በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላካዊ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች የምትመሩ ሁኑ

አምላካዊ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች የምትመሩ ሁኑ

አምላካዊ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች የምትመሩ ሁኑ

‘[ይሖዋ] የሚረባህን ነገር ያስተምርሃል።’​—⁠ኢሳይያስ 48:​17

1. ፈጣሪ የሰው ልጆችን የሚመራው እንዴት ነው?

 ሳይንቲስቶች ስለ አጽናፈ ዓለም ይበልጥ ለማወቅ ጥረት ባደረጉ መጠን በዙሪያችን በሚገኘው ጠፈር ውስጥ ባለው እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ዕምቅ ኃይል ይገረማሉ። መካከለኛ መጠን ያላት ኮከብ የሆነችው ፀሐያችን “በእያንዳንዱ ሴኮንድ የሚፈነዱ 100 ቢልዮን የሃይድሮጂን ቦንቦች” የሚያወጡትን ያህል ኃይል ታመነጫለች። ፈጣሪ ገደብ በሌለው ኃይሉ አማካኝነት እንደዚህ የመሰሉ ግዙፍ ሰማያዊ አካላትን መቆጣጠርና መምራት ይችላል። (ኢዮብ 38:​32፤ ኢሳይያስ 40:​26) የመምረጥ ነፃነት፣ የሥነ ምግባር ባሕርይ፣ የማመዛዘን ችሎታና መንፈሳዊ ነገሮችን የመረዳት ተሰጥኦ ስላለን ስለ እኛ የሰው ልጆችስ ምን ለማለት ይቻላል? ሠሪያችን እኛን መምራት የሚፈልገው በምን መንገድ ነው? በሚገባ ከሰለጠነው ህሊናችን ጋር ተዳምሮ ፍጹም በሆኑት ሕጎቹና የላቀ ደረጃ ባላቸው መሠረታዊ ሥርዓቶቹ አማካኝነት በፍቅራዊ መንገድ ይመራናል።​—⁠2 ሳሙኤል 22:​31፤ ሮሜ 2:​14, 15

2, 3. አምላክ ምን ዓይነት ታዛዥነት ያስደስተዋል?

2 አምላክ እሱን ለማገልገል በሚመርጡ የማሰብ ችሎታ ባላቸው ፍጡራን ይደሰታል። (ምሳሌ 27:​11) ይሖዋ ማሰብ እንደማይችሉ ሮቦቶች በጭፍን እንድንታዘዘው አድርጎ ከመፍጠር ይልቅ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ በእውቀት የተደገፈ ውሳኔ ላይ መድረስ እንችል ዘንድ ነፃ ምርጫ ሰጥቶናል።​—⁠ዕብራውያን 5:​14

3 የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ የነበረው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 15:​14, 15) በጥንት ዘመን አንድ ባሪያ ወደደም ጠላም የጌታውን ትእዛዝ ማክበር ነበረበት። ከዚህ በተቃራኒ ግን ወዳጅነት የሚመሠረተው ልብን የሚማርኩ ባሕርያት በማንጸባረቅ ነው። የይሖዋ ወዳጆች መሆን እንችላለን። (ያዕቆብ 2:​23) ይህ ወዳጅነት አንዱ ለሌላው በሚያሳየው ፍቅር ይጠናከራል። ኢየሱስ “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል” በማለት ለአምላክ መታዘዝን ከፍቅር ጋር አያይዞ ገልጿል። (ዮሐንስ 14:​23) ይሖዋ ስለሚወድደንና ጉዳት እንዳይደርስብን ስለሚፈልግ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን እንድንከተል ይጋብዘናል።

አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች

4. መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንዴት ትገልጻቸዋለህ?

