በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሌላውን ችግር እንደራስ መመልከት—ደግና ሩኅሩኅ ለመሆን የሚረዳ ባሕርይ

የሌላውን ችግር እንደራስ መመልከት—ደግና ሩኅሩኅ ለመሆን የሚረዳ ባሕርይ

የሌላውን ችግር እንደራስ መመልከት—ደግና ሩኅሩኅ ለመሆን የሚረዳ ባሕርይ

ሔለን ኬለር “የሌላውን ሥቃይ ላስታገሰ ሰው፣ ሕይወት ትርጉም አለው” በማለት ጽፋለች። ኬለር የስሜት ቁስል የሚያስከትለውን ሥቃይ እንደተገነዘበች ምንም ጥርጥር የለውም። ገና የ19 ወር ሕፃን ሳለች ባደረባት ሕመም ምክንያት ማየትም ሆነ መስማት ተሳናት። ይሁን እንጂ አንዲት ሩኅሩኅ መምህር በመጀመሪያ በብሬል ማንበብና መጻፍ በኋላም መናገር አስተማረቻት።

አን ሱሊቫን የተባለችው የኬለር መምህር ከአካል ጉዳተኝነት ጋር የሚደረገው ትግል ምን ያህል ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ አሳምራ ታውቅ ነበር። እርሷም ብትሆን በአንድ ወቅት ልትታወር ተቃርባ ነበር። ሆኖም አን በኬለር መዳፍ ላይ “ፊደል በመጻፍ” ከእርስዋ ጋር መግባባት የምትችልበትን መንገድ በትዕግሥት ቀየሰች። ሔለን መምህሯ ባሳየቻት ርኅራኄ በመገፋፋት በቀሪ ሕይወቷ ማየትና መስማት የተሳናቸውን ለመርዳት ቆርጣ ተነሳች። የራሷን ችግሮች በብዙ ትግል ካሸነፈች በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ችግር በመገንዘቧ ልትረዳቸው ፈለገች።

በዚህ ራስ ወዳድ በሆነ ዓለም ውስጥ ‘ርኅራኄ አለማሳየት’ እና የሌሎችን ችግር ችላ ብሎ ማለፍ የተለመደ እንደሆነ አስተውለህ ይሆናል። (1 ዮሐንስ 3:​17) ክርስቲያኖች ግን ባልንጀሮቻቸውን እንዲወድዱና እርስ በርሳቸውም አጥብቀው እንዲዋደዱ ታዝዘዋል። (ማቴዎስ 22:​39፤ 1 ጴጥሮስ 4:​8) ሆኖም የሚከተለውን ሐቅ ሳትገነዘብ አትቀርም:- እርስ በርስ መዋደድ እንዳለብን ብናውቅም የሌሎችን ሥቃይ ማስታገስ የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች ብዙውን ጊዜ ሳንጠቀምባቸው እንቀራለን። ይህ የሚሆንበት ምክንያት ምናልባት ችግራቸውን ሳንገነዘብ በመቅረታችን ሊሆን ይችላል። የሌላውን ችግር እንደራስ የመመልከት ባሕርይ ደጎችና ሩኅሩኆች እንድንሆን ይረዳናል።

የሌላውን ችግር እንደራስ መመልከት ሲባል ምን ማለት ነው?

አንድ መዝገበ ቃላት የሌላውን ችግር እንደራስ መመልከት የሚለውን ሐረግ “የሌላውን ሰው ሁኔታ፣ ስሜትና ዝንባሌ ማወቅና መረዳት” በማለት ይፈታዋል። ራስን በሌላው ቦታ የማስቀመጥ ችሎታ የሚል ፍቺም ተሰጥቶታል። ስለዚህ የሌላውን ችግር እንደራስ ለመመልከት በመጀመሪያ የግለሰቡን ሁኔታ መረዳትን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሁኔታው በግለሰቡ ላይ ያስከተለውን ችግር መጋራትን ይጠይቃል። አዎን፣ የሌላውን ችግር እንደራስ መመልከት የሌላው ሰው ሥቃይ በልባችን ጠልቆ እንዲሰማን ማድረግን ይጨምራል።

“የሌላውን ችግር እንደራስ መመልከት” የሚለው ሐረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኝም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቅሷል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፣ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፣ ርኀሩኆች . . . ሁኑ” በማለት ክርስቲያኖችን መክሯል። (1 ጴጥሮስ 3:​8) “የሌላውን ሰው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “አብሮ መሠቃየት” ወይም “ርኅራኄ ማሳየት” የሚል ቀጥተኛ ትርጉም አለው። ሐዋርያው ጳውሎስም ክርስቲያን ባልንጀሮቹን “ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፣ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ” በማለት ሲያሳስብ ተመሳሳይ ሐሳብ ማስተላለፉ ነው። አክሎም “እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 12:​15, 16) ራሳችንን በባልንጀራችን ቦታ ካላስቀመጥን እርሱን እንደራሳችን አድርገን መውደድ ያስቸግራል ቢባል አትስማማም?

