በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ነገሩ ሁሉ እንቆቅልሽ የሆነው ተርቱሊያን

ነገሩ ሁሉ እንቆቅልሽ የሆነው ተርቱሊያን

ነገሩ ሁሉ እንቆቅልሽ የሆነው ተርቱሊያን

‘በክርስቲያንና በፈላስፋ፣ እውነትን በሚያጣምምና ከተዳፈነበት አውጥቶ በሚያስተምር መካከል ምን መመሳሰል አለ? በፍልስፍና አካዳሚውና በቤተ ክርስቲያን መካከል ምን መስማማት አለ?’ እነዚህን ከባድ ጥያቄዎች ያነሳው በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ይኖር የነበረው ተርቱሊያን የተባለ ጸሐፊ ነው። ይህ ሰው “ስለ ቤተ ክርስቲያን ታሪክና በዘመኑ ይሰጥ ስለነበረው መሠረተ ትምህርት በርካታ ጽሑፎችን ካዘጋጁ ጸሐፊዎች መካከል አንዱ” እንደሆነ ይነገርለታል። ሳይዳስሰው ያለፈው አንድም የሃይማኖታዊ ሕይወት ገጽታ የለም ማለት ይቻላል።

ተርቱሊያን በይበልጥ የሚታወቀው ግራ በሚያጋቡ ወይም እርስ በርስ የሚጻረሩ በሚመስሉ አባባሎቹ ሳይሆን አይቀርም። ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል:- “አምላክ ትንሽ ሆኖ ሳለ እጅግ ታላቅ ነው።” “[የአምላክ ልጅ መሞት] ሊታመን ይገባዋል፤ ምክንያቱም የማይመስል ነገር ነው።” “[ኢየሱስ] ተቀብሯል ከተቀበረበትም ተነስቷል፤ ይህ የማይታበል ሐቅ ነው፤ ምክንያቱም ሊሆን የማይችል ነገር ነው።”

የተርቱሊያንን ሁኔታ እንቆቅልሽ ያደረጉት አባባሎቹ ብቻ አይደሉም። በጽሑፍ ሥራዎቹ አማካኝነት ለእውነት የመሟገት እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንንና መሠረተ ትምህርቶቿን የማስከበር ዓላማ ይዞ የተነሳ ቢሆንም እውነተኛውን ትምህርት ከመበከል አልተመለሰም። ለሕዝበ ክርስትና ያበረከተው ትልቅ ነገር ቢኖር ከጊዜ በኋላ የተነሱ ጸሐፊዎች ለሥላሴ ትምህርት መሠረት አድርገው የተጠቀሙበትን ፅንሰ ሐሳብ ነው። ይህ እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል እንድንችል በመጀመሪያ ስለራሱ ስለ ተርቱሊያን በአጭሩ እንመልከት።

“የማይሰለች ሰው ነው”

ስለ ተርቱሊያን ሕይወት እምብዛም የሚታወቅ ነገር የለም። ብዙ ምሁራን በ160 እዘአ ገደማ ሰሜን አፍሪካ ካርቴጅ ውስጥ እንደተወለደ ይስማማሉ። በደንብ የተማረና በዘመኑ ይሰጥ የነበረውን ፍልስፍና ጠንቅቆ የሚያውቅ እንደነበረ ይታመናል። ወደ ክርስትና እንዲለወጥ ያነሳሳው ክርስቲያን ነን ይሉ የነበሩ ሰዎች ለእምነታቸው ለመሞት ያሳዩት የፈቃደኝነት መንፈስ ሳይሆን አይቀርም። ክርስቲያናዊ ሰማዕትነትን አስመልክቶ የሚከተለውን ጥያቄ አንስቷል:- “በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያሰላስል ማንኛውም ሰው ለሰማዕትነት የሚያነሳሳው ነገር ምንድን ነው ብሎ ለመጠየቅ አይገፋፋምን? ከጠየቀ በኋላ ደግሞ የምናምንበትን መሠረተ ትምህርት ለመቀበል አይነሳሳምን?”

