አምላክ ማን ነው?
አምላክ ማን ነው?
“አምላክ የሚለው ስም አጽናፈ ዓለሙን ለፈጠረውና አምልኮ ለሚሰጠው ታላቅ ኃይል በተለምዶ የሚሰጥ ስም ነው” በማለት ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና ይገልጻል። አንድ መዝገበ ቃላት “አምላክ” የሚለውን ቃል “ከሁሉ በላይ የሆነ ህላዌ” በማለት ተርጉሞታል። ታላቅ ግርማን ስለተላበሰው ስለዚህ ህላዌ ማንነት ምን ለማለት ይቻላል?
አምላክ የተወሰነ አካል የሌለው ኃይል ነው ወይስ እውን አካል? ስምስ አለው? ብዙዎች እንደሚያምኑት አንድም ሦስትም የሆነ ሥላሴ ነው? አምላክን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች እውነተኛና አጥጋቢ መልስ ይሰጠናል። እንዲያውም “ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም” በማለት አምላክን እንድንፈልገው ያበረታታናል።—ሥራ 17:26, 27
የተወሰነ አካል የሌለው ኃይል ወይስ እውን አካል?
በአምላክ የሚያምኑ አብዛኞቹ ሰዎች እርሱን የሚመለከቱት እውን እንደሆነ አካል ሳይሆን ኃይል እንደሆነ አድርገው ነው። ለምሳሌ በአንዳንድ ባሕሎች አማልክት ከተፈጥሮ ኃይላት ጋር ተዛምደዋል። የአጽናፈ ዓለሙን አቀማመጥና የሕይወትን አመጣጥ በተመለከተ በሳይንሳዊ ምርምር የተገኙ ማስረጃዎችን ያጠኑ አንዳንዶች ሁሉንም ነገር ወደ ሕልውና ያመጣ የመጀመሪያ ምክንያት መኖር አለበት ወደሚል መደምደሚያ ደርሰዋል። ይሁን እንጂ ለዚህ የመጀመሪያ ምክንያት ስብዕና ለመስጠት ያመነታሉ።
ታዲያ ውስብስብ የሆነው ፍጥረት የመጀመሪያው ምክንያት ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ እንዳለው አያመለክትም? የማሰብ ችሎታ ደግሞ አእምሮን ይጠይቃል። ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው ታላቅ አእምሮ የአምላክ አእምሮ ነው። አዎን፣ አምላክ አካል ማለትም የእኛ ዓይነት ሰብዓዊ ሳይሆን መንፈሳዊ አካል አለው። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 15:44) መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን አካል በሚመለከት “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ዮሐንስ 4:24) መንፈስ ከእኛ በእጅጉ የተለየ የሕይወት ዓይነት ሲሆን በሰው ዓይን አይታይም። (ዮሐንስ 1:18) በዓይን የማይታዩ መንፈሳዊ ፍጥረታትም አሉ። እነርሱም “የአምላክ ልጆች” የሆኑት መላእክት ናቸው።—ኢዮብ 1:6፤ 2:1
አምላክ ፍጡር ባይሆንም መንፈሳዊ አካል ያለው እንደመሆኑ መጠን የሚኖርበት ቦታ እንደሚኖረው የተረጋገጠ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊውን ዓለም አስመልክቶ ሲገልጽ ሰማያት የአምላክ “ማደሪያ” እንደሆኑ ይነግረናል። (1 ነገሥት 8:43) በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱሱ ጸሐፊ ጳውሎስ ‘ክርስቶስ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ’ በማለት ተናግሯል።—ዕብራውያን 9:24
“መንፈስ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሌላ መልኩም ተሠርቶበታል። መዝሙራዊው ወደ አምላክ ሲጸልይ “መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 104:30) ይህ መንፈስ አምላክ ራሱ ሳይሆን እርሱ የፈለገውን ሁሉ ለመሥራት የሚልከው ወይም የሚጠቀምበት ኃይል ነው። አምላክ መንፈሱን ተጠቅሞ ግዑዙን ሰማይ፣ ምድርንና ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ ፈጥሯል። (ዘፍጥረት 1:2፤ መዝሙር 33:6) ይህ መንፈስ መንፈስ ቅዱስ ይባላል። አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉትን ሰዎች ለማነሳሳት የተጠቀመው በዚህ መንፈስ ነው። (2 ጴጥሮስ 1:20, 21) ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ዓላማዎቹን ለማስፈጸም የሚጠቀምበት የማይታይ አንቀሳቃሽ ኃይል ነው።
አምላክ ልዩ ስም አለው
