በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መለኮታዊ ሕጎች የተሰጡን ለጥቅማችን ነው

መለኮታዊ ሕጎች የተሰጡን ለጥቅማችን ነው

መለኮታዊ ሕጎች የተሰጡን ለጥቅማችን ነው

“ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ!”​—⁠መዝሙር 119:​97

1. መለኮታዊ ሕጎችን መታዘዝን በተመለከተ ተስፋፍቶ የሚገኘው አመለካከት ምንድን ነው?

 በዛሬው ጊዜ መለኮታዊ ሕጎችን መታዘዝ ተቀባይነት እያጣ መጥቷል። ብዙዎች ለአንድ የማይታይ ከፍተኛ ባለሥልጣን መገዛት ትርጉም የለሽ እንደሆነ ይሰማቸዋል። የምንኖረው ተለዋዋጭ የሥነ ምግባር ደንቦች ባሉበትና ትክክልና ስህተት በሆነው መካከል ያለው ልዩነት ግልጽ ባልሆነበት ዘመን ውስጥ ነው። (ምሳሌ 17:​15፤ ኢሳይያስ 5:​20) በቅርቡ የተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት “አብዛኞቹ አሜሪካውያን ትክክል፣ ጥሩና ተገቢ የሆነውን ነገር ለራሳቸው መወሰን ይፈልጋሉ” ሲል በመጥቀስ ከሃይማኖት የራቁ ብዙ ኅብረተሰቦች የሚጋሩትን አስተሳሰብ ገልጿል። “ጥብቅ የሆነ አምላክ አይፈልጉም። ጥብቅ መመሪያ አይፈልጉም። ጥብቅ የሆነ የሥነ ምግባርም ሆነ ሌላ ዓይነት አቋም ያላቸውን አለቆች አይፈልጉም።” አንድ የማኅበራዊ ጉዳይ ተንታኝ በዛሬው ጊዜ “ግለሰቦች ጥሩ ሥነ ምግባር የተከተለ ንጹሕ ሕይወት መኖር ምን ማለት እንደሆነ ለራሳቸው እንዲወስኑ ይጠበቅባቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም “የትኛውም የበላይ ባለሥልጣን የሚያወጣው መመሪያ የሕዝቡን ፍላጎት ያገናዘበ መሆን አለበት” ብለዋል።

2. መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሕግ የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኝበት ዘገባ መለኮታዊ በረከትና ተቀባይነት ከማግኘት ጋር በቅርብ የሚዛመደው እንዴት ነው?

2 ብዙ ሰዎች የይሖዋ ሕጎች ያላቸውን ጠቀሜታ ስለሚጠራጠሩ መለኮታዊ መሥፈርቶች ለጥቅማችን የተዘጋጁ እንደሆኑ ያለንን ጽኑ እምነት ማጠናከር ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሕግ የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኝበትን ዘገባ መመርመሩ ትኩረት ይስባል። ዘፍጥረት 26:​5 ላይ “አብርሃም . . . ፍርዴን ትእዛዜን ሥርዓቴን ሕጌንም ጠብቆአልና” የሚሉትን የአምላክ ቃላት እናነብባለን። እነዚህ ቃላት የተነገሩት ይሖዋ ለአብርሃም ዘሮች ዝርዝር ሕግ ከመስጠቱ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ነበር። አምላክ፣ አብርሃም ለሕጉ ጭምር ላሳየው ታዛዥነት ወሮታ የከፈለው እንዴት ነበር? ይሖዋ አምላክ “የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ” ሲል ቃል ገባለት። (ዘፍጥረት 22:18) በመሆኑም መለኮታዊ ሕጎችን መታዘዝ መለኮታዊ በረከትና ተቀባይነት ከማግኘት ጋር በቅርብ ይዛመዳል።

3. (ሀ) አንድ መዝሙራዊ ለይሖዋ ሕግ ያለውን ስሜት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ትኩረታችንን የሚሹ ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?