ተርቱሊያን ወደ ስመ ክርስትና ከተለወጠ በኋላ እጥር ምጥን ያሉና ለዛ ያላቸው አባባሎችን በመጻፍ ረገድ የተዋጣለት ጸሐፊ ለመሆን በቅቷል። ዘ ፋዘርስ ኦቭ ዘ ቸርች የተባለው መጽሐፍ “[ተርቱሊያን] ብዙ የሃይማኖት ምሁራን እምብዛም የሌላቸው አንድ ችሎታ አለው። ፈጽሞ የማይሰለች ሰው ነው” በማለት ተናግሯል። አንድ ምሁር ደግሞ እንዲህ ብለዋል:- “ተርቱሊያን ከዓረፍተ ነገር አሰካክ ይልቅ በቃላት አጠቃቀሙ ይበልጥ የተካነ ሲሆን የመከራከሪያ ነጥቦቹን ከመረዳት ይልቅ በቀልድ እያዋዛ የሚሰነዝረውን አስተያየት መረዳት በጣም ይቀላል። የእርሱ ሐሳቦች ብዙ ጊዜ የሚጠቀሱ ቢሆንም አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ከእርሱ የጽሑፍ ሥራ ላይ ከጥቂት ቃላት ያለፈ ነገር የማይጠቀሰው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም።”

ለክርስትና ተሟግቷል

በሰፊው የሚታወቀው የተርቱሊያን የጽሑፍ ሥራ አፖሎጂ የተሰኘው ሲሆን ይህ ጽሑፍ ለስመ ክርስትና ለመሟገት ከተዘጋጁት ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደር የቻሉ የጽሑፍ ሥራዎች አንዱ እንደሆነ ይገመታል። የተጻፈው ክርስቲያኖች አጉል እምነት በሚከተሉ ሰዎች የጥቃት ዒላማ በሆኑበት ወቅት ላይ ነበር። ተርቱሊያን እነዚህ ክርስቲያኖች ይደርስባቸው የነበረውን ጭፍን ጥላቻ በመቃወም ተሟግቶላቸዋል። እንዲህ ብሏል:- “[ተቃዋሚዎች] ማንኛውም ዓይነት መቅሰፍትም ሆነ ክፉ አጋጣሚ በሕዝብ ላይ የሚደርሰው በክርስቲያኖች ምክንያት እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። . . . የናይል ወንዝ ሞልቶ በማሳው ላይ መፍሰስ ባይችል፣ የአየር መዛባት ቢያጋጥም፣ የምድር መናወጥ ቢከሰት፣ የምግብ እጦት ቢያጋጥም፣ ወረርሽኝ ቢነሳ ወዲያውኑ ‘ክርስቲያኖችን ለአንበሳ ስጧቸው’ የሚል ጩኸት ይሰማል።”

ምንም እንኳን ክርስቲያኖች ለመንግሥት ታማኞች አይደሉም ተብለው በተደጋጋሚ ቢወነጀሉም ተርቱሊያን በግዛቱ ውስጥ ከማንም ይበልጥ እምነት የሚጣልባቸው ዜጎች መሆናቸውን ለማስረዳት ጥረት አድርጓል። መንግሥት ለመገልበጥ ተደርገው የነበሩትን ተደጋጋሚ ሙከራዎች በምሳሌነት ከጠቃቀሰ በኋላ ተቃዋሚዎቹ የሴራው ጠንሳሾች የሚነሱት ከአረማውያን እንጂ ከክርስቲያኖች መካከል አለመሆኑን ልብ እንዲሉ አሳስቧል። ተርቱሊያን ክርስቲያኖች በሞት ሲቀጡ ዞሮ ዞሮ የሚጎዳው መንግሥት እንደሆነ አመልክቷል።

ተርቱሊያን በክርስቲያናዊ አኗኗር ላይ ያተኮሩ ሌሎች ጽሑፎችም አሉት። ለምሳሌ ያህል ኦን ዘ ሾውስ በሚል ርዕስ በሰጠው ማብራሪያ ላይ በአንዳንድ የመዝናኛ ቦታዎች፣ የአረማውያን ጨዋታዎችና ቲያትሮች ላይ መገኘት ተገቢ እንዳልሆነ ምክር ሰጥቷል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በሚሰጥባቸው ስብሰባዎች ላይ እየተካፈሉ በአረማውያን ጨዋታዎችም ላይ መገኘታቸው ምንም ስህተት እንደሌለበት ሆኖ የተሰማቸው አንዳንድ ወደ ክርስትና የተለወጡ ሰዎች የነበሩ ይመስላል። ተርቱሊያን የማሰብ ችሎታቸውን እንዲያሠሩት ለማነሳሳት አስቦ “ከአምላክ ቤተ ክርስቲያን ወጥቶ ወደ ዲያብሎስ ሥፍራ መሄድ፤ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ቆይቶ በእንስሳዊ ተግባራት መካፈል ምንኛ አስጸያፊ ነው” በማለት ጽፏል። “በድርጊት የማትደግፉትን ነገር በአንደበታችሁም መደገፍ አይገባችሁም” በማለት ተናግሯል።

