በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መለኮታዊ ብቃቶችን ማሟላት ይሖዋን ከፍ ከፍ ያደርጋል

መለኮታዊ ብቃቶችን ማሟላት ይሖዋን ከፍ ከፍ ያደርጋል

መለኮታዊ ብቃቶችን ማሟላት ይሖዋን ከፍ ከፍ ያደርጋል

“በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ።”​—⁠መዝሙር 69:​30

1. (ሀ) ይሖዋ ከፍ ከፍ መደረግ የሚገባው ለምንድን ነው? (ለ) በምስጋና ከፍ ከፍ ልናደርገው የምንችለው እንዴት ነው?

 ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ፣ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥና ፈጣሪ ነው። በመሆኑም ስሙና ዓላ​ማው ከፍ ከፍ ሊደረጉ ይገባቸዋል። ይሖዋን ከፍ ከፍ ማድረግ ሲባል በቃልም ሆነ በድርጊት ከሁሉ የላቀ ቦታ መስጠት፣ ማሞገስ፣ ማወደስ ማለት ነው። ‘በምስጋና’ እንዲህ ለማድረግ አሁን እያደረገልን ስላለውና ወደፊት ስለሚያደርግልን ነገር ምንጊዜም አመስጋኝ መሆን ይጠይቅብናል። በዚህ ረገድ ሊኖረን የሚገባው አመለካከት በሰማይ የሚኖሩ ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታት ባወጁት ራእይ 4:​10, 11 ላይ ይገኛል። እንዲህ ይላል:- “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል።” ይሖዋን ከፍ ከፍ የምናደርገው እንዴት ነው? ስለ እርሱ በመማርና ከእኛ የሚፈልግብንን በማሟላት ነው። መዝሙራዊው “አንተ አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ” በማለት በተናገረ ጊዜ የተሰማው ዓይነት ስሜት ሊያድርብን ይገባል።​—⁠መዝሙር 143:​10

2. ይሖዋ እሱን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ሰዎችን እንዴት ይመለከታቸዋል? ከፍ ከፍ የማያደርጉትንስ?

2 ይሖዋ ከፍ ከፍ የሚያደርጉትን ሰዎች በአድናቆት ይመለከታቸዋል። ‘ለሚፈልጉት ዋጋ ይሰጣል’ የተባለውም ለዚህ ነው። (ዕብራውያን 11:​6) የሚሰጠው ዋጋ ምንድን ነው? ኢየሱስ በሰማይ ለሚኖረው አባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል። (ዮሐንስ 17:​3) አዎን፣ “[ይሖዋን] በምስጋና ከፍ ከፍ” የሚያደርጉ ሁሉ “ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝሙር 37:​29) በሌላ በኩል ደግሞ “ለኃጢአተኛ . . . ተስፋ የለውም።” (ምሳሌ 24:​20) እንዲሁም ይሖዋ በቅርቡ ክፉዎችን አጥፍቶ ጻድቃንን ስለሚያድን በእነዚህ የፍጻሜ ቀናት ይሖዋን ከፍ ከፍ ማድረግ አጣዳፊ ነው። “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”​—⁠1 ዮሐንስ 2:​17፤ ምሳሌ 2:​21, 22

3. የሚልክያስን መጽሐፍ በትኩረት መከታተል የሚገባን ለምንድን ነው?

