በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የራስልን ጽሑፎች ያደነቁ ሁለት ፓስተሮች

የራስልን ጽሑፎች ያደነቁ ሁለት ፓስተሮች

የራስልን ጽሑፎች ያደነቁ ሁለት ፓስተሮች

በ1891 ይሖዋን በሚያመልኩ እውነተኛ ክርስቲያኖች ታሪክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተው ቻርልስ ቴዝ ራስል ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፓን ጎበኘ። በአንዳንድ ሪፖርቶች መሠረት ራስል በኢጣሊያ ፒኔሮሎ ባደረገው ጥቂት ቆይታ ዎልደንሳውያን በሚል ስያሜ የሚታወቅ የአንድ ሃይማኖታዊ ቡድን የቀድሞ ፓስተር ከሆኑት ከፕሮፌሰር ዳንኤሌ ሪቫር ጋር ተገናኘ። a ሪቫር አገልግሎታቸውን ካቆሙም በኋላ ከዎልደንሳውያን ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው ቢሆንም አእምሮአቸውን ክፍት በማድረግ ሲ ቲ ራስል የጻፋቸውን በርካታ መጻሕፍት ያነብቡ ነበር።

በ1903 ሪቫር፣ መለኮታዊው የዘመናት ዕቅድ በሚል ርዕስ ራስል ያዘጋጀውን መጽሐፍ ወደ ኢጣሊያንኛ ከተረጎሙ በኋላ በራሳቸው ወጪ አሳተሙት። ይህ የሆነው በኢጣሊያንኛ የተዘጋጀው ኦፊሴላዊ እትም ከመውጣቱ በፊት ነበር። ሪቫር በመጽሐፉ መቅድም ላይ የሚከተለውን ጽፈዋል:- “ይህንን የመጀመሪያ የኢጣሊያንኛ እትም ጌታ እንዲጠብቀው እንለምናለን። መጽሐፉ ፍጹም ባይሆንም እንኳ ቅዱስ ስሙ እንዲወደስ አስተዋጽኦ የሚያደርግና ኢጣሊያንኛ ተናጋሪ ልጆቹ ለእርሱ ይበልጥ ያደሩ እንዲሆኑ የሚያበረታታ ይሆን ዘንድ እንመኛለን። ይህንን መጽሐፍ በማንበብ በአምላክ ዕቅድና ፍቅር ረገድ የተንጸባረቀው ባለጠግነት፣ ጥበብና እውቀት ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ የሚያስተውሉ ሁሉ ልባቸው የዚህን መጽሐፍ ዝግጅት በጸጋው ዳር ላደረሰው አምላክ በአመስጋኝነት ስሜት ይሞላ ዘንድ ምኞታችን ነው።”

ሪቫር የጽዮን መጠበቂያ ግንብ እና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ የተባሉትንም መጽሔቶች ወደ ኢጣሊያንኛ ተርጉመዋል። በ1903 ይህ የመጠበቂያ ግንብ የቀድሞ እትም በየሦስት ወሩ ይወጣ ነበር። ፕሮፌሰር ሪቫር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ (የይሖዋ ምሥክሮች የቀድሞ አጠራር ነው) ባይሆኑም በተማሪዎቹ ጽሑፎች ላይ የተገለጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለማሰራጨት ከፍተኛ ቅንዓት አሳይተዋል።

“ከዓይኔ ላይ ቅርፊት የወደቀልኝ ያህል ነው”

ለራስል ጽሑፎች ከፍተኛ አድናቆት የነበራቸው ሌላው ዎልደንሳዊ ፓስተር ደግሞ ጁሴፔ ባንቼቲ ናቸው። ከካቶሊክ ወደ ዎልደንሳዊነት ከተለወጡት አባታቸው ዎልደንሳዊ ትምህርት አግኝተው ነበር። በ1894 ጁሴፔ ፓስተር ከሆኑ በኋላ በአፑሊያ፣ በአብሩዚ እንዲሁም በኤልባና በሲሲሊ ደሴቶች በሚገኙ የዎልደንሳውያን ማኅበረሰቦች ውስጥ አገልግለዋል።

ራስል ያዘጋጀው መለኮታዊ የዘመናት ዕቅድ የተባለ መጽሐፍ በ1905 ኦፊሴላዊ በሆነ መንገድ በኢጣልያንኛ ሲታተም ባንቼቲ መጽሐፉን በተመለከተ ልብ የሚነካ ሐሳብ ሰጥተዋል። ሐሳቡ ላ ሪቪስታ ክሪስቲያና በተባለው የፕሮቴስታንት መጽሔት ላይ ወጥቷል። “በእኛ አመለካከት” አሉ ባንቼቲ የራስል መጽሐፍ “ማንኛውም ክርስቲያን ጠቃሚና የሚክስ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት ለማድረግ ሊጠቀምበት የሚችል ከፍተኛ ብርሃን የፈነጠቀበትና ትክክለኛ መመሪያ የሚሰጥ መጽሐፍ ነው። . . . መጽሐፉን እንዳነበብኩት ከዓይኔ ላይ ቅርፊት የወደቀልኝ ያህል ሆኖ ተሰማኝ። ወደ አምላክ የሚወስደው መንገድ ይበልጥ ቀጥ ያለና ቀላል ሆኖ ታየኝ። የሚጋጩ የሚመስሉ ሐሳቦች እንኳ ሳይቀሩ ተወግደዋል። በአንድ ወቅት ለመረዳት ይከብዱ የነበሩ መሠረተ ትምህርቶች ቀላልና ለመቀበል የማያስቸግሩ ሆነዋል። ቀደም ሲል ለመረዳት ያዳግቱ የነበሩ ሐሳቦች አሁን ግልጽ ሆነዋል። ዓለምን በክርስቶስ በኩል ለማዳን የተደረገው ድንቅ ዝግጅት ግልጽና ሕያው ሆኖ በመቅረቡ የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው የሚሉትን የሐዋርያውን ቃላት ለማስተጋባት ተገድጃለሁ!”​—⁠ሮሜ 11:​33