3 የይሁዳ መስፍንና አልጋ ወራሽ እንደሆነ የሚገመት አንድ መዝሙራዊ በአመዛኙ ከሕግ ጋር በተያያዘ የማይጠቀስ አንድ ስሜት ገልጿል። “ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ!” ሲል የተሰማውን ጥልቅ ስሜት ለአምላክ ገልጿል። (መዝሙር 119:​97፤ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ይህ እንዲሁ በስሜታዊነት ተገፋፍቶ የተናገረው ነገር አይደለም። በሕጉ ላይ ለሠፈረው የአምላክ ፈቃድ ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ነበር። ፍጹም የሆነው የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስም ተመሳሳይ ስሜት ነበረው። ኢየሱስ “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፣ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው” ብሎ እንደተናገረ በትንቢታዊ ሁኔታ ተገልጿል። (መዝሙር 40:​8፤ ዕብራውያን 10:​9) የእኛስ ሁኔታ እንዴት ነው? የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ያስደስተናል? የይሖዋ ሕጎች ዋጋማና ጠቃሚ እንደሆኑ ጽኑ እምነት አለን? ለይሖዋ ሕጎች የምናሳየው ታዛዥነት በአምልኮታችን፣ በዕለታዊ ሕይወታችን፣ በምናደርገው ውሳኔ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ምን ቦታ አለው? መለኮታዊ ሕጎችን መውደድ እንድንችል አምላክ ሕግ ለማውጣትና ሕጎቹን ለማስከበር ያለውን መብት መገንዘባችን ተገቢ ነው።

ይሖዋ​—⁠ሕግ የመስጠት መብት ያለው ፈጣሪ

4. ይሖዋ ሕግ የማውጣት መብት ያለው የመጨረሻው ባለሥልጣን የሆነው ለምንድን ነው?

4 ይሖዋ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ሕግ የመስጠት መብት ያለው የመጨረሻው ባለሥልጣን ነው። (ራእይ 4:​11) ነቢዩ ኢሳይያስ “እግዚአብሔር ሕግን ሰጪያችን ነው” ብሏል። (ኢሳይያስ 33:​22) ሕይወት ያላቸውንም ሆኑ የሌላቸውን ፍጥረታት የሚቆጣጠሩ የተፈጥሮ ሕጎች ደንግጓል። (ኢዮብ 38:​4-38፤ 39:​1-12፤ መዝሙር 104:​5-19) ሰው የአምላክ ፍጥረት እንደመሆኑ መጠን ይሖዋ ላወጣቸው የተፈጥሮ ሕጎች ይገዛል። በተጨማሪም ሰው በራሱ ማመዛዘን የሚችል ነፃ ምርጫ ያለው ፍጡር ቢሆንም እንኳ ደስተኛ መሆን የሚችለው አምላክ ላወጣቸው ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ሕጎች ራሱን ሲያስገዛ ብቻ ነው።​—⁠ሮሜ 12:​1፤ 1 ቆሮንቶስ 2:​14-16

5. መለኮታዊ ሕጎችን በተመለከተ ገላትያ 6:​7 ላይ የሠፈረው መሠረታዊ ሥርዓት ትክክል ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው?

5 ሁላችንም እንደምናውቀው የይሖዋን የተፈጥሮ ሕጎች መጣስ አይቻልም። (ኤርምያስ 33:​20, 21) አንድ ሰው እንደ ስበት ሕግ ያሉትን የተፈጥሮ ሕጎች ከተጻረረ መዘዙን መቀበሉ የማይቀር ነው። በተመሳሳይ የአምላክ የሥነ ምግባር ሕጎች የማይለወጡ ከመሆኑም በላይ ሕጎቹን ገሸሽ አድርጎ ወይም ጥሶ ከቅጣት ማምለጥ አይቻልም። ውጤቱ ቅጽበታዊ ባይሆንም እንኳ የተፈጥሮ ሕጎችን ያህል መፈጸማቸው አይቀርም። “እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና።”​—⁠ገላትያ 6:7፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:​24

የይሖዋ ሕግ የሚያካትታቸው ነገሮች

6. መለኮታዊ ሕጎች ምን ያህል ስፋት አላቸው?

