በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በልጆቻችን ልብ ውስጥ የይሖዋን ፍቅር መትከል

በልጆቻችን ልብ ውስጥ የይሖዋን ፍቅር መትከል

የሕይወት ታሪክ

በልጆቻችን ልብ ውስጥ የይሖዋን ፍቅር መትከል

ቨርነር ማትሰን እንደተናገረው

ከጥቂት ዓመታት በፊት የመጀመሪያው ልጄ ሃንስ ቨርነር አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ሰጠኝ። ሽፋኑ ውስጥ “ውድ አባቴ፣ የይሖዋ ቃል ቤተሰባችንን በሕይወት መንገድ ላይ መምራቱን እንዲቀጥል እመኛለሁ። ከምስጋና ጋር፣ የመጀመሪያ ልጅህ” የሚሉትን ቃላት አስፍሮ ነበር። እነዚህ ቃላት ልቤን ምን ያህል በአመስጋኝነትና በደስታ ስሜት እንደሞሉት ወላጆች ይገነዘባሉ። ሆኖም በወቅቱ ቤተሰባችን ገና ምን ዓይነት ፈተና እንደሚጠብቀው አልተገነዘብኩም ነበር።

በ1924 ሃምቡርግ ከሚባለው የጀርመን ወደብ 20 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ በሚገኘው በሃልስተንቤክ ተወለድኩ። ያሳደጉኝ እናቴና ወንድ አያቴ ነበሩ። የሙያ ትምህርት በመከታተል ላይ ሳለሁ በ1942 ለውትድርና ተመልምዬ ቬርማክት ከተባለው የጦር ኃይል ጋር እንድቀላቀል ተደረግኩ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከሩሲያ ጋር ስንዋጋ ያጋጠመኝ ሁኔታ በጣም ዘግናኝ ከመሆኑ የተነሳ በቃላት መግለጽ እንኳ ያቅተኛል። የአንጀት ተስቦ በሽታ የያዘኝ ሲሆን ከሕክምናው በኋላ እንደገና ወደ ጦር ግንባር ተላክሁ። ጥር 1945 በፖላንድ ሉትዝ ከባድ የመቁሰል አደጋ ደረሰብኝና በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ገባሁ። ጦርነቱ ሲያበቃም እዚያው ነበርኩ። በሆስፒታልና በኋላም ኖለንጋሚ በሚገኘው እሥር ቤት በቆየሁባቸው ጊዜያት ለማሰላሰል የሚያስችል ጊዜ አግኝቼ ነበር። በእርግጥ አምላክ አለ? ካለስ እንዲህ ያለ ጭካኔ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? የሚሉት ጥያቄዎች አእምሮዬን ፋታ ነሱት።

ከእስር ከተለቀቅሁ ብዙም ሳይቆይ መስከረም 1947 ካርላን አገባሁ። በአንድ ከተማ ውስጥ ብናድግም ካርላ ካቶሊክ ነበረች። በአስተዳደጌ ውስጥ ሃይማኖት ምንም ቦታ አልነበረውም። ያጋባን ቄስ ቢያንስ በየምሽቱ የጌታን ጸሎት አንድ ላይ ሆነን እንድንጸልይ ነገረን። ስለምን ነገር እንደምንጸልይ ባናውቅም እርሱ እንዳለን አደረግን።

ከአንድ ዓመት በኋላ ሃንስ ቨርነር ተወለደ። በዚሁ ጊዜ አካባቢ ማለት ይቻላል ቪልሄልም አሬንስ የተባለ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አስተዋወቀኝ። እንዲሁም አንድ ቀን ጦርነት እንደሚቆም ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳየኝ። (መዝሙር 46:​9) በ1950 መከር ላይ ራሴን ለአምላክ ወስኜ ተጠመቅሁ። ከአንድ ዓመት በኋላ ውዷ ባለቤቴ ስትጠመቅ የተሰማኝ ደስታ ከፍተኛ ነበር!