4 መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንድን ናቸው? መሠረታዊ ሥርዓት “አጠቃላይ ወይም መሠረታዊ እውነት:- ሰፊና መሠረታዊ ሕግ፣ መሠረተ ትምህርት ወይም ለሌሎች ሐሳቦች መሠረት ሆኖ የሚያገለግል ወይም ሌሎች ሐሳቦች የሚፈልቁበት መሠረታዊ ሐሳብ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። (ዌብስተርስ ሰርድ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ) መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ማጥናት ሰማያዊ አባታችን የተለያዩ ሁኔታዎችንና የሕይወት ዘርፎችን የሚዳስሱ መሠረታዊ መመሪያዎች እንደሚሰጥ ለመገንዘብ ያስችላል። ይህን የሚያደርገው ዘላለማዊ ጥቅማችንን በማሰብ ነው። ይህም ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ከጻፈው ሐሳብ ጋር ይስማማል:- “ልጄ ሆይ፣ ስማ፣ ንግግሬንም ተቀበል፤ የሕይወትህም ዘመን ትበዛልሃለች። የጥበብን መንገድ አስተማርሁህ፤ በቀናች ጎዳና መራሁህ።” (ምሳሌ 4:10, 11) ይሖዋ የሰጠን ቁልፍ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከእሱና ከሰዎች ጋር ያለንን ዝምድና፣ አምልኳችንን እንዲሁም የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን ይነካል። (መዝሙር 1:​1) እስቲ ከእነዚህ ቁልፍ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዳንዶቹን እንመርምር።

5. ቁልፍ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የያዙ አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

5 ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና በተመለከተ ኢየሱስ ሲናገር “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” ብሏል። (ማቴዎስ 22:​37) በተጨማሪም አምላክ ወርቃማውን ሕግ የመሳሰሉ ከሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት ልናሳየው የሚገባውን ጠባይ በተመለከተ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሰጥቶናል:- “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው።” (ማቴዎስ 7:​12፤ ገላትያ 6:​10፤ ቲቶ 3:​2) አምልኮን በተመለከተ “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ . . . መሰብሰባችንን አንተው” የሚል ጥብቅ ምክር ተሰጥቶናል። (ዕብራውያን 10:​24, 25) የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ “የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 10:31) በአምላክ ቃል ውስጥ ሌሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ይገኛሉ።

6. መሠረታዊ ሥርዓቶች ከሕግ የሚለዩት በምንድን ነው?

6 መሠረታዊ ሥርዓቶች ሕያውና ዐቢይ እውነቶች ሲሆኑ ጥበበኛ ክርስቲያኖች እነዚህን መውደድ ይማራሉ። ይሖዋ እንዲህ ብሎ እንዲጽፍ ሰሎሞንን በመንፈሱ አነሳስቶታል:- “ንግግሬን አድምጥ ወደ ቃሌም ጆሮህን አዘንብል። ከዓይንህ አታርቃት፣ በልብህም ውስጥ ጠብቃት። ለሚያገኙአት ሕይወት፣ ለሥጋቸውም ሁሉ ፈውስ ነውና።” (ምሳሌ 4:20-22) መሠረታዊ ሥርዓቶች ከሕግ የሚለዩት በምንድን ነው? መሠረታዊ ሥርዓቶች ለሕግ መሠረት ሆነው ያገለግላሉ። ደንቦች በተወሰነ ነገር ላይ የማተኮር ባሕርይ ያላቸው ሲሆን የሚያገለግሉት ለአንድ የተወሰነ ጊዜ ወይም ሁኔታ ነው፤ መሠረታዊ ሥርዓቶች ግን ጊዜ አይሽራቸውም። (መዝሙር 119:​111) መለኮታዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጊዜ የሚያልፍባቸው አይሆኑም ወይም አይጠፉም። ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፋቸው ቃላት እውነተኛ ሆነው ተገኝተዋል:- “ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፣ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።”​—⁠ኢሳይያስ 40:8

አስተሳሰባችሁም ሆነ ድርጊታችሁ በመሠረታዊ ሥርዓት ይመራ

7. የአምላክ ቃል አስተሳሰባችንንም ሆነ ድርጊታችንን በመሠረታዊ ሥርዓቶች እንድንመራ የሚያበረታታን እንዴት ነው?