3 “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ” በመሆኑ የይሖዋ ፈቃድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​16 NW ) ይህ የአምላክ ቃል ይሖዋ እሱን ከፍ ከፍ የሚያደርጉትን ሰዎች እንዴት እንደሚባርክና እሱን ከፍ ከፍ የማያደርጉ ደግሞ ምን እንደሚደርስባቸው የሚገልጹ በርካታ ታሪኮችን ይዘግባል። ከእነዚህ ዘገባዎች መካከል አንዱ በነቢዩ ሚልክያስ ዘመን በእስራኤል ውስጥ የተፈጸሙ ታሪኮችን ይዟል። ሚልክያስ በስሙ የሚጠራውን መጽሐፍ የጻፈው ነህምያ የይሁዳ ገዥ ሆኖ ባገለገለበት በ443 ከዘአበ ገደማ ነበር። ኃይለኛና ስሜት ቀስቃሽ የሆነው ይህ መጽሐፍ ‘እኛን የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን እንዲገሥጸን ሲባል የተጻፈ’ እውቀትና ትንቢት ይዟል። (1 ቆሮንቶስ 10:​11) ሚልክያስ የተናገራቸውን ቃላት በትኩረት መከታተላችን ይህ ክፉ ሥርዓት የሚጠፋበትን ‘ታላቁና የሚያስፈራውን የይሖዋን ቀን’ ተዘጋጅተን እንድንጠብቅ ሊረዳን ይችላል።​—⁠ሚልክያስ 4:​5

4. በሚልክያስ ምዕራፍ 1 ውስጥ ትኩረታችንን የሚስቡት ስድስት ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?

4 ከዛሬ 2, 400 ዓመታት በፊት የተጻፈው የሚልክያስ መጽሐፍ፣ በዚህ በ21ኛው መቶ ዘመን የምንኖረውን ለዚህ ታላቅና አስፈሪ የይሖዋ ቀን ተዘጋጅተን እንድንጠብቅ የሚረዳን እንዴት ነው? የመጀመሪያው ምዕራፍ ይሖዋን በምስጋና ከፍ ከፍ በማድረግ የእርሱን ሞገስና የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ የሚያስችሉንን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ቢያንስ ስድስት ነጥቦችን እንድናስተውል ይረዳናል። (1) ይሖዋ ሕዝቡን ይወድዳል። (2) ለቅዱሳን ነገሮች አድናቆት ማሳየት ይገባናል። (3) ይሖዋ ምርጣችንን እንድንሰጠው ይጠብቅብናል። (4) ለእውነተኛ አምልኮ የሚያንቀሳቅሰው ከራስ ወዳድነት የጠራ ፍቅር እንጂ ስግብግብነት አይደለም። (5) በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አገልግሎት ለይስሙላ የሚደረግ ከባድ ሸክም አይደለም። (6) እያንዳንዳችን ለአምላክ መልስ መስጠት አለብን። እንግዲያው በሚልክያስ መጽሐፍ ላይ ከተመሠረቱት ሦስት ርዕሶች መካከል የመጀመሪያ በሆነው በዚህ ርዕስ ውስጥ ሚልክያስ ምዕራፍ 1ን በጥልቀት በመመርመር እነዚህን ነጥቦች በየተራ እንመልከት።

ይሖዋ ሕዝቡን ይወድዳል

5, 6. (ሀ) ይሖዋ ያዕቆብን የወደደው ለምንድን ነው? (ለ) እኛም የያዕቆብን የታማኝነት ምሳሌ ከኮረጅን ምን ልንጠብቅ እንችላለን?

5 ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚወድድ በሚልክያስ ትንቢት መግቢያ ቁጥሮች ላይ በግልጽ ሰፍሯል። መጽሐፉ “ለእስራኤል የሆነ የእግዚአብሔር ቃል ሸክም ይህ ነው” በሚሉት ቃላት መልእክቱን ይከፍታል። ከዚህም በላይ አምላክ ሕዝቡን “ወድጃችኋለሁ” ይላቸዋል። ይሖዋ ምሳሌ ሲጠቅስ በዚያው ቁጥር ላይ “ያዕቆብንም ወደድሁ” ይላል። ያዕቆብ በይሖዋ ላይ እምነት ያለው ሰው ነበር። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ የያዕቆብን ስም ለውጦ እስራኤል ብሎ የጠራው ሲሆን እሱም ለመላው የእስራኤል ብሔር አባት ለመሆን በቅቷል። ይህ የሆነው ያዕቆብ በነበረው እምነት ምክንያት ይሖዋ ስለወደደው ነው። ይሖዋ የያዕቆብ ዓይነት ዝንባሌ የነበራቸውን በሕዝቡ መካከል የነበሩትንም ሌሎች ሰዎች እንዲሁ ወድዷል።​—⁠ሚልክያስ 1:​1, 2

