በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ፍቅራዊ ደግነት አሳዩ

እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ፍቅራዊ ደግነት አሳዩ

እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ፍቅራዊ ደግነት አሳዩ

“ቸርነትን [“ፍቅራዊ ደግነትን፣” Nw ] . . . ሁላችሁ ለወንድሞቻችሁ አድርጉ።”​—⁠ዘካርያስ 7:​9

1, 2. (ሀ) ፍቅራዊ ደግነት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

 የይሖዋ አምላክ ቃል ‘ምሕረትን [“ፍቅራዊ ደግነትን፣” NW ]’ እንድንወድ ያሳስበናል። (ሚክያስ 6:​8) መውደድ ያለብን ለምን እንደሆነም ይነግረናል። አንደኛው ምክንያት “ቸር [“ፍቅራዊ ደግነትን የሚያሳይ፣” NW ] ሰው ለራሱ መልካም ያደርጋል።” (ምሳሌ 11:​17) ይህ ምንኛ ትክክል ነው! ፍቅራዊ ደግነት ወይም ታማኝ ፍቅር ማሳየት ከሌሎች ጋር ሞቅ ያለና የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችላል። ከዚህም የተነሳ ታማኝ ወዳጆች እናፈራለን። ይህ በእርግጥ አስደሳች ውጤት ነው!​—⁠ምሳሌ 18:​24

2 በተጨማሪም “ጽድቅንና ምሕረትን [“ፍቅራዊ ደግነትን፣” NW ] የሚከተል ሕይወትን . . . ያገኛል” በማለት ቅዱሳን ጽሑፎች ይናገራሉ። (ምሳሌ 21:​21) አዎን፣ ፍቅራዊ ደግነት መከተላችን በአምላክ ፊት ተወዳጅ የሚያደርገን ከመሆኑም በላይ የዘላለም ሕይወትን ጨምሮ ወደፊት የሚመጡ በረከቶችን እንድናገኝ አጋጣሚ ይሰጠናል። ሆኖም ፍቅራዊ ደግነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ማሳየት ያለብንስ ለማን ነው? ደግሞስ ፍቅራዊ ደግነት ከተለመደው ሰብዓዊ ደግነት ወይም በጥቅሉ ከደግነት ይለያል?

ሰብዓዊ ደግነትና ፍቅራዊ ደግነት

3. ፍቅራዊ ደግነት ከሰብዓዊ ደግነት የሚለየው እንዴት ነው?

3 ተፈጥሮአዊው ሰብዓዊ ደግነትና ፍቅራዊ ደግነት በብዙ መንገዶች ይለያያሉ። ለምሳሌ ያህል ሰብዓዊ ደግነት የሚያሳዩ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ የሚያደርጉት ከግለሰቡ ጋር የጠበቀና የግል ቅርርብ ወይም ዝምድና ሳይኖራቸው ነው። ይሁን እንጂ ለአንድ ሰው ፍቅራዊ ደግነት የምናሳየው ከዚያ ሰው ጋር ፍቅራዊ ቅርርብ ሲኖረን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰዎች መካከል ፍቅራዊ ደግነት የተገለጠው ቀደም ሲል በተመሠረተ ዝምድና ላይ ሊሆን ይችላል። (ዘፍጥረት 20:​13፤ 2 ሳሙኤል 3:​8፤ 16:​17) ወይም ቀደም ሲል የተገለጹ የደግነት ድርጊቶች በፈጠሩት ዝምድና ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል። (ኢያሱ 2:​1, 12-14፤ 1 ሳሙኤል 15:​6፤ 2 ሳሙኤል 10:​1, 2) ይህን ልዩነት በግልጽ ለማየት እንድንችል በሰዎች መካከል የተገለጡ ሰብዓዊ ደግነትንና ፍቅራዊ ደግነትን የሚያሳዩ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እናወዳድር።

4, 5. እዚህ ላይ የተጠቀሱት ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች በሰብዓዊ ደግነትና በፍቅራዊ ደግነት መካከል ያለውን ልዩነት የሚያሳዩት እንዴት ነው?

