በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከይሖዋ ቀን በሕይወት የሚተርፈው ማን ነው?

ከይሖዋ ቀን በሕይወት የሚተርፈው ማን ነው?

ከይሖዋ ቀን በሕይወት የሚተርፈው ማን ነው?

“እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል።”​—⁠ሚልክያስ 4:​1

1. ሚልክያስ የዚህን ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ የገለጸው እንዴት ነው?

 ነቢዩ ሚልክያስ በአምላክ መንፈስ ተገፋፍቶ በጣም በቅርቡ ስለሚፈጸሙ አስደናቂ ክንውኖች የሚናገሩ ትንቢቶችን መዝግቧል። እነዚህ ክንውኖች በምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱን ግለሰብ የሚነኩ ናቸው። ሚልክያስ 4:​1 እንዲህ ይላል:- “እነሆ፣ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፣ ሥርንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ የሚደርሰው ጥፋት ምንኛ ታላቅ ነው? ዳግመኛ እንደማያቆጠቁጥ ከሥሩ እንደተነቀለ ዛፍ ይሆናል።

2. አንዳንድ ጥቅሶች የይሖዋን ቀን የሚገልጹት እንዴት ነው?

2 ‘ነቢዩ ሚልክያስ ትንቢት የተናገረው ስለየትኛው “ቀን” ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ይህ “ቀን” በኢሳይያስ 13:​9 ላይ ከተተነበየው ቀን ጋር አንድ ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “እነሆ፣ ምድሪቱን ባድማ ሊያደርግ፣ ኃጢአተኞችዋንም ከእርስዋ ዘንድ ሊያጠፋ ጨካኝ ሆኖ በመዓትና በጽኑ ቁጣ ተሞልቶ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል።” ሶፎንያስ 1:​15 ደግሞ ስለዚያ ቀን “ያ ቀን የመዓት ቀን፣ የመከራና የጭንቀት ቀን፣ የመፍረስና የመጥፋት ቀን፣ የጨለማና የጭጋግ ቀን፣ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን” የሚል መግለጫ ይሰጣል።

“ታላቁ መከራ”

3. “የይሖዋ ቀን” የተባለው ምንድን ነው?

3 በሚልክያስ ትንቢት ዋነኛ ፍጻሜ መሠረት “የይሖዋ ቀን” በሚከሰተው ‘ታላቅ መከራ’ ተለይቶ የሚታወቅ ወቅት ነው። ኢየሱስ “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና” በማለት ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:​21) ዓለም በተለይ ከ1914 ጀምሮ የተፈራረቀበትን ችግር አስብ። (ማቴዎስ 24:​7-12) ሌላው ቢቀር ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ብቻ እንኳን ከ50 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል! ሆኖም ‘በታላቁ መከራ’ ከሚደርሰው መቅሰፍት ጋር ሲወዳደር ይህ እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም። ይህ ክስተት ማለትም የይሖዋ ቀን በአርማጌዶን ሲደመደም ለዚህ ክፉ ሥርዓት መቋጫ ይበጅለታል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5, 13፤ ራእይ 7:​14፤ 16:​14, 16

4. የይሖዋ ቀን ወደ መደምደሚያው ሲቃረብ ምን ይከሰታል?

4 በይሖዋ ቀን መጨረሻ ላይ የሰይጣን ዓለምና አጫፋሪዎቹ በሙሉ ድምጥማጣቸው ይጠፋል። በመጀመሪያ የሚሰናበተው መላው የሃሰት ሃይማኖት ይሆናል። ከዚያም የይሖዋ ፍርድ በሰይጣን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት ላይ ይገለጣል። (ራእይ 17:​12-14፤ 19:​17, 18) ሕዝቅኤል “ብራቸውን በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ ወርቃቸውም እንደ ጉድፍ ይሆናል፤ በእግዚአብሔር መዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ያድናቸው ዘንድ አይችልም” በማለት ትንቢት ተናግሯል። (ሕዝቅኤል 7:​19) ያንን ቀን በሚመለከት ሶፎንያስ 1:⁠14 “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኖአል” ይላል። መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ቀን አስመልክቶ ከሚናገረው አንጻር ሲታይ ከአምላክ የጽድቅ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተን ለመኖር ቆርጠን መነሳት ይኖርብናል።

5. የይሖዋን ስም የሚፈሩ ምን ያገኛሉ?