7 አስተሳሰባችንንም ሆነ ድርጊታችንን በመሠረታዊ ሥርዓቶች እንድንመራ “የአምላካችን ቃል” በተደጋጋሚ ያበረታታናል። ኢየሱስ የሕጉን ፍሬ ሐሳብ ሲጠየቅ፣ አንደኛው ለይሖዋ ያለንን ፍቅር የሚያጎላ ሌላው ደግሞ ሰዎችን እንድንወድ የሚያሳስብ እጥር ምጥን ያሉ ሁለት ዓረፍተ ነገሮች ተናገረ። (ማቴዎስ 22:​37-40) ኢየሱስ ይህንንም ያደረገው በዘዳግም 6:​4, 5 ላይ የሠፈረውን “አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ” የሚለውን የሙሴ ሕግ በአጭሩ በክለሳ መልክ የቀረበበትን ሐሳብ በመጥቀስ ነው። ኢየሱስ ዘሌዋውያን 19:⁠18 ላይ የሚገኘውን የአምላክን መመሪያ በአእምሮው ይዞ እንደነበረም ግልጽ ነው። ንጉሥ ሰሎሞን በመክብብ መጽሐፍ መደምደሚያ ላይ ያሠፈራቸው ግልጽ፣ አጭርና ኃይለኛ ቃላት በርካታ መለኮታዊ ሕጎችን ጠቅለል ባለ መንገድ አቅርበዋቸዋል:- “የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ። እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፣ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፣ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።”​—⁠መክብብ 12:13, 14፤ ሚክያስ 6:8

8. ቁልፍ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ጠንቅቀን መረዳታችን ጥበቃ ያስገኛል የምንለው ለምንድን ነው?

8 እንደዚህ የመሳሰሉ ቁልፍ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በተሟላ መልኩ መረዳታችን በአንድ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ቀጥተኛ መመሪያዎችን እንድንረዳና ተግባራዊ እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል። በተጨማሪም ቁልፍ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሙሉ በሙሉ ካልተረዳናቸውና ካልተቀበልናቸው ጥበብ የተሞላባቸው ውሳኔዎች ማድረግ ሊሳነንና እምነታችን በቀላሉ ሊናጋ ይችላል። (ኤፌሶን 4:​14) እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ እንዲተከሉ ካደረግን ውሳኔዎችን ስናደርግ በቀላሉ እንጠቀምባቸዋለን። ማስተዋል በተሞላበት መንገድ በተግባር የምናውላቸው ከሆነ ስኬት ያስገኙልናል።​—⁠ኢያሱ 1:​8፤ ምሳሌ 4:​1-9

9. የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መረዳትና በሥራ ላይ ማዋል ሁልጊዜ ቀላል የማይሆነው ለምንድን ነው?

9 የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መረዳትና በሥራ ላይ ማዋል ዝርዝር ሕጎችን እንደመከተል ቀላል አይደለም። ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን በመሠረታዊ ሥርዓቶች እየተመሩ ማሰብ የሚጠይቀውን ጥረት እንሸሽ ይሆናል። ውሳኔ የሚጠይቅ ጉዳይ ሲገጥመን ወይም አጣብቂኝ ውስጥ ስንገባ የተወሰነ ደንብ ብናገኝ እንመርጥ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ከሁኔታችን ጋር የሚስማማ አንድ የተወሰነ ሕግ እንዲሰጠን በመጠበቅ ወደ አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ምናልባትም ወደ ጉባኤ ሽማግሌ እንሄድ ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ቀጥተኛ ደንብ አያቀርቡ ይሆናል። ደግሞም ቀጥተኛ ደንብ ብናገኝም እንኳ በማንኛውም ጊዜና በሁሉም ሁኔታዎች ሥር የሚሠራ ላይሆን ይችላል። አንድ ሰው ኢየሱስን “መምህር ሆይ፣ ርስቱን ከእኔ ጋር እንዲካፈል ለወንድሜ ንገረው” ሲል ያቀረበለትን ጥያቄ ታስታውስ ይሆናል። ኢየሱስ በወንድማማቾች መካከል የተፈጠረውን ቅራኔ ለመፍታት የሚያገለግል ሕግ ወዲያውኑ ከመስጠት ይልቅ “ተጠንቀቁ፣ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” በማለት ይበልጥ ስፋት ያለው መሠረታዊ ሥርዓት ነግሮታል። በመሆኑም ኢየሱስ በዚያን ጊዜም ሆነ አሁን የሚጠቅም መመሪያ ሰጥቷል።​—⁠ሉቃስ 12:​13-15

10. ከመሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተን መኖራችን የልባችንን ዝንባሌ የሚገልጠው እንዴት ነው?

10 ቅጣት እንዳይደርስባቸው በመፍራት ብቻ ሕግ የሚያከብሩ ሰዎችን ታውቅ ይሆናል። ለመሠረታዊ ሥርዓት አክብሮት ማሳየት እንዲህ ዓይነቱን ዝንባሌ ለማስወገድ ይረዳል። የመሠረታዊ ሥርዓት ባሕርይ በራሱ፣ የሚመሩበትን ሰዎች ከልብ እንዲታዘዙ ያንቀሳቅሳቸዋል። እንዲያውም አብዛኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ሳያደርጓቸው በቀሩ ሰዎች ላይ ወዲያውኑ ቅጣት አያስከትሉም። ይህም ይሖዋን ለምን እንደምንታዘዝ ለማሳወቅ የሚያስችል አጋጣሚ በመስጠት ምን ዓይነት የልብ ግፊት እንዳለን ያሳያል። ዮሴፍ የጶጢፋር ሚስት ያቀረበችለትን ሥነ ምግባር የጎደለው ጥያቄ እምቢ ማለቱ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። ምንም እንኳ ይሖዋ ምንዝርን የሚቃወም ሕግ በጽሑፍ ገና ያልሰጠና ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ግንኙነት መፈጸም የሚያስከትለው መለኮታዊ ቅጣት የተገለጸ ባይሆንም ዮሴፍ አምላክ ያወጣውን ለጋብቻ ታማኝ የመሆን መሠረታዊ ሥርዓት ያውቅ ነበር። (ዘፍጥረት 2:​24፤ 12:​18-20) “እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?” ሲል ከሰጠው መልስ እንዲህ ዓይነቱ መሠረታዊ ሥርዓት ምን ያህል ተጽዕኖ አሳድሮበት እንደነበር መረዳት እንችላለን።​—⁠ዘፍጥረት 39:​9

11. ክርስቲያኖች የይሖዋ መሠረታዊ ሥርዓቶች በየትኞቹ መስኮች እንዲመሯቸው ይፈልጋሉ?

11 በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች የጓደኛ፣ የመዝናኛ፣ የሙዚቃና የሚነበብ ጽሑፍ ምርጫ በመሳሰሉ የግል ጉዳዮች ረገድ በይሖዋ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራት ይፈልጋሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:​33፤ ፊልጵስዩስ 4:​8) ለይሖዋና ላወጣቸው መሥፈርቶች ያለን እውቀት፣ ማስተዋልና አድናቆት እያደገ ሲሄድ ህሊናችን ማለትም የሥነ ምግባር ስሜታችን የግል ጉዳዮችን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን መለኮታዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ እንድናደርግ ይረዳናል። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የምንመራ ከሆነ በአምላክ ሕግ ውስጥ ማምለጫ ቀዳዳ ለማግኘት አንሞክርም። ወይም አንዱን የአምላክ ሕግ ሳይጥሱ ምን ያህል ርቀው መሄድ እንደሚችሉ ለማየት የሚሞክሩትን ሰዎች መምሰል አንፈልግም። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ራስን ለውድቀት የሚዳርግና ጎጂ መሆኑን እንገነዘባለን።​—⁠ያዕቆብ 1:​22-25

12. በአምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመመራት ቁልፉ ምንድን ነው?