ሁላችንም ለማለት ይቻላል በተፈጥሯችን በተወሰነ መጠን የሌላውን ችግር እንደ ራሳችን አድርገን የመመልከት ዝንባሌ አለን። ድርቅ ያጠቃቸውን ልጆች አሊያም በጭንቀት የተዋጡ ስደተኞችን ሲመለከት ስሜቱ የማይነካ ማን አለ? የልጅዋን ለቅሶ ችላ የሚል አንጀት ያላት የትኛዋ እናት ናት? እንዲህ ሲባል ግን ሁሉም ዓይነት ሥቃይ በቀላሉ ይታወቃል ማለት አይደለም። ችግሩ በእኛው በራሳችን ላይ ደርሶ እስካላየነው ድረስ የመንፈስ ጭንቀት ያለበትን፣ በውስጥ አካል ላይ በሚደርስ ሕመም የሚሠቃይን ሌላው ቀርቶ የአመጋገብ ሥርዓቱ የተዛባበትን ሰው ስሜት መረዳቱ ምንኛ ከባድ ነው! የሆነ ሆኖ ቅዱሳን ጽሑፎች ችግራቸውን የማንጋራቸውን ሰዎች ችግር እንደራሳችን አድርገን መመልከት እንደምንችልና መመልከትም እንዳለብን ያሳያሉ።

የሌላውን ችግር እንደራሳቸው አድርገው የተመለከቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች

የሌላውን ችግር በመረዳት ረገድ ይሖዋ ዓይነተኛው ምሳሌያችን ነው። ይሖዋ ፍጹም ቢሆንም ‘ፍጥረታችንን ስለሚያውቅና አፈር እንደሆንን ስለሚያስብ’ ፍጽምናን አይጠብቅብንም። (መዝሙር 103:​14፤ ሮሜ 5:​12) ከዚህም በተጨማሪ የአቅማችንን ውስንነት ስለሚገነዘብ ‘ከሚቻለን መጠን ይልቅ እንድንፈተን አይፈቅድም።’ (1 ቆሮንቶስ 10:​13) በአገልጋዮቹና በመንፈሱ አማካኝነት መውጫውን ያዘጋጅልናል።​—⁠ኤርምያስ 25:​4, 5፤ ሥራ 5:​32

ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ የሚደርሰው ሥቃይ ይሰማዋል። ከባቢሎን የተመለሱትን አይሁዳውያን “የሚነካችሁ የዓይኑን [“የዓይኔን፣” NW ] ብሌን የሚነካ ነው” ብሏቸው ነበር። (ዘካርያስ 2:​8) አምላክ የሌላውን ችግር እንደሚረዳ ጠንቅቆ የሚያውቀው የመጽሐፍ ቅዱሱ ጸሐፊ ዳዊት “እንባዬን በዕቃህ አጠራቅም፤ ሁሉስ በመዝገብህ የተያዘ አይደለምን?” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 56:​8 አ.መ.ት ) ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ ጽኑ አቋማቸውን ለመጠበቅ በሚያደርጉት ትግል የሚያፈስሱትን እንባ በመዝገብ የተጻፈ ያህል እንደሚያስታውሰው ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው!

ኢየሱስ ክርስቶስም ልክ እንደ ሰማያዊ አባቱ የሌሎች ሥቃይ ቶሎ ይሰማው ነበር። አንድን መስማት የተሳነው ሰው ሲፈውስ ሰውዬው እንዳያፍር ወይም እንዳይደነግጥ በማሰብ ይመስላል ከሕዝቡ ለይቶ ለብቻው ወስዶታል። (ማርቆስ 7:​32-35) በሌላ ጊዜ ደግሞ አንድያ ልጅዋ የሞተባትንና ለመቅበር በጉዞ ላይ የነበረችን መበለት ተመለከተ። ሥቃይዋ ወዲያው ስለተሰማው ቀርቦ ቃሬዛውን በመንካት ወጣቱን ከሞት አስነሳው።​—⁠ሉቃስ 7:​11-16