5 የይሖዋ ቀን በሰይጣን ዓለም ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት ከተነበየ በኋላ ሚልክያስ 4:​2 “ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች፣ ፈውስም በክንፎችዋ ውስጥ ይሆናል፤ እናንተም ትወጣላችሁ፣ እንደ ሰባም እምቦሳ ትፈነጫላችሁ” በማለት ይሖዋ የተናገረውን መዝግቧል። “የጽድቅ ፀሐይ” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ ‘የዓለም መንፈሳዊ ብርሃን’ ነው። (ዮሐንስ 8:​12) ኢየሱስ የፈውስ ብርሃን ይፈነጥቃል። ይህ ዛሬም ጭምር ያገኘነው መንፈሳዊ ፈውስና በአዲሱ ዓለም ውስጥ የምናገኘው የተሟላ አካላዊ ፈውስ ነው። ይሖዋ እንዳለው ፈውስ ያገኙት ሁሉ ከእስራቱ በመፈታቱ ደስ ብሎት እንደሚቦርቅ ‘እምቦሳ ይፈነጫሉ።’

6. የይሖዋ አገልጋዮች ምን የድል ክብረ በዓል ያደርጋሉ?

6 ይሖዋ ያወጣቸውን ብቃቶች ችላ የሚሉ ሰዎችስ? ሚልክያስ 4:​3 እንዲህ ይላል:- “በምሠራበት ቀን በደለኞች ከእግራችሁ ጫማ [ከአምላክ አገልጋዮች] በታች አመድ ይሆናሉና እናንተ ትረግጡአቸዋላችሁ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች የሰይጣንን ዓለም በማጥፋቱ ተግባር ተካፋዮች አይሆኑም። ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ቀን ማግስት በሚከበረው ታላቅ የድል በዓል ላይ በመካፈል በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘በደለኞችን ይረግጧቸዋል።’ የፈርዖን ሠራዊት በቀይ ባሕር ውስጥ ሰጥመው ከጠፉ በኋላ ታላቅ ክብረ በዓል ተደርጎ ነበር። (ዘጸአት 15:​1-21) በታላቁ መከራ ወቅት የሰይጣንንና የእርሱን ዓለም መጥፋት ተከትሎ ተመሳሳይ የድል ክብረ በዓል ይደረጋል። የይሖዋን ቀን በሕይወት የሚያልፉ ታማኝ ተራፊዎች “በማዳኑም ደስ ይለናል፣ ሐሴትም እናደርጋለን” በማለት በደስታ ይጮሃሉ። (ኢሳይያስ 25:​9) የይሖዋ ልዕልና ሲረጋገጥና ምድር ጸድታ ለሰላማዊ ኑሮ የተመቻቸች በምትሆንበት በዚያን ጊዜ እንዴት ያለ ታላቅ ሐሴት ይሆናል!

ሕዝበ ክርስትና እስራኤልን መስላለች

7, 8. በሚልክያስ ዘመን እስራኤል የነበረበትን መንፈሳዊ ሁኔታ ግለጽ።

7 የይሖዋን ሞገስ በሚያስገኝ ሁኔታ ላይ የሚገኙት እሱን ከማያመልኩ ሰዎች በተቃራኒ እሱን በማገልገል ላይ የሚገኙት ሰዎች ናቸው። ሚልክያስ መጽሐፉን በጻፈበት ወቅትም ሁኔታው ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነበር። በ537 ከዘአበ እስራኤላውያን ቀሪዎች ለ70 ዓመት ከቆዩበት የባቢሎን ግዞት ተመልሰው ተቋቋሙ። ይሁን እንጂ ተመልሶ የተቋቋመው ብሔር ቀጥሎ በነበሩት መቶ ዓመታት ውስጥም እንደገና የክህደትና የክፋት መንገድ ተከትሏል። አብዛኛው ሕዝብ የይሖዋን ስም አቃልለዋል፣ የጽድቅ ሕግጋቱን ችላ ብለዋል፣ ዕውር፣ አንካሳና ታማሚ እንስሳትን ለመሥዋዕትነት በማቅረብ ቤተ መቅደሱን አርክሰዋል እንዲሁም የልጅነት ሚስቶቻቸውን ፈትተዋል።