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ አጉር የሚከተለውን ጠይቋል:- “ነፋስንስ በእጁ የጨበጠ ማን ነው? ውኃንስ በልብሱ የቋጠረ ማን ነው? የምድርን ዳርቻ ሁሉ ያጸና ማን ነው? ይህን ታውቅ እንደ ሆንህ፣ ስሙ ማን የልጁስ ስም ማን ነው?” (ምሳሌ 30:4) በሌላ አባባል አጉር ‘እነዚህን ነገሮች የሠራውን ሰው ስም ወይም የዘር ሐረጉን ታውቃለህ?’ ማለቱ ነበር። የተፈጥሮ ኃይላትን የመቆጣጠር ኃይል ያለው አምላክ ብቻ ነው። ፍጥረት አምላክ መኖሩን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ቢሆንም የአምላክን ስም ግን አይነግረንም። እንዲያውም አምላክ ራሱ ስሙን ባይገልጥልን ኖሮ ስሙን ማወቅ የምንችልበት አጋጣሚ ፈጽሞ አይኖረንም ነበር። ፈጣሪ “እኔ ይሖዋ ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው” በማለት ስሙን ገልጦልናል።—ኢሳይያስ 42:8 NW
ይሖዋ የተባለው የአምላክ ልዩ ስም በጥንቱ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ብቻ 7, 000 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ስም ለሌሎች አሳውቋል እንዲሁም በሌሎች ፊት አወድሶታል። (ዮሐንስ 17:6, 26) ይህ ስም በመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ “ሃሌ ሉያ” ማለትም “ያህን አመስግኑ” በሚለው መግለጫ ውስጥ ይገኛል። “ያህ” ደግሞ “የይሖዋ” አጭር አጠራር ነው። (ራእይ 19:1-6) ሆኖም አብዛኞቹ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በዚህ ስም አይጠቀሙም። ከዚህ ይልቅ በአብዛኛው ስሙን “ጌታ” እና “አምላክ” ከሚሉት በተለምዶ ከሚሰጡ የማዕረግ ስሞች ለመለየት በአንዳንድ ቋንቋዎች በትልልቅ ፊደላት በተጻፉ “ጌታ” ወይም “አምላክ” በሚሉት ቃላት ይጠቀማሉ። አንዳንድ ምሁራን መለኮታዊው ስም ያህዌህ ነው በማለት ይናገራሉ።
ዘጸአት 6:3 የ1879 ትርጉም፤ ኢሳይያስ 26:4 NW
የአጽናፈ ዓለሙ ታላቅ አካል የሚጠራበትን ስም በተመለከተ እንዲህ ዓይነት ልዩነት ሊፈጠር የቻለው ለምንድን ነው? ችግሩ የጀመረው ከብዙ ዓመታት በፊት አይሁዳውያን በአጉል እምነት ተነሳስተው መለኮታዊውን ስም መጥራት ሲያቆሙና በምትኩ ቅዱሳን ጽሑፎችን በሚያነቡበት ጊዜ ስሙ ጋር ሲደርሱ የዕብራይስጡን ቃል “ሉዓላዊ ጌታ” በሚለው መተካት ሲጀምሩ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት የዕብራይስጥ ቋንቋ አናባቢ ስላልነበረው ሙሴ፣ ዳዊትና ሌሎች የጥንት ሰዎች መለኮታዊውን ስም የሚወክሉትን ፊደላት እንዴት ያነቧቸው እንደነበር በትክክል ማወቅ የሚቻልበት መንገድ የለም። ይሁን እንጂ ይሖዋ የሚለው አጠራር ለብዙ ዓመታት ሲሠራበት የቆየ ሲሆን ከዚህ ጋር የሚመሳሰሉ ሌሎች አጠራሮችም በብዙ ቋንቋዎች ሰፊ ተቀባይነት አግኝተዋል።—የአምላክ የግል ስም በጥንት የዕብራውያን ዘመን እንዴት ይጠራ እንደነበር አስረግጦ መናገር ባይቻልም ትርጉሙ ግን የተሰወረ አይደለም። የስሙ ትርጉም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ነው። ይሖዋ ራሱን ታላቅ የዓላማ አምላክ እንደሆነ አድርጎ ገልጿል። ስለዚህ ይሖዋ ዓላማዎቹና ተስፋዎቹ እውን እንዲሆኑ ያደርጋል። ይህንን ስም መሸከም የሚችለው እነዚህን ነገሮች የማድረግ ኃይል ያለው እውነተኛው አምላክ ብቻ ነው።—ኢሳይያስ 55:11
ይሖዋ የሚለው ስም ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ከሌሎች አማልክት ለመለየት እንደሚያገለግል ምንም ጥርጥር የለውም። ብዙ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ የምናገኘውም በዚህ ምክንያት ነው። ብዙ ትርጉሞች መለኮታዊውን ስም ባይጠቀሙም መዝሙር 83:18 [NW] “ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ በምድር ሁሉ ላይ አንተ ብቻ ልዑል እንደሆንክ ሰዎች ሁሉ ይወቁ” በማለት በግልጽ ይናገራል። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ደቀ መዛሙርቱን “እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ:- በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” በማለት አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9) ስለዚህ ወደ አምላክ ስንጸልይ፣ ስለ እርሱ ስንናገርና በሌሎች ፊት ስናወድሰው በስሙ መጠቀም ይኖርብናል።
ኢየሱስ አምላክ ነውን?