ለእውነት እየተሟገተ እውነትን አጣምሟል

ተርቱሊያን ኤጌይንስት ፕራክሰስ በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ድርሰት መግቢያ ላይ እንዲህ ብሏል:- “ዲያብሎስ በተለያዩ መንገዶች እውነትን ተገዳድሯል እንዲሁም ተቃውሟል። አንዳንድ ጊዜ ግቡ ለእውነት በመሟገት እውነትን ማጥፋት ነበር።” በዚህ ድርሰት ውስጥ የተጠቀሰው ፕራክሰስ የተባለው ሰው ማንነቱ በግልጽ አይታወቅም። ሆኖም ተርቱሊያን ይህ ሰው አምላክንና ክርስቶስን አስመልክቶ ያስተማረውን ትምህርት ተቃውሟል። ፕራክሰስን የተመለከተው ሰይጣን ክርስትናን ለመበከል በእጅ አዙር የሚጠቀምበት መሣሪያ እንደሆነ አድርጎ ነው።

በዚያ ዘመን ክርስቲያን ነን ይሉ በነበሩ ሰዎች መካከል የነገሠው ዋነኛ አከራካሪ ጉዳይ በአምላክና በክርስቶስ መካከል ያለው ዝምድና ነበር። ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹ በተለይም በግሪክ ባሕል ሥር ያደጉት አንድ አምላክ አለ የሚለውን እምነት ኢየሱስ አዳኝም ነው ሰዎችንም ይቤዣል ከሚለው ሐሳብ ጋር ማጣጣም ከብዷቸው ነበር። ፕራክሰስ ኢየሱስ የአብ ሌላ መገለጫ እንደሆነና በአብና በወልድ መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት እንደሌለ በማስተማር ችግራቸውን ለመፍታት ሙከራ አድርጓል። ሞዳሊዝም በመባል የሚታወቀው ይህ ፅንሰ ሐሳብ አምላክ ራሱን “በፍጥረትና ሕግ በመስጠት እንደ አብ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ወልድ እንዲሁም ከክርስቶስ ዕርገት በኋላ እንደ መንፈስ ቅዱስ” ገልጧል የሚል ነው።

ተርቱሊያን ቅዱሳን ጽሑፎች በአባትና በልጅ መካከል ያለውን ግልጽ ልዩነት ቁልጭ አድርገው ማስቀመጣቸውን ገልጿል። አንደኛ ቆሮንቶስ 15:​27, 28ን ከጠቀሰ በኋላ “(ሁሉን) ያስገዛለትና ሁሉ የተገዛለት የግድ ሁለት የተለያዩ አካላት መሆን ይኖርባቸዋል” በማለት አስረድቷል። ተርቱሊያን ኢየሱስ ራሱ “ከእኔ አብ ይበልጣል” ያለውን በማስረጃነት ጠቅሷል። (ዮሐንስ 14:​28) ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እንደ መዝሙር 8:​5 ያሉ አንዳንድ ጥቅሶችን በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስ ወልድ ከአብ “የሚያንስ” መሆኑን እንደሚናገር በግልጽ ለማስረዳት ሞክሯል። ተርቱሊያን “ስለሆነም አብ ከወልድ የተለየና ከእርሱ የሚበልጥ አካል ነው። አባት አንድ አካል ሲሆን ልጁ ደግሞ ሌላ አካል ነው፤ ላኪ አንድ አካል ሲሆን ተላኪው ሌላ አካል ነው፤ እንዲሁም ፈጣሪ አንድ አካል ሲሆን ሁሉ በእርሱ በኩል የተፈጠረበት አካል ደግሞ ሌላ ነው” በማለት ደምድሟል።