8 በዚህ ምክንያት ይሖዋ እንዲህ አላቸው:- “ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በመተተኞችና በአመንዝሮች፣ በሐሰትም በሚምሉ፣ የምንደኛውን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቲቱንና ድሀ አደጉን በሚያስጨንቁ፣ የመጻተኛውንም ፍርድ በሚያጣምሙ፣ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፣ . . . እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም።” (ሚልክያስ 3:​5, 6) ሆኖም ይሖዋ ከመጥፎ መንገዳቸው ዘወር ለሚሉ ሁሉ “ወደ እኔ ተመለሱ፣ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” በማለት ግብዣ አቅርቧል።​—⁠ሚልክያስ 3:​7

9. የሚልክያስ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

9 እነዚህ ቃላት በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ዳግም ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። አይሁዳውያን ቀሪዎች ይሖዋን ማገልገልና ከጊዜ በኋላ አሕዛብን ያቀፈው በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች አዲስ “ብሔር” አባል መሆን ችለው ነበር። ሆኖም በጣም የሚበዙት ሥጋዊ እስራኤላውያን ኢየሱስን አልተቀበሉትም። በመሆኑም ኢየሱስ በወቅቱ ለነበረው የእስራኤል ሕዝብ “እነሆ፣ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 23:​38፤ 1 ቆሮንቶስ 16:​22) በሚልክያስ 4:​1 ላይ በትንቢት እንደተነገረው በ70 እዘአ በሥጋዊ እስራኤላውያን ላይ “እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን” መጥቶባቸው ነበር። ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደስዋ የወደሙ ሲሆን በረሃብ፣ በሥልጣን ሽኩቻና የሮማውያን ሠራዊት በሰነዘረው ጥቃት ምክንያት ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች እንደሞቱ ተዘግቧል። ይሁን እንጂ ይሖዋን ያመልኩ የነበሩ ሰዎች በዚያ ወቅት ከደረሰው መከራ አምልጠዋል።​—⁠ማርቆስ 13:​14-20

10. ሰዎች በአጠቃላይና ቀሳውስት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው የእስራኤል ብሔር ጋር የሚመሳሰል ተግባር የፈጸሙት በምን መንገድ ነው?

10 መላው የሰው ዘር በተለይም ደግሞ ሕዝበ ክርስትና በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው የእስራኤል ብሔር ጋር የሚመሳሰል ተግባር ፈጽሟል። የሕዝበ ክርስትና መሪዎችም ሆኑ ሕዝቡ በአጠቃላይ ኢየሱስ ካስተማረው የአምላክ እውነት ይልቅ የራሳቸውን ሃይማኖታዊ ትምህርቶች መርጠዋል። በተለይ ቀሳውስቱ ይበልጥ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል። የይሖዋን ስም ለመጠቀም ፈቃደኞች ካለመሆናቸውም በላይ ስሙን ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው ውስጥ አውጥተውታል። በሲኦል እሳት ለዘላለም መቃጠል አለ፣ ሥላሴ፣ የነፍስ አለመሞትና አዝጋሚ ለውጥ የመሳሰሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ አረማዊ ትምህርቶችን በማስተማር ይሖዋን አዋርደዋል። በሚልክያስ ዘመን የነበሩት ካህናት እንዳደረጉት ለይሖዋ የሚገባውን ክብርና ውዳሴ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

11. የዓለም ሃይማኖቶች ማንን እንደሚያገለግሉ በግልጽ ያሳዩት እንዴት ነው?