ከትንሣኤው በኋላም ኢየሱስ ወደ ደማስቆ ይጓዝ የነበረው ሳውል በተከታዮቹ ላይ ያደርስ የነበረው ስደት ምን ያህል እንደተሰማው እንዲገነዘብ አድርጓል። “አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ” ብሎታል። (ሥራ 9:​3-5) አንዲት እናት የታመመ ልጅዋ ሥቃይ እንደሚሰማት ሁሉ ኢየሱስም በተከታዮቹ ላይ የደረሰው ሥቃይ ተሰምቶታል። በተመሳሳይም ሰማያዊው ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ‘በድካማችን ይራራልናል’ ወይም እንደ ሮተርዳም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ድካማችን የእርሱ እንደሚሆን ያደርጋል።”​—⁠ዕብራውያን 4:​15

ሐዋርያው ጳውሎስ የሌሎችን መከራና ሥቃይ መጋራትን ተምሯል። “የሚደክም ማን ነው፣ እኔም አልደክምምን? የሚሰናከል ማን ነው፣ እኔም አልናደድምን?” በማለት ጠይቋል። (2 ቆሮንቶስ 11:​29) አንድ መልአክ ጳውሎስንና ሲላስን በፊልጵስዩስ ታስረው ከነበሩበት እስር ቤት ባስፈታቸው ጊዜ በመጀመሪያ ወደ ጳውሎስ አእምሮ የመጣው ነገር ማንም እንዳላመለጠ ለእስር ቤቱ ጠባቂ መንገር ነበር። ጠባቂው ራሱን ሲገድል ታየው። ጳውሎስ በሮማውያን ልማድ መሠረት አንድ የእስር ቤት ጠባቂ በተለይ ተጠንቅቆ እንዲጠብቀው የተነገረው እስረኛ ቢያመልጥ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚደርስበት ያውቅ ነበር። (ሥራ 16:​24-28) የእስር ቤቱ ጠባቂ በጳውሎስ ሕይወት አድን የደግነት ድርጊት በጥልቅ በመነካቱ እርሱና ቤተሰቡ ክርስትናን ለመቀበል እርምጃ እንዲወስዱ አነሳስቷቸዋል።​—⁠ሥራ 16:​30-34

የሌላውን ችግር እንደራስ የመመልከትን ባሕርይ ማዳበር የሚቻልበት መንገድ

ቅዱሳን ጽሑፎች በተደጋጋሚ ጊዜያት የሰማያዊ አባታችንንና የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ እንድንከተል ስለሚያበረታቱን የሌላውን ችግር እንደራስ መመልከት ልናዳብረው የሚገባ ባሕርይ ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የሌሎችን ችግርና ስሜት ቶሎ የመረዳት ችሎታችንን ማዳበር የምንችልባቸው ሦስት ዋና ዋና መንገዶች አሉ። እነዚህም ማዳመጥ፣ አስተውሎ መመልከትና ራስን በሌሎች ቦታ ማስቀመጥ ናቸው።

አዳምጥ። በጥንቃቄ በማዳመጥ ሌሎች ምን ዓይነት ችግሮችን እየተጋፈጡ እንዳሉ መረዳት እንችላለን። እንዲሁም ይበልጥ ባዳመጥናቸው መጠን እነርሱም ልባቸውን ለመክፈትና ስሜታቸውን ግልጥልጥ አድርገው ለመናገር ይገፋፋሉ። ሚሪያም “እንደሚያዳምጠኝ እርግጠኛ ከሆንኩ አንድን ሽማግሌ ቀርቤ ማነጋገር እችላለሁ” በማለት ተናግራለች። “ችግሬን በእርግጥ እንደሚረዳልኝ ማወቅ እፈልጋለሁ። በጥንቃቄ እንዳዳመጠኝ የሚያሳዩ አመራማሪ ጥያቄዎች ሲጠይቀኝ በእርሱ ላይ ያለኝ ትምክህት ይጨምራል።”

አስተውለህ ተመልከት። ምን እንደሚሰማውም ሆነ በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለ የሚናገረው ሁሉም ሰው አይደለም። ይሁን እንጂ አስተውሎ የሚመለከት አንድ ክርስቲያን የእምነት ባልደረባው መጨነቁን፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ አንድ ወጣት መቆዘሙን አሊያም አንድ ቀናተኛ አገልጋይ መቀዝቀዙን ሊያስተውል ይችላል። እንዲህ ያለው ችግርን ገና ከጅምሩ የማወቅ ችሎታ ለወላጆች በጣም አስፈላጊ ነው። ሜሬ “እንዴት እንደሆነ ባላውቅም እናቴ ገና ሳላናግራት ምን እንደሚሰማኝ ታውቃለች” ብላለች። “ይህም ችግሬን ግልጥልጥ አድርጌ እንድነግራት ይገፋፋኛል።”