6 ይሖዋን የምንወድድና በታማኝነት ከሕዝቡ ጋር የምንተባበር ከሆነ 1 ሳሙኤል 12:​22 ላይ “እግዚአብሔር ስለ ታላቅ ስሙ ሕዝቡን አይተውም” ከሚለው መግለጫ መጽናኛ ማግኘት እንችላለን። ይሖዋ ሕዝቡን ይወድዳል እንዲሁም የዘላለም ሕይወት በመስጠት ወሮታ ይከፍላቸዋል። ስለዚህም እንዲህ የሚል እናነብባለን:- “በእግዚአብሔር ታመን፣ መልካምንም አድርግ፣ በምድርም ተቀመጥ፣ ታምነህም ተሰማራ። በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፣ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።” (መዝሙር 37:​3, 4) ለይሖዋ ያለን ፍቅር በሚልክያስ ምዕራፍ 1 ላይ የተጠቀሰውን ሁለተኛ ነጥብም ይጨምራል።

ለቅዱስ ነገሮች አድናቆት አሳይ

7. ይሖዋ ዔሳውን የጠላው ለምንድን ነው?

7 ሚልክያስ 1:​2, 3ን ስናነብብ ይሖዋ “ያዕቆብንም ወደድሁ” ካለ በኋላ “ዔሳውንም ጠላሁ” በማለት ተናግሯል። ልዩነት የፈጠረው ምንድን ነው? ያዕቆብ ይሖዋን ከፍ ከፍ ሲያደርግ መንትያ ወንድሙ ዔሳው ግን እንደዚያ አላደረገም። በተጨማሪም ዔሳው ኤዶም ተብሎ ተጠርቷል። በሚልክያስ 1:​4 ላይ የኤዶም ምድር የበደል ዳርቻ ተብሎ ከመጠራቱም በላይ ነዋሪዎቹም ተወግዘዋል። ኤዶም የሚለው ስም (“ቀይ” ማለት ነው) ለዔሳው የተሰጠው ለጥቂት ቀይ ወጥ ሲል የብኩርና መብቱን ለያዕቆብ ከሸጠ በኋላ ነበር። ዘፍጥረት 25:​34 “ዔሳው ብኩርናውን አቃለላት” ይላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሴሰኛም የሚሆን እንዳይገኝ ወይም ስለ አንድ መብል በኩርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይሆን ተጠንቀቁ” በማለት የእምነት ባልንጀሮቹን አሳስቧል።​—⁠ዕብራውያን 12:​14-16

8. ጳውሎስ ዔሳውን ከሴሰኛ ጋር እንዲያዛምደው ያደረገው ምንድን ነው?

8 ጳውሎስ ዔሳው የፈጸመውን ድርጊት ከሴሰኝነት ጋር ያዛመደው ለምን ነበር? ምክንያቱም የዔሳው ዓይነት የአእምሮ ዝንባሌ መያዝ አንድን ሰው ቅዱስ ነገሮችን ወደ ማቃለል ሊመራው ስለሚችል ነው። ይህ ደግሞ እንደ ዝሙት ያለ ከባድ ኃጢአት ወደ መሥራት ሊያደርስ ይችላል። ስለሆነም እያንዳንዳችን ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን:- ‘ክርስቲያናዊ ውርሻዬን ማለትም የዘላለም ሕይወቴን እንደ ምስር ወጥ ላለ መናኛና ጊዜያዊ ነገር ለመለወጥ የምፈተንበት ጊዜ አለን? ምናልባት ሳይታወቀኝ ቅዱስ ነገሮችን አቃልላለሁን?’ ዔሳው ሥጋዊ ፍላጎቱን ለማርካት ተጣድፎ ነበር። ያዕቆብን “ቶሎ በል፤ . . . ከዚህ ቀይ ወጥ አብላኝ” ብሎታል። (ዘፍጥረት 25:​30 አ.መ.ት ፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን) የሚያሳዝነው አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች “ቶሎ ልበል! ክቡር ጋብቻ እስክፈጽም ምን አስጠበቀኝ” ከማለት የሚያስቆጥር ድርጊት ፈጽመዋል። የተከፈለው ተከፍሎ ወሲባዊ እርካታ ማግኘት የምስር ወጥ ሆኖባቸዋል።