12 ጎልማሳ ክርስቲያኖች መለኮታዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለመከተል የሚያስችለው ቁልፍ ይሖዋ በአንድ ጉዳይ ላይ ያለውን አመለካከት የማወቅ ፍላጎት ማዳበር እንደሆነ ይገነዘባሉ። መዝሙራዊው “እግዚአብሔርን የምትወድዱ፣ ክፋትን ጥሉ” ሲል በጥብቅ አሳስቧል። (መዝሙር 97:​10) ምሳሌ 6:​16-19 አምላክ እንደ ክፋት የሚቆጥራቸውን አንዳንድ ነገሮች ሲዘረዝር እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፣ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤ ትዕቢተኛ ዓይን፣ ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፣ ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ፣ ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፣ በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር፣ በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ።” ይሖዋ በእነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን አመለካከት የማንጸባረቅ ፍላጎት ሕይወታችንን ሲቆጣጠር ከመሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምቶ መኖር የዘወትር ልማዳችን ይሆናል።​—⁠ኤርምያስ 22:​16

ጥሩ ውስጣዊ ግፊት ያስፈልጋል

13. ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ አበክሮ የገለጸው ምን ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖረን ነው?

13 መሠረታዊ ሥርዓቶችን ማወቅና ተግባራዊ ማድረግ ከንቱና የታይታ አምልኮ ከማቅረብ ወጥመድም ይጠብቀናል። መሠረታዊ ሥርዓቶችን በመከተልና ሕጎችን በጭፍን በማክበር መካከል ልዩነት አለ። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ይህን በግልጽ አስቀምጧል። (ማቴዎስ 5:​17-48) ኢየሱስን ያዳምጡ የነበሩ ሰዎች አይሁዳውያን በመሆናቸው አኗኗራቸውን ይመሩ የነበሩት በሙሴ ሕግ እንደነበር አስታውስ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ለሕጉ ያላቸው አመለካከት የተዛባ ነበር። ትኩረት የሰጡት ለሕጉ ቃል እንጂ ሕጉ ለሚያስተላልፈው መንፈስ አልነበረም። እንዲሁም ከአምላክ ትምህርት ይልቅ ወጋቸውን አስበልጠው በማየት የላቀ ትኩረት ይሰጡ ነበር። (ማቴዎስ 12:​9-12፤ 15:​1-9) ከዚህም የተነሳ ሕዝቡ በአጠቃላይ ከመሠረታዊ ሥርዓቶች አንጻር እንዲያስቡ አልተማሩም።

14. ኢየሱስ አድማጮቹ ከመሠረታዊ ሥርዓት አንጻር ማሰብ እንዲችሉ የረዳቸው እንዴት ነው?

14 ከዚህ በተቃራኒ ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ሥነ ምግባርን የሚመለከቱ አምስት ነጥቦችን አካትቷል፤ እነዚህም ቁጣ፣ ጋብቻና ፍቺ፣ ቃል መግባት፣ በቀል እንዲሁም ፍቅርና ጥላቻ ናቸው። ኢየሱስ በእያንዳንዱ ነጥብ ላይ መሠረታዊ ሥርዓትን መከተል ያለውን ጥቅም አሳይቷል። በመሆኑም ኢየሱስ ተከታዮቹ የሚመሩበትን የሥነ ምግባር ደረጃ ከፍ አድርጓል። ለምሳሌ ያህል ምንዝርን በተመለከተ ድርጊታችንን ብቻ ሳይሆን ሐሳባችንንና ምኞታችንን ጭምር የሚጠብቅ መሠረታዊ ሥርዓት ሰጥቶናል:- “ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል።”​—⁠ማቴዎስ 5:28

15. በጭፍን ሕግ የመከተልን ዝንባሌ ማስወገድ የምንችለው እንዴት ነው?