ራስህን በእነርሱ ቦታ አስቀምጥ። የሌላውን ችግር እንደራስ ለመመልከት የሚረዳው አንዱና ዋነኛው መንገድ ራስን እንደሚከተለው እያሉ መጠየቅ ነው:- ‘እኔ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ብሆን ኖሮ ምን ይሰማኝ ነበር? ምን ዓይነት ምላሽስ እሰጥ ነበር? ምንስ ያስፈልገኝ ነበር?’ ሦስቱ የኢዮብ ሐሰተኛ አጽናኞች ራሳቸውን በእርሱ ቦታ ማስቀመጥ ተስኗቸው ነበር። በዚህም ምክንያት ኃጢአት ሠርቶ ሊሆን ይችላል በሚል ስሜት ተነሳስተው ፈረዱበት።

ፍጽምና የሌላቸው የሰው ዘሮች አብዛኛውን ጊዜ ስሜትን ከመረዳት ይልቅ ስህተቶችን መለቃቀም ይቀናቸዋል። ይሁን እንጂ ራሳችንን በእነርሱ ቦታ በማስቀመጥ ስሜታቸውን ለመረዳት መጣራችን ከመፍረድ ይልቅ ችግራቸውን እንደራሳችን አድርገን እንድንመለከት ይረዳናል። አንድ ተሞክሮ ያካበተ ሽማግሌ “ምንም ዓይነት ሐሳብ ከመሰንዘሬ በፊት በጥንቃቄ ለማዳመጥና የሁኔታውን አጠቃላይ ገጽታ ለመረዳት ከጣርኩ የተሻለ ምክር እሰጣለሁ” በማለት ተናግሯል።

በዚህ ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሠራጯቸው ጽሑፎች ብዙዎችን ረድተዋል። የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች የመንፈስ ጭንቀትንና በሕፃናት ላይ የሚደርስ በደልን የመሳሰሉትን ውስብስብ ችግሮች የሚዳስሱ ትምህርቶች ይዘው ወጥተዋል። ይህ ወቅታዊ መረጃ አንባቢዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ በይበልጥ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። በተመሳሳይም ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለው መጽሐፍ ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው የሚገጥሟቸውን ችግሮች እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል።

የሌላውን ችግር እንደራስ መመልከት ለክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ይረዳል

ማናችንም ብንሆን በእጃችን ምግብ እያለን እርቦት የሚያለቅስ ልጅ ብናይ ዝም አንልም። የሌላውን ችግር እንደራሳችን አድርገን የምንመለከት ከሆነ የግለሰቡን መንፈሳዊ ሁኔታም እናስተውላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፣ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው” ይላል። (ማቴዎስ 9:​36) ዛሬም በተመሳሳይ መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያሉ ሲሆን እነርሱም እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

በኢየሱስ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም የአንዳንዶችን ልብ ለመንካት ጭፍን ጥላቻን ወይም ሥር የሰደደ ባሕልን ማሸነፍ ይኖርብን ይሆናል። የሌሎችን ችግር እንደራሱ አድርጎ የሚመለከት አገልጋይ በጋራ ሊያስማሙ የሚችሉ ነጥቦችን በማንሳት አሊያም ሰዎችን ይበልጥ ስለሚያሳስቧቸው ነገሮች በመናገር መልእክቱን ይበልጥ ማራኪ ለማድረግ ይጥራል። (ሥራ 17:​22, 23፤ 1 ቆሮንቶስ 9:​20-23) በፊልጵስዩሱ የእስር ቤት ጠባቂ ሁኔታ ላይ እንደታየው የሌላውን ችግር እንደራስ ከመመልከት በመነሳሳት የተከናወነ የደግነት ድርጊት አድማጮቻችን ለመንግሥቱ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ ሊገፋፋቸው ይችላል።

