በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፊሊፒንስ ተራሮች አምላክን ከፍ ከፍ ማድረግ

በፊሊፒንስ ተራሮች አምላክን ከፍ ከፍ ማድረግ

በፊሊፒንስ ተራሮች አምላክን ከፍ ከፍ ማድረግ

ፊሊፒንስ ሲባል ወደ አእምሮህ የሚመጣልህ አንዲት ደሴት አገር ከሆነች አልተሳሳትክም። ይሁንና አስገራሚ የሆኑ ተራሮችም ያሏት አገር ነች። የይሖዋ ምሥክሮች በዚህች አገር ከተሞችና ሜዳማ አካባቢዎች መስበክ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ቀላልና ውጤታማ ሆኖ አግኝተውታል። ተራራማ በሆኑት አካባቢዎች ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው።

የአገሪቱ ታላላቅ ተራሮች ከአሸዋማዎቹ የባህር ዳርቻዎች፣ ከዛጎል ተሬዎች (coral reefs)፣ ከዓሣ ማጥመጃ መንደሮች እንዲሁም በደሴቲቱ ሜዳማ ቦታዎች ላይ ከተቆረቆሩት የደሩ ከተማዎች ጋር ሲወዳደሩ ጉብ ብለው ይታያሉ። እነዚሁ ተራሮች የአምላክን መንግሥት “ምሥራች” የመስበኩን ሥራም ተፈታታኝ አድርገውታል።​—⁠ማቴዎስ 24:14

የፊሊፒንስ ደሴቶች ሁለት የስፍሃን ቴክቶኒካዎች (plates tectonic) በሚነባበሩበት ቦታ ላይ ይገኛሉ። በአካባቢው ያለው የመሬት መቆላለፍ በትላልቆቹ ደሴቶች ላይ ሹል የሆኑ የተራራ ሰንሰለቶችን ፈጥሯል። አንድ ላይ ተዳምረው ፊሊፒንስ የተባለችውን አገር ያስገኙት ከ7, 100 የሚበልጡት ደሴቶች የሚገኙት የፓስፊክ የእሳት ቀለበት (Pacific Ring of Fire) እየተባለ በሚጠራው ክልል ምዕራባዊ ዳርቻ ነው። ከዚህ የተነሳ ደሴቶቹ እሳተ ገሞራ በብዛት የሚገኝባቸው ሲሆኑ ይህም በአካባቢው ተራራማ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንዲኖር አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህ ወጣ ገባ የሆነ የመሬት አቀማመጥ በተራራው ላይ የሚኖሩት ሰዎች እንዲገለሉ አድርጓል። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ለሞተር ተሽከርካሪዎች ተስማሚ የሆኑት መንገዶች በጣም ጥቂት በመሆናቸው እነዚህ ሰዎች የሚኖሩበት ቦታ ድረስ መሄድ አስቸጋሪ ነው።

እነዚህ እንቅፋቶች ቢኖሩም የይሖዋ ምሥክሮች ‘ሰዎች ሁሉ’ ምሥራቹ ሊደርሳቸው እንደሚገባ ይገነዘባሉ። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ስለሆነም በፊሊፒንስ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች “በሴላ [“በገደል፣” NW ] የሚኖሩ እልል ይበሉ፣ በተራሮችም ራስ ላይ ሆነው ይጩኹ። ለእግዚአብሔር ክብርን ይስጡ፣ ምስጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ” ከሚለው በኢሳይያስ 42:11, 12 ላይ ካለው ሐሳብ ጋር ተስማምተው ሲሠሩ ቆይተዋል።

በተራሮቹ ላይ ለሚኖሩት ሰዎች ለመመስከር የተጠናከረ ጥረት ማድረግ የተጀመረው ከ50 ዓመት በፊት ነው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሚስዮናውያን ሥራው እንዲፋጠን በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ብዙ የአካባቢው ነዋሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተቀበሉ ሲሆን እነሱም በተራቸው በተራሮቹ አናት ላይ ለሚገኙት መንደሮች ይህን እውነት አዳርሰዋል። ይህም ግሩም ውጤቶችን አስገኝቷል። ለምሳሌ ያህል በሰሜናዊ ሉዞን በሚገኙት የኮርዲጄራ ሴንትራል ተራሮች ከ6, 000 የሚበልጡ የምሥራቹ አስፋፊዎች አሉ። የኢባሎይ፣ የኢፉጋኦና የካሊንጋ ጎሳዎችን ጨምሮ አብዛኞቹ የአካባቢው ተወላጆች ናቸው።

