በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአካል ጉዳተኝነት የሚወገደው እንዴት ነው?

የአካል ጉዳተኝነት የሚወገደው እንዴት ነው?

የአካል ጉዳተኝነት የሚወገደው እንዴት ነው?

ማየት የተሳናቸው ሰዎች ዓይን ሲገለጥ፣ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ጆሮ ሲከፈት፣ የዲዳዎች ምላስ በደስታ ሲዘምርና ሽባ የነበረ እግር ጠንክሮ መራመድ ሲችል በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት! እየተናገርን ያለነው የሕክምናው መስክ ስለሚያደርገው እመርታ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ በሰው ልጅ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ሲገባ ስለሚሆነው ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ተንብዮአል:- “በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፣ የድዳም ምላስ ይዘምራል።” (ኢሳይያስ 35:​5, 6) ታዲያ ይህ እጅግ አስደናቂ የሆነ እውነተኛ ትንቢት እንደሚፈጸም እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር በነበረበት ጊዜ ሁሉንም ዓይነት በሽታና አካላዊ እንከን ፈውሷል። ከዚህም በተጨማሪ ያደረጋቸውን አብዛኞቹን ተአምራት ጠላቶቹን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተመልክተውታል። ቢያንስ በአንድ ወቅት ተጠራጣሪ ተቃዋሚዎች የኢየሱስን ስም ለማጥፋት በማሰብ መፈወሱን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ምርመራ አካሂደው ነበር። የሚያስገርመው ግን ያደረጉት ምርመራ ተአምር መፈጸሙን ከማረጋገጥ ውጪ ምንም የፈየደላቸው ነገር አልነበረም። (ዮሐንስ 9:​1, 5-34) ኢየሱስ እንደገና ሊካድ የማይቻል አንድ ሌላ ተዓምር ሲፈጽም ተበሳጭተው “ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶች ያደርጋልና” በማለት ተናገሩ። (ዮሐንስ 11:​47) ሆኖም ተራው ሕዝብ ከእነርሱ የተለየ አመለካከት በማዳበር በኢየሱስ ማመን ጀመረ።​—⁠ዮሐንስ 2:​23፤ 10:​41, 42፤ 12:​9-​11

የኢየሱስ ተአምራት ወደፊት ዓለም አቀፍ ፈውስ እንደሚካሄድ ይጠቁማሉ

የኢየሱስ ተአምራት እርሱ መሲሕና የአምላክ ልጅ መሆኑን ከማረጋገጥ የበለጠ ነገር አከናውነዋል። ታዛዥ የሰው ልጆች ወደፊት ፈውስ እንደሚያገኙ በሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ላይ እምነት ለመገንባት የሚያስችል መሠረት ጥለዋል። እነዚህ ተስፋዎች በመግቢያው አንቀጽ ላይ የተጠቀሰውን የኢሳይያስ ምዕራፍ 35ን ተስፋ ይጨምራሉ። ኢሳይያስ 33:​24 ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን ሰዎች የወደፊት ጤንነት በተመለከተ “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም” በማለት ይናገራል። በተመሳሳይም ራእይ 21:​4 የሚከተለውን ተስፋ ይሰጣል:- “[አምላክ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት [የዛሬው መከራና ሥቃይ] አልፎአልና።”

ሰዎች “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” የሚለውን የኢየሱስን የናሙና ጸሎት ሲደግሙ እነዚህ ትንቢቶች እንዲፈጸሙ መጠየቃቸው ነው። (ማቴዎስ 6:​10) አዎን፣ የአምላክ ፈቃድ ምድርንና የሰው ዘሮችን ይጨምራል። በሽታና የአካል ጉዳተኝነት እንዲኖሩ የተፈቀደበት ምክንያት ቢኖርም በቅርቡ ግን ጨርሰው ይወገዳሉ። ከዚህ በኋላ የአምላክን ‘የእግር መረገጫ’ ማበላሸታቸው ለዘላለም ያከትማል።​—⁠ኢሳይያስ 66:​1 a

ያላንዳች ሕመምና ወጪ ተፈወሱ

ሰዎችን የሚያሠቃያቸው በሽታ ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ ሕመም ሳይሰማቸው፣ ሳይዘገይ እንዲሁም ያለ ወጪ ፈውሷቸዋል። ስለሁኔታው የሚገልጸው ወሬ ልክ እንደ ሰደድ እሳት በፍጥነት መዛመቱ የማይቀር ነው። ብዙም ሳይቆይ “ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፣ ዕውሮችንም፣ ዲዳዎችንም፣ ጉንድሾችንም፣ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ ቀረቡ፣ በኢየሱስም እግር አጠገብ ጣሉአቸው፤ ፈወሳቸውም።” ሕዝቡ ምን ተሰማው? የዓይን ምሥክር የነበረው የማቴዎስ ዘገባ በመቀጠል “ሕዝቡ ዲዳዎች ሲናገሩ፣ ጕንድሾችም ሲድኑ፣ አንካሶችም ሲሄዱ፣ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ” በማለት ይናገራል።​—⁠ማቴዎስ 15:​30, 31