4 ሰብዓዊ ደግነት የታየበት አንደኛው ምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስን ጨምሮ የመርከብ መሰበር አደጋ ስለደረሰባቸው ሰዎች የሚናገረው ታሪክ ነው። ሰዎቹ በማዕበል ተገፍተው የመላጥያ ደሴት ላይ ደረሱ። (ሥራ 27:​37–28:​1) ምንም እንኳ የመላጥያ ሰዎች በማዕበል ለተመቱት መንገደኞች በፊት የገቡት ቃልም ሆነ ከሰዎቹ ጋር የቆየ ዝምድና ባይኖራቸውም የደሴቲቱ ነዋሪዎች ለእንግዶቹ “የሚያስገርም ቸርነት [“ሰብዓዊ ደግነት፣” NW ]” በማሳየት ጥሩ መስተንግዶ አደረጉላቸው። (ሥራ 28:​2, 7) እንግዳ ተቀባይነታቸው ደግነት የተሞላበት ቢሆንም በአጋጣሚና ለማያውቋቸው ሰዎች ያደረጉት ነበር። በመሆኑም አድራጎታቸው ሰብዓዊ ደግነት ነበር።

5 በአንጻሩ ንጉሥ ዳዊት የወዳጁ የዮናታን ልጅ ለሆነው ለሜምፊቦስቴ ያሳየውን እንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ተመልከት። ዳዊት ሜምፊቦስቴን “አንተም ሁልጊዜ ከገበታዬ እንጀራ ትበላለህ” ሲል ነገረው። ዳዊት ይህን ዝግጅት ያደረገበትን ምክንያት ሲያስረዳው “ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ቸርነት [“ፍቅራዊ ደግነት፣” NW ] ፈጽሜ አደርግልሃለሁ” አለው። (2 ሳሙኤል 9:​6, 7, 13) ዳዊት ያሳየው ጽኑ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ቀደም ሲል ተመሥርቶ ለነበረ ዝምድና ታማኝ እንደሆነ የሚያረጋግጥ በመሆኑ ሰብዓዊ ደግነት ሳይሆን የፍቅራዊ ደግነት መግለጫ እንደሆነ ተደርጎ መገለጹ ትክክል ነው። (1 ሳሙኤል 18:​3፤ 20:​15, 42) በተመሳሳይ ዛሬ የአምላክ አገልጋዮች ለሰው ልጆች በአጠቃላይ ሰብዓዊ ደግነት ያሳያሉ። ሆኖም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ዝምድና ለመሠረቱ ሰዎች የማይናወጥ ፍቅራዊ ደግነት ወይም ታማኝ ፍቅር ያሳያሉ።​—⁠ማቴዎስ 5:​45፤ ገላትያ 6:​10

6. በአምላክ ቃል ውስጥ ጎልተው የሚታዩ በሰዎች መካከል ሊገለጹ የሚችሉ የፍቅራዊ ደግነት ገጽታዎች ምንድን ናቸው?

6 ፍቅራዊ ደግነት የሚገለጽበትን አንዳንድ ተጨማሪ ገጽታዎች ለማየት ይህ ባሕርይ የተንጸባረቀባቸውን ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በአጭሩ እንመለከታለን። እነዚህን ዘገባዎች ስንመለከት ሰዎች ፍቅራዊ ደግነትን (1) በአንድ ዓይነት ድርጊት እንደገለጹ፣ (2) በፈቃደኝነት መንፈስ እንዳሳዩና (3) ይህንንም ያሳዩት በተለይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንደሆነ እንገነዘባለን። በተጨማሪም እነዚህ ዘገባዎች በዛሬው ጊዜ ፍቅራዊ ደግነትን እንዴት መግለጽ እንደምንችል ያሳያሉ።

ፍቅራዊ ደግነት ያሳየ አባት

7. የአብርሃም ሎሌ ለባቱኤልና ለላባ ምን ብሎ ነገራቸው? ሎሌው ምን አሳሳቢ ጥያቄ አነሳ?