ተርቱሊያን ወልድን የሚመለከተው የአብ የበታች እንደሆነ አድርጎ ነበር። ይሁን አንጂ የሞዳሊዝምን ፅንሰ ሐሳብ ውድቅ ለማድረግ ሲሞክር ‘ከተጻፈው አልፎ’ ሄዷል። (1 ቆሮንቶስ 4:​6) ተርቱሊያን የኢየሱስን መለኮትነት ለማስረዳት በወሰደው የተሳሳተ እርምጃ “ሦስት አካል አንድ አምላክ” የሚል ፅንሰ ሐሳብ አፍልቋል። ይህን ፅንሰ ሐሳብ በመጠቀም አምላክ፣ የእርሱ ልጅና መንፈስ ቅዱስ ሦስት የተለያዩ አካላት ግን አንድ አምላክ እንደሆኑ አድርጎ ለማስረዳት ሞክሯል። በዚህ መንገድ ተርቱሊያን “ሥላሴ” የሚል መልእክት ያለውን የላቲን ቃል ለአብ፣ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ የተጠቀመ የመጀመሪያው ሰው ለመሆን በቅቷል።

ከዓለማዊ ፍልስፍና ተጠበቁ

ተርቱሊያን “ሦስት አካል አንድ አምላክ” ወደሚለው ፅንሰ ሐሳብ ሊደርስ የቻለው እንዴት ነበር? ምሥጢሩ ያለው ተርቱሊያን ፍልስፍናን በተመለከተ በነበረው እንቆቅልሽ የሆነ አመለካከት ላይ ነው። ተርቱሊያን ፍልስፍናን “የሰዎችና ‘የአጋንንት ትምህርት’” በማለት ጠርቶታል። ፍልስፍናን ለክርስትና እውነቶች ድጋፍ አድርጎ መጠቀምን በአደባባይ አውግዟል። “በስቶይክ፣ በፕላቶኒክ እንዲሁም በዲያሌክቲክ ፍልስፍናዎች የተበረዘ ብልሹ ክርስትና ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት መቆም ይገባዋል” በማለት ተናግሯል። ሆኖም ተርቱሊያን ከራሱ ሐሳብ ጋር የሚስማማ ሆኖ በሚያገኘው ጊዜ ዓለማዊ ፍልስፍናን ከመጠቀም ወደኋላ አላለም።​—⁠ቆላስይስ 2:​8

አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ብሏል:- “የሥላሴ መሠረተ ትምህርት እየዳበረ ለመሄድም ሆነ ማብራሪያዎቹን ለመስጠት የሔለናውያን ንድፈ ሐሳብና ፍልስፍና እገዛ አስፈልጎታል።” ዘ ቲኦሎጂ ኦቭ ተርቱሊያን የተባለው መጽሐፍ ደግሞ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቷል:- “ምንም እንኳን የተርቱሊያን ሐሳብ የራሱ ጉድለቶችና ድክመቶች ቢኖሩትም ከጊዜ በኋላ የኒቂያ ጉባኤ ላጸደቀው የሥላሴ ትምህርት የመሠረት ድንጋይ የሆነውን ይህን ፅንሰ ሐሳብ ያፈለቀው ሕገ ደንብን እንግዳ በሆነ መንገድ ከፍልስፍና ሐሳቦችና መግለጫዎች ጋር አጣምሮ በማቅረብ ነበር።” ስለሆነም ሦስት አካል አንድ አምላክ የሚለው የተርቱሊያን ፅንሰ ሐሳብ በመላው ሕዝበ ክርስትና ውስጥ የተሳሳተ ሃይማኖታዊ ትምህርት እንዲስፋፋ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

ተርቱሊያን ለእውነት ለመሟገት እየሞከሩ እውነትን የሚያጠፉ ሰዎችን አውግዟል። የሚያስገርመው ግን እርሱ ራሱ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከሰዎች ፍልስፍና ጋር በመበረዝ ተመሳሳይ ስህተት ሠርቷል። እንግዲያው እኛም ‘ለሚያስቱ መናፍስትና ለአጋንንት ትምህርት’ ጆሮ እንዳንሰጥ የሚያሳስበውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስጠንቀቂያ ልብ እንበል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​1

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተርቱሊያን ፍልስፍናን ቢያወግዝም የራሱን አመለካከት ለማስፋፋት ተጠቅሞበታል

[ምንጭ]

ገጽ 29 እና 30:- © Cliché Bibliothèque nationale de France, Paris

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እውነተኛ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በሰዎች ፍልስፍና ከመበረዝ ይቆጠባሉ