6 የሙሴ ሕግ ጉልህ ሥፍራ ያለው የመለኮታዊ ሕግ መግለጫ ነበር። (ሮሜ 7:​12) ከጊዜ በኋላ ይሖዋ አምላክ የሙሴን ሕግ ‘በክርስቶስ ሕግ’ ተካው። a (ገላትያ 6:⁠2፤ 1 ቆሮንቶስ 9:​21) ‘ነጻ በሚያወጣው ፍጹም ሕግ’ ሥር ያለን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን አምላክ የሚሰጠን መመሪያ እንደ መሠረታዊ የእምነት ትምህርቶች ወይም ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች በመሳሰሉ አንዳንድ የሕይወታችን ዘርፎች ላይ ብቻ የተገደቡ አለመሆናቸውን እንገነዘባለን። መሥፈርቶቹ የቤተሰብ ጉዳዮችን፣ የንግድ ግንኙነቶችን፣ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ባለን ግንኙነት ሊኖረን የሚገባውን ምግባር፣ ለክርስቲያን ወንድሞቻችን የሚኖረንን አመለካከት እንዲሁም በእውነተኛው አምልኮ የምናደርገውን ተሳትፎ ጨምሮ ሁሉንም የሕይወታችንን ዘርፎች ይዳስሳሉ።​—⁠ያዕቆብ 1:​25, 27

7. ጠቃሚ የሆኑ የመለኮታዊ ሕግ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

7 ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) አዎን፣ ሴሰኝነትና ምንዝር እንደ ቀላል ነገር የሚታዩ “የፍቅር ግንኙነቶች” አይደሉም። ግብረ ሰዶም ተራ የሆነ “አማራጭ የሕይወት ዘይቤ” አይደለም። እነዚህ የይሖዋን ሕግ የሚጻረሩ ተግባሮች ናቸው። እንዲሁም እንደ ስርቆት፣ ውሸትና ስም ማጥፋት የመሳሰሉ ነገሮችም ከዚህ ተለይተው አይታዩም። (መዝሙር 101:​5፤ ቆላስይስ 3:​9፤ 1 ጴጥሮስ 4:​15) ያዕቆብ ትምክህተኝነትን ያወገዘ ሲሆን ጳውሎስ ደግሞ የስንፍና ንግግርና ዋዛ ፈዛዛ እንድናስወግድ መክሮናል። (ኤፌሶን 5:​4፤ ያዕቆብ 4:​16) እነዚህ ሁሉ የሥነ ምግባር ደንቦች ክርስቲያኖች ሊከተሏቸው የሚገቡ ፍጹም የሆነው የአምላክ ሕግ ክፍል ናቸው።​—⁠መዝሙር 19:​7

8. (ሀ) የይሖዋ ሕግ ምን ዓይነት ባሕርይ አለው? (ለ) “ሕግ”ን ለማመልከት የተሠራበት የዕብራይስጥ ቃል የሚያስተላልፈው መሠረታዊ ትርጉም ምንድን ነው?