በ1925 ሬሚዦ ኩሚኔቲ የተባሉ ሰው እንደገለጹት ባንቼቲ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ሥራ ጋር “በእጅጉ የተስማሙ” ሲሆን መሠረተ ትምህርቶቻቸውንም “ሙሉ በሙሉ አሳማኝ” ሆነው አግኝተዋቸዋል። ባንቼቲ በራሳቸው መንገድ እነዚህን መሠረተ ትምህርቶች ለሌሎች ለማሳወቅ ጥረዋል።

እንደ ይሖዋ ምሥክሮች ሁሉ ባንቼቲም በቅዱስ ጽሑፉ መሠረት በምድራዊ ትንሣኤ ያምኑ እንደነበረ ካዘጋጁአቸው ጽሑፎች መረዳት ይቻላል። በተጨማሪም ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ጋር በመስማማት ኢየሱስ የሞተበት ዓመት አስቀድሞ መወሰኑንና ስለ 70ዎቹ ሳምንታት በሚናገረው በዳንኤል ትንቢት ውስጥ መገለጹን ያምኑ ነበር። (ዳንኤል 9:​24-27) ከአንድ ጊዜ በላይ የገዛ ቤተ ክርስቲያናቸውን ትምህርቶች በግልጽ በመቃወም የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል በዓመት አንድ ጊዜ ማለትም “በዓሉ በሚውልበት ትክክለኛ ዕለት ላይ” መከበር አለበት የሚል እምነት ነበራቸው። (ሉቃስ 22:​19, 20) ባንቼቲ የዳርዊንን የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ከመቃወማቸውም በላይ እውነተኛ ክርስቲያኖች በጦርነት መካፈል የለባቸውም የሚል ጽኑ እምነት ነበራቸው።​—⁠ኢሳይያስ 2:​4

በአንድ ወቅት ባንቼቲ ስለ ራስል ጽሑፎች ጄ ካምቤል ዎል ከተባለ ሰው ጋር ተወያይተዋል። ዎል ላነሳቸው ትችቶች መልስ ሲሰጡ ባንቼቲ የሚከተለውን ብለዋል:- “የራስልን ስድስት ጥራዞች ብታነብብ ከፍተኛ ደስታና ጥልቅ እርካታ እንደምታገኝና እኔንም ከልብ እንደምታመሰግነኝ እርግጠኛ ነኝ። እንዲህ ስል በመሠረተ ትምህርቱ መኩራራቴ አይደለም። ሆኖም እነዚያን መጻሕፍት ያነበብኳቸው ከአሥራ አንድ ዓመታት በፊት ነው። ሙሉ በሙሉ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በተመሠረተና አስተማማኝ በሆነ ሥራ አማካኝነት እንዲህ ያለውን ብርሃንና መጽናኛ አምላክ በፊቴ ስላስቀመጠልኝ በየቀኑ አመሰግነዋለሁ።”

“አዳምጡ፣ አዳምጡ፣ አዳምጡ”

ዳንኤሌ ሪቫር እና ጁሴፔ ባንቼቲ የተባሉት እነዚህ ሁለት ዎልደንሳውያን ፓስተሮች ራስል መጽሐፍ ቅዱስን ስላብራራበት መንገድ ያላቸውን አድናቆት መግለጻቸው ትልቅ ትርጉም ያዘለ ነው። ባንቼቲ የሚከተለውን ጽፈዋል:- “ፓስተሮቻችንንና የሃይማኖት ፕሮፌሰሮቻችንን ጨምሮ የኢቫንጀሊካል አማኞች የሆንን ማንኛችንም ብንሆን ምንም አናውቅም። ገና ልንማራቸው የሚገቡ ብዙ ብዙ ነገሮች አሉ። . . . መቆየትና ማዳመጥ [አለብን።] ሁሉንም እናውቃለን ብለን ማሰብም ሆነ እንድንመረምረው የተሰጠንን ከመመርመር ወደኋላ ማለት አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ አዳምጡ፣ አዳምጡ፣ አዳምጡ።”

በየዓመቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ቤታቸው ድረስ የሚያመጡላቸውን የመንግሥት መልእክት ያዳምጣሉ። በየትኛውም ቦታ የሚገኙ አእምሮአቸውን ክፍት ያደረጉና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተጠሙ ሰዎች ኢየሱስ “ና፣ ተከተለኝ” በማለት ያቀረበውን ግብዣ በመቀበል ላይ ናቸው።​—⁠ማርቆስ 10:​17-21፤ ራእይ 22:​17

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ዎልደንሳውያን ይህንን ስያሜ ያገኙት ፒዬር ቮዴ ወይም ፒተር ዋልዶ ከተባለው በ12ኛው መቶ ዘመን ከኖረ የሊዮን ፈረንሳይ ነጋዴ ነው። ዋልዶ በእምነቱ ምክንያት ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተገለለ። ዎልደንሳውያንን በሚመለከት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት “ዎልደንሳውያን​—⁠ከመናፍቅነት ወደ ፕሮቴስታንትነት” በሚል ርዕስ በመጋቢት 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፕሮፌሰር ዳንኤሌ ሪቫር

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጁሴፔ ባንቼቲ

[ምንጭ]

ባንቼቲ:- La Luce, April 14, 1926