9. ለይሖዋ አክብሮታዊ ፍርሃት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

9 የሥነ ምግባር ንጽሕናን፣ የአቋም ጽናትንና መንፈሳዊ ውርሻችንን በመናቅ ቅዱስ ነገሮችን ፈጽሞ አናቃልል። እንደ ዔሳው ከመሆን ይልቅ የታማኙን የያዕቆብን ምሳሌ የምንከተልና መለኮታዊ ብቃቶችን በማሟላት ለቅዱስ ነገሮች የጠለቀ አድናቆት የምናሳይ እንሁን። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ የሚፈልግብንን ብቃቶች በጥንቃቄ በማሟላት ነው። ይህ ደግሞ ሚልክያስ ምዕራፍ 1 ወደሚያሳስበን ሦስተኛ ነጥብ ይመራናል። ይህ ነጥብ ምንድን ነው?

ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት

10. ካህናቱ የይሖዋን ገበታ ያቃለሉት በምን መንገድ ነው?

10 በሚልክያስ ዘመን ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ ያገለግሉ የነበሩ የይሁዳ ካህናት ለይሖዋ ምርጥ መሥዋዕት አያቀርቡም ነበር። ሚልክያስ 1:​6-8 እንዲህ ይላል:- “እናንተ ስሜን የምታቃልሉ ካህናት ሆይ፣ ልጅ አባቱን፣ ባሪያም ጌታውን ያከብራል፤ እኔስ አባት ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” ካህናቱም “ስምህን ያቃለልን በምንድር ነው?” ብለው መልሰው ጠየቁት። ይሖዋ “በመሠዊያዬ ላይ ርኩስ እንጀራ ታቀርባላችሁ” በማለት መለሰላቸው። ካህናቱ “ያረከስንህ በምንድር ነው?” ብለው ጠየቁት። ይሖዋ “የእግዚአብሔር ገበታ የተነቀፈ ነው በማለታችሁ ነው” ሲል መለሰላቸው። እነዚህ ካህናት “ይህ ክፉ አይደለም” እያሉ ጉድለት ያለባቸውን እንስሳት ለመሥዋዕት ባቀረቡ ቁጥር የይሖዋን ገበታ ማቃለላቸው ነበር።

11. (ሀ) ይሖዋ ተቀባይነት የሌላቸውን መሥዋዕቶች በተመለከተ ምን ብሎ ተናገረ? (ለ) ሕዝቡ በአጠቃላይ በደለኛ ነበር ሊባል የሚችለው በምን መንገድ ነው?

11 በዚህ የተነሳ ይሖዋ እነዚህን ተቀባይነት የሌላቸውን መሥዋዕቶች በሚመለከት “ያንን ለአለቃህ አቅርብ፤ በውኑ በአንተ ደስ ይለዋልን? ወይስ ፊትህን ይቀበላልን?” በማለት በምክንያት ያስረዳቸው ጀመር። አለቃቸው እንዲህ ባለው እጅ መንሻ አይደሰትም። ታዲያ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ እንደነዚህ ያሉትን ጎዶሎ ስጦታዎች እንዴት ሊቀበል ይችላል! ስህተቱን የፈጸሙት ካህናቱ ብቻ አልነበሩም። እርግጥ ነው፣ እነርሱም ጉድለት ያለባቸውን መሥዋዕቶች በመቀበል ለይሖዋ ንቀት እንዳላቸው አሳይተዋል። ሆኖም ሕዝቡ በአጠቃላይ ከበደለኝነት ነጻ ነበርን? በፍጹም! ዕውር፣ አንካሳና ታማሚ የሆኑ እንስሳትን መርጦ መሥዋዕት ለማድረግ ወደ ካህናቱ የሚያመጣው ሕዝቡ ነበር። ይህ እንዴት ያለ ኃጢአት ነው!