8 የይሖዋ ቃል የያዛቸው እንደዚህ የመሳሰሉ መሠረታዊ ደንቦች ሕጉ እንዲሁ ድርቅ ያለ፣ ጥብቅ የመመሪያዎች ዝርዝር ብቻ አለመሆኑን ያሳያሉ። ሕጉ በመላው አኗኗራችን ላይ በጎ ተጽዕኖ በማሳደር ሚዛናዊና አመርቂ ሕይወት እንድንኖር የሚያስችል መሠረት ይጥላል። መለኮታዊ ሕግ ገንቢ፣ ሥነ ምግባራዊና ትምህርት ሰጪ ነው። (መዝሙር 119:​72) መዝሙራዊው የተጠቀመበት “ሕግ” የሚለው ቃል ቶራ ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተተረጎመ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ ብለዋል:- “ይህ ቃል አቅጣጫ ማስያዝ፣ መምራት፣ ማነጣጠር፣ ወደፊት መተኮስ የሚል ሐሳብ ከሚያስተላልፍ ግስ የተገኘ ነው። በመሆኑም ቃሉ . . . የሥነ ምግባር ደንብ የሚል ትርጉም ይኖረዋል።” መዝሙራዊው ሕጉን ከአምላክ ያገኘው ስጦታ አድርጎ ተመልክቶታል። በተመሳሳይ እኛም ሕጉ አኗኗራችንን እንዲመራ በመፍቀድ ከፍ አድርገን ልንመለከተው አይገባም?

9, 10. (ሀ) አስተማማኝ መመሪያ ማግኘት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (ለ) አስደሳችና የተሳካ ሕይወት መኖር የምንችለው ምን ካደረግን ብቻ ነው?

9 ፍጡራን ሁሉ አስተማማኝ መመሪያና እምነት የሚጣልበት አመራር ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ይህ ከሰው በላይ የሆኑትን ኢየሱስንና ሌሎች መላእክትንም ይጨምራል። (መዝሙር 8:​5፤ ዮሐንስ 5:​30፤ 6:​38፤ ዕብራውያን 2:​7፤ ራእይ 22:​8, 9) እነዚህ ፍጹም የሆኑ ፍጡራን ከመለኮታዊ አመራር ከተጠቀሙ፣ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎችማ ምንኛ ይጠቀማሉ! የሰው ልጅ ታሪክና የግል ተሞክሯችን ነቢዩ ኤርምያስ ያስተዋለው ነገር ትክክል መሆኑን ይመሰክራል:- “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።”​—⁠ኤርምያስ 10:23

10 አስደሳችና የተሳካ ሕይወት መኖር ከፈለግን የአምላክን አመራር ለማግኘት መጣር አለብን። ንጉሥ ሰሎሞን ከመለኮታዊ አመራር ውጪ ራሳችን ባወጣነው መሥፈርት መኖር አደገኛ መሆኑን ተገንዝቧል:- “ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው።”​—⁠ምሳሌ 14:12

የይሖዋን ሕግ ከፍ አድርገን እንድንመለከት የሚገፋፉን ምክንያቶች

11. የአምላክን ሕግ የማስተዋል ፍላጎት ሊያድርብን የሚገባው ለምንድን ነው?

11 የይሖዋን ሕግ ለማስተዋል ጥልቅ ፍላጎት መኮትኮታችን አስፈላጊ ነው። መዝሙራዊው “ከሕግህ ድንቅ ነገርን እንዳይ፣ ዐይኖቼን ክፈት” ብሎ ሲናገር እንዲህ ዓይነት ጥልቅ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል። (መዝሙር 119:​18 አ.መ.ት) አምላክንና መንገዶቹን ይበልጥ ባወቅን መጠን “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ” የሚሉት የኢሳይያስ ቃላት እውነተኝነት የዚያኑ ያህል ግልጽ ይሆንልናል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ይሖዋ ሕዝቦቹ ለትእዛዙ ትኩረት በመስጠት ከአደጋ እንዲጠበቁና በሕይወት እንዲኖሩ ልባዊ ፍላጎት አለው። የአምላክን ሕግ ከፍ አድርገን መመልከት ያለብን ለምን እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ ዋና ዋና ምክንያቶችን እስቲ እንመርምር።

12. ይሖዋ ስለ እኛ ያለው እውቀት ከሁሉ የተሻለ ሕግ ሰጪ የሚያደርገው እንዴት ነው?

