በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአካል ጉዳተኝነት ድንበር አይወስነውም

የአካል ጉዳተኝነት ድንበር አይወስነውም

የአካል ጉዳተኝነት ድንበር አይወስነውም

በአንድ አፍሪካ አገር የሚኖረው ክሪስቸን ከጦር ኃይሉ ጋር እንዲቀላቀል ለማስገደድ ወታደሮች አፍነው ወሰዱት። እርሱ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናው ምክንያት በጥያቄያቸው እንደማይስማማ ገለጸላቸው። በዚህ ጊዜ ክሪስቸንን ወደ አንድ የጦር ካምፕ በመውሰድ ለአራት ቀናት ሲደበድቡት ከቆዩ በኋላ አንደኛው ወታደር እግሩ ላይ ተኮሰበት። ክሪስቸን ሐኪም ቤት መድረስ ቢችልም እግሩ ከጉልበቱ በታች መቆረጥ ነበረበት። በአንድ ሌላ የአፍሪካ አገር ደግሞ ሕፃናት መሣሪያ በታጠቁ አማፅያን በተተኮሰ ጥይት እጅና እግሮቻቸውን አጥተዋል። በተጨማሪም ከካምቦዲያ እስከ ባልካን እንዲሁም ከአፍጋኒስታን እስከ አንጎላ የተቀበሩ ፈንጂዎች ወጣት ሽማግሌ ሳይሉ የብዙዎችን አካል መቆራረጣቸውንና ለአካል ጉዳተኝነት መዳረጋቸውን ቀጥለዋል።

ብዙዎችን ለዚህ ችግር እየዳረጉ ያሉት ሌሎች ምክንያቶች ደግሞ ድንገተኛ አደጋዎችና እንደ ስኳር ያሉ በሽታዎች ናቸው። ከዚህም በላይ የአካባቢ መመረዝ እንኳ የአካል ጉዳተኝነት ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል በአንድ የምሥራቅ አውሮፓ ከተማ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች አንዳንድ ልጆች አንድ እጃቸው ክንድ አልባ ሆኖ ተወልደዋል። የኬሚካል ብክለት የጅን ብልሽት ሊያስከትል እንደሚችል ማስረጃው ይጠቁማል። ሌሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ደግሞ እጅና እግር ቢኖራቸውም እንኳ ሽባ ናቸው አሊያም በሌሎች በሽታዎች ሳቢያ የአካል ጉዳተኛ ሆነዋል። በእርግጥም የአካል ጉዳተኝነት ድንበር የማይወስነው ችግር ነው።

መንስኤው ምንም ይሁን ምን የአካል ጉዳተኝነት ቅስም የሚሰብር ሊሆን ይችላል። ጁንየር በ20 ዓመቱ ከጉልበቱ በታች ያለውን ግራ እግሩን አጣ። ጁንየር ቆየት ብሎ የሚከተለውን ብሏል:- “ብዙ ስሜታዊ ችግሮች ነበሩብኝ። እግሬን መልሼ እንደማላገኘው ስገነዘብ በጣም አለቀስኩ። የማደርገው ጠፋኝ። ግራ ተጋብቼ ነበር።” ሆኖም ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የጁንየር አስተሳሰብ በእጅጉ ተለወጠ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረና የአካል ጉዳተኝነቱ ያስከተለበትን ችግር እንዴት መቋቋም እንደሚችል ብቻ ሳይሆን ወደፊት በዚህችው ምድር ላይ ስለሚገኝ ሕይወት የሚገልጽ አስደናቂ ተስፋም ከጥናቱ ተማረ። አንተም የአካል ጉዳተኛ ከሆንክ እንዲህ ያለው ተስፋ እንዲኖርህ ትፈልጋለህ?

የምትፈልግ ከሆነ እባክህ ተከታዩን ርዕስ አንብብ። ፈጣሪ ስለ ዓላማዎቹ ለሚማሩና ሕይወታቸውን ከዓላማው ጋር አስማምተው ለሚመሩ ሰዎች ምን እንዳዘጋጀ ራስህ መመልከት ትችል ዘንድ ጥቅሶቹን ከራስህ መጽሐፍ ቅዱስ እያወጣህ እንድታነብባቸው ሐሳብ እናቀርብልሃለን።