ልጆችን በይሖዋ መንገዶች ማሳደግ

ጋብቻን የመሠረተው ይሖዋ እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ አነበብኩ። (ዘፍጥረት 1:​26-28፤ 2:​22-24) ሃንስ ቨርነር፣ ካርል ሄንዝ፣ ሚካኤል፣ ጋብሪኤል እና ቶማስ የተባሉት ልጆቻችን ሲወለዱ በቦታው መገኘቴ ጥሩ ባልና አባት ለመሆን የገባሁትን ቃል አጠንክሮልኛል። ካርላ እና እኔ እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ በጣም ተደስተን ነበር።

በ1953 ኑረምበርግ ውስጥ የተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ቤተሰባችን በልዩ ትዝታ የሚያስታውሰው ወቅት ነው። አርብ ከሰዓት በኋላ “ልጆችን በአዲሱ ዓለም ኅብረተሰብ ማሳደግ” በሚል ርዕስ በቀረበው ንግግር ላይ ተናጋሪው ፈጽሞ የማንረሳውን ነገር ተናገረ:- “ለልጆቻችን ልንሰጥ የምንችለው ከሁሉ የላቀ ውርሻ በውስጣቸው የአምላክ አገልጋይ የመሆንን ፍላጎት መትከል ነው።” በይሖዋ እርዳታ ካርላና እኔ እንዲህ ማድረግ ፈለግን። ግን እንዴት?

በመጀመሪያ በእያንዳንዱ ቀን በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን የመጸለይ ልማድ አዳበርን። ይህም በልጆቹ አእምሮ ውስጥ የጸሎትን አስፈላጊነት ቀርጿል። እያንዳንዱ ልጅ ገና ከትንሽነቱ ጀምሮ ከምግብ በፊት ሁልጊዜ መጸለይን ተምሯል። እንዲያውም ገና ሕፃናት ሳሉ ጡጧቸውን ሲያዩ ወዲያው ትንንሽ እጆቻቸውን ያቆላልፉና ትንሿን ራሳቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር። በአንድ ወቅት የይሖዋ ምሥክር ባልሆኑ በአንድ የባለቤቴ ዘመድ ሠርግ ላይ እንድንገኝ ተጋበዝን። የሠርጉን ሥነ ሥርዓት ተከትሎ የሙሽራይቱ ወላጆች እንግዶቹን ምግብ ለመጋበዝ ወደ ቤታቸው ጠሯቸው። ሁሉም ሰው ወዲያው መመገብ ፈልጎ ነበር። ሆኖም የአምስት ዓመቱ ካርል ሄንዝ ይህ ተገቢ ሆኖ አልተሰማውም። “እባካችሁ፣ በመጀመሪያ እንጸልይ” በማለት ተናገረ። ወዲያው የተጠሩት እንግዶች በመጀመሪያ እርሱን ከዚያም እኛን በመጨረሻም ጋባዦቹን ተመለከቱ። ማንኛውንም ዓይነት ግራ መጋባት ለማስቀረት ስል ጋባዦቹን አስፈቅጄ የምስጋና ጸሎት አቀረብኩ።

ይህ አጋጣሚ “ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት አስታውሶኛል። (ማቴዎስ 21:​16) ቋሚና ልባዊ የሆነው የጸሎት ልማዳችን ልጆቹ ይሖዋን አፍቃሪ ሰማያዊ አባታቸው እንደሆነ አድርገው እንዲመለከቱት እንደረዳቸው እርግጠኞች ነን።

በይሖዋ ፊት ያለብን ኃላፊነት

ልጆች አምላክን እንዲወድዱ ማስተማር ቃሉን አዘውትሮ ማንበብንና ማጥናትን ይጠይቃል። ይህንን በአእምሮአችን ይዘን በየሳምንቱ ብዙውን ጊዜ ሰኞ ማታ የቤተሰብ ጥናት እናደርግ ነበር። በመጀመሪያውና በመጨረሻው መካከል የዘጠኝ ዓመት ልዩነት ስለነበረ የልጆቹ ፍላጎት የዚያኑ ያህል የተለያየ ነበር። ስለዚህ ለሁሉም ተመሳሳይ ትምህርት በአንድ ጊዜ አንሸፍንም ነበር።