12 መለኮታዊ ሕግ የመጣው ከማንም በተሻለ ከሚያውቀን አካል ነው። ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን የሰው ልጆችን አሳምሮ እንደሚያውቅ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው። (መዝሙር 139:​1, 2፤ ሥራ 17:​24-28) የቅርብ ጓደኞቻችን፣ ዘመዶቻችን፣ አልፎ ተርፎም ወላጆቻችን የይሖዋን ያህል ሊያውቁን አይችሉም። እንዲያውም አምላክ እኛ ራሳችንን ከምናውቀው በተሻለ ያውቀናል! ሠሪያችን መንፈሳዊ፣ ስሜታዊ፣ አእምሯዊና ሥጋዊ ፍላጎቶቻችንን ከማንም በተሻለ ይረዳልናል። በእኛ ላይ ትኩረቱን ሲያሳርፍ አፈጣጠራችንን፣ ፍላጎቶቻችንንና ምኞቶቻችንን ጠንቅቆ እንደሚረዳ ያሳያል። ይሖዋ ያሉብንን የአቅም ገደቦች ይረዳል። ሆኖም ጥሩ ነገር የማከናወን ችሎታም እንዳለን ያውቃል። መዝሙራዊው “ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፣ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ” ብሏል። (መዝሙር 103:​14) በመሆኑም ራሳችንን ለመለኮታዊ አመራር በፈቃደኝነት በማስገዛት በሕጉ ለመመላለስ ስንጥር መንፈሳዊ ደኅንነት እንዳገኘን ሊሰማን ይችላል።​—⁠ምሳሌ 3:​19-26

13. ይሖዋ ሁልጊዜ ለእኛ የሚበጀንን ነገር እንደሚያስብ እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን?

13 መለኮታዊ ሕግ የተሰጠን ከሚወደን አካል ነው። አምላክ ስለ ዘላለማዊ ደኅንነታችን በጥልቅ ያስባል። ከፍተኛ መሥዋዕትነት በመክፈል ልጁን “ለብዙዎች ቤዛ” አድርጎ አልሰጠም? (ማቴዎስ 20:​28) ይሖዋ ‘ከሚቻለን መጠን ይልቅ እንድንፈተን እንደማይፈቅድ’ ቃል አልገባልንም? (1 ቆሮንቶስ 10:​13) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ‘እንደሚያስብልን’ ዋስትና አልሰጠንም? (1 ጴጥሮስ 5:​7) ለሰው ዘር ጠቃሚ መመሪያዎች በመስጠት ረገድ የይሖዋን ያህል ፍቅራዊ አሳቢነት የሚያሳይ የለም። ለእኛ የሚጠቅመን ምን እንደሆነ እንዲሁም ደስታና ሐዘን በሚያስከትሉ ነገሮች መካከል ያለው ድንበር የት ላይ እንደሚገኝ ያውቃል። ፍጽምና የጎደለንና የምንሳሳት ብንሆንም እንኳ ጽድቅን ከተከታተልን ለሕይወትና ለበረከት እንድንበቃ በሚያስችል መንገድ ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳየናል።​—⁠ሕዝቅኤል 33:​11

14. የአምላክ ሕግ ከሰዎች አስተሳሰብ የሚለየው በየትኛው ዐቢይ ጉዳይ ነው?

14 የአምላክ ሕግ ፈጽሞ አይለዋወጥም። በዚህ በምንኖርበት ተነዋዋጭ ዘመን ውስጥ ይሖዋ ምንጊዜም የማይለወጥ ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚኖር አምላክ ነው። (መዝሙር 90:​2) ስለ ራሱ ሲናገር “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” ብሏል። (ሚልክያስ 3:​6) መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የአምላክ መሥፈርቶች እንደ እንቧይ ካብ ዕድሜ ከሌለውና ምንጊዜም ተለዋዋጭ ከሆነው የሰው ሐሳብ በተለየ ፍጹም አስተማማኝ ናቸው። (ያዕቆብ 1:​17) ለምሳሌ ያህል የሥነ ልቦና ጠበብት ልጆችን ለቀቅ አድርጎ ማሳደግን ለበርካታ ዓመታት ሲያበረታቱ ቢቆዩም ከጊዜ በኋላ አንዳንዶቹ አስተሳሰባቸውን የለወጡ ሲሆን ምክራቸው የተሳሳተ እንደነበረም አምነዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የወጡ ዓለማዊ መሥፈርቶችና መመሪያዎች በነፋስ የተመቱ ያህል ወዲያ ወዲህ ይዋልላሉ። የይሖዋ ቃል ግን አይለዋወጥም። መጽሐፍ ቅዱስ ልጆችን እንዴት በፍቅር ማሳደግ እንደሚቻል ለበርካታ መቶ ዓመታት ምክር ሲሰጥ ቆይቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ “አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቈጡአቸው” ሲል ጽፏል። (ኤፌሶን 6:4) ፈጽሞ በማይለዋወጡት የይሖዋ መሥፈርቶች ላይ ትምክህት መጣል እንደምንችል ማወቁ ምንኛ ያበረታታል!