ይሁን እንጂ በተራሮቹ አናት ላይ አሁንም በቀላሉ ሊደረስባቸው የማይቻሉ አካባቢዎች አሉ። በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች አልተረሱም። አንዳንዶቹን ማግኘት የተቻለው እንዴት ነው? የተገኘው ምላሽስ ምን ይመስላል?

እውነተኛ እምነት ባሕልን ሲተካ

በስተሰሜን በምትገኘው በሉዞን ደሴት ላይ ባለችው በአብራ አውራጃ ውስጥ የሚገኙት ተራራማ ስፍራዎች የቲንጊያውያን መኖሪያ ናቸው። ይህ ስም “ተራራ” የሚል ትርጓሜ ካለው ቲንጊ ከሚባለው ከጥንታዊው የማላይ ቋንቋ ቃል የመጣ ሳይሆን አይቀርም። በእርግጥም ተስማሚ የሆነ ስም ነው! ሰዎቹም ጭምር ራሳቸውንም ሆነ ቋንቋቸውን የሚጠሩት ኢትኔግ እያሉ ነው። ካቡንያን በሚባል አምላክ የሚያምኑ ሲሆን የዕለት ተዕለት ሕይወታቸው በአጉል እምነቶች የተሞላ ነው። ለምሳሌ የሆነ ቦታ ለመሄድ ያቀደ አንድ ሰው ቢያስነጥሰው እንደ መጥፎ ገድ ስለሚቆጠር ጉዞውን ለመጀመር ገዱ የሚያስከትለው መጥፎ ውጤት እስኪጠፋ ድረስ ለሁለት ሰዓታት ያህል መቆየት አለበት።

በ1572 ስፓኒሾች ወደ አካባቢው የካቶሊክ ሃይማኖትን ይዘው ቢመጡም ለቲንጊያውያን ያስተማሩት ግን እውነተኛውን ክርስትና አልነበረም። ወደ ካቶሊክነት የተለወጡት ቲንጊያውያን ካቡንያን በተባለው አምላክ ማመናቸውን የቀጠሉ ሲሆን የአካባቢውን ወግና ልማድም ይከተሉ ነበር። እነዚህ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ያገኙት በ1930ዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ ተራራማ አካባቢዎች መስበክ በጀመሩበት ጊዜ ነበር። ከዚያ ወዲህ ቅን ልብ ያላቸው ብዙ ቲንጊያውያን “በተራሮች ራስ ላይ ሆነው” ይሖዋን ማወደስ ጀምረዋል።

ለምሳሌ ሊንባኡዋን በአካባቢው የተከበረ የጎሳ መሪ ነበር። በቲንጊያውያን ባሕል በጣም የተጠላለፈ ነበር። “የቲንጊያውያንን ባሕል በጥብቅ እከተል ነበር። አንድ ሰው ሲሞት ከቀብሩ በኋላ የምንጨፍር ሲሆን ጎንግ የተባለውን የሙዚቃ መሣሪያ እየመታን እንጫወት ነበር። እንስሳትንም እንሠዋ ነበር። የምናምነው ካቡንያን በተባለው አምላክ ነው፤ ስለ መጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ አላውቅም ነበር።” ይህ ሰው ለስሙ ካቶሊክ ነበር።