ይሖዋ አምላክ ራሱ የልጁን ማንነት በማያሻማ መንገድ ገልጿል። የማቴዎስ ወንጌል ዘገባ ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ “ድምፅ ከሰማያት መጥቶ:- በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” እንዳለ ይገልጻል። (ማቴዎስ 3:16, 17) ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ልጅ ነው።
ሆኖም አንዳንድ ሃይማኖታዊ ሰዎች ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው በማለት ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ አምላክ ሥላሴ ነው ይላሉ። በዚህ ትምህርት መሠረት “አብ እግዚአብሔር ነው፣ ወልድ እግዚአብሔር ነው መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር ነው። ሆኖም አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አይደሉም።” ሦስቱም “ዘላለማዊና እኩል” ናቸው ተብሎ ይታሰባል። (ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ) እንዲህ ያለው አመለካከት ትክክል ነው?
በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች ይሖዋን አስመልክተው “ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ” በማለት ይናገራሉ። (መዝሙር 90:2) እርሱ መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ የሌለው ‘ዘላለማዊ ንጉሥ’ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:17) በሌላው በኩል ግን ኢየሱስ “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር” እና “በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ” ነው። (ቆላስይስ 1:13-15፤ ራእይ 3:14) ኢየሱስ፣ አምላክ አባቱ እንደሆነ ሲገልጽ “አብ ከእኔ ይበልጣል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:28) በተጨማሪም ኢየሱስ እርሱም ሆኑ መላእክት የማያውቋቸው ሆኖም አምላክ ብቻ የሚያውቃቸው አንዳንድ ነገሮች እንደነበሩ ገልጿል። (ማርቆስ 13:32) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ “የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ” በማለት ወደ አባቱ ጸልዮአል። (ሉቃስ 22:42) ኢየሱስ ከእርሱ በላይ ለሆነ አካል ካልሆነ በቀር ለማን ሊጸልይ ይችላል? በተጨማሪም ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው አምላክ እንጂ ኢየሱስ ራሱ አልነበረም።—ሥራ 2:32
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነና ኢየሱስ ደግሞ ልጁ እንደሆነ ያሳያል። ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትም ሆነ ምድር ከመጣ በኋላ ከአባቱ ጋር እኩል አልነበረም። ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ ካረገም በኋላ ቢሆን ከአባቱ ጋር እኩል አልሆነም። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ 15:28) ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የሥላሴ ሦስተኛ ክፍል ነው የሚባለው መንፈስ ቅዱስ አካል አይደለም። ከዚያ ይልቅ አምላክ ዓላማዎቹን ለማስፈጸም የሚጠቀምበት ኃይል ነው። ስለዚህ ሥላሴ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት አይደለም። a መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ፣ አምላካችን አንድ ይሖዋ ነው” በማለት ይናገራል።—ዘዳግም 6:4 NW
አምላክን በተሻለ መንገድ እወቅ
አምላክን ለመውደድና ለእርሱ ብቻ የሚገባውን አምልኮ ለመስጠት እውነተኛ ማንነቱን ማወቅ ይኖርብናል። አምላክን በተሻለ መንገድ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያል” በማለት ይናገራል። (ሮሜ 1:20) አምላክን በተሻለ መንገድ ማወቅ የሚቻልበት አንደኛው መንገድ የፈጠራቸውን ነገሮች በመመልከትና በአመስጋኝነት ስሜት በማሰላሰል ነው።
ይሁን እንጂ ፍጥረት ስለ አምላክ ልናውቃቸው የሚገቡንን ነገሮች በሙሉ አይነግረንም። ለምሳሌ አምላክ ልዩ ስም ያለው እውን መንፈሳዊ አካል መሆኑን ለመገንዘብ መጽሐፍ ቅዱስን መመልከት አለብን። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት አምላክን ይበልጥ ለማወቅ የሚረዳ ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው። ይሖዋ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ በግልጽ አስፍሮልናል። በተጨማሪም ዓላማዎቹን ይገልጥልናል እንዲሁም መንገዶቹን ያስተምረናል። (አሞጽ 3:7፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) አምላክ “እውነቱን ወደ ማወቅ” በመድረስ ከፍቅራዊ ዝግጅቶቹ እንድንጠቀም የሚፈልግ መሆኑን በማወቃችን ምንኛ ደስተኞች ነን! (1 ጢሞቴዎስ 2:4) ስለዚህ አቅማችን የፈቀደውን ያህል ስለ ይሖዋ ለመማር ጥረት እናድርግ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስለዚህ ርዕስ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በሥላሴ ማመን ይገባሃልን? የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ብሮሹር ተመልከት።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ ምድርን ለመፍጠርና ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጽፉ ለማነሳሳት በመንፈሱ ተጠቅሟል
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሰማያት የመጣ ድምፅ “ልጄ ይህ ነው” በማለት ተናግሯል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ከእርሱ ወደሚበልጥ አካል ይኸውም ወደ አምላክ ጸልዮአል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የአምላክን ስም ለሌሎች አሳውቋል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክን በተሻለ መንገድ ማወቅ እንችላለን