በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

ዮሐንስ በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ቅዱስ አገልግሎት ሲያቀርቡ የተመለከታቸው “እጅግ ብዙ ሰዎች” አገልግሎታቸውን የሚያቀርቡት በየትኛው የቤተ መቅደሱ ክፍል ሆነው ነበር?​—ራእይ 7:9-15

እጅግ ብዙ ሰዎች ይሖዋን የሚያመልኩት ከታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባዮች በአንዱ በተለይም ከሰሎሞን ቤተ መቅደስ ውጨኛ አደባባይ ጋር በሚመሳሰለው አደባባይ ነው ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው።

ቀደም ባሉት ዓመታት እጅግ ብዙ ሰዎች በኢየሱስ ዘመን ከነበረው የአሕዛብ አደባባይ ጋር በሚመሳሰል ወይም እሱ ጥላ በሆነለት መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ተደርጎ ይታመን ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረገ ተጨማሪ ምርምር ይህ አባባል ትክክል የማይሆንባቸውን ቢያንስ አምስት ምክንያቶች አመልክቷል። በመጀመሪያ፣ ለታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ጥላ የሚሆኑት ሁሉም የሄሮድስ ቤተ መቅደስ ገጽታዎች አይደሉም። ለምሳሌ ያህል፣ የሄሮድስ ቤተ መቅደስ የሴቶች አደባባይና የእስራኤል አደባባይ ነበረው። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ወደ ሴቶች አደባባይ መግባት የሚችሉ ሲሆን ወደ እስራኤል አደባባይ መግባት የሚፈቀድላቸው ግን ወንዶች ብቻ ነበሩ። በታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ ውስጥ ወንዶችና ሴቶች አምልኳቸውን የሚያቀርቡት አንድ ላይ ነው። (ገላትያ 3:28, 29) በመሆኑም በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ የሴቶች አደባባይና የእስራኤል አደባባይ የሚባል ቦታ የለም።

ሁለተኛ፣ ከመለኮታዊ ምንጭ በተገኘው የግንባታ ንድፍ መሠረት በተገነባው የሰሎሞን ቤተ መቅደስም ሆነ ሕዝቅኤል በራእይ በተመለከተው ቤተ መቅደስ ወይም ዘሩባቤል እንደገና በገነባው ቤተ መቅደስ ውስጥ የአሕዛብ አደባባይ አልነበረም። በመሆኑም የአሕዛብ አደባባይ በታላቁ የይሖዋ ቤተ መቅደስ የአምልኮ ዝግጅት ውስጥ ተመሳሳይ ይኖረዋል ብለን የምንደመድምበት ምንም ምክንያት የለም። በተለይ ሦስተኛው ነጥብ ይህንን ያጎላል።

ሦስተኛ፣ የአሕዛብን አደባባይ የገነባው ራሱን ከፍ ከፍ የማድረግና በሮማውያን ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ዓላማ የነበረው ኤዶማዊ ንጉሥ ሄሮድስ ነው። ሄሮድስ የዘሩባቤልን ቤተ መቅደስ ማደስ የጀመረው በ18 ወይም 17 ከዘአበ ገደማ ሳይሆን አይቀርም። ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ እንዲህ ይላል:- “በዘመኑ የነበረው የምዕራቡ ዓለም [ሮም] ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዝ . . . በምሥራቃውያን ከተሞች ከሚሠሩ ቤተ መቅደሶች የሚበልጥ ቤተ መቅደስ እንዲገነባ ይጠይቅ ነበር።” ይሁን እንጂ የቤተ መቅደሱ ወርድና ስፋት አስቀድሞ የተወሰነ ነበር። ይኸው መዝገበ ቃላት እንዲህ ሲል ያብራራል:- “ቤተ መቅደሱ ከእርሱ በፊት ከተሠሩት ቤተ መቅደሶች [የሰሎሞንና የዘሩባቤል] ጋር ተመሳሳይ ወርድና ስፋት ሊኖረው የሚገባ ቢሆንም እንኳ ቤተ መቅደሱ የሚገኝበት ተራራ ተጨማሪ ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችል ስፋት ነበረው።” በመሆኑም ሄሮድስ ዛሬ የአሕዛብ አደባባይ ተብሎ የሚጠራውን ቦታ በመጨመር የቤተ መቅደሱን ቅጥር ግቢ አሰፋው። እንዲህ ባለ መንገድ የተገነባ ሕንፃ ለይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ዝግጅት እንዴት ጥላ ሊሆን ይችላል?

አራተኛ፣ ዓይነ ስውራንን፣ አንካሶችንና ያልተገረዙ አሕዛብን ጨምሮ ማንኛውም ሰው ለማለት ይቻላል ወደ አሕዛብ አደባባይ መግባት ይችል ነበር። (ማቴዎስ 21:14, 15) እርግጥ ነው ይህ አደባባይ ለአምላክ መሥዋዕት ማቅረብ ለሚፈልጉ ብዙ ያልተገረዙ አሕዛብ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። ኢየሱስም በተለያዩ ጊዜያት ሕዝቡን ያስተማረውና ሁለት ጊዜ ደግሞ የአባቱን ቤት እንዳዋረዱት በመናገር ገንዘብ ለዋጮቹንና ነጋዴዎቹን ያባረረው ከዚሁ የአሕዛብ አደባባይ ነበር። (ማቴዎስ 21:12, 13፤ ዮሐንስ 2:14-16) ያም ሆኖ ዘ ጁውሽ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ውጫዊ አደባባይ የቤተ መቅደሱ ክፍል አልነበረም። አፈሩ ቅዱስ አልነበረም፤ ማንኛውም ሰው ወደዚህ መግባት ይችል ነበር።”

አምስተኛ፣ በባርክሌይ ኤም ኒውማን እና ፈሊፕ ሲ ስታይን የተዘጋጀው ኤ ሀንድቡክ ኦን ዘ ጎስፕል ኦቭ ማቲው የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው የአሕዛብን አደባባይ ለማመልከት የተሠራበትና “ቤተ መቅደስ” ተብሎ የተተረጎመው (ሂሮን) የሚለው ግሪክኛ ቃል “የሚያመለክተው ቤተ መቅደሱን ራሱን ሳይሆን ጠቅላላውን ሕንፃ ነው።” ከዚህ በተቃራኒ (ኔኦስ) የተባለውና ዮሐንስ እጅግ ብዙ ሰዎችን በተመለከተበት ራእይ ውስጥ “ቤተ መቅደስ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል ሁኔታውን ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል። የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ በተመለከተ ይህ ቃል ሁልጊዜ ለማለት ይቻላል የሚያመለክተው ቅድስተ ቅዱሳኑን ወይም ቤተ መቅደሱን ነው። አንዳንድ ጊዜ “መቅደስ” ተብሎ ተተርጉሟል።​—⁠ማቴዎስ 27:5, 51፤ ሉቃስ 1:9, 21 NW

የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ያምናሉ። ‘ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም በማንጻት’ በመንፈሳዊ ንጹህ ሆነዋል። ስለዚህ የአምላክ ወዳጆች የመሆንና ታላቁን መከራ በሕይወት የማለፍ ተስፋ ይዘው ጻድቃን ሆነው ተቆጥረዋል። (ያዕቆብ 2:23, 25) ራሳቸውን ለሕጉ ቃል ኪዳን ካስገዙትና ከእስራኤላውያን ጋር ሆነው ያመልኩ ከነበሩት ወደ ይሁዲነት ከተለወጡ ሰዎች ጋር በብዙ መንገዶች ይመሳሰላሉ።

እርግጥ ነው እነዚያ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ካህናቱ ተግባራቸውን በሚያከናውኑበት በውስጠኛው አደባባይ ውስጥ አያገለግሉም ነበር። የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላትም በመንፈስ የተቀቡት የይሖዋ “ቅዱሳን ካህናት” ምድር እያሉ የሚገኙበትን መንፈሳዊ ሁኔታ በሚያመለክተው የይሖዋ ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጠኛ አደባባይ ውስጥ አይደሉም። (1 ጴጥሮስ 2:5) ሆኖም በሰማይ ያለው ሽማግሌ ለዮሐንስ እንደነገረው እጅግ ብዙ ሰዎች ያሉት በቤተ መቅደሱ ውስጥ እንጂ ከቤተ መቅደሱ ውጪ በሚገኝ በአንድ መንፈሳዊ የአሕዛብ አደባባይ ውስጥ አይደለም። የሰሎሞን ቤተ መቅደስ ውጨኛ አደባባይ ጥላ በሆነለት ንጹህና ጻድቅ መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ ናቸው። ይህ እንዴት ያለ መብት ነው! ደግሞም ሁሉም መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ንጽህናቸውን ዘወትር ጠብቀው የመኖራቸውን አስፈላጊነት ምንኛ የሚያጎላ ነው!

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የሰሎሞን ቤተ መቅደስ

1. ቅድስተ ቅዱሳን

2. ውስጠኛ አደባባይ

3. ውጨኛ አደባባይ

4. ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ የሚያስገባ ደረጃ