7 ዘፍጥረት 24:​28-67 በፊተኛው ርዕስ ላይ የተጠቀሰውን የአብርሃም ሎሌ ቀሪ ታሪክ ይተርካል። ከርብቃ ጋር ከተገናኘ በኋላ ወደ አባቷ ወደ ባቱኤል ቤት እንዲገባ ተጋበዘ። (ቁጥር 28-32) እዚያም ሎሌው ለአብርሃም ልጅ፣ ሚስት ለማግኘት ያደረገውን ፍለጋ በዝርዝር ተረከላቸው። (ቁጥር 33-47) እስከዚህ ጊዜ ድረስ ሎሌው ያገኘውን ስኬት በተመለከተ “የጌታዬን የወንድሙን ልጅ ለልጁ እወስድ ዘንድ በቀና መንገድ የመራኝ” ብሎ በመግለጽ ከይሖዋ የመጣ ምልክት እንደሆነ አድርጎ አበክሮ ገልጿል። (ቁጥር 48) ሎሌው ያጋጠመውን ሁኔታ ከልቡ መናገሩ ተልዕኮው የይሖዋ እጅ እንዳለበት ባቱኤልንና ልጁ ላባን እንደሚያሳምናቸው እርግጠኛ ነበር። በመጨረሻም ሎሌው “ቸርነትና [“ፍቅራዊ ደግነትና፣” NW ] እውነት ለጌታዬ ትሠሩ እንደ ሆነ ንገሩኝ፤ ይህም ባይሆን ንገሩኝ፣ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ እል ዘንድ” አላቸው።​—⁠ቁጥር 49

8. ከርብቃ ጋር በተያያዘ ጉዳይ የባቱኤል ምላሽ ምን ነበር?

8 ይሖዋ ቀደም ብሎም ለአብርሃም ፍቅራዊ ደግነት አሳይቷል። (ዘፍጥረት 24:​12, 14, 27) ባቱኤል ልጁ ርብቃ ከአብርሃም ሎሌ ጋር እንድትሄድ በመፍቀድ ተመሳሳይ ነገር ያደርግ ይሆን? መለኮታዊ ፍቅራዊ ደግነት ግቡን እንዲመታ ሰብዓዊ ፍቅራዊ ደግነት ድጋፍ ይሰጥ ይሆን? ወይስ ሎሌው ያደረገው ረጅም ጉዞ መና ይቀር ይሆን? ላባና ባቱኤል “ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥቶአል” ብለው መናገራቸው የአብርሃምን ሎሌ በጣም አስደስቶት መሆን አለበት። (ቁጥር 50) በሁኔታዎቹ ላይ የይሖዋ እጅ እንዳለበት የተገነዘቡ ከመሆኑም በላይ ውሳኔውን ምንም ሳያቅማሙ ተቀብለዋል። ቀጥሎም ባቱኤል እንዲህ ሲል አክሎ በመናገር ፍቅራዊ ደግነቱን ገልጿል:- “ርብቃ እንኋት በፊትህ ናት፤ ይዘሃት ሂድ፣ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ለጌታህም ልጅ ሚስት ትሁን።” (ቁጥር 51) ርብቃ በፈቃደኝነት ከአብርሃም ሎሌ ጋር የሄደች ሲሆን ከጥቂት ጊዜ በኋላ የይስሐቅ ተወዳጅ ሚስት ለመሆን በቅታለች።​—⁠ቁጥር 49, 52-58, 67

ልጅ ለአባቱ ያሳየው ፍቅራዊ ደግነት

9, 10. (ሀ) ያዕቆብ ልጁን ዮሴፍን ምን እንዲያደርግለት ጠየቀው? (ለ) ዮሴፍ ለአባቱ ፍቅራዊ ደግነት ያሳየው እንዴት ነው?