11 የመጨረሻዎቹ ቀናት በጀመሩበት በ1914 የዚህ ዓለም ሃይማኖቶች በተለይም ክርስቲያን ነን የሚሉት በእርግጥ ማንን እንደሚያገለግሉ በግልጽ አሳይተዋል። በሁለቱም የዓለም ጦርነቶች ወቅት አባሎቻቸው በብሔራት ግጭቶች ምክንያት በተቆሰቆሱ ጦርነቶች ውስጥ ገብተው ከራሳቸው ሃይማኖት አባሎች ጋር ሳይቀር እንዲጨፋጨፉ አበረታተዋል። የአምላክ ቃል ይሖዋን በሚታዘዙትና በማይታዘዙት መካከል ያለውን ልዩነት እንዲህ በማለት በግልጽ አስቀምጦታል:- “የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። ከመጀመሪያ የሰማችኋት መልእክት:- እርስ በርሳችን እንዋደድ የምትል ይህች ናትና፤ ከክፉው እንደ ነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ እንደ ቃየል አይደለም።”​—⁠1 ዮሐንስ 3:​10-12

ፍጻሜውን እያገኘ ያለ ትንቢት

12, 13. በዘመናችን በአምላክ አገልጋዮች አማካኝነት ፍጻሜአቸውን ያገኙት ትንቢቶች የትኞቹ ናቸው?

12 የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ባበቃበት ዓመት ማለትም በ1918 የይሖዋ አገልጋዮች አምላክ ሕዝበ ክርስትናንና የቀሩትን የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ ጥፋት እንደበየነባቸው ማስተዋል ችለው ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ “ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤ ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፣ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ” የሚል ጥሪ ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ሲተላለፍ ቆይቷል። (ራእይ 18:​4, 5) ይሖዋን ለማገልገል ከልባቸው የሚፈልጉ ሁሉ ከሐሰት ሃይማኖት እድፍ ጸድተው ይህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ከመጥፋቱ በፊት መሰበክ ያለበትን የተቋቋመውን መንግሥት ምሥራች በዓለም ዙሪያ የማዳረስ ሥራ ጀመሩ።​—⁠ማቴዎስ 24:​14

13 ይህ የሆነው በሚልክያስ 4:​5 ላይ የሚገኘውንና ይሖዋ “እነሆ፣ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ” በማለት ያስነገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ ነው። ይህ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው ኤልያስ ጥላ ሆኖለት የነበረው አጥማቂው ዮሐንስ ባከናወነው ሥራ ነበር። ዮሐንስ በሕጉ ቃል ኪዳን ላይ ከሠሩት ኃጢአት የተጸጸቱትን አይሁዳውያን በማጥመቅ የኤልያስ ዓይነት ሥራ አከናውኗል። ከዚህ ይበልጥ ደግሞ ዮሐንስ የመሲሑ መንገድ ጠራጊ ሆኗል። ይሁን እንጂ የሚልክያስ ትንቢት ዮሐንስ ባከናወነው ሥራ አማካኝነት ገና የመጀመሪያ ፍጻሜውን ማግኘቱ ነበር። ኢየሱስ ዮሐንስን እንደ ሁለተኛው ኤልያስ መግለጹ ገና ወደፊት የሚከናወን ‘የኤልያስን የመሰለ’ ሥራ መኖሩን ያመለክታል።​—⁠ማቴዎስ 17:​11, 12

14. ይህ ሥርዓት ፍጻሜውን ከማግኘቱ በፊት እጅግ አስፈላጊ የሆነ ምን ሥራ መሠራት ይኖርበታል?