15 ይህ ምሳሌ የይሖዋን መሠረታዊ ሥርዓቶች ዓላማና መንፈስ ፈጽሞ መሳት እንደሌለብን ያሳያል። የሥነ ምግባር ደንብ በመከተል ብቻ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ፈጽሞ ማሰብ የለብንም። ኢየሱስ የአምላክን ምህረትና ፍቅር በመጥቀስ እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት የተሳሳተ መሆኑን አጋልጧል። (ማቴዎስ 12:​7፤ ሉቃስ 6:​1-11) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመከተል ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ውጪ ያሉ አድርግ፣ አታድርግ የሚሉ ሰፊና ግትር ደንቦችን ለመከተል ከመሞከር (ወይም ሌሎች እንዲከተሉ ከመጠበቅ) እንቆጠባለን። ይበልጥ ትኩረት የምንሰጠው ከውጭ ለሚታይ አምልኮ ሳይሆን አምላክን መውደድንና መታዘዝን ለሚመለከቱት መሠረታዊ ሥርዓቶች ይሆናል።​—⁠ሉቃስ 11:​42

አስደሳች ውጤቶች

16. ከአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በስተጀርባ ስላሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምሳሌዎች ጥቀስ።

16 ይሖዋን ለመታዘዝ ስንጥር ሕጎቹ ቁልፍ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን መገንዘባችን ወሳኝ ነው። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያኖች ከጣዖት አምልኮ፣ ከፆታ ብልግናና ደምን አላግባብ ከመጠቀም መራቅ ይገባቸዋል። (ሥራ 15:​28, 29) እነዚህ ክርስቲያናዊ አቋሞች የተመሠረቱት በምን ላይ ነው? አምላክ ለእሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ ይፈልጋል፤ ለትዳር ጓደኛችን ታማኝ መሆን ይገባናል፤ ይሖዋ ሕይወት ሰጪ ነው። (ዘፍጥረት 2:​24፤ ዘጸአት 20:​5፤ መዝሙር 36:​9) መሠረታዊ ሥርዓቶቹ የተመሠረቱባቸውን እነዚህን ነጥቦች መገንዘባችን ተዛማጅ የሆኑትን ሕጎች ለመቀበልና ለመታዘዝ ይበልጥ ቀላል ያደርግልናል።

17. የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ማስተዋልና በሥራ ማዋል የሚያስገኛቸው ጥሩ ውጤቶች ምንድን ናቸው?

17 መሠረት ሆነው የሚያገለግሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ስንረዳና ተግባራዊ ስናደርግ ለጥቅማችን የተሰጡን እንደሆኑ እንገነዘባለን። የአምላክ ሕዝቦች የሚያገኟቸው መንፈሳዊ በረከቶች አብዛኛውን ጊዜ በተጨባጭ በምናገኛቸው ጥቅሞች ይታያሉ። ለምሳሌ ያህል ሲጋራ ከማጨስ የሚርቁ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ ሕይወት የሚመሩና የደምን ቅድስና የሚያከብሩ ሰዎች ለአንዳንድ በሽታዎች ከመጋለጥ ይድናሉ። በተመሳሳይም ከመለኮታዊ እውነት ጋር ተስማምቶ መኖር በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ወይም በቤተሰብ ሕይወታችን ሊጠቅመን ይችላል። እንደዚህ ያሉ በተጨባጭ የምናገኛቸው ጥቅሞች የይሖዋ መሥፈርቶች በእርግጥ ተግባራዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው በማሳየት ዋጋማነታቸውን ያረጋግጣሉ። ሆኖም የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ የምናውልበት ዋነኛው ምክንያት እንደዚህ ያሉትን ተግባራዊ ጥቅሞች ለማግኘት አይደለም። እውነተኛ ክርስቲያኖች ይሖዋን የሚታዘዙት ስለሚወድዱት፣ ሊመለክ የሚገባው ስለሆነና መደረግ ያለበት ትክክለኛ ነገር ስለሆነ ነው።​—⁠ራእይ 4:​10, 11

18. በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ስኬታማ ለመሆን በምን መመራት አለብን?