9 የአብርሃም የልጅ ልጅ ያዕቆብም ፍቅራዊ ደግነት ተደርጎለታል። ዘፍጥረት ምዕራፍ 47 እንደሚተርከው ያዕቆብ በወቅቱ በግብፅ ይኖር የነበረ ሲሆን ‘የሞቱም ቀን ተቃርቦ ነበር።’ (ቁጥር 27-29) አምላክ ለአብርሃም ቃል ከገባለት አገር ውጪ የሚሞት መሆኑ በጣም አሳስቦት ነበር። (ዘፍጥረት 15:​18፤ 35:​10, 12፤ 49:​29-32) ያዕቆብ በግብፅ መቀበር ስላልፈለገ አስከሬኑ ወደ ከነዓን ምድር እንዲወሰድ ዝግጅት አደረገ። ፍላጎቱ እንዲሟላ ለማድረግ ከፍተኛ ሥልጣን ካለው ከልጁ ከዮሴፍ በቀር በተሻለ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ማን አለ?

10 ዘገባው እንዲህ ይላል:- “[ያዕቆብ] ልጁን ዮሴፍንም ጠርቶ እንዲህ አለው:- በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ . . . በግብፅ ምድርም እንዳትቀብረኝ ምሕረትንና [“ፍቅራዊ ደግነትንና፣” NW ] እውነትን አድርግልኝ፤ ከአባቶቼም ጋር በተኛሁ ጊዜ ከግብፅ ምድር አውጥተህ ትወስደኛለህ፣ በመቃብራቸውም ትቀብረኛለህ።” (ዘፍጥረት 47:29, 30) ዮሴፍ ፍላጎቱን እንደሚያሟላለት ቃል ገባ፤ ያዕቆብም ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሞተ። ዮሴፍና ሌሎቹ የያዕቆብ ልጆች አስከሬኑን ይዘው “ወደ ከነዓን ምድር አጓዙት፣ ባለ ሁለት ክፍል በሆነች ዋሻም ቀበሩት፣ እርስዋም በመምሬ ፊት ያለች፣ አብርሃም . . . የገዛት ዋሻ ናት።” (ዘፍጥረት 50:​5-8, 12-14) በዚህ መንገድ ዮሴፍ ለአባቱ ፍቅራዊ ደግነት አሳይቷል።

አንዲት ምራት ያሳየችው ፍቅራዊ ደግነት

11, 12. (ሀ) ሩት ለኑኃሚን ፍቅራዊ ደግነት ያሳየችው እንዴት ነው? (ለ) ሩት “በመጨረሻው ጊዜ” ያሳየችው ፍቅራዊ ደግነት “ከፊተኛው” ይልቅ የበለጠ የሆነው በምን መንገድ ነው?

11 የሩት መጽሐፍ መበለት የሆነችው ኑኃሚን ሞዓባዊት ምራትዋ (እርሷም መበለት ነበረች) ፍቅራዊ ደግነት እንዳደረገችላት ይተርካል። ኑኃሚን ይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ቤተ ልሔም ለመመለስ በወሰነች ጊዜ ሩት እንዲህ በማለት ፍቅራዊ ደግነትና ቆራጥነት አሳየች:- “ወደምትሄጅበት እሄዳለሁና፣ በምታድሪበትም አድራለሁና . . . ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል።” (ሩት 1:​16) ከጊዜ በኋላም ሩት በዕድሜ የገፋውን የኑኃሚንን ዘመድ ቦዔዝን ለማግባት ፈቃደኝነቷን በመግለጽ ፍቅራዊ ደግነቷን አሳይታለች። a (ዘዳግም 25:​5, 6፤ ሩት 3:​6-9) ቦዔዝ ሩትን “ባለጠጋም ድሀም ብለሽ ጐበዛዝትን አልተከተልሽምና ከፊተኛው ይልቅ በመጨረሻው ጊዜ ቸርነት [“ፍቅራዊ ደግነት፣” NW ] አድርገሻል” ብሏታል።​—⁠ሩት 3:​10