12. ለይሖዋ ምርጣችንን እንድንሰጥ እርዳታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

12 የምንችለውን ያህል ምርጣችንን ለይሖዋ መስጠታችን እርሱን በእርግጥ እንደምንወደው የምናሳይበት መንገድ ነው። (ማቴዎስ 22:​37, 38) ዛሬ የይሖዋ ድርጅት በሚልክያስ ዘመን ከነበሩት ዓመፀኛ ካህናት በተለየ መንገድ መለኮታዊ ብቃቶችን በማሟላት ይሖዋን በምስጋና ከፍ ከፍ እንድናደርግ የሚረዱ ግሩም ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶችን ይሰጠናል። ከሚልክያስ ምዕራፍ 1 ልንገነዘብ የምንችለው አራተኛው አስፈላጊ ነጥብ ከዚህ ጋር የሚዛመድ ነው።

ለእውነተኛ አምልኮ የሚያነሳሳን ፍቅር እንጂ ስግብግብነት አይደለም

13. ካህናቱ ለአምልኮ የሚያነሳሳቸው ስግብግብነት እንደነበረ የሚያሳየው የትኛው ድርጊታቸው ነው?

13 በሚልክያስ ዘመን የነበሩት ካህናት ራስ ወዳዶች፣ ፍቅር የጎደላቸውና የገንዘብ ፍቅር የተጠናወታቸው ነበሩ። ይህን እንዴት እናውቃለን? ሚልክያስ 1:​10 [NW ] እንዲህ ይላል:- “ከእናንተ መካከል አለዋጋ በሮችን የሚዘጋ ማን ነው? አለዋጋም በመሠዊያዬ ላይ እሳት አናቀርብም ብላችኋል። በእናንተ ደስ አይለኝም፣ ቁርባንንም ከእጃችሁ አልቀበልም፣ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።” አዎን፣ እነዚህ ስግብግብ ካህናት በጣም ቀላል ለሆኑ የቤተ መቅደስ አገልግሎቶች፣ በሮችን ለመዝጋትና የመሠዊያውን እሳት ለማቀጣጠል እንኳን ሳይቀር ክፍያ ይጠይቁ ነበር! ይሖዋ ቁርባኑን ከእጃቸው አልቀበልም ማለቱ የሚያስደንቅ አይደለም!

14. የይሖዋ ምሥክሮችን ለስብከት የሚያነሳሳቸው ፍቅር ነው ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

14 በጥንቷ ኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩት የኃጢአተኛ ካህናት ስግብግብነትና ስስት የአምላክ ቃል ስግብግቦች የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ የሚናገረውን ሐሳብ ያስታውሰናል። (1 ቆሮንቶስ 6:​9, 10 አ.መ.ት ) ስለ እነዚህ ካህናት የግል ጥቅም አሳዳጅነት ማሰባችን የይሖዋ ምሥክሮች በማከናወን ላይ ለሚገኙት ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ ያለንን አድናቆት ከፍ ያደርግልናል። በበጎ ፈቃድ የምናከናውነው ከመሆኑም በላይ ለአገልግሎታችን የምናስከፍለው ምንም ዋጋ የለም። ‘የአምላክን ቃል በፍጹም አንሸቃቅጥም።’ (2 ቆሮንቶስ 2:​17) ሁላችንም እንደ ጳውሎስ “የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ደመወዝ [“ያለ ደመወዝ በደስታ፣” NW ] ሰበክሁላችሁ” ለማለት እንችላለን። (2 ቆሮንቶስ 11:​7) ጳውሎስ ምሥራቹን ‘በደስታ እንደሰበከ’ ልብ በል። ይህ ደግሞ ከሚልክያስ ምዕራፍ 1 የምናገኘውን አምስተኛ ነጥብ ይጠቁመናል።

ለአምላክ የሚቀርበው አምልኮ ለይስሙላ የሚደረግ ከባድ ሸክም አይደለም

15, 16. (ሀ) መሥዋዕት ማቅረብን በሚመለከት ካህናቱ ምን ዓይነት አመለካከት ነበራቸው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች መሥዋዕቶቻቸውን የሚያቀርቡት እንዴት ነው?

