በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህን?

ታስታውሳለህን?

ታስታውሳለህን?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች አንብበሃቸዋልን? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር:-

የሚሰማህን ውጥረት በማቃለል ረገድ ከኢየሱስ የተራራ ስብከት ጋር በተያያዘ ምን የግል ፕሮግራም ልታወጣ ትችላለህ?

በእያንዳንዱ ቀን ኢየሱስ በዚያ የተራራ ስብከት ላይ አሊያም በሌሎች የወንጌል ክፍሎች ላይ ከጠቀሳቸው ቁልፍ ትምህርቶች ውስጥ አንዱን ማንበብ ትችላለህ። ትምህርቱን በማሰላሰልና በግለሰብ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ በመጣር ውጥረትህን ማቃለልና ይበልጥ ደስተኛ መሆን ትችላለህ።​—⁠12/15 ገጽ 12-14

የጉባኤ አገልጋዮች ተጨማሪ ኃላፊነቶች መሸከም ይችሉ ዘንድ የጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲያሰለጥኗቸው የሚገፋፏቸው ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በማደጉ አዲሶች እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት ኃላፊነት መሸከም የሚችሉ ተጨማሪ ወንዶች ያስፈልጋሉ። የእድሜ መግፋት ወይም የጤና ችግሮች የቆዩ ሽማግሌዎች ሊያከናውኑ የሚችሉትን ሥራ ገድቦባቸዋል። በተጨማሪም አንዳንድ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሽማግሌዎች ከጉባኤ ኃላፊነቶቻቸው በተጨማሪ ሌሎች ኃላፊነቶችን በመሸከማቸው በጉባኤዎቻቸው ውስጥ እንደቀድሞው ብዙ መሥራት አይችሉ ይሆናል።​—⁠1/1 ገጽ 29

ሰዎች እውን ባልሆኑ አማልክት የሚታመኑት እንዴት ነው?

ብዙዎች በሃይማኖታቸው ውስጥ የሚገኙትን አማልክት ያመልካሉ። ሆኖም በኤልያስ ዘመን እንደነበረው በኣል እነዚህም አማልክት ማዳን የማይችሉ ሕይወት አልባ አማልክት ናቸው። (1 ነገሥት 18:​26, 29፤ መዝሙር 135:​15-17) ሌሎች ደግሞ ምንም ዓይነት የወደፊት ተስፋ መስጠት የማይችሉትን ታዋቂ ግለሰቦች አሊያም ስፖርተኞች ያመልካሉ። ከዚህ በተቃራኒው ግን ይሖዋ እውንና ዓላማዎቹን በእርግጥ የሚፈጽም አምላክ ነው።​—⁠1/15 ገጽ 3-5

ቃየን ለአምላክ ማስጠንቀቂያ ከሰጠው ምላሽ ምን እንማራለን?

አምላክ የመምረጥ ነጻነት ሰጥቶናል። ስለዚህ ቃየን እንዳደረገው መልካም ለማድረግ ከመቆጠብ ይልቅ ትክክል የሆነውን ለማድረግ ልንመርጥ እንችላለን። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚያሳየው ይሖዋ ንስሐ በማይገቡ ላይ የቅጣት ፍርዱን ያስፈጽማል።​—⁠1/15 ገጽ 22-3

በተለይ በአሁኑ ጊዜ ንጽሕና በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

በአሁኑ ጊዜ ማኅበራዊ ሁኔታዎች በመለወጣቸው ብዙዎች እንደ በፊቱ ጊዜ ወስደው ቤታቸውን አያጸዱም። ምግብንና ውኃን በንጽሕና ከመያዝ ቸል ማለት በጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ከአካላዊ ንጽሕናችን በተጨማሪ ለመንፈሳዊ፣ ለሥነ ምግባራዊና ለአእምሮአዊ ንጽሕናችን ትኩረት እንድንሰጥ ያበረታታናል።​—⁠2/1 ገጽ 3-6

ጳውሎስ ከክርስትና በፊት የነበሩትን ምሥክሮች አስመልክቶ ‘ያለ እኛ ፍጹማን አይሆኑም’ በማለት ተናግሯል። ምን ማለቱ ነው? (ዕብራውያን 11:​39, 40)