12 ሩት ፍቅራዊ ደግነት ያሳየችበት ‘የፊተኛው ጊዜ’ ሕዝቧን ትታ ከኑኃሚን ጋር የሆነችበትን ወቅት ያመለክታል። (ሩት 1:​14፤ 2:​11) “በመጨረሻው ጊዜ” ማለትም ሩት ቦዔዝን ለማግባት ፈቃደኛ ስትሆን ያሳየችው ፍቅራዊ ደግነት ከፊተኛው ይበልጣል። አሁን ሩት ልጅ የመውለጃ ዕድሜዋ ላለፈባት ለኑኃሚን ወራሽ መተካት ትችላለች። ጋብቻው ተፈጽሞ ሩት ልጅ ስትወልድ በቤተ ልሔም የሚኖሩ ሴቶች “ለኑኃሚን ወንድ ልጅ ተወለደላት” በማለት በደስታ ተናግረዋል። (ሩት 4:​14, 17) በእርግጥም ሩት “ምግባረ መልካም ሴት” በመሆኗ ይሖዋ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት የመሆን ድንቅ መብት በመስጠት ወሮታዋን ከፍሏታል።​—⁠ሩት 2:​12፤ 3:​11፤ 4:​18-22፤ ማቴዎስ 1:​1, 5, 6

በተግባር የተገለጸ

13. ባቱኤል፣ ዮሴፍና ሩት ፍቅራዊ ደግነታቸውን ያሳዩት እንዴት ነው?

13 ባቱኤል፣ ዮሴፍና ሩት ፍቅራዊ ደግነታቸውን እንዴት እንዳሳዩ አስተዋልክ? ይህን ያደረጉት የደግነት ቃላት በመናገር ብቻ ሳይሆን በተግባርም ነበር። ባቱኤል “ርብቃ እንኋት” ከማለቱም በላይ በእርግጥ ‘ርብቃን አሰናብቷታል።’ (ዘፍጥረት 24:​51, 59) ዮሴፍ “እንደ ቃልህ አደርጋለሁ” ማለት ብቻ ሳይሆን እሱና ወንድሞቹ ያዕቆብ “እንዳዘዛቸው እንደዚያው አደረጉለት።” (ዘፍጥረት 47:​30፤ 50:​12, 13) ሩት “ወደምትሄጅበት እሄዳለሁና” ማለት ብቻ ሳይሆን ሕዝቧን ትታ ከኑኃሚን ጋር በመሆን “ሁለቱም እስከ ቤተ ልሔም ድረስ ሄዱ።” (ሩት 1:​16, 19) በይሁዳ እያሉም ሩት “አማትዋ ያዘዘቻትን ሁሉ አደረገች።” (ሩት 3:​6) አዎን፣ እንደ ሌሎቹ ሁሉ ሩት ያሳየችው ፍቅራዊ ደግነትም በተግባር የተገለጸ ነበር።

14. (ሀ) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች ፍቅራዊ ደግነት በተግባር የሚያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) አካባቢህ በሚኖሩ ክርስቲያኖች ዘንድ የሚደረግ ምን የፍቅራዊ ደግነት መግለጫ ታውቃለህ?