የአምላክን ሕግ የሚታዘዙ የሚያገኟቸው በረከቶች

15, 16. (ሀ) የይሖዋን መሥፈርቶች ተግባራዊ ካደረግን ምን እናገኛለን? (ለ) የአምላክ ሕግ በትዳር ውስጥ አስተማማኝ መመሪያ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

15 አምላክ በነቢዩ በኢሳይያስ በኩል “ከአፌ የሚወጣ ቃሌ . . . የላክሁትን ይፈጽማል” ሲል ተናግሯል። (ኢሳይያስ 55:​11) የዚያኑ ያህል በቃሉ ውስጥ የሚገኙትን መሥፈርቶች ለመከተል ከልብ ጥረት ስናደርግ ስኬት እንደምናገኝ፣ ጠቃሚ ነገር እንደምናከናውንና ደስታ እንደምናገኝ የተረጋገጠ ነው።

16 የአምላክ ሕግ ለተሳካ ትዳር እንዴት አስተማማኝ መመሪያ እንደሆነ ተመልከት። ጳውሎስ “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 13:4) የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላው አክብሮትና ፍቅር እንዲያሳዩ ይጠበቅባቸዋል:- “ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፣ ሚስቱም ባልዋን ትፍራ [“ታክብር፣” አ.መ.ት ]።” (ኤፌሶን 5:​33) ተፈላጊ የሆነው የፍቅር ዓይነት 1 ቆሮንቶስ 13:​4-8 ላይ ተገልጿል:- “ፍቅር ይታገሣል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፣ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም አይፈልግም፣ አይበሳጭም፣ በደልን አይቈጥርም፤ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፤ ሁሉን ይታገሣል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል። ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም።” እንዲህ ዓይነት ፍቅር የሚታይበት ትዳር አይፈርስም።

17. የአልኮል መጠጥን በተመለከተ የይሖዋን መሥፈርቶች ተግባራዊ ማድረግ ምን ጥቅሞች ያስገኛል?

17 የይሖዋ መሥፈርቶች ጠቃሚ መሆናቸውን የሚያሳየው ሌላው ማስረጃ ይሖዋ ስካርን የሚያወግዝ መሆኑ ነው። ‘ለብዙ ወይን ጠጅ መጎምጀትን’ ጭምር ይቃወማል። (1 ጢሞቴዎስ 3:​3, 8፤ ሮሜ 13:​13) በዚህ ረገድ አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ችላ የሚሉ አብዛኞቹ ሰዎች ከልክ በላይ መጠጣት በሚያስከትላቸው ወይም በሚያባብሳቸው በሽታዎች ይጠቃሉ። አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ ልከኝነትን በተመለከተ የሚሰጠውን ምክር ችላ በማለት “ዘና እንዲያደርጋቸው” በማሰብ ብዙ መጠጣት ልማድ ሆኖባቸዋል። ከልክ በላይ መጠጣት በርካታ ችግሮች የሚያስከትል ሲሆን ከነዚህም መካከል አክብሮት ማጣት፣ ውጥረት የሞላበት የቤተሰብ ግንኙነት ወይም የቤተሰብ መፈራረስ፣ ገንዘብ ማባከን እንዲሁም ከሥራ መባረር ይገኙበታል። (ምሳሌ 23:​19-21, 29-35) ይሖዋ የአልኮል መጠጥ አወሳሰድን በተመለከተ ያወጣቸው መሥፈርቶች ጥበቃ የሚያስገኙ አይደሉም?