14 የሚልክያስ ትንቢት የኤልያስን የመሰለው ይህ ታላቅ ሥራ “ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን” ከመምጣቱ በፊት እንደሚሠራ ያመለክታል። ይህ ቀን የሚቋጨው በፍጥነት እየገሰገሰ በሚገኘው ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን በአርማጌዶን ነው። እንዲህ ሲባል ከዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜና በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት የሺህ ዓመት ግዛት ከመጀመሩ በፊት ኤልያስ አከናውኖት ከነበረው ሥራ ጋር የሚመሳሰል ሥራ መካሄድ አለበት ማለት ነው። በዚህ ትንቢት መሠረት ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት ከማጥፋቱ በፊት በዚህ ዘመን ያለው የኤልያስ ክፍል ምድራዊ ተስፋ ባላቸው በሚልዮን በሚቆጠሩ የእምነት ባልንጀሮቹ እየተረዳ ንጹሑን አምልኮ መልሶ የማቋቋም፣ የአምላክን ስም ከፍ ከፍ የማድረግና በግ መሰል ሰዎችን የማስተማር ሥራውን በግለት ያከናውናል።

ይሖዋ አገልጋዮቹን ይባርካል

15. ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚያስታውሳቸው እንዴት ነው?

15 ይሖዋ የሚያገለግሉትን ሰዎች ይባርካል። ሚልክያስ 3:​16 እንዲህ ይላል:- “የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም አደመጠ፣ ሰማም፣ እግዚአብሔርንም ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ።” አምላክ ከአቤል ዘመን ጀምሮ ለዘላለም ሕይወት የሚታሰቡትን ሰዎች ስም በመጽሐፍ እንደተጻፉ ያህል ሲያስታውስ ቆይቷል። ይሖዋ ለእነዚህ ሰዎች እንዲህ ይላቸዋል:- “በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ፤ የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፣ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ።”​—⁠ሚልክያስ 3:​10

16, 17. ይሖዋ ሕዝቡንና ሥራቸውን የባረከው እንዴት ነው?

16 በእርግጥም ይሖዋ አገልጋዮቹን ባርኳል። እንዴት? አንደኛው መንገድ ዓላማዎቹን ይበልጥ እንዲያስተውሉ በማድረግ ነው። (ምሳሌ 4:​18፤ ዳንኤል 12:​10) ሌላው ደግሞ በስብከቱ ሥራቸው አስደናቂ ፍሬ በመስጠት ነው። ቅን ልብ ያላቸው ብዙ ሰዎች በእውነተኛው አምልኮ ከእነርሱ ጋር የተባበሩ ሲሆን በአንድነት ‘ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች’ ሆነዋል። “በታላቅም ድምፅ እየጮኹ:- በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው” ይላሉ። (ራእይ 7:​9, 10) ይህ እጅግ ብዙ ሕዝብ አስደናቂ በሆነ መንገድ የተገለጠ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን በትጋት የሚያገለግሉ ሰዎች በመላው ዓለም በሚገኙ ከ93, 000 በሚበልጡ ጉባኤዎች ከስድስት ሚልዮን በላይ ሆነዋል!

17 በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች በማንኛውም የታሪክ ዘመን ታይቶ በማይታወቅ መጠን የሚያዘጋጁአቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የይሖዋን በረከት የሚያሳዩ ናቸው። አሁን ባለው ሁኔታ በእያንዳንዱ ወር 90 ሚልዮን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ቅጂዎች የሚታተሙ ሲሆን መጠበቂያ ግንብ በ141 ቋንቋዎች፣ ንቁ! ደግሞ በ87 ቋንቋዎች ይዘጋጃል። በ1968 ወጥቶ የታተመውና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ መጽሐፍ በ117 ቋንቋዎችና በ107 ሚልዮን ቅጂዎች ሊሰራጭ ችሏል። በ1982 ወጥቶ የነበረው በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለው መጽሐፍ እስከ አሁን በ131 ቋንቋዎች ከ81 ሚልዮን ቅጂዎች በላይ ታትሟል። በ1995 የወጣው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው መጽሐፍ በ154 ቋንቋዎችና በ85 ሚልዮን ቅጂዎች ታትሟል። በ1996 የታተመው አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለው ብሮሹር እስከ አሁን ድረስ በ244 ቋንቋዎች በ150 ሚልዮን ቅጂዎች ተሠራጭቷል።

18. ተቃውሞ ቢኖርም እንኳን መንፈሳዊ ብልጽግና የምናገኘው ለምንድን ነው?