14 በዛሬው ጊዜ የአምላክ አገልጋዮች ፍቅራዊ ደግነት በተግባር ሲያሳዩ መመልከቱም የሚያስደስት ነው። ለምሳሌ ያህል አቅመ ደካማ ለሆኑ፣ የመንፈስ ጭንቀት ላደረባቸው ወይም በሐዘን ለተደቆሱ የእምነት ጓደኞቻቸው ቀጣይነት ያለው ስሜታዊ ድጋፍ ስለሚሰጡ ሰዎች አስብ። (ምሳሌ 12:​25) ወይም በመንግሥት አዳራሹ ወደሚደረጉት ሳምንታዊ የጉባኤ ስብሰባዎች አረጋውያንን በታማኝነት ይዘው ስለሚመጡት በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች አስብ። በአርትራይተስ በሽታ የሚሠቃዩት የ82 ዓመቷ አና እንዲህ ሲሉ የብዙዎችን ስሜት ገልጸዋል:- “በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘት የይሖዋ በረከት ነው። ይሖዋ እንደዚህ ያሉ አፍቃሪ ወንድሞችና እህቶች ስለሰጠኝ ከልቤ አመሰግነዋለሁ።” በጉባኤህ ውስጥ እንደዚህ በመሳሰሉ ተግባሮች እየተካፈልክ ነው? (1 ዮሐንስ 3:​17, 18) እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የምታሳየው ፍቅራዊ ደግነት ከፍ ተደርጎ እንደሚታይ እርግጠኛ ሁን።

በፈቃደኝነት የሚደረግ

15. በተመለከትናቸው ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ላይ የጎላው ሌላ የፍቅራዊ ደግነት ገጽታ ምንድን ነው?

15 የተመለከትናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ፍቅራዊ ደግነት የሚገለጸው በግዴታ ሳይሆን በፍላጎትና በፈቃደኝነት መሆኑንም ያሳያሉ። ባቱኤል ከአብርሃም ሎሌ ጋር በፈቃደኝነት የተባበረ ሲሆን ርብቃም ተመሳሳይ እርምጃ ወስዳለች። (ዘፍጥረት 24:​51, 58) ዮሴፍ የሌሎች ጉትጎታ ሳያስፈልገው ፍቅራዊ ደግነቱን አሳይቷል። (ዘፍጥረት 50:​4, 5) ሩት ‘ከኑኃሚን ጋር ለመሄድ ቆርጣ ነበር።’ (ሩት 1:​18) ሩት ቦዔዝን ቀርባ እንድታነጋግረው ኑኃሚን ሐሳብ ስታቀርብላት ሞዓባዊቷ በፍቅራዊ ደግነት ተነሳስታ “የተናገርሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ” ብላለች።​—⁠ሩት 3:​1-5

16, 17. ባቱኤል፣ ዮሴፍና ሩት ያሳዩት ፍቅራዊ ደግነት ከፍተኛ ትርጉም እንዲኖረው ያደረገው ምንድን ነው? ይህን ባሕርይ እንዲያሳዩ ያነሳሳቸውስ ምንድን ነው?

16 ምንም እንኳ አብርሃም፣ ያዕቆብና ኑኃሚን በእነሱ ላይ ማሳደር የሚችሉት ግፊት ባይኖርም ባቱኤል፣ ዮሴፍና ሩት ያሳዩት ፍቅራዊ ደግነት ከፍተኛ ትርጉም አለው። ባቱኤል ሴት ልጁ ተለይታው እንድትሄድ የሚጠይቅ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ግዴታ አልነበረበትም። ለአብርሃም ሎሌ ‘ታታሪ የሆነችው ልጄ ከአጠገቤ እንድትርቅ አልፈልግም፤ በጭራሽ አልፈቅድም’ ሊለው ይችል ነበር። (ዘፍጥረት 24:​18-20) በተመሳሳይ ያዕቆብ ስለሚሞትና ቃሉን እንዲያከብርለት ሊያስገድደው ስለማይችል ዮሴፍ አባቱ የጠየቀውን ለማድረግም ሆነ ላለማድረግ የመወሰን ነፃነት ነበረው። ሩት በሞዓብ መቅረት እንደምትችል ኑኃሚን ራሷ ነግራታለች። (ሩት 1:​8) ሩት በዕድሜ በገፋው ቦዔዝ ፋንታ ‘ከጐበዛዝት’ መካከል አንዱን የማግባት ነፃነትም ነበራት።

