በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መሸሽ ጥበብ የሚሆንበት ጊዜ

መሸሽ ጥበብ የሚሆንበት ጊዜ

መሸሽ ጥበብ የሚሆንበት ጊዜ

ይህ ዓለም በጀብደኝነትና በጠበኝነት መንፈስ ወይም በፈተናዎች የተሞላ ነው። ከአንድ ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ የሚሸሽ ሰው እንደ ደካማ ወይም ፈሪ ተደርጎ ይቆጠራል። ከዚያም አልፎ መዘባበቻም ሊሆን ይችላል።

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ መሸሽ ጥበብና ድፍረት የተሞላበት እርምጃ የሚሆንባቸው ጊዜያት እንዳሉ በግልጽ ይናገራል። ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር በሚስማማ መልኩ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ አገልግሎት ከመላኩ በፊት “በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 10:23) አዎን፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከአሳዳጆቻቸው ለማምለጥ መሞከር ነበረባቸው። የሌሎችን እምነት በኃይል ለማስቀየር በማሰብ ሃይማኖታዊ ጦርነት ማካሄድ አልነበረባቸውም። የያዙት የሰላም መልእክት ነበር። (ማቴዎስ 10:11-14፤ ሥራ 10:34-37) በመሆኑም ክርስቲያኖች በቁጣ ከመገንፈል ይልቅ መሸሽ ማለትም ቁጣ ከሚያነሳሱ ነገሮች መራቅ ነበረባቸው። በዚህ መንገድ ንጹሕ ሕሊናቸውንና ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ውድ ዝምድና ጠብቀው መኖር ችለዋል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:1, 2

ከዚህ ጋር ተቃራኒ የሆነ ታሪክ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ እናገኛለን። ታሪኩ ፈታኝ የሆነ ሁኔታ ሲያጋጥመው ከመሸሽ ይልቅ ልክ “በሬ ለመታረድ እንዲነዳ” ጋለሞታን ሴት ተከትሎ ስለሄደ ወጣት ይናገራል። ውጤቱ ምን ሆነ? ነፍሱን አደጋ ላይ ሊጥል በሚችል ፈተና በመሸነፉ ጥፋት ገጥሞታል።​—⁠ምሳሌ 7:5-8, 21-23

የጾታ ብልግና እንድትፈጽም የሚገፋፋ ወይም ሌላ ዓይነት አደጋ ሊያስከትል የሚችል ፈተና ቢያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ? የአምላክ ቃል እንደሚለው ትክክለኛው እርምጃ ከቦታው ወዲያውኑ መሸሽ ወይም መራቅ ነው።​—⁠ምሳሌ 4:14, 15፤ 1 ቆሮንቶስ 6:18፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:22