የይሖዋ ምሥክር የሆኑ አገልጋዮች በዚያ አካባቢ ለመስበክ ሲመጡ ሊንባኡዋንን አገኙትና መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነብ አበረታቱት። እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “ይሖዋ እውነተኛው አምላክ እንደሆነ እንዳምን ያደረገኝ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።” አንድ የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስን ካስጠናው በኋላ እውነተኛውን አምላክ ለማገልገል ውሳኔ አደረገ። የጎሳ መሪ የመሆን ስልጣኑን ጨምሮ የቀድሞ አኗኗሩን ተወ። ይህ እርምጃው የአካባቢውን ቄሶችና የቀድሞ ወዳጆቹን አስቆጣ። ይሁን እንጂ ሊንባኡዋን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያገኘውን እውነት ለመከተል ቆርጦ ነበር። አሁን የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል።

ሰባት ቀንና ስድስት ሌሊት

በዚህ ጊዜ የተወሰኑ የአብራ ክፍሎች ምሥራቹን በተደጋጋሚ የሚሰሙ ቢሆንም ሌሎች ግን ሩቅ ከመሆናቸውም አልፎ ምሥክርነቱን የሚሰሙት ከስንት አንዴ ነው። ከተወሰነ ጊዜ በፊት ከእነዚህ አካባቢዎች በአንዱ ምሥክርነቱን ለማድረስ ጥረት ተደርጎ ነበር። ሠላሳ አምስት ምሥክሮችን ያቀፈ አንድ ቡድን በቴኔግ አብራ ወደሚገኝ ለ27 ዓመታት ያልተሠራበት ገለልተኛ ክልል ለመስበክ ተንቀሳቀሰ።

በእግር የተደረገው ይህ የስብከት ጉዞ ከሰባት ቀን በላይ ወስዷል። ተንጠልጣይ ድልድዮችንና ጥልቀት ያላቸው ወንዞችን ማቋረጥንና በጀርባህ ጓዝህን ተሸክመህ በተራራ ሰንሰለቶች ላይ ለሰዓታት በእግር መጓዝን እስቲ አስበው። ይህ ሁሉ ምሥራቹን ለመስማት እምብዛም አጋጣሚ ላላገኙ ሰዎች ለመስበክ ነው! በጉዞው ካሳለፉት ስድስት ሌሊት ውስጥ አራቱን ያደሩት ውጪ ነበር።

ምንም እንኳ በጉዞው ውስጥ የታቀፉት እነዚህ ብርቱ ምሥክሮች የተወሰነ ምግብ ይዘው የነበረ ቢሆንም ለጠቅላላ ጉዞው የሚበቃ አልነበረም። ይሁን እንጂ ሕዝቡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በደስታ በምግብ ይለውጥ ስለነበር አልተቸገሩም። ምሥክሮቹ የእርሻ ውጤቶችን፣ ዓሣና የአጋዘን ሥጋ እንደልብ ያገኙ ነበር። አንዳንድ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ቡድኑ እንዲህ ብሏል፦ “የከፈልናቸው እነዚህ መስዋዕትነቶች ባገኘነው ይህ ነው የማይባል ደስታ ተካክሰዋል።”

በሰባቱ ቀናት ውስጥ እነዚህ አገልጋዮች በአሥር መንደሮች የመሠከሩ ሲሆን 60 መጽሐፎችን፣ 186 መጽሔቶችን፣ 50 ብሮሹሮችንና ብዙ ትራክቶችን አበርክተዋል። ለ74 ቡድኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት እንደሚካሄድ አሳይተዋል። በቲኔግ ከተማ የአካባቢው ባለሥልጣናትና ተሰሚነት ያላቸው አንዳንድ ሰዎች ባቀረቡት ጥያቄ 78 ተሰብሳቢዎች የተገኙበት የጉባኤ ስብሰባ ተደርጎ ነበር። በስብሰባው ላይ የተገኙት አብዛኛዎቹ መምህራንና ፖሊሶች ነበሩ። ብዙ ተጨማሪ ቲንጊያውያን ከተራሮች ራስ ላይ ሆነው ‘ከሚጮኹትና’ ይሖዋን ከሚያወድሱት ጋር እንደሚተባበሩ ተስፋ እናደርጋለን።