17 ባቱኤል፣ ዮሴፍና ሩት ልባቸው ስላነሳሳቸው በፈቃደኝነት ፍቅራዊ ደግነት አሳይተዋል። ከጊዜ በኋላ ንጉሥ ዳዊት ለሜምፊቦስቴ ፍቅራዊ ደግነት የማሳየት ግዴታ እንዳለበት እንደተሰማው ሁሉ እነዚህም ከእነሱ ጋር ዝምድና ላላቸው ሰዎች ይህን ባሕርይ የማሳየት የሞራል ግዴታ እንዳለባቸው ተሰምቷቸዋል።

18. (ሀ) ክርስቲያን ሽማግሌዎች ‘መንጋውን የሚጠብቁት’ በምን ዓይነት ዝንባሌ ነው? (ለ) አንድ ሽማግሌ ለእምነት ጓደኞቹ እርዳታ መስጠትን በተመለከተ ያለውን ስሜት የገለጸው እንዴት ነው?

18 በአሁኑ ጊዜም ፍቅራዊ ደግነት የአምላክን መንጋ የሚጠብቁትን ወንዶች ጨምሮ የአምላክ ሕዝቦች መለያ ምልክት ነው። (መዝሙር 110:​3 አ.መ.ት ፤ 1 ተሰሎንቄ 5:​12) እነዚህ ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች ከተሰጣቸው ሹመት የተነሳ የተጣለባቸውን አደራ የመወጣት ኃላፊነት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። (ሥራ 20:​28) ሆኖም የእረኝነት ሥራቸውንና ለጉባኤው የሚያደርጓቸውን ሌሎች የፍቅራዊ ደግነት ተግባሮች የሚያከናውኑት “በውድ እንጂ በግድ” አይደለም። (1 ጴጥሮስ 5:​2) ሽማግሌዎች መንጋውን የሚጠብቁት ኃላፊነቱም ሆነ ፍላጎቱ ስላላቸው ነው። ለክርስቶስ በጎች ፍቅራዊ ደግነት የሚያሳዩት ይህን ማድረግ ስላለባቸውና ማድረግ ስለሚፈልጉም ነው። (ዮሐንስ 21:​15-17) አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ “ወንድሞችን ቤታቸው ሄዶ መጠየቅ አሊያም እንደማስታውሳቸው ለመግለጽ ስል ብቻ ስልክ መደወል ያስደስተኛል። ወንድሞችን መርዳት ታላቅ ደስታና እርካታ ያስገኝልኛል!” ሲል ተናግሯል። በየትኛውም ቦታ ያሉ አሳቢ ሽማግሌዎች በዚህ አባባል በሙሉ ልብ ይስማማሉ።

እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ፍቅራዊ ደግነት አሳዩ

19. በዚህ ርዕስ በተብራሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ላይ ስለ ፍቅራዊ ደግነት ጎላ ተደርጎ የተገለጸው ጉዳይ ምንድን ነው?

