በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት መጠቀም

ከይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት መጠቀም

ከይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት መጠቀም

“ጥበበኛ የሆነ . . . ማን ነው? እርሱ የእግዚአብሔርን ምሕረት [“ፍቅራዊ ደግነት፣” NW ] ያስተውላል።”​—⁠መዝሙር 107:​43

1. “ፍቅራዊ ደግነት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠራበት መቼ ነው? ይህን ባሕርይ በተመለከተስ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

 ከዛሬ 4, 000 ዓመት ገደማ በፊት የአብርሃም የወንድሙ ልጅ ሎጥ ይሖዋን በተመለከተ “ምሕረትህንም [“ፍቅራዊ ደግነትህንም፣” NW ] አብዝተሃል” ሲል ተናግሯል። (ዘፍጥረት 19:​19) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ፍቅራዊ ደግነት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኘው እዚህ ላይ ነው። ያዕቆብ፣ ኑኃሚን፣ ዳዊትና ሌሎች የአምላክ አገልጋዮችም ስለዚሁ የይሖዋ ባሕርይ ተናግረዋል። (ዘፍጥረት 32:​10፤ ሩት 1:​8፤ 2 ሳሙኤል 2:​6) a እንዲያውም “ፍቅራዊ ደግነት” የሚለው ሐረግ በነጠላና በብዙ ቁጥር በአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ውስጥ 250 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል። ይሁን እንጂ የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ምንድን ነው? በጥንት ዘመን ፍቅራዊ ደግነቱን ለእነማን አሳይቷል? በዛሬው ጊዜ ከፍቅራዊ ደግነቱ መጠቀም የምንችለውስ እንዴት ነው?

2. “ፍቅራዊ ደግነት” ተብሎ ለተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ፍቺ መስጠት ያን ያህል አዳጋች የሆነው ለምንድን ነው? ተስማሚ የሆነው አማራጭ ትርጉሙስ ምንድን ነው?

2 ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ፍቅራዊ ደግነት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በጣም ሰፊ ትርጉም ያለው ከመሆኑ የተነሳ አብዛኞቹ ቋንቋዎች ሙሉ ሐሳቡን በሚገባ የሚያስተላልፍ አንድ ቃል የላቸውም። በመሆኑም “ፍቅር፣” “ምሕረት” እና “ታማኝነት” እንደሚሉት ያሉ ትርጉሞች ቃሉ ያዘለውን አጠቃላይ ትርጉም አሟልተው አይዙም። ይሁን እንጂ ይበልጥ ስፋት ያለው “ፍቅራዊ ደግነት” የሚለው አተረጓጎም “ቃሉ ከሚያስተላልፈው ሙሉ ሐሳብ የራቀ አይደለም” ሲል ቲኦሎጂካል ወርድቡክ ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት ገልጿል። ባለማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም “ፍቅራዊ ደግነት” ተብሎ ለተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ታማኝ ፍቅር” የሚለውን ትርጉም አማራጭ አድርጎ ማቅረቡ ተስማሚ ነው።​—⁠ዘጸአት 15:​13፤ መዝሙር 5:​7የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ

ከፍቅርና ከታማኝነት ይለያል

3. ፍቅራዊ ደግነት ከፍቅር የሚለየው እንዴት ነው?

3 ፍቅራዊ ደግነት ወይም ታማኝ ፍቅር ከፍቅርና ከታማኝነት ጋር በቅርብ ይዛመዳል። ሆኖም ከእነዚህ ባሕርያት ጉልህ በሆኑ መንገዶች ይለያል። ፍቅራዊ ደግነትና ፍቅር እንዴት እንደሚለያዩ ተመልከት። ለነገሮችና ጽንሰ ሐሳቦች ፍቅር ማሳየት ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የወይን ጠጅንና ዘይትን ስለመውደድ’ እንዲሁም ‘ጥበብን ስለመውደድ’ ይናገራል። (ምሳሌ 21:​17፤ 29:​3) ሆኖም ፍቅራዊ ደግነት የሚሠራበት ለጽንሰ ሐሳቦች ወይም ሕይወት ለሌላቸው ነገሮች ሳይሆን ለሰዎች ነው። ለምሳሌ ያህል ዘጸአት 20:​6 ይሖዋ ‘እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ፍቅራዊ ደግነትን ያደርጋል’ በማለት የሚናገረው ሰዎችን በተመለከተ ነው።

4. ፍቅራዊ ደግነት ከታማኝነት የሚለየው እንዴት ነው?

