ የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ያለኝ ሲሆን ስለዚህ ጉዳይ አጥንቻለሁ። ልረዳህ እፈልጋለሁ። ረዘም ላለ ሰዓት ዓሣ ማጥመድ ይኖርብሃል። ከዚህ የበለጠ ገንዘብ ታገኝና ብዙም ሳይቆይ ከዚህች ታንኳ የሚበልጥ ሌላ ጀልባ ትገዛለህ። በምትገዛው ትልቅ ጀልባ ተጨማሪ ገንዘብ ታገኝና ብዙም ሳይቆይ ትላልቅ የዓሣ ማጥመጃ መረቦች ይኖሩሃል።”

“ከዚያስ?” በማለት ዓሣ አጥማጁ ይጠይቀዋል።

“ከዚያም የምታጠምደውን ዓሣ ለነጋዴ ከምታስረክብ ቀጥታ ከፋብሪካው ጋር መዋዋል ወይም የራስህን የዓሣ ሰርዲን ማምረቻ ፋብሪካ መገንባት ትችላለህ። ወደ ኮትኑ ወይም ፓሪስ ወይም ኒው ዮርክ ሄደህ ከዚያ ሥራውን ማካሄድ ትችላለህ። እንዲያውም ምርትህ በዓለም ገበያ ውስጥ ይቀርብና ሚልዮነር ትሆናለህ።”

ዓሣ አጥማጁ “እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?” በማለት ይጠይቃል።

“ምናልባት ከ15 እስከ 20 ዓመታት” ሲል ኤክስፐርቱ ይመልስለታል።

“ከዚያ በኋላስ?” ዓሣ አጥማጁ ጥያቄውን ይቀጥላል።

“ያን ጊዜማ አርፈህ ተቀምጠህ ዓለምህን ትቀጫለህ” በማለት ያብራራለታል። “ሩጫና ግርግር የበዛበትን የከተማ ኑሮ ትተህ ራቅ ወዳለ አንድ መንደር ሄደህ መኖር ትችላለህ።”

“ከዚያ በኋላስ?” በማለት ዓሣ አጥማጁ ይጠይቃል።

“ከዚያ በኋላማ ለትንሽ ጊዜ ዓሣ ታጠምዳለህ፣ ከልጆችህ ጋር ትጫወታለህ፣ የቀኑ ሙቀት እየበረታ ሲመጣ ትንሽ ትተኛለህ፣ ከቤተሰብህ ጋር አንድ ላይ እራት ትበላለህ እንዲሁም ከጓደኞችህ ጋር እየዘፈንክ ትጨፍራለህ።”

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሥራ እድገት መተማመኛ ሊሆን ይችላል?

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የእምነት ባልንጀሮችህ ስለ ደህንነትህ ከልብ ያስባሉ