19 የተወያየንባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ራሳቸው ሊያሟሉት የማይችሉት ሁኔታ የገጠማቸውን ሰዎች ለመርዳት ፍቅራዊ ደግነት ማሳየት እንደሚያስፈልግ ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። አብርሃም የቤተሰቡ የዘር ሐረግ እንዲቀጥል ለማድረግ የባቱኤል ድጋፍ አስፈልጎት ነበር። ያዕቆብ አስከሬኑ ወደ ከነዓን እንዲወሰድ የዮሴፍ እርዳታ አስፈልጎት ነበር። ኑኃሚንም ወራሽ ማግኘት እንድትችል የሩት ትብብር አስፈልጓት ነበር። አብርሃምም ሆነ ያዕቆብ እንዲሁም ኑኃሚን እነዚህ ፍላጎቶቻቸው እንዲሟሉ የግድ እርዳታ አስፈልጓቸው ነበር። በተመሳሳይ ዛሬም በተለይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ፍቅራዊ ደግነት ማሳየት ይኖርብናል። (ምሳሌ 19:​17) ‘ለሚጮኸው ችግረኛ፣ ለድሀ አደጉና ረጂ ለሌለው’ እንዲሁም ‘ወደ ጥፋት ለቀረበው’ ትኩረት የሰጠውን ፓትሪያርኩ ኢዮብን መምሰል ይኖርብናል። ከዚህም በላይ ኢዮብ ‘የባልቴቲቱን ልብ እልል ያሰኘ’ ከመሆኑም በላይ “ለዕውር ዓይን፣ ለአንካሳ እግር” ሆኖ ነበር።​—⁠ኢዮብ 29:​12-15

20, 21. ፍቅራዊ ደግነት ልናሳያቸው የሚገባቸው እነማን ናቸው? እያንዳንዳችንስ ምን ለማድረግ ቆርጠን መነሳት አለብን?

20 እንደ እውነቱ ከሆነ በእያንዳንዱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለእርዳታ ‘የሚጮኹ ችግረኞች’ አሉ። ችግሮቹን ያስከተሉት ነገሮች እንደ ብቸኝነት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ የከንቱነት ስሜት፣ በሌሎች መጎዳት፣ ከባድ ሕመም ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣትን የመሳሰሉ ሁኔታዎች ሊሆኑ ይችላሉ። መንስኤው ምንም ይሁን ምን እንደነዚህ የመሳሰሉ የምንወዳቸው ሰዎች በፈቃደኝነት መንፈስ ተነሳስተን በፍቅራዊ ደግነት ላይ የተመሠረተ ቀጣይነት ያለው ተግባር በማከናወን ልናሟላላቸው የምንችለውና ማሟላትም ያለብን አንድ ዓይነት ችግር ይኖራቸዋል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 5:​14

21 በመሆኑም “ባለ ብዙ ቸርነት [“ፍቅራዊ ደግነት፣” NW ]” የሆነው ይሖዋ አምላክን መምሰላችንን እንቀጥል። (ዘጸአት 34:​6፤ ኤፌሶን 5:​1) በተለይ በችግር ላይ ላሉት በፈቃደኝነት በምናከናውናቸው አንዳንድ ድርጊቶች ይህን ማድረግ እንችላለን። ደግሞም ‘ቸርነትን [“ፍቅራዊ ደግነትን፣” NW ] ለወንድሞቻችን ማድረጋችንን’ በቀጠልን መጠን ይሖዋን እናከብ​ራለን እንዲሁም ታላቅ ደስታ እናገኛለን።​—⁠ዘካርያስ 7:​9

[የግርጌ ማስታወሻ]

a እዚህ ላይ የተጠቀሰውን የጋብቻ ዓይነት በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት የይሖዋ ምሥክሮች ያዘጋጁትን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 370ን ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ፍቅራዊ ደግነት ከሰብዓዊ ደግነት የሚለየው እንዴት ነው?

• ባቱኤል፣ ዮሴፍና ሩት ፍቅራዊ ደግነትን በምን መንገዶች አሳይተዋል?

• ፍቅራዊ ደግነትን በምን ዓይነት ዝንባሌ ማሳየት አለብን?

• የእኛ ፍቅራዊ ደግነት የሚያስፈልጋቸው እነማን ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባቱኤል ፍቅራዊ ደግነት ያሳየው እንዴት ነው?

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሩት ያሳየችው ታማኝ ፍቅር ለኑኃሚን በረከት ሆኖላታል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰዎች የሚያሳዩት ፍቅራዊ ደግነት እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ በፈቃደኝነት መንፈስና በአንድ ዓይነት ድርጊት ይገለጣል