15 በጥንቷ ኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩት እምነት የለሾቹ ካህናት መሥዋዕት ማቅረብን ለደንቡ ያህል የሚቀርብ አሰልቺ ሥራ አድርገው ቆጥረውት ነበር። ከባድ ሸክም ሆኖባቸው ነበር። በሚልክያስ 1:​13 ላይ እንደምናነበው አምላክ “እነሆ፣ ይህ ድካም ነው ብላችሁ ጢቅ አላችሁበት” ብሏቸዋል። እነዚህ ካህናት በአምላክ ቅዱስ ነገሮች ላይ ጢቅ ብለዋል ወይም ቅዱስ ነገሮችን አንቋሽሸዋል። ከእኛ መካከል ማናችንም ብንሆን እንደነርሱ እንዳንሆን መጸለይ ይኖርብናል። አልፎ ተርፎም በ1 ዮሐንስ 5:⁠3 ላይ በሚገኙት ቃላት ላይ የተንጸባረቀውን መንፈስ ሁልጊዜ እናሳይ:- “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።”

16 ለአምላክ መንፈሳዊ መሥዋዕቶችን ደስ እያለን እናቅርብ እንጂ እንደ አድካሚ ሸክም አንቁጠረው። “ኃጢአትን ሁሉ አስወግድ፣ በቸርነትም ተቀበለን፣ በወይፈንም ፋንታ [“ተመልሰንም፣” NW ] የከንፈራችንን ፍሬ [“ወይፈን፣” NW ] እንሰጣለን” የሚለውን ትንቢታዊ ቃል እንስማ። (ሆሴዕ 14:​2) “የከንፈራችንን ወይፈን” የሚለው ሐረግ መንፈሳዊ መሥዋዕቶችን ማለትም ይሖዋን ለማወደስና ዓላማውን ለማሳወቅ የምንናገራቸውን ቃላት ያመለክታል። ዕብራውያን 13:​15 “እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምሥጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፣ በእርሱ [በኢየሱስ ክርስቶስ] እናቅርብለት” ይላል። መንፈሳዊ መሥዋዕታችን ለአምላክ ያለን ልባዊ ፍቅር መግለጫ እንጂ ለይስሙላ የሚደረግ የአምልኮ ሥርዓት ባለመሆኑ ምንኛ ደስተኞች ነን! ይህ ደግሞ ከሚልክያስ ምዕራፍ 1 ልናገኝ ወደምንችለው ስድስተኛ ነጥብ ይመራናል።

እያንዳንዱ ስለ ራሱ መልስ መስጠት አለበት

17, 18. (ሀ) ይሖዋ ‘በሽንገላ የሚሄደውን’ የሚረግመው ለምንድን ነው? (ለ) በሽንገላ የሚሄዱ ሰዎች ግምት ውስጥ ሳያስገቡ የቀሩት ምንድን ነው?