18 ይህ መንፈሳዊ ብልጽግና የተገኘው ከሰይጣን ዓለም ከባድና የማያባራ ተቃውሞ እያለ ነው። ይህም የኢሳይያስ 54:​17ን እውነተኝነት የሚያሳይ ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም፤ በፍርድም በሚነሣብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፣ ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው፣ ይላል እግዚአብሔር።” ሚልክያስ 3:​17 ዋነኛ ፍጻሜውን በእነርሱ ላይ እያገኘ መሆኑን ማወቃቸው ለይሖዋ አገልጋዮች ምንኛ የሚያጽናና ነው። “እኔ በምሠራበት ቀን እነርሱ የእኔ ገንዘብ ይሆናሉ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።”

ይሖዋን በደስታ ማገልገል

19. ይሖዋን በሚያገለግሉ እና በማያገለግሉ ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት የሚታየው እንዴት ነው?

19 ታማኝ በሆኑ የይሖዋ አገልጋዮችና በሰይጣን ዓለም ውስጥ ባሉ ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት ከቀን ወደ ቀን ይበልጥ ግልጽ እየሆነ ነው። ሚልክያስ 3:​18 “ተመልሳችሁም በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል፣ ለእግዚአብሔር በሚገዛውና በማይገዛው መካከል ትለያላችሁ” በማለት ተንብዮአል። ከብዙ ልዩነቶች መካከል አንዱ ይሖዋን በከፍተኛ ደስታ ማገልገላቸው ነው። ለዚህ አንዱ ምክንያት ስለወደፊቱ ጊዜ ያላቸው አስደናቂ ተስፋ ነው። ይሖዋ “እነሆ፣ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም። ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሤት አድርጉ” በማለት በተናገራቸው ቃላት ላይ ፍጹም ትምክህት አላቸው።​—⁠ኢሳይያስ 65:​17, 18፤ መዝሙር 37:​10, 11, 29፤ ራእይ 21:​4, 5

20. ደስተኛ ሕዝብ የሆንነው ለምንድን ነው?

20 ይሖዋ ታማኝ ሕዝቦቹን ከእርሱ ታላቅ ቀን አትርፎ ወደ አዲስ ዓለም እንደሚያስገባቸው የሰጠውን ተስፋ እናምናለን። (ሶፎንያስ 2:​3፤ ራእይ 7:​13, 14) ምንም እንኳን አንዳንዶች በእርጅና፣ በበሽታ ወይም በድንገተኛ አደጋዎች ምክንያት ከዚያ ቀድመው በሞት ቢያንቀላፉ እንኳ ይሖዋ ከሞት እንደሚያስነሳቸውና የዘላለም ሕይወት እንደሚያጎናጽፋቸው ቃል ገብቷል። (ዮሐንስ 5:​28, 29፤ ቲቶ 1:​2) ስለዚህ ሁላችንም የሚፈታተኑን የየራሳችን ችግሮች ቢኖሩብንም እንኳን የይሖዋን ቀን ስንጠባበቅ በምድር ገጽ ከሚኖር ከማንኛውም ሕዝብ ይበልጥ ደስተኛ የምንሆንበት በቂ ምክንያት አለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• “የይሖዋ ቀን” ምንድን ነው?

• የዓለም ሃይማኖቶች ከጥንቷ እስራኤል ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?

• የይሖዋ አገልጋዮች እየፈጸሟቸው ያሉት ትንቢቶች የትኞቹ ናቸው?

• ይሖዋ ሕዝቦቹን የባረከው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሩሳሌም ‘እንደ ምድጃ እሳት ነድዳለች’

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ የሚያገለግሉትን ሰዎች ፍላጎት ያሟላል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ አገልጋዮች ከፊታቸው በተዘረጋላቸው አስደናቂ ተስፋ ምክንያት ደስተኞች ናቸው