18. የአምላክ ሕግ በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ረገድ ተግባራዊ ጠቀሜታ አለው? አብራራ።

18 የአምላክ መሥፈርቶች በገንዘብ ነክ ጉዳዮችም ረገድ ተግባራዊ መሆናቸው ታይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ሐቀኞችና ትጉዎች እንዲሆኑ በጥብቅ ያሳስባል። (ሉቃስ 16:​10፤ ኤፌሶን 4:​28፤ ቆላስይስ 3:​23) ብዙ ክርስቲያኖች ይህን ምክር በመከተላቸው ምክንያት እድገት አግኝተዋል አሊያም ሌሎች ከሥራ ሲቀነሱ በሥራ ገበታቸው ላይ መቀጠል ችለዋል። አንድ ሰው እንደ ቁማር፣ ማጨስና ዕፅ መውሰድን የመሳሰሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ልማዶችንና ሱሶችን ሲያስወግድ ገንዘብ ከማባከን ይድናል። የአምላክ መሥፈርቶች ከኢኮኖሚ አንጻር ተግባራዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው የሚያሳዩ ሌሎች ምሳሌዎችን መጥቀስ እንደምትችል የታወቀ ነው።

19, 20. መለኮታዊ ሕጎችን መቀበልና መከተል የጥበብ አካሄድ የሆነው ለምንድን ነው?

19 ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች ከአምላክ ሕጎችና መሥፈርቶች በቀላሉ ሊርቁ ይችላሉ። በሲና ተራራ የነበሩትን እስራኤላውያን ተመልከት። አምላክ “ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፣ . . . ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ” ብሏቸው ነበር። “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” የሚል ምላሽ ሰጡ። ሆኖም የመረጡት አካሄድ ከዚህ ፍጹም ተቃራኒ ነበር! (ዘጸአት 19:​5, 8፤ መዝሙር 106:​12-43) ከዚህ በተለየ ሁኔታ የአምላክን መሥፈርቶች የምንቀበልና የምንከተል እንሁን።

20 ይሖዋ ለሕይወታችን መመሪያ እንዲሆን የሰጠንን አቻ የማይገኝለት ሕግ በጥብቅ መከተላችን ጥበብና ደስታ የሚያስገኝ አካሄድ ነው። (መዝሙር 19:​7-11) ይህን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን እንድንችል አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያላቸውን ጠቀሜታ መገንዘብና ከፍ አድርገን መመልከት መቻልም ይኖርብናል። የሚቀጥለው ትምህርት ይህን ርዕሰ ጉዳይ ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ‘የክርስቶስን ሕግ’ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ለማግኘት የመስከረም 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 14-24⁠ን ተመልከት።

ታስታውሳለህ?

• የአምላክ ሕጎች ለጥቅማችን የተዘጋጁ እንደሆኑ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

• የይሖዋን ሕግ ከፍ አድርገን እንድንመለከት የሚያደርጉን ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

• የአምላክ ሕጎች ጠቃሚ የሆኑት በምን መንገዶች ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብርሃም የይሖዋን ሕግ በማክበሩ የተትረፈረፈ በረከት አግኝቷል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ በጥድፊያ የተሞላ ሕይወት የሚያስከትለው ጭንቀት ብዙዎች ለመለኮታዊ ሕግ ትኩረት እንዳይሰጡ አድርጓቸዋል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተራራ ላይ እንዳለ የፋና ቤት ሁሉ መለኮታዊ ሕግም ቋሚና የማይለዋወጥ ነው