17 በሚልክያስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ግለሰቦች ለድርጊቶቻቸው በግል በአምላክ ፊት ተጠያቂዎች ነበሩ፤ እኛም ተጠያቂዎች ነን። (ሮሜ 14:​12፤ ገላትያ 6:​5) በዚህ መሠረት ሚልክያስ 1:​14 “ስሜም በአሕዛብ ዘንድ የተፈራ ነውና በመንጋው ውስጥ [እንከን የሌለበት] ተባት እያለው ለጌታ ተስሎ ነውረኛውን የሚሠዋ ሸንጋይ ሰው ርጉም ይሁን” ይላል። መንጋ የነበረው ማንኛውም ሰው በዛ ብለው የሚነዱ በርካታ ከብቶች ይኖሩታል። አንድ ከብት ወይም አንድ በግ ብቻ ኖሮት ምንም ዓይነት ሌላ ምርጫ የሌለው ሰው አይደለም። ለመሥዋዕት የሚቀርብ እንስሳ በሚመርጥበት ጊዜ ዕውር ወይም አንካሳ ወይም ታማሚ ለመምረጥ አይገደድም። እንዲህ ያለውን የአካል ጉድለት ያለበትን እንስሳ ቢመርጥ ለይሖዋ መሥዋዕት የማቅረብን ዝግጅት እንዳቃለለ ያሳያል። አንድ መንጋ ከብት ያለው ሰው እንከን የሌለበትን እንስሳ ማግኘት እንደማያቅተው የታወቀ ነው!

18 ስለዚህ ተስማሚ የሆነ ተባት እንስሳ እያለው ዕውር፣ አንካሳ ወይም ታማሚ የሆነውን ወደ ካህናቱ የሚወስድን ምናልባትም መሬት ለመሬት እየጎተተ የሚያመጣውን “ሸንጋይ” ሰው ይሖዋ መርገሙ አለበቂ ምክንያት አልነበረም። ሆኖም አንድም ካህን ከአምላክ ሕግ ጠቅሶ እንዲህ ያለውን እንስሳ ለመሥዋዕት ማቅረብ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን እንዳስረዳ የሚያሳይ አንድም ፍንጭ አናገኝም። (ዘሌዋውያን 22:​17-20) ማንኛውም ምክንያታዊ የሆነ ግለሰብ እንዲህ ያለውን ስጦታ ለአለቃው ቢያቀርብ የአለቃውን ሞገስ እንደማያገኝ ያውቃል። ይሁን እንጂ እስራኤላውያኑ ስጦታ የሚያቀርቡት ከአለቃቸው እጅግ የላቀ ክብር ላለው አካል ይኸውም ለአጽናፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ ለይሖዋ ነበር። ሚልክያስ 1:​14 ሁኔታውን እንዲህ በማለት አስቀምጦታል:- “እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝና፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ ስሜም በአሕዛብ ዘንድ የተፈራ ነው።”

19. ምን ለማየት እንናፍቃለን? ምን ማድረግስ ይኖርብናል?

19 የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች እንደመሆናችን ታላቁ ንጉሥ ይሖዋ በመላው የሰው ልጅ የሚከበርበትን ጊዜ በናፍቆት እንጠባበቃለን። በዚያን ጊዜ “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።” (ኢሳይያስ 11:​9) እስከዚያው ድረስ ግን “በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ” በማለት ውዳሴ ያቀረበውን መዝሙራዊ ምሳሌ በመኮረጅ የይሖዋን መለኮታዊ ብቃቶች ለማሟላት የተቻለንን እናድርግ። (መዝሙር 69:​30) በዚህ ረገድ የሚልክያስ ትንቢት ሊጠቅመን የሚችል ተጨማሪ ምክር ይዞልናል። እንግዲያው በሚቀጥሉት ሁለት ርዕሶች ውስጥ ለተቀሩት የሚልክያስ መጽሐፍ ክፍሎች ከፍ ያለ ትኩረት እንስጥ።

ታስታውሳለህ?

• ይሖዋን ከፍ ከፍ ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

• በሚልክያስ ዘመን ካህናት ያቀርቡት የነበረው መሥዋዕት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያላገኘው ለምን ነበር?

• ለይሖዋ የውዳሴ መሥዋዕት ማቅረብ የምንችለው እንዴት ነው?

• ለእውነተኛ አምልኮ የሚያነሳሳን ምን መሆን ይኖርበታል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሚልክያስ ትንቢት የእኛን ዘመን ያመለክታል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዔሳው ቅዱስ ነገሮችን አላደነቀም

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካህናቱና ሕዝቡ ተቀባይነት የሌለው መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ያለ ክፍያ የውዳሴ መሥዋዕት ያቀርባሉ