ኢየሱስ የፈወሳቸው ሰዎች አንዳንድ አታላዮች እንደሚያደርጉት ከሕዝቡ መካከል በጥንቃቄ የተመረጡ እንዳልሆኑ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ የታማሚው ዘመዶችና ወዳጆች በሽተኞቹን ‘በኢየሱስ እግር አጠገብ ጣሏቸው ኢየሱስም ፈወሳቸው።’ እስቲ አሁን የኢየሱስን የመፈወስ ችሎታ የሚያረጋግጡ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንከልስ።

ዓይነ ስውርነት:- ኢየሱስ ኢየሩሳሌም በነበረበት ወቅት “ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር” የነበረን ሰው ፈውሷል። ይህ ዓይነ ስውር ለማኝ በከተማው ውስጥ በደንብ የታወቀ ሰው ነበር። ሰዎች ዓይኑ በርቶለት ሲራመድ ሲመለከቱት የተሰማቸውን ደስታና ያሰሙትን የሁካታ ድምፅ መገመት ትችላለህ! ይሁንና በሁኔታው የተደሰቱት ሁሉም አልነበሩም። ቀደም ሲል ኢየሱስ ክፋታቸውን በማጋለጡ የተናደዱት ፈሪሳውያን የሚባል የታወቀና ተደማጭነት ያለው የአይሁድ ሃይማኖታዊ ቡድን አንዳንድ አባላት ኢየሱስ የማታለል ድርጊት መፈጸሙን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ለማግኘት ቋምጠው ነበር። (ዮሐንስ 8:​13, 42-​44፤ 9:​1, 6-​31) በዚህም ምክንያት በመጀመሪያ የተፈወሰውን ሰው በኋላ ደግሞ ወላጆቹን እንደገና ደግሞ ሰውዬውን በጥያቄ አፋጠጡት። ሆኖም የፈሪሳውያኑ ምርመራ ኢየሱስ በእርግጥ መፈወሱን ከማረጋገጥ ውጪ ምንም የፈየደላቸው ነገር አልነበረም። ይህ ደግሞ በጣም አናደዳቸው። በእነዚህ ሃይማኖታዊ ግብዞች ክፋት ግራ የተጋባው የተፈወሰው ሰውዬ ራሱ “ዕውር ሆኖ የተወለደውን ዓይኖች ማንም እንደ ከፈተ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም፤ ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ምንም ሊያደርግ ባልቻለም ነበር” በማለት ተናገረ። (ዮሐንስ 9:​32, 33) በአንድ ወቅት ዓይነ ስውር የነበረው ይህ ሰው ከቅንነትና ከልብ በመነጨ ስሜት ተነሳስቶ መልስ ሲሰጥ ፈሪሳውያኑ ‘ወደ ውጭ አወጡት’ ማለትም ከምኩራብ አባረሩት።​—⁠ዮሐንስ 9:​22, 34

የመስማት ችግር:- ኢየሱስ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ በምትገኘው በዲካፖሊስ (አሥር ከተማ) በነበረበት ጊዜ “ደንቆሮና ኰልታፋም የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ።” (ማርቆስ 7:​31, 32) ኢየሱስ ይህንን ሰው መፈወስ ብቻ ሳይሆን በሕዝቡ መካከል ኃፍረት ሊሰማው እንደሚችል በመገንዘብ ስለ ስሜቱ ጥልቅ ማስተዋል እንዳለው አሳይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ሰውዬውን “ከሕዝቡም ለይቶ ለብቻው” እንደወሰደውና እንደፈወሰው ይነግረናል። አሁንም የዓይን ምሥክሮቹ ‘ያለ መጠንም ተገርመው’ “ሁሉን ደኅና አድርጎአል ደንቆሮችም እንዲሰሙ ዲዳዎችም እንዲናገሩ ያደርጋል አሉ።”​—⁠ማርቆስ 7:​33-37

ሽባነት:- ኢየሱስ በቅፍርናሆም በነበረበት ጊዜ አልጋ ላይ የተኛ ሽባ ሰው ይዘው ወደ እርሱ አመጡ። (ማቴዎስ 9:​2) ከቁጥር 6 እስከ 8 ያለው ሐሳብ ቀጥሎ የተፈጸመውን ሁኔታ ይገልጻል:- “[ኢየሱስም] ሽባውን:- ተነሣ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ አለው። ተነሥቶም ወደ ቤቱ ሄደ። ሕዝቡም አይተው ተደነቁ፣ ለሰውም እንዲህ ያለ ሥልጣን የሰጠ እግዚአብሔርን አከበሩ።” ይህ ተአምርም ቢሆን የተፈጸመው የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትና ጠላቶች በተገኙበት ቦታ ነበር። በጥላቻና በዘረኝነት ያልታወሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ባዩት ነገር ‘እግዚአብሔርን እንዳከበሩ’ ልብ በል።

በሽታ:- “ለምጻምም ወደ እርሱ [ኢየሱስ] መጥቶ ተንበረከከና:- ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ ብሎ ለመነው። ኢየሱስም አዘነለት እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና:- እወድዳለሁ ንጻ አለው። በተናገረም ጊዜ ለምጹ ወዲያው ለቀቀው።” (ማርቆስ 1:​40-42) ኢየሱስ ይህንን ሰው የፈወሰው እንዲያው ቅር እያለው ሳይሆን ከአንጀት በመራራት ስሜት እንደሆነ ልብ በል። የሥጋ ደዌ ሕመምተኛ ነህ እንበል። ሰውነትህን ቀስ በቀስ ካበላሸና ከኅብረተሰቡ ተገልለህ እንድትኖር ካደረገህ ከዚህ አሰቃቂ ሕመም ድንገት ያላንዳች ሥቃይ ብትፈወስ ምን ይሰማህ ነበር? ተአምራዊ በሆነ መንገድ የተፈወሰ አንድ ሌላ የሥጋ ደዌ ሕመምተኛ ‘እያመሰገነው በእግሩ ፊት በግንባሩ የወደቀው’ ለምን እንደሆነ እንደምትገነዘብ ምንም ጥርጥር የለውም።​—⁠ሉቃስ 17:​12-​16

ጉዳት:- ኢየሱስ ከመያዙና ከመሰቀሉ በፊት ያከናወነው የመጨረሻ ተአምር ፈውስ ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስን ለመውሰድ የመጡትን ሰዎች ሲመለከት ወዲያው “ሰይፍ ስለ ነበረው መዘዘው፣ የሊቀ ካህናቱንም ባርያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቆረጠ።” (ዮሐንስ 18:​3-5, 10) በሉቃስ ላይ የሰፈረው ተመሳሳይ ዘገባ ‘ኢየሱስ ጆሮውን ዳስሶ እንደፈወሰው’ ይነግረናል። (ሉቃስ 22:​50, 51) አሁንም ቢሆን ኢየሱስ ይህንን የደግነት ድርጊት የፈጸመው በወዳጆቹና በጠላቶቹ ማለትም ሊይዙት በመጡት ሰዎች ፊት ነበር።

አዎን፣ የኢየሱስን ተአምራት ይበልጥ ጠለቅ ብለን በመረመርን መጠን የታሪኩን ትክክለኛነት የሚያሳዩትን ነጥቦች ይበልጥ እየተገነዘብን እንሄዳለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:​16) እንዲሁም አስቀድሞ እንደተጠቀሰው እንዲህ ያለው ጥናት አምላክ ታዛዥ የሰው ልጆችን ለመፈወስ በገባው ቃል ላይ ያለንን እምነት ያጠነክርልናል። መጽሐፍ ቅዱስ የክርስትናን እምነት “ተስፋ ያደረግነው ነገር እንደሚፈጸም እርግጠኛ የምንሆንበት፤ የማናየውም ነገር እውን መሆኑን የምንረዳበት ነው” በማለት ይገልጸዋል። (ዕብራውያን 11:​1 አ.መ.ት ፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው አምላክ የሚፈልገው ሁሉንም ነገር በጭፍን እንድንቀበል አሊያም የማይሆን ነገር እንድንመኝ ሳይሆን በአሳማኝ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ ጠንካራ እምነት እንዲኖረን ነው። (1 ዮሐንስ 4:​1) እንዲህ ያለውን እምነት ስናገኝ በመንፈሳዊ ጠንካሮች፣ ጤናሞችና ደስተኞች እንሆናለን።​—⁠ማቴዎስ 5:​3፤ ሮሜ 10:​17

መንፈሳዊ ፈውስ በመጀመሪያ መከናወን አለበት!

አብዛኞቹ አካላዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች ደስተኞች አይደሉም። አንዳንዶች የወደፊት ተስፋቸው በመጨለሙ አሊያም ሕይወታቸው በችግር የተሞላ በመሆኑ ራሳቸውን ለመግደል እንኳ ሳይቀር ይሞክራሉ። በሌላ አባባል እነዚህ ሰዎች የመንፈስ ጉዳተኞች ናቸው። ይህ ደግሞ በአምላክ ዓይን ከአካል ጉዳተኝነት እጅግ የከፋ ችግር ነው። (ዮሐንስ 9:​41) በሌላው በኩል ደግሞ በፊተኛው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሱት ክሪስቸን እና ጁንየር ያሉ በርካታ የአካል ጉዳተኞች ደስተኛና አርኪ ሕይወት ይመራሉ። ለምን? ምክንያቱም በመንፈሳዊ ጤናማ ስለሆኑና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ተስፋ ኃይል ስለሰጣቸው ነው።

ኢየሱስ ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ስለሚያስፈልገን ልዩ የሆነ ነገር ሲገልጽ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ብሏል። (ማቴዎስ 4:​4) አዎን፣ ሰዎች ከእንስሳት በተለየ ከሰብዓዊ ምግብ የበለጠ ነገር ያስፈልጋቸዋል። በአምላክ “መልክ” ስለተፈጠርን መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልገናል። ይህም ስለ አምላክ፣ ፈቃዱን ስለማድረግና በዓላማው አፈጻጸም ረገድ ስላለን ቦታ እውቀት ማግኘት ይኖርብናል ማለት ነው። (ዘፍጥረት 1:​27፤ ዮሐንስ 4:​34) ስለ አምላክ የምናገኘው እውቀት ሕይወታችን ትርጉም እንዲኖረውና መንፈሳዊ ብርታት እንድናገኝ ያደርጋል። በተጨማሪም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለሚገኘው የዘላለም ሕይወት መሠረት ይጥልልናል። ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 17:​3

በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ሰዎች ኢየሱስን “መምህር” እንጂ “ፈዋሽ” ብለው እንዳልጠሩት ማወቁ ትኩረት የሚስብ ነው። (ሉቃስ 3:​12፤ 7:​40) ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ የሰው ልጆችን ችግር ለዘለቄታው ስለሚፈታው የአምላክ መንግሥት ያስተምር ስለነበረ ነው። (ሉቃስ 4:​43፤ ዮሐንስ 6:​26, 27) በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው ይህ ሰማያዊ መስተዳድር መላዋን ምድር የሚገዛ ሲሆን ጻድቃንና ምድራዊ መኖሪያቸው ዘላቂ የሆነ ተሃድሶ እንደሚያገኙ የሚገልጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች እንዲፈጸሙ ያደርጋል። (ራእይ 11:​15) ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ የመንግሥቱን መምጣት የአምላክ ፈቃድ ምድር ላይ ከመፈጸሙ ጋር ያያያዘው ለዚህ ነው።​—⁠ማቴዎስ 6:​10

ብዙ የአካል ጉዳተኞች ስለዚህ አስደናቂ ተስፋ መማራቸው የሃዘን እንባቸው ወደ ደስታ እንባ እንዲለወጥ አድርጓል። (ሉቃስ 6:​21) እንዲያውም አምላክ በሽታንና የአካል ጉዳተኝነትን ከማስወገድ የበለጠ ነገርም ያደርጋል። ለሰው ልጆች መከራና ሥቃይ ዋነኛ መንስኤ የሆነውን ኃጢአትን ራሱን ያስወግደዋል። በእርግጥም አስቀድመው የተጠቀሱት የኢሳይያስ 33:​24 እና የማቴዎስ 9:​2-7 ጥቅሶች በሽታን ከኃጢአት ጋር ማዛመዳቸው የተገባ ነው። (ሮሜ 5:​12) ስለዚህ ኃጢአት ሲወገድ የሰው ዘር በመጨረሻ “ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት” ይደርሳል። ይህ ነጻነት አእምሯዊና አካላዊ ፍጽምናን ይጨምራል።​—⁠ሮሜ 8:​21

በአሁኑ ጊዜ መጠነኛ ጤንነት ያላቸው ሰዎች ሁኔታቸውን ላያደንቁ ይችላሉ። የአካል ጉዳተኝነት በሚያስከትለው ችግር ቅስማቸው ለተሰበረ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። ጤንነትና ሕይወት ምን ያህል ውድ እንደሆኑና ነገሮች እንዴት በአንድ ጀንበር ሊለወጡ እንደሚችሉ ይገነዘባሉ። (መክብብ 9:​11) ስለዚህ ከአንባቢዎቻችን መካከል የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ቢኖሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለተገለጹት የአምላክ አስደናቂ ተስፋዎች ልዩ ትኩረት ይሰጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ኢየሱስ ሕይወቱን በመስጠት እነዚህ ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ አረጋግጧል። ከዚህ የተሻለ ምን ዋስትና ሊኖረን ይችላል?​—⁠ማቴዎስ 8:​16, 17፤ ዮሐንስ 3:​16

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? የተባለውን ብሮሹር ተመልከት።