የሌላውን ችግር እንደራስ መመልከት በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችን ድካም እንድናልፍ በመርዳትም ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ያስቀየመንን ወንድም ስሜት ለመረዳት ከጣርን ይቅር ማለቱ ይበልጥ እንደሚቀልለን ምንም ጥርጥር የለውም። እኛም ተመሳሳይ ሁኔታ ቢደርስብን ወይም የእርሱ ዓይነት አስተዳደግ ቢኖረን ኖሮ ተመሳሳይ ነገር እናደርግ ይሆናል። ይሖዋ ችግራችንን ስለሚረዳ ‘አፈር መሆናችንን ለማስታወስ’ ይገፋፋል። እኛስ የሌላውን ችግር እንደራሳችን አድርገን መመልከታችን የሌሎችን አለፍጽምና ግምት ውስጥ እንድናስገባና ‘በነጻ ይቅር እንድንላቸው’ ሊገፋፋን አይገባም?​—⁠መዝሙር 103:​14፤ ቆላስይስ 3:​13

ምክር መስጠት ቢያስፈልገን እንኳ አስቀድመን ስህተት የሠራውን ሰው ስሜትና ችግር መገንዘባችን ምክሩን ይበልጥ ደግነትንና አሳቢነትን በሚያሳይ መንገድ ለመስጠት ያስችለናል። የሌላውን ችግር እንደራሱ የሚመለከት ክርስቲያን ሽማግሌ ራሱን እንደሚከተለው በማለት ያሳስባል:- ‘እኔም እንዲህ ያለውን ስህተት ልሠራ እችላለሁ። እኔም እንዲህ በመሰለ ሁኔታ ውስጥ ልወድቅ እችላለሁ።’ ጳውሎስ “እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ” በማለት አሳስቧል።​—⁠ገላትያ 6:​1

የሌላውን ችግር እንደራስ መመልከት አንድ ክርስቲያን ባልንጀራችን አፍ አውጥቶ ባይጠይቀንም እንኳ አቅማችን ከፈቀደ የእርዳታ እጃችንን እንድንዘረጋለት ሊገፋፋንም ይችላል። ሐዋርያው ዮሐንስ የሚከተለውን ጽፏል:- “የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፣ ወንድሙም የሚያስፈልገውን ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፣ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ [እ]ንዴት ይኖራል? . . . በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ።”​—⁠1 ዮሐንስ 3:​17, 18

“በሥራና በእውነት” ለመውደድ በመጀመሪያ ወንድማችን የጎደለውን ለይተን ማወቅ ይኖርብናል። ሌሎችን የመርዳት ዓላማ በመያዝ የጎደሏቸውን ነገሮች በጥንቃቄ እንመለከታለን? የሌሎችን ችግር እንደራስ መመልከት ትርጉሙ ይኸው ነው።

የሌላውን ችግር እንደራስ የመመልከት ባሕርይን አዳብሩ

በተፈጥሯችን የሌላውን ችግር እንደራስ የመመልከት ባሕርይ እምብዛም አይኖረን ይሆናል። ሆኖም ማዳበር እንችላለን። በጥንቃቄ የምናዳምጥ፣ አስተውለን የምንመለከትና አዘውትረን ራሳችንን በሌሎች ቦታ የምናስቀምጥ ከሆነ የሌላውን ችግር እንደራስ የመመልከት ባሕርያችን ይዳብራል። በውጤቱም ለልጆቻችን፣ ለሌሎች ክርስቲያኖችና ለጎረቤቶቻችን የበለጠ ፍቅር፣ ደግነትና ርኅራኄ ለማሳየት እንገፋፋለን።

ራስ ወዳድነት የሌላውን ችግር እንደራስ የመመልከት ችሎታህን እንዲያጠፋብህ ፈጽሞ አትፍቀድ። ጳውሎስ “እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፣ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ” በማለት ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 2:​4) ዘላለማዊ ተስፋችን የተመካው የሌላውን ችግር በሚረዱት በይሖዋና በሊቀ ካህኑ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነው። ስለዚህ ይህንን ባሕርይ የማዳበር ሥነ ምግባራዊ ግዴታ አለብን። የሌላውን ችግር እንደራስ መመልከታችን የተሻልን አገልጋዮችና ወላጆች እንድንሆን ያስችለናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የሌላውን ችግር እንደራስ የመመልከት ባሕርይ ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ እንደሚያስገኝ’ እንድንገነዘብ ይረዳናል።​—⁠ሥራ 20:​35

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሌላውን ችግር እንደራስ መመልከት ሌሎችን የመርዳት ዓላማ በመያዝ የጎደሏቸውን ነገሮች በጥንቃቄ ማስተዋልን ይጨምራል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዲት አፍቃሪ እናት በተፈጥሮ ለልጅዋ ከምታሳየው ስሜት የሌላውን ችግር እንደራስ መመልከትን መማር እንችል ይሆን ?