በመጪው የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ኢየሱስና ነገሥታት እንዲሁም ካህናት ሆነው በሰማይ የሚያገለግሉት ቅቡዓን ወንድሞቹ የቤዛውን ጥቅሞች ትንሣኤ ላገኙት ሰዎች ያዳርሳሉ። ያን ጊዜ በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ የተገለጹት እነዚህ ታማኞች ‘ፍጹማን ይሆናሉ።’​—⁠2/1 ገጽ 23

ጳውሎስ የዕብራውያን ክርስቲያኖችን “ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም” ሲላቸው ምን ማለቱ ነበር? (ዕብራውያን 12:​4)

እስከ ሞት ድረስ አልተቃወማችሁም ማለቱ ነበር። እስከ ሞት ድረስ በመጽናት ታማኝነታቸውን የጠበቁ ታሪካዊ ምሳሌዎች ነበሩ። ጳውሎስ የጻፈላቸው የዕብራውያን ክርስቲያኖች እስከ ሞት ድረስ ባይፈተኑም ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን ማንኛውንም ዓይነት ፈተና ለመቋቋም የሚያስችላቸውን እምነት ለመገንባት ወደ ጉልምስና ማደግ ነበረባቸው።​—⁠2/15 ገጽ 29

ይሖዋ ፍትሑን በምሕረቱ ያለዝበዋል ብሎ መናገሩ ተገቢ የማይሆነው ለምንድን ነው?

በአንዳንድ ቋንቋዎች “ማለዘብ” ማለት ማለስለስ ወይም መግራት ማለት ሊሆን ይችላል። ይሖዋ የፍትሕም የምሕረትም አምላክ ነው። ስለዚህ ሁለቱም ባሕርያት ስምም ሆነው በአንድ ላይ የሚሠሩ ናቸው። (ዘጸአት 34:​6, 7፤ ዘዳግም 32:​4፤ መዝሙር 116:​5፤ 145:​9) የይሖዋ ፍትሕ በምሕረት መለስለስም ሆነ መለዘብ አያስፈልገውም።​—⁠3/1 ገጽ 30

አንድ ክርስቲያን የአንድን የሞተ የቤተሰብ አባል ሬሳ ቢያደርቅ ስህተት ነውን?

ሬሳን ማድረቅ አስከሬኑ ሳይፈርስ እንዲቆይ ለማድረግ የሚረዳ ዘዴ ነው። አንዳንድ የጥንት ሰዎች በሃይማኖታዊ ምክንያቶች የተነሣ ይህንን ልማድ ይከተሉ ነበር። እውነተኛ አምላኪዎች ግን ይህን ልማድ አልተከተሉም። (መክብብ 9:​5፤ ሥራ 24:​15) ሬሳውን ማድረቅ መምጣቱ የማይቀረውን ወደ አፈር የመመለስ ሂደት ከማዘግየት ውጪ ሌላ የሚፈይደው ነገር አይኖርም። (ዘፍጥረት 3:​19) ይሁን እንጂ ሕጉ ሬሳን ማድረቅ የሚያዝዝ ከሆነ፣ አንዳንድ የቤተሰብ አባላት እንዲህ እንዲደረግ የሚፈልጉ ከሆነ አሊያም አንዳንዶች ቀብር ቦታው ለመድረስ ረዥም ጉዞ ማድረግ ካለባቸው ልማዱን መከተሉ ምንም ችግር የለውም።​—⁠3/15 ገጽ 29-31

አምላክ ሁሉንም ሰው እንደሚቀበል የሚያሳዩን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?

ይሖዋ የነነዌን ሰዎች እንዲያስጠነቅቅ ነቢዩ ዮናስን ከመላኩም በተጨማሪ ንስሐ መግባታቸውን አምኖ እንዲቀበልም አሳስቦታል። ኢየሱስ በቃልና በተግባር ለሳምራውያን ፍቅር ማሳየትን አበረታቷል። ሐዋርያው ጴጥሮስና ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹን አይሁዳውያን ላልሆኑ ሰዎች በማድረስ በኩል ሚና ነበራቸው። ከእነዚህ ምሳሌዎች ማየት እንደሚቻለው የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸውን ሰዎች ለመርዳት መጣር በጣም አስፈላጊ ነው።​—⁠4/1 ገጽ 21-4