ለምሳሌ ዕድሜያቸው ለትምህርት ላልደረሱት ልጆች ጥናቱን ቀለል እናደርግላቸዋለን። ካርላ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አንስታ ታወያያቸዋለች። አሊያም በጽሑፎቹ ላይ የሚገኙትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥዕሎች ትጠቀምባቸዋለች። ትንንሽ ልጆቻችን በጠዋት ተነስተው አልጋችን ላይ ለመውጣት እየታገሉ አዲሱ ዓለም   a በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን የሚወዷቸውን ሥዕሎች ለማሳየት ይቀሰቅሱን የነበረበትን ጊዜ ፈጽሞ አልረሳውም።

ካርላ ይሖዋን እንድንወደው የሚያደርጉንን በርካታ ምክንያቶች ለልጆቹ በትዕግሥት ለማስተማር የሚያስችል ዘዴ ቀየሰች። ይህ ቀላልና የማያስቸግር ሊመስል ይችላል። ሆኖም ይህ ሥራ በአካላዊና በስሜታዊ መንገድ ለካርላም ሆነ ለእኔ የሙሉ ጊዜ ሥራ ያህል ሆኖ ነበር። ቢሆንም ተስፋ አልቆረጥንም። ይሖዋን የማያውቁ ሰዎች በእነርሱ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ከመጀመራቸው በፊት በጨቅላ አእምሮአቸው ውስጥ የይሖዋን ፍቅር መትከል ፈለግን። በዚህም ምክንያት ልጆቻችን ገና መቀመጥ እንደጀመሩ በቤተሰብ ጥናት ላይ እንዲገኙ ለማድረግ ወሰንን።

ካርላ እና እኔ ወላጆች እንደመሆናችን መጠን በአምልኮ ጉዳዮች ረገድ ለልጆቻችን ጥሩ ምሳሌ መተው እንዳለብን ተገነዘብን። ስለዚህ ስንበላም ሆነ አትክልት ስንኮተኩት አሊያም በእግር ስንጓዝ እያንዳንዱ ልጅ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና እንዲያጠነክር ለመርዳት እንጥር ነበር። (ዘዳግም 6:6, 7) እያንዳንዱ ልጅ ገና ከትንሽነቱ ጀምሮ የራሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ እንዲኖረው እናደርግ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ጽሑፎች እንደደረሱን የእያንዳንዱን የቤተሰብ አባል ስም በራሱ የግል ቅጂ ላይ እጽፋለሁ። በዚህም ልጆቹ የራሳቸውን ቅጂ መለየትን ተምረዋል። ከጊዜ በኋላ እያንዳንዱ ልጅ ከንቁ! መጽሔት እትሞች ላይ አንድ ክፍል አንብቦ እንዲመጣ ማድረግ ጀመርን። እሁድ ምሳ ከበላን በኋላ ልጆቹ ትምህርቱን እንዴት እንደተረዱት ያብራሩልን ነበር።

ለልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን ትኩረት መስጠት

እርግጥ ነው፣ ሁኔታዎች ሁልጊዜ ቀላል ነበሩ ማለት አይደለም። ልጆቹ እያደጉ ሲሄዱ በልባቸው ውስጥ የይሖዋን ፍቅር ለመትከል በመጀመሪያ በልባቸው ውስጥ ምን ነገር እንዳለ መረዳት እንዳለብን ተገነዘብን። ይህ ደግሞ እነርሱን ማዳመጥ ማለት ነበር። አንዳንድ ጊዜ ልጆቻችን ቅር የሚያሰኙ ነገሮች ሲያጋጥሟቸው ካርላ እና እኔ ቁጭ ብለን ከእነርሱ ጋር በጉዳዩ ላይ እንወያይበታለን። ከቤተሰብ ጥናት በኋላ ሌላ ግማሽ ሰዓት ጨመርን። በዚህ ጊዜ ውስጥ እያንዳንዱ ልጅ የሚሰማውን ሁሉ የመናገር ነጻነት ነበረው።