18 ሕይወታችን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲመራ ማድረጋችን እጅግ የላቀ ሕይወት እንድንመራ የሚያስችለን ከመሆኑም በላይ ሌሎችን ወደ አምላክ ጎዳና እንዲመጡ ሊስባቸው ይችላል። ከሁሉም በላይ አኗኗራችን ይሖዋን ያስከብራል። ይሖዋ በእርግጥ የሚበጀንን የሚያስብልን አፍቃሪ አምላክ መሆኑን እንገነዘባለን። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመሥርተን ውሳኔዎች ስናደርግና ይሖዋ እንዴት እየባረከን እንዳለ ስናይ ከበፊቱ የበለጠ ወደ እሱ እንደቀረብን ሆኖ ይሰማናል። አዎን፣ ከሰማያዊ አባታችን ጋር ያለን ፍቅራዊ ዝምድና ይበልጥ እየጎለበተ ይሄዳል።

ታስታውሳለህን?

• መሠረታዊ ሥርዓት ምንድን ነው?

• መሠረታዊ ሥርዓት ከሕግ የሚለየው እንዴት ነው?

• አስተሳሰባችንም ሆነ ድርጊታችን በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ መሆኑ የሚጠቅመን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በጋና የሚኖር ዊልሰን የተባለ አንድ ክርስቲያን ከጥቂት ቀናት በኋላ ከሥራ እንደሚባረር ተነገረው። በመጨረሻው የሥራ ቀን የኩባንያውን የአስተዳደር ዲሬክተር የግል መኪና እንዲያጥብ ታዘዘ። ዊልሰን መኪናው ውስጥ በርከት ያለ ገንዘብ ሲያገኝ አለቃው፣ ከሥራ በሚባረርበት ዕለት ገንዘቡን ማግኘቱ የአምላክ ስጦታ እንደሆነ ነገረው። ይሁን እንጂ ዊልሰን መጽሐፍ ቅዱስ ሐቀኝነትን በተመለከተ የሚናገረውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ በማድረግ ገንዘቡን ለዲሬክተሩ መለሰለት። በሁኔታው የተገረመውና የተደነቀው ዲሬክተር ዊልሰንን ወዲያውኑ ቋሚ ሠራተኛ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ የኩባንያው ነባር አባል አድርጎ እድገት ሰጠው።​—⁠ኤፌሶን 4:​28

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሩኪያ በ60ዎቹ ዕድሜ የምትገኝ አልባንያዊት ናት። በቤተሰቡ ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ ከ17 ዓመታት በላይ ወንድሟን አኩርፋው ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረችና እውነተኛ ክርስቲያኖች ቂም ከመያዝ በመራቅ ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር እንዳለባቸው ተማረች። ሌሊቱን በሙሉ ስትጸልይ አድራ በማግስቱ በፍርሃት ስሜት ተውጣ ወደ ወንድሟ ቤት ሄደች። በሩን የከፈተችላት የወንድሟ ልጅ በጣም ተገርማ ሩኪያን “ማን ሞተ? ምን ልታደርጊ መጣሽ?” ስትል ጠየቀቻት። ሩኪያ ወንድሟን እንድትጠራላት ጠየቀቻት። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ስለ ይሖዋ ያገኘችው ትምህርት ከወንድሟ ጋር ሰላም ለመፍጠር እንዳነሳሳት በረጋ መንፈስ ገለጸችለት። ተቃቅፈው ከተላቀሱ በኋላ እርቅ የፈጠሩበትን ይህን ልዩ ቀን አከበሩ!​—⁠ሮሜ 12:​17, 18

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማቴዎስ 5:​27, 28

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማቴዎስ 5:​3

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማቴዎስ 5:​24

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ አፉንም ከፍቶ አስተማራቸው።”​—⁠ማቴዎስ 5:1, 2