ከወርቅ የተሻለ ነገር

በስተደቡብ ራቅ ብለው ከሚገኙት የፊሊፒንስ ደሴቶች አንዳንዶቹ ስፓኞች ወርቅ ያገኙባቸው ቦታዎች ናቸው። ይህም በስፓኒሽ ቋንቋ ሚና ደ ኦሮ ወይም “የወርቅ ማዕድን ሥፍራ” የሚለውን ቃል በማሳጠር የተገኘውን ሚንዶሮ የሚል ስያሜ ሊያሰጣቸው ችሏል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በእነዚህ ደሴቶች ላይ ከወርቅ የላቀ ነገር በመገኘት ላይ ነው፤ ይህም እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ማገልገል የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው።

ማንያን ተብለው የሚጠሩት ብዛታቸው ወደ 125,000 የሚጠጋው የአገሬው ተወላጆች ሩቅ በሆኑት የሚንዶሮ ደኖች ውስጥ ይኖራሉ። አኗኗራቸው ቀላል ነው፣ ከውጭ ሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ውስን ነው፣ እንዲሁም የራሳቸው ቋንቋ አላቸው። አብዛኞቹ በሙታን መናፍስት የሚያምኑና ብዙ አማልክትን የሚያመልኩ ሲሆን በተፈጥሮ ውስጥ ከሰብዓዊ ባሕርይ ውጭ የሆኑ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ አካላት እንዳሉ ያምናሉ።

አልፎ አልፎ ምግብ ወይም ሌሎች አላቂ እቃዎች ሲያጡ አንዳንድ ማንያኖች በባሕር ጠረፍ ላይ ወደሚገኙ አካባቢዎች ሥራ ፍለጋ ይመጣሉ። ባታንጋን ከተባለ በማንያኖች ውስጥ የሚገኝ የአንድ ወገን ተወላጅ የሆነው ፓይሊንግም የመጣው እንዲሁ ሥራ ለመፈለግ ነበር። ያደገው በዘመዶቹ መካከል ተራራዎቹ ላይ በሚገኙት ደኖች ውስጥ ሲሆን የባታንጋንን እምነቶችና ልማዶች ይከተል ነበር። የተለመደው ልብሳቸው እንዲያው ወገብ ላይ የሚገለደም እራፊ ጨርቅ ነበር። ባታንጋዎች ጥሩ የሰብል ምርት ለማግኘት ዶሮ ካረዱ በኋላ ደሟን ውኃ ውስጥ እያንጠባጠቡ የመጸለይ ልማድ ነበራቸው።

አሁን ፓይሊንግ እነዚህን ልማዶች አይከተልም። ለምን? ወደ ቆላው አካባቢ ሲመጣ የይሖዋ ምሥክር በሆኑ ቤተሰቦች ዘንድ ሥራ ተቀጠረ። ከነዚህ ቤተሰቦች አንዱ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ለፓይሊንግ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ነገረው። ፓይሊንግ አዎንታዊ ምላሽ የሰጠ ሲሆን ይሖዋ ለሰው ዘርና ለምድር ስላለው ዓላማ በመማሩ ተደሰተ። አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲገባ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ዝግጅት አደረጉለት። ፓይሊንግ በ24 ዓመቱ ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። በ30 ዓመቱ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ የነበረ ሲሆን ትምህርት ቤቱን እንደ አገልግሎት ክልሉ አድርጎ ይጠቀምበት ነበር። አሁን ሮላንዶ (በቆላማ አካባቢዎች የሚሰጥ ስም) እያሉ ይጠሩታል።

አሁን ሮላንዶ በሚሮንዶ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ የሙሉ ጊዜ ሰባኪና የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ የሚያገለግል ፈገግተኛና ግሩም አለባበስ ያለው ሰው ነው። በቅርቡ ሮላንዶ ወደ ተራራዎቹ ተመልሶ ሄዷል። የሄደው ግን ወደ ባታንጋውያኑ ባሕል ለመመለስ ሳይሆን ሕይወት ሰጪ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሊያካፍላቸው ነው።