ለምሳሌ ያህል ቶማስና ጋብሪኤል የተባሉት የመጨረሻዎቹ ልጆቻችን እኛ ወላጆች ለትልቁ ወንድማቸው እንደምናዳላ ተሰምቷቸው ነበር። በውይይቱ መካከል “አባባ፣ እማማና አንተ ሃንስ ቨርነር ሁልጊዜ የፈለገውን እንዲያደርግ የምትፈቅዱለት ይመስለናል” በማለት የተሰማቸውን በግልጽ ተናገሩ። በመጀመሪያ ጆሮዬን ማመን አቅቶኝ ነበር። ጉዳዩን በሐቀኝነት ከመረመርነው በኋላ ግን ልጆቹ እውነታቸውን እንደሆነ ተገነዘብን። በመሆኑም ሁሉንም በእኩል ዓይን ለማየት ይበልጥ ጥረት አደረግን።

አንዳንድ ጊዜ ልጆቹን በችኮላ ወይም ያለ አግባብ እቀጣቸው ነበር። እንዲህ ባሉት ጊዜያት እኛ ወላጆች ይቅርታ መጠየቅን መማር ነበረብን። ከዚያ በኋላ ወደ ይሖዋ በጸሎት እንቀርባለን። ልጆቹ አባታቸው ይሖዋንና እነርሱን ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ እንደሆነ ማወቃቸው አስፈላጊ ነበር። ይህም ከእነርሱ ጋር ሞቅ ያለና የተቀራረበ ዝምድና እንድንመሠርት አስችሎናል። አብዛኛውን ጊዜ “እናንተ እውነተኛ ጓደኞቻችን ናችሁ!” በማለት ይነግሩናል። ይህም በጣም ያስደስተን ነበር።

በቤተሰብ መልክ አብሮ መሥራት አንድነት ያስገኛል። ለዚህም ሲባል እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የራሱ የሆነ የሥራ ድርሻ ነበረው። ሃንስ ቨርነር በሳምንት አንድ ጊዜ ገበያ ወጥቶ የቤቱን አስቤዛ እንዲያደርግ ተመድቦ ነበር። ለዚህም የሚገዛቸውን ሸቀጣ ሸቀጦች የያዘ ዝርዝርና የተወሰነ ገንዘብ ይሰጠው ነበር። በአንድ ወቅት ገንዘብም ሆነ የሚገዛውን የሸቀጥ ዝርዝር ሳንሰጠው ቀረን። እናቱን ሲጠይቃት ገንዘብ እንዳላገኘን ነገረችው። ከዚያም ልጆቹ እርስ በርስ መንሾካሾክ ጀመሩ። ወዲያው ሁሉም የገንዘብ ሣጥኖቻቸውን በጠረጴዛው ላይ ዘረገፉት። ከዚያም ሁሉም በአንድ ድምፅ “እማማ፣ አሁን ገበያ መውጣት እንችላለን!” በማለት ተናገሩ። አዎን፣ ልጆቹ ለችግር ጊዜ መድረስን የተማሩ ሲሆን ይህም ቤተሰቡን ከምንጊዜውም ይበልጥ አቀራርቦታል።

ልጆቹ እያደጉ ሲሄዱ ወንዶቹ በሴቶች ላይ ዓይናቸውን መጣል ጀመሩ። ለምሳሌ ያህል ቶማስ ከአንዲት የ16 ዓመት ምሥክር ጋር ፍቅር ቢጤ ጀማምሮት ነበር። ልጅትዋን ለቁም ነገር የሚያስባት ከሆነ እርስዋን ለማግባትና ሚስትና ልጆች ለማስተዳደር ዝግጁ መሆን እንዳለበት ገለጽኩለት። ቶማስ ገና የ18 ዓመት ልጅ ስለነበር ለትዳር እንዳልደረሰ ተገነዘበ።

