በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ማን እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል

አምላክ ማን እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል

አምላክ ማን እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል

በከዋክብት የተሞላ ጥርት ያለ ሰማይ ስትመለከት በአድናቆት አትሞላም? በቀለም ካሸበረቁ አበቦች የሚወጣው መዓዛ አይማርክህም? የወፎችን ዝማሬና በቀስታ የሚነፍሰው ነፋስ የዛፎቹን ቅርንጫፎች ሲያወዛውዝ የሚፈጠረውን ድምፅ መስማት አያስደስትህም? በባሕር ውስጥ የሚኖሩት ዓሣ ነባሪዎችና ሌሎች ሕያዋን ፍጥረታትስ ምንኛ አስደናቂ ናቸው! የሚያመዛዝን ኅሊና እንዲሁም አስደናቂና ውስብስብ የሆነ አእምሮ ያላቸው የሰው ልጆችም አሉ። በዙሪያችን ያሉ እነዚህ ሁሉ አስደናቂ ነገሮች እንዴት እንደተገኙ ማብራራት ትችላለህ?

አንዳንዶች ይህ ሁሉ እንዲያው በአጋጣሚ የተገኘ ነው ብለው ያስባሉ። ታዲያ ይህ ትክክል ከሆነ ሰዎች በአምላክ የሚያምኑት ለምንድን ነው? የኬሚካሎች ድንገተኛ ውህደት መንፈሳዊ ፍላጎት ያላቸው ፍጥረታት እንዴት ሊያስገኝ ይችላል?

“ሃይማኖት በማንኛውም የኢኮኖሚና የትምህርት ደረጃ ላይ በሚገኝ ሰው ሁሉ ዘንድ ያለ የሰው ልጆች ባሕርይ ክፍል ነው።” ይህ አባባል ፕሮፌሰር አሊስተር ሃርዲ ዘ ስፒሪቹዋል ኔቸር ኦቭ ማን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ያቀረቡትን ምርምር ጠቅለል አድርጎ የሚገልጽ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአእምሮ ላይ የተደረጉ ሙከራዎች አንዳንድ የነርቭ ሳይንቲስቶች ሰው ሃይማኖታዊ እንዲሆን ተደርጎ “የተሠራ” ሊሆን ይችላል ወደሚል መደምደሚያ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል። ኢዝ ጎድ ዚ ኦንሊ ሪያሊቲ? በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፍ የሚከተለውን ብሏል፦ “በሃይማኖት አማካኝነት የሕይወትን ትርጉም ለማወቅ መጣር . . . የሰው ዘር ወደ ሕልውና ከመጣበት ጊዜ አንስቶ በሁሉም ባሕልና የእድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች የጋራ ልማድ ሆኖ ቆይቷል።”

አንድ የተማረ ሰው ከ2, 000 ዓመታት በፊት የደረሰበትን መደምደሚያ ተመልከት። እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “እያንዳንዱ ቤት በአንድ ሰው ተዘጋጅቶአልና፣ ሁሉን ያዘጋጀ ግን እግዚአብሔር ነው።” (ዕብራውያን 3:​4) እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስ የመክፈቻ ቃላት “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” የሚሉ ናቸው።​—⁠ዘፍጥረት 1:​1

ታዲያ አምላክ ማን ነው? የሰው ልጅ በዚህ ጥያቄ ረገድ በእጅጉ የተከፋፈለ ነው። ዮሺ የተባለ በአሥራዎቹ እድሜ ውስጥ የሚገኝ አንድ ጃፓናዊ አምላክ ማን እንደሆነ ሲጠየቅ “እርግጠኛ አይደለሁም። እኔ የቡዲስት እምነት ተከታይ ነኝ፤ አምላክ ማን እንደሆነ ማወቅም አያስፈልገኝም” የሚል መልስ ሰጠ። ሆኖም ዮሺ ቡድሃ በብዙዎች ዘንድ እንደ አምላክ ተደርጎ እንደሚቆጠር አምኗል። በ60ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ኒክ የተባለ አንድ ነጋዴ በአምላክ የሚያምን ሲሆን እጅግ ታላቅ ኃይል እንደሆነ አድርጎ ያስባል። ኒክ ስለ አምላክ የሚያውቀውን እንዲናገር ሲጠየቅ ከረዥም ዝምታ በኋላ “የእኔ ወንድም፣ ይህ በጣም ከባድ ጥያቄ ነው። እኔ የማውቀው አምላክ እንዳለ ብቻ ነው” በማለት መልሷል።

አንዳንድ ሰዎች ‘በፈጣሪ ፈንታ የተፈጠረውን ያመልካሉ እንዲሁም ያገለግላሉ።’ (ሮሜ 1:​25) በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ አምላክ ሩቅና ሊደረስበት የማይችል እንደሆነ አድርገው ስለሚያስቡ የሞቱ የቀድሞ አባቶቻቸውን ያመልካሉ። በሂንዱ ሃይማኖት በርካታ የወንድና የሴት አማልክት አሉ። እንደ ድያ እና ሄርሜን ያሉ ብዙ አማልክት በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ዘመን ይመለኩ ነበር። (ሥራ 14:​11, 12) ብዙ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አምላክ እግዚአብሔር አብን፣ እግዚአብሔር ወልድንና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን የያዘ ሥላሴ ነው በማለት ያስተምራሉ።

በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ።” ይሁን እንጂ በማከል “ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ . . . አንድ አምላክ አብ አለን” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 8:​5, 6) አዎን፣ እውነተኛው አምላክ አንድ ብቻ ነው። ግን ማን ነው? ምን ይመስላል? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማግኘታችን አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ ራሱ ለዚሁ አምላክ የሚከተለውን ጸሎት አቅርቧል፦ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” (ዮሐንስ 17:​3) ዘላለማዊ ደህንነታችን የተመካው ስለ አምላክ እውነቱን በማወቃችን ላይ ነው ብሎ ለማመን የሚያበቃ ምክንያት አለ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንዴት ተገኙ?

[የሥዕል ምንጭ]

Whale: Courtesy of Tourism Queensland

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

COVER: Index Stock Photography © 2002