የመንግሥት አዳራሽ ለማግኘት የነበራቸው ጉጉት

በሴቡዋኖ ቋንቋ “የተራሮች ሰዎች” የሚል ትርጓሜ ያላት የቡኪድኖን አውራጃ በደቡባዊዋ የሚንድናው ደሴት ላይ ትገኛለች። ይህ አካባቢ ተራሮች፣ ገደላማ ሸለቆዎች፣ ወንዞችና አምባዎች በብዛት ያሉበት ነው። ለም የሆነው መሬት አናናስ፣ በቆሎ፣ ቡና፣ ሩዝና ሙዝ ያበቅላል። ታላአንዲግና ሂጋኦኖን የተባሉት ደገኛ ጎሳዎች በዚህ አካባቢ ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎችም ስለ ይሖዋ መማር ያስፈልጋቸዋል። በቅርቡ በታላካግ ከተማ አቅራቢያ ይህ አጋጣሚ በአስገራሚ ሁኔታ ተከፈተ።

ወደ ተራራዎቹ የሚወጡ ምሥክሮች አየሩን ቀዝቃዛ ሆኖ ቢያገኙትም በዚያ የተደረገላቸው አቀባበል ግን ሞቅ ያለ ነበር። የአካባቢው ሰዎች ሁሉን ቻይ አምላክ በሆነው በአብ እንደሚያምኑ ይናገራሉ፤ ስሙን ግን አያውቁትም። አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በጫካ ውስጥ ስለሆነ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው። አምላክ ስሙ ማን እንደሆነና ከመንግሥቱ ጋር በተያያዘ ምን ግሩም ዓላማ እንዳለው ተነገራቸው። ሰዎቹ በመልእክቱ ስለተደሰቱ መንደራቸው በድጋሚ መጎብኘት እንዳለበት ተወሰነ።

ተደጋጋሚ ጉብኝት ተደረገላቸው። በዚህ የተነሳ የአካባቢው ሰዎች ለይሖዋ ምሥክሮች “ቤት” መሥሪያ የሚሆን ቦታ ሰጡ። ምሥክሮቹ ስጦታውን በደስታ ተቀበሉ። ቦታው መንገድ ዳር ባለ ትልቅ ኮረብታ ላይ ይገኛል። ቤቱ የተሠራው ከእንጨት፣ ከቀርከሃና ከዘንባባ ቅጠሎች ነበር። ሥራው በሦስት ወር ከአሥር ቀን ተጠናቀቀ። “የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ” የሚለው ምልክት ቤቱ ፊት ለፊት በጉልህ ይታያል። እስቲ አስቡት፣ ገና ጉባኤ ከመቋቋሙ በፊት የመንግሥት አዳራሽ ተሠራ!

ከዚያም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነ አንድ የጉባኤ ሽማግሌና አንድ የጉባኤ አገልጋይ ወደ እዚያ ተዛወሩ። በአጎራባች አካባቢዎች ካሉ ምሥክሮች ጋር ተባብረው አንድ ጉባኤ ለማቋቋም መስራት ጀመሩ። ነሐሴ 1998 ይህ ግባቸው እውን ሆነ። በአሁኑ ወቅት አነስተኛ አባላትን ያቀፈ አንድ ጉባኤ የተራራማ አካባቢ ነዋሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ በመርዳት ይህን የመንግሥት አዳራሽ በሚገባ እየተጠቀመበት ነው።

እውነትም፣ ይሖዋ በቀላሉ ሊደረስባቸው ወደማይቻሉ ተራሮች እንኳን የመንግሥቱን መልዕክት ለማሰራጨት በፊሊፒንስ የሚገኙ ፈቃደኛ አገልጋዮቹን በእጅጉ ተጠቅሞባቸዋል። ይህም “የምስራች የሚናገር፣ . . . ሰው እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ያማረ ነው” የሚሉትን በኢሳይያስ 52:​7 ላይ የሚገኙትን ቃላት ያስታውሰናል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

አብራ

ሚንዶሮ

ቡኪድኖን

[ምንጭ]

ሉል፦ Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በተራራማ አካባቢዎች መስበክ አስቸጋሪ በሆነ መልክዓ ምድር ለሰዓታት በእግር መጓዝን ይጠይቃል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በተራራ ላይ በሚገኝ አንድ ጅረት ውስጥ ጥምቀት ሲከናወን