አምላክ ያሳየንን ፍቅር ታደንቃለህ?
አምላክ ያሳየንን ፍቅር ታደንቃለህ?
አንድ ወቅት ኢዮብ ፍጹም ያልሆነው የሰው ዘር ያለበትን ሁኔታ እንደሚከተለው በማለት ገልጾት ነበር:- “ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው፣ መከራም ይሞላዋል። እንደ አበባ ይወጣል፣ ይረግፋልም፤ እንደ ጥላም ይሸሻል፣ እርሱም አይጸናም።” (ኢዮብ 14:1, 2) ሕይወት ለኢዮብ በሐዘንና በሰቆቃ የተሞላ ሆኖበት ነበር። አንተስ እንደዚህ ተሰምቶህ ያውቃል?
ይሁን እንጂ ብዙ ችግሮችና መከራዎች ቢደርሱብንም በአምላክ ርኅራኄና ፍቅር ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ተስፋ አለን። በመጀመሪያ ደረጃ መሐሪ የሆነው ሰማያዊ አባታችን የሰው ልጆችን ከወደቁበት የኃጢአት አዘቅት ለመቤዠት ቤዛዊ መሥዋዕቱን አዘጋጅቷል። በዮሐንስ 3:16, 17 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፣ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና” በማለት ተናግሯል።
እንዲሁም አምላክ ፍጽምና ለጎደለን ለእኛ ለሰው ልጆች ያሳየውን ደግነት አስብ። ሐዋርያው ጳውሎስ “ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፣ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፣ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም” በማለት ተናግሯል። (ሥራ 17:26, 27) እስቲ አስበው! ፍጹም ባንሆንም አፍቃሪ ከሆነው ፈጣሪያችን ከይሖዋ አምላክ ጋር አሁንም የግል ዝምድና መመሥረት እንችላለን።
እንግዲያው አምላክ እንደሚያስብልንና በፍቅር ተነሳስቶ ለዘላቂ ጥቅማችን ሲል ዝግጅት እንዳደረገልን በማወቃችን በልበ ሙሉነት የወደፊቱን ጊዜ መጠባበቅ እንችላለን። (1 ጴጥሮስ 5:7፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) በእርግጥም ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ስለ አፍቃሪው አምላካችን ይበልጥ እንድንማር የሚገፋፋን በቂ ምክንያት አለን።