4 “ፍቅራዊ ደግነት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ታማኝነት” ከሚለው ቃልም የበለጠ ሰፊ ትርጉም አለው። በአንዳንድ ቋንቋዎች “ታማኝነት” የሚለው ቃል በአብዛኛው የሚሠራበት የበታች የሆነ ሰው ለአለቃው ማሳየት ያለበትን ዝንባሌ ነው። ሆኖም አንዲት ተመራማሪ እንዳሉት ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ሲታይ ፍቅራዊ ደግነት “አብዛኛውን ጊዜ በተቃራኒ አቅጣጫ ያለውን ግንኙነት ያመለክታል:- የበላይ የሆነው ለደካማው ወይም ለችግረኛው ወይም ለበታቹ ታማኝ ነው።” በመሆኑም ንጉሥ ዳዊት ይሖዋን እንዲህ ሲል ሊማጸን ችሏል:- “ፊትህን በባሪያህ ላይ አብራ፣ ስለ ምሕረትህም [“ፍቅራዊ ደግነትህም፣” NW ] አድነኝ።” (መዝሙር 31:​16) ኃያል የሆነው ይሖዋ ችግረኛ ለሆነው ለዳዊት ፍቅራዊ ደግነት ወይም ታማኝ ፍቅር እንዲያሳየው ተለምኗል። ችግረኛው ኃያል በሆነው ላይ ምንም ሥልጣን ስለማይኖረው በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ፍቅራዊ ደግነት የሚገለጸው በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት ነው።

5. (ሀ) በቃሉ ውስጥ ጎልተው የሚታዩ የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት ገጽታዎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) የትኞቹን የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት መግለጫዎች እንመረምራለን?

5 መዝሙራዊው “ጥበበኛ . . . ማን ነው?” ሲል ጠይቋል። “እርሱ የእግዚአብሔርን ምሕረት [“ፍቅራዊ ደግነት፣” NW ] ያስተውላል።” (መዝሙር 107:​43) የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ከጥፋት መዳንን ሊያስገኝ እንዲሁም ሕይወትን ሊጠብቅ ይችላል። (መዝሙር 6:​4፤ 119:​88, 159) ጥበቃ የሚያስገኝና ከመከራ የሚገላግል አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ ነው። (መዝሙር 31:​16, 21፤ 40:​11፤ 143:​12) ይህ ባሕርይ ከኃጢአት መንጻት የሚቻልበት አጋጣሚ ከፍቷል። (መዝሙር 25:​7) አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ታሪኮችን በመከለስና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በመመልከት የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት (1) ይሖዋ ራሱ ባደረጋቸውና (2) ታማኝ አገልጋዮቹ በሕይወታቸው ባሳለፏቸው ነገሮች እንደተንጸባረቀ እንገነዘባለን።

ከመከራ መዳን​—⁠የፍቅራዊ ደግነት መግለጫ

6, 7. (ሀ) በሎጥ ሁኔታ ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነቱን ያበዛው እንዴት ነው? (ለ) ሎጥ ስለ ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት የተናገረው መቼ ነው?

6 የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነት ስፋት ለማወቅ የሚያስችለው ከሁሉ የተሻለው መንገድ ይህ ባሕርይ ተንጸባርቆ የሚገኝባቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ዘገባዎች መመርመር ሊሆን ይችላል። ዘፍጥረት 14:​1-16 ላይ የአብርሃም የወንድሙ ልጅ ሎጥ በጠላት ጦር ተማርኮ መወሰዱን እናነባለን። ይሁን እንጂ አብርሃም ሎጥን ከምርኮ አዳነው። ይሖዋ ሎጥና ቤተሰቡ የሚኖሩባትን በክፋት የተሞላችውን የሰዶም ከተማ ለማጥፋት ሲወስን የሎጥ ሕይወት እንደገና ለአደጋ ተጋለጠ።​—⁠ዘፍጥረት 18:​20-22፤ 19:​12, 13