በቤተሰብ መልክ እድገት ማድረግ

ልጆቹ ገና ለጋ ሳሉ ተራ በተራ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መካፈል ጀመሩ። ክፍላቸውን ሲያቀርቡ በጥንቃቄ እናዳምጣቸው ነበር። ለአምላክ ያላቸውን ልባዊ ፍቅር ሲገልጹ በመመልከታችን ተበረታትተናል። አልፎ አልፎ ቤታችን ያርፉ የነበሩ የወረዳና የአውራጃ የበላይ ተመልካቾች የራሳቸውን ተሞክሮ ይነግሩን አሊያም ከመጽሐፍ ቅዱስ ያነብቡልን ነበር። እነዚህ ወንዶችና ሚስቶቻቸው በቤተሰባችን ልብ ውስጥ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ፍቅር ለመትከል አስተዋጽኦ አድርገዋል።

የአውራጃ ስብሰባዎች በናፍቆት የሚጠበቁ ጊዜያት ነበሩ። እነዚህ ስብሰባዎች በልጆቻችን ልብ ውስጥ የአምላክ አገልጋይ የመሆንን ምኞት ለመትከል በምናደርገው ጥረት ቁልፍ ሚና ነበራቸው። ይህ ወቅት ልጆቹ ካርዳቸውን በደረቶቻቸው ላይ ለጥፈው ወደ ስብሰባው የሚሄዱበት ወቅት ስለነበር ለእነርሱ ልዩ ወቅት ነበር። ሃንስ ቨርነር በአሥር ዓመቱ ሲጠመቅ በጣም ተደሰትን። ብዙዎች ለመጠመቅ ገና ትንሽ እንደሆነ ቢሰማቸውም በ50 ዓመቱ ይሖዋን 40 ለሚያክሉ ዓመታት ማገልገል በመቻሉ ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆነ ነግሮኛል።

ለልጆቻችን ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና መመሥረት አስፈላጊ እንደሆነ ብንነግራቸውም ራሳቸውን እንዲወስኑ ግን አልተጫንናቸውም። ይሁን እንጂ ሌሎቹም በራሳቸው ተነሳሽነት ሲጠመቁ መመልከቱም አስደስቶናል።

ሸክማችንን በይሖዋ ላይ መጣልን መማር

በ1971 ሃንስ ቨርነር ከ51ኛው የመጠበቂያ ግንብ የጊልያድ ትምህርት ቤት ተመርቆ በሚስዮናዊነት እንዲያገለግል ወደ ስፔይን ሲላክ ደስታችን ወሰን አልነበረውም። ሌሎቹም ልጆች ለተወሰነ ጊዜ በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ተካፍለዋል። ይህም ለእኛ ለወላጆች በጣም የሚያስደስት ነበር። በዚህ ጊዜ አካባቢ ሃንስ ቨርነር በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን መጽሐፍ ቅዱስ ሰጠኝ። አሁን በቤተሰብ መልክ ያሳለፍነው አስደሳች ሕይወት ያበቃለት መሰለ።

በዚህ ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከይሖዋ ጋር መጣበቅ እንዳለብን ተገነዘብን። ለምን? ምክንያቱም አንዳንዶቹ ልጆቻችን እምነታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈትኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው በመመልከታችን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ጋብሪኤል የተባለችው ውዷ ልጃችን ከፈተና አላመለጠችም ነበር። በ1976 ሎታርን አገባች። ከሠርጋቸው ብዙም ሳይቆይ ሎታር ታመመ። ከቀን ወደ ቀን እየደከመ በመምጣቱ እስከሞተበት ዕለት ድረስ ተንከባክባዋለች። ጤናማ የነበረ አንድ የቤተሰብ አባል ሲታመምና ሲሞት መመልከቱ የይሖዋ ፍቅራዊ እርዳታ በእጅጉ እንደሚያስፈልገን አስገንዝቦናል።​—⁠ኢሳይያስ 33:​2

በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያገኘኋቸው መብቶች

በ1955 የጉባኤ አገልጋይ (ዛሬ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች የሚባለው ነው) ሆኜ ስሾም ኃላፊነቱን ለመሸከም ብቃቱ እንዳለኝ ሆኖ አልተሰማኝም ነበር። ብዙ የሚሠራ ስለነበር የጉባኤ ኃላፊነቶቼን ለመወጣት አንዳንድ ጊዜ ከሌሊቱ 10 ሰዓት መነሳት ነበረብኝ። ባለቤቴና ልጆቼ ቤት ውስጥ የሚሠራ ሥራ ቢኖርም እንኳ እኔን ላለመረበሽ ጥንቃቄ በማድረግ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጉልኝ ነበር።

እንዲሁም በቤተሰብ መልክ የቻልነውን ያህል አብረን ጊዜ እናሳልፍ ነበር። አንዳንድ ጊዜ አሠሪዬ መኪናውን ስለሚያውሰኝ ቤተሰቡን ራቅ ወዳለ ቦታ ይዤ እሄድ ነበር። ልጆቹ ጫካ ውስጥ ሆነን መጠበቂያ ግንብ የምናጠናባቸው ጊዜያት በጣም ያስደስቷቸው ነበር። በተጨማሪም አንዳንድ ጊዜ በሃርሞኒካዬ አጃቢነት መዝሙር እየዘመርን ጫካው ውስጥ በእግራችን እንንሸራሸር ነበር።

በ1978 ተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካች (ተጓዥ አገልጋይ) ሆኜ ተሾምኩ። በጭንቀት ተውጬ “ይሖዋ፣ የሚሆንልኝ አይመስለኝም። እንድሞክረው ከፈለግህ ግን አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርጋለሁ” በማለት ጸለይኩ። ከሁለት ዓመታት በኋላ ማለትም በ54 ዓመቴ አነስተኛ ንግዴን ለመጨረሻው ልጄ ለቶማስ አስተላለፍኩ።

ልጆቻችን ራሳቸውን በመቻላቸው ካርላና እኔ በይሖዋ አገልግሎት የምናሳልፈው ተጨማሪ ጊዜ አገኘን። በዚያው ዓመት የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩና የሃምቡርግን የተወሰኑ ክፍሎች እንዲሁም መላውን ሽሌዚዊግሆልስቲን እንድሸፍን ተመደብኩ። ልጆች በማሳደግ ተሞክሮ ስለነበረን ወላጆችንና ልጆቻቸውን በተሻለ መንገድ መያዝ ችለናል። ብዙ ወንድሞች የወረዳችን ወላጆች ብለው ይጠሩን ነበር።

ካርላ ለአሥር ዓመታት ከእኔ ጋር በወረዳ ሥራ ስትካፈል ከቆየች በኋላ የቀዶ ሕክምና ማድረግ አስፈለጋት። በዚያው ዓመት ሐኪሞች እኔም በአንጎሌ ውስጥ እብጠት እንዳለ አረጋገጡ። ስለዚህ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ አከናውን የነበረውን ሥራ በማቆም የአንጎል ቀዶ ሕክምና አደረግሁ። እንደገና ተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ መሥራት የቻልኩት ከሦስት ዓመታት በኋላ ነበር። አሁን ካርላና እኔ በ70ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የምንገኝ ሲሆን የተጓዥነቱንም ሥራ አቁመናል። ይሖዋ ተቀብዬ መፈጸም የማልችለውን መብት ለማግኘት መፍጨርጨሩ ምንም ዋጋ እንደሌለው እንድንገነዘብ ረድቶናል።

ካርላና እኔ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት ይሖዋ በልጆቻችን ልብ ውስጥ የእውነትን ፍቅር ለመትከል ያደረግነውን ጥረት ስለባረከልን በጣም አመስጋኞች ነን። (ምሳሌ 22:​6) ባለፉት ዓመታት ይሖዋ መመሪያና ሥልጠና በመስጠት ኃላፊነቶቻችንን እንድንወጣ ረድቶናል። አሁን እድሜያችን የገፋና አቅመ ደካሞች ብንሆንም እንኳ ለይሖዋ ያለን ፍቅር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጠንካራና ሕያው ነው።​—⁠ሮሜ 12:​10, 11

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። አሁን ግን መዘጋጀቱን አቁሟል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1965 ቤተሰባችን ሃምቡርግ በሚገኘው የኤልቤ ወንዝ ዳርቻ ሲጓዝ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1998 በርሊን በተደረገው ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኙ አንዳንድ የቤተሰቡ አባላት

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከካርላ ጋር