7 በሰዶም ላይ ጥፋት ሊደርስ ሲል የይሖዋ መላእክት ሎጥንና ቤተሰቡን ከከተማው ይዘው አወጧቸው። በዚህ ጊዜ ሎጥ “ባሪያህ በፊትህ ሞገስን አግኝቶአል፣ ነፍሴን ለማዳን ያደረግህልኝን ምሕረትህንም [“ፍቅራዊ ደግነትህንም፣” NW ] አብዝተሃል” ሲል ተናገረ። (ዘፍጥረት 19:​16, 19) ሎጥ እንዲህ ብሎ በመናገር ይሖዋ እሱን በማዳን በዓይነቱ ልዩ የሆነ ፍቅራዊ ደግነት እንዳሳየው ገልጿል። በዚህ ረገድ የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት ከመከራ በማዳንና ሕይወትን በመጠበቅ ተገልጿል።​—⁠2 ጴጥሮስ 2:​7

የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነትና አመራር

8, 9. (ሀ) የአብርሃም ሎሌ የተሰጠው ተልዕኮ ምን ነበር? (ለ) ሎሌው የአምላክን ፍቅራዊ ደግነት ለማግኘት የጸለየው ለምንድን ነው? እየጸለየ ሳለስ ምን ተፈጸመ?

8 ዘፍጥረት ምዕራፍ 24 ላይ መለኮታዊ ፍቅራዊ ደግነት ወይም ታማኝ ፍቅር የታየበት ሌላ መግለጫ እናነባለን። ዘገባው አብርሃም ዘመዶቹ ወደሚኖሩበት አገር ሄዶ ለልጁ ለይስሐቅ ሚስት እንዲፈልግ ለሎሌው ተልዕኮ እንደሰጠው ይተርካል። (ቁጥር 2-4) ተልዕኮው ቀላል አልነበረም፤ ሆኖም ሎሌው የይሖዋ መልአክ እንደሚመራው ማረጋገጫ አግኝቷል። (ቁጥር 7) በመጨረሻም ሎሌው የከተማው ሴቶች ውኃ ለመቅዳት እየመጡ ሳለ ‘ከናኮር ከተማ’ (ወይ ካራን አሊያም በአቅራቢያው ያለ ቦታ) ውጪ የሚገኝ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ደረሰ። (ቁጥር 10, 11) ሴቶቹ ወደ ጉድጓዱ እየቀረቡ መሆናቸውን ሲመለከት ውጤቱ የሚታወቅበት ወሳኝ ሰዓት መድረሱን ተገነዘበ። ሆኖም ትክክለኛዋ ሴት የትኛዋ እንደሆነች እንዴት ማወቅ ይችላል?

9 የአብርሃም ሎሌ መለኮታዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ስለተገነዘበ እንዲህ ሲል ጸለየ:- “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፣ እለምንሃለሁ፤ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ፣ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን [“ፍቅራዊ ደግነትን፣” NW ] አድርግ።” (ቁጥር 12) ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነቱን የሚያሳየው እንዴት ይሆን? ሎሌው አምላክ የመረጣትን ቆንጆ ለይቶ ማወቅ እንዲችል የተወሰነ ምልክት እንዲሰጠው ጠየቀ። (ቁጥር 13, 14) አንደኛዋ ሴት ሎሌው ይሖዋን የጠየቀውን ነገር በትክክል አደረገች። እንዲያውም ሲጸልይ የሰማችው ይመስል ነበር! (ቁጥር 15-20) ሎሌው በመገረም “ትክ ብሎ ይመለከታት ነበር።” ይሁንና ገና መታወቅ ያለባቸው አንዳንድ ወሳኝ ጉዳዮች አሉ። ይህች መልከ ቀና ሴት ከአብርሃም ዘመዶች አንዷ ትሆን? ደግሞስ ገና ያላገባች ናት? በመሆኑም ሎሌው “እግዚአብሔር መንገዱን አቅንቶለት እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅ ዝም” ብሎ ጠበቀ።​—⁠ቁጥር 16, 21

10. የአብርሃም ሎሌ ይሖዋ ለጌታው ፍቅራዊ ደግነት አሳይቷል ብሎ የደመደመው ለምንድን ነው?

10 ከዚያ ጥቂት ቆይቶ ወጣቷ ልጅ “ሚልካ [ለአብርሃም ወንድም] ለናኮር የወለደችው የባቱኤል ልጅ” መሆኗን ተናገረች። (ዘፍጥረት 11:​26፤ 24:​24) በዚህ ጊዜ ሎሌው ይሖዋ ለጸሎቱ መልስ እንደሰጠው ተገነዘበ። ስሜቱ በጥልቅ ተነክቶ ለአምላክ በመስገድ እንዲህ አለ:- “ቸርነቱንና [“ፍቅራዊ ደግነቱንና፣” NW ] እውነቱን ከጌታዬ ያላራቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እኔ በመንገድ ሳለሁ እግዚአብሔር ወደ ጌታዬ ወንድሞች ቤት መራኝ።” (ቁጥር 27) አምላክ አመራር በመስጠት ለሎሌው ጌታ ለአብርሃም ፍቅራዊ ደግነት አሳይቷል።

የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት ነፃነትና ጥበቃ ያስገኛል

11, 12. (ሀ) ዮሴፍ የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነት የቀመሰው በምን ዓይነት መከራ ሥር እያለ ነው? (ለ) ከዮሴፍ ጋር በተያያዘ የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት የታየው እንዴት ነበር?

11 አሁን ደግሞ ዘፍጥረት ምዕራፍ 39ን እንመልከት። ታሪኩ የአብርሃም የልጅ ልጅ፣ ልጅ በሆነው ለባርነት ተሸጦ ወደ ግብፅ በተወሰደው በዮሴፍ ላይ ያተኩራል። ይሁንና “እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበረ።” (ቁጥር 1, 2) እንዲያውም ግብፃዊው የዮሴፍ ጌታ ጲጥፋራ እንኳ እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር እንዳለ ማወቅ ችሏል። (ቁጥር 3) ይሁን እንጂ ዮሴፍ በጣም ከባድ ፈተና ደረሰበት። የጲጥፋራን ሚስት በፆታ ሊደፍር ሞክሯል በሚል በሐሰት ተወንጅሎ ታሰረ። (ቁጥር 7-20) “በግዞት” እያለ “እግሮቹም በእግር ብረት ደከሙ፣ እርሱም በብረት ውስጥ ገባ።”​—⁠ዘፍጥረት 40:​15፤ መዝሙር 105:​18

12 በዚህ እጅግ ፈታኝ በሆነ ወቅት ምን ተፈጸመ? “እግዚአብሔርም ከዮሴፍ ጋር ነበረ ምሕረትንም [“ፍቅራዊ ደግነትንም፣” NW ] አበዛለት።” (ቁጥር 21ሀ) ይሖዋ ያሳየው ፍቅራዊ ደግነት ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ ከመከራ ነፃ እንዲወጣ ያስቻሉ በርካታ ክስተቶች ደረጃ በደረጃ እንዲፈጸሙ አድርጓል። ይሖዋ ‘በግዞት ቤቱ አለቃ ፊት [ዮሴፍ] ሞገስ እንዲያገኝ አደረገ።’ (ቁጥር 21ለ) ከዚህም የተነሳ የግዞት ቤቱ አለቃ ለዮሴፍ ኃላፊነት ሰጠው። (ቁጥር 22) ከዚያ በኋላ ዮሴፍ ከአንድ ሰው ጋር የተገናኘ ሲሆን ይህም ሰው ውሎ አድሮ ዮሴፍ ያለበትን ሁኔታ ለግብፁ ገዢ ለፈርዖን አሳወቀለት። (ዘፍጥረት 40:​1-4, 9-15፤ 41:​9-14) በኋላም ንጉሡ ዮሴፍን በግብፅ ላይ ሁለተኛ ገዢ አድርጎ የሾመው ሲሆን ይህም በረሃብ በተመታችው በግብፅ ምድር ሕይወት አድን ሥራ እንዲያከናውን አጋጣሚ ከፈተለት። (ዘፍጥረት 41:​37-55) ዮሴፍ የገጠመው መከራ የጀመረው የ17 ዓመት ልጅ እያለ ሲሆን ከ12 ዓመት በላይ በመከራ ሥር ኖሯል! (ዘፍጥረት 37:​2, 4፤ 41:​46) ሆኖም ችግርና መከራ ይደርስበት በነበረበት በእነዚያ ሁሉ ዓመታት ይሖዋ አምላክ ዮሴፍን ከከፋ አደጋ በመጠበቅና በመለኮታዊ ዓላማ ውስጥ ልዩ ሚና እንዲጫወት ሕይወቱን በመታደግ ፍቅራዊ ደግነቱን ገልጦለታል።

የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት ለዘላለም ይኖራል

13. (ሀ) መዝሙር 136 ላይ የትኞቹ የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት መግለጫዎች ይገኛሉ? (ለ) ፍቅራዊ ደግነት ምን ዓይነት ባሕርይ ነው?

13 ይሖዋ በብሔር ደረጃ ለእስራኤላውያን ፍቅራዊ ደግነቱን በተደጋጋሚ አሳይቷል። መዝሙር 136 በፍቅራዊ ደግነቱ ነፃ እንዳወጣቸው (ቁጥር 10-15)፣ አመራር እንደሰጣቸው (ቁጥር 16) እና ጥበቃ እንዳደረገላቸው (ቁጥር 17-20) ይገልጻል። አምላክ ለግለሰቦችም ፍቅራዊ ደግነቱን አሳይቷል። አንድ ሰው በችግር ላይ ለወደቀ ሰው በፈቃደኝነት ተነሳስቶ ተግባራዊ እርምጃ በመውሰድ ፍቅራዊ ደግነት ያሳያል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ፍቅራዊ ደግነትን በማስመልከት እንዲህ ብሏል:- “ሕይወትን ጠብቆ የሚያቆይ ወይም የሚያበለጽግ ድርጊት ነው። ጣልቃ በመግባት አደጋ ወይም ችግር ለደረሰበት ሰው የሚደረግ እርዳታ ነው።” አንድ ምሁር ፍቅራዊ ደግነትን “ፍቅር በተግባር ሲተረጎም” በማለት ገልጸውታል።

14, 15. ሎጥ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አገልጋይ እንደነበረ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

14 ይሖዋ ለሚወድዱት ሰዎች ፍቅራዊ ደግነት ከማሳየት ወደኋላ እንደማይል ከመረመርናቸው ከዘፍጥረት ዘገባዎች መገንዘብ ችለናል። ሎጥ፣ አብርሃምና ዮሴፍ በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር የኖሩ ከመሆኑም በላይ የየራሳቸው ፈተናዎች ገጥመዋቸዋል። ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ናቸው። ሆኖም በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ አገልጋዮች ነበሩ። እንዲሁም መለኮታዊ እርዳታ አስፈልጓቸው ነበር። አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን እንደነዚህ ላሉ ሰዎች ፍቅራዊ ደግነት እንደሚያሳይ ማወቃችን ሊያጽናናን ይችላል።

15 ሎጥ ለመከራ የዳረጉት አንዳንድ ጥበብ የጎደላቸው ውሳኔዎች አድርጓል። (ዘፍጥረት 13:​12, 13፤ 14:​11, 12) ሆኖም የሚያስመሰግኑ ባሕርያትም አሳይቷል። ሁለት የአምላክ መላእክት ወደ ሰዶም በመጡ ጊዜ ሎጥ ተቀብሎ አስተናግዷቸዋል። (ዘፍጥረት 19:​1-3) በሰዶም ላይ ሊመጣ ስላለው አፋጣኝ ጥፋት አማቾቹን በእምነት አስጠንቅቋቸዋል። (ዘፍጥረት 19:​14) አምላክ ለሎጥ ያለው አመለካከት 2 ጴጥሮስ 2:​7-9 ላይ የሚገኝ ሲሆን ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ [ይሖዋ] ካዳነ፣ ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፣ . . . ያውቃል።” አዎን፣ ሎጥ ጻድቅ ሰው ሲሆን እዚህ ላይ በተገለጸው መሠረት ለአምላክ ያደረ ሰው ነበር። እኛም “በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል” በተመላለስን መጠን እንደ ሎጥ የአምላክን ፍቅራዊ ደግነት እናያለን።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:​11, 12

16. መጽሐፍ ቅዱስ አብርሃምንና ዮሴፍን በጥሩ ሁኔታ የሚገልጻቸው እንዴት ነው?

16 ዘፍጥረት ምዕራፍ 24 ላይ የሚገኘው ዘገባ አብርሃም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንደነበረው በግልጽ ያሳያል። የመጀመሪያው ቁጥር “እግዚአብሔርም አብርሃምን በሥራው ሁሉ ባረከው” ሲል ይገልጻል። የአብርሃም ሎሌ ይሖዋን “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ” ሲል ጠርቶታል። (ቁጥር 12, 27) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ደግሞ አብርሃም ‘ጻድቅ’ እንደሆነና ‘የእግዚአብሔር ወዳጅ እንደተባለ’ ተናግሯል። (ያዕቆብ 2:​21-23) የዮሴፍ ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም። በይሖዋና በዮሴፍ መካከል ያለው የጠበቀ ዝምድና በዘፍጥረት ምዕራፍ 39 ውስጥ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። (ቁጥር 2, 3, 21, 23) በተጨማሪም ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስ ዮሴፍን በማስመልከት “እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ” ሲል ተናግሯል።​—⁠ሥራ 7:​9

17. ከሎጥ፣ ከአብርሃምና ከዮሴፍ ምሳሌ ምን መማር እንችላለን?

17 እስከ አሁን የተመለከትናቸው የይሖዋ አምላክን ፍቅራዊ ደግነት የቀመሱ ሰዎች ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና የነበራቸውና በተለያዩ መንገዶች መለኮታዊውን ዓላማ የደገፉ ግለሰቦች ናቸው። በራሳቸው ሊወጧቸው የማይችሏቸው እንቅፋቶች አጋጥመዋቸዋል። የሎጥ ሕይወት አደጋ ላይ ወድቆ ነበር፤ የአብርሃም የዘር ሐረግ የሚቋረጥበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፤ ዮሴፍም የተፈለገውን ሚና ለመጫወት የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ወድቆ ነበር። እነዚህ አምላካዊ ሰዎች ያስፈልጋቸው የነበረውን ነገር ማሟላት የሚችለው ይሖዋ ብቻ ሲሆን ይህንም ለማድረግ ፍቅራዊ ደግነቱን የሚያሳዩ እርምጃዎችን ወስዷል። እኛም የይሖዋ አምላክን ፍቅራዊ ደግነት ለዘላለም ማግኘት ከፈለግን ከእሱ ጋር የጠበቀ የግል ዝምድና መመሥረትና ፈቃዱን ማድረጋችንን መቀጠል ይኖርብናል።​—⁠ዕዝራ 7:​28፤ መዝሙር 18:​50

የአምላክ አገልጋዮች ልዩ ሞገስ አግኝተዋል

18. የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነት በተመለከተ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ምን ይላሉ?

18 የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ‘ምድርን ሁሉ ሞልቷል።’ ለዚህ የአምላክ ባሕርይ ምንኛ አመስጋኝ ነን! (መዝሙር 119:​64) መዝሙራዊው “ለሰው ልጆች ስላደረገው ተአምራት ስለ ምሕረቱም [“ፍቅራዊ ደግነቱም፣” NW ] እግዚአብሔርን ያመስግኑ” ሲል ላቀረበው ማሳሰቢያ በሙሉ ልባችን ምላሽ እንሰጣለን። (መዝሙር 107:​8, 15, 21, 31) ይሖዋ በግለሰብ ደረጃም ይሁን በቡድን በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ላገኙ አገልጋዮቹ ፍቅራዊ ደግነቱን የሚገልጽ መሆኑ ያስደስተናል። ነቢዩ ዳንኤል ለይሖዋ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ከሚወድዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ጋር ቃል ኪዳንንና ምሕረትን [“ፍቅራዊ ደግነትን፣” NW ] የምትጠብቅ ታላቅና የምታስፈራ አምላክ” ሲል ተናግሯል። (ዳንኤል 9:​4) ንጉሥ ዳዊት “ምሕረትህን [“ፍቅራዊ ደግነትህን፣” NW ] በሚያውቁህ ላይ . . . ዘርጋ” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 36:​10) ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ፍቅራዊ ደግነት የሚያሳይ በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን!​—⁠1 ነገሥት 8:​23፤ 1 ዜና መዋዕል 17:​13

19. በሚቀጥለው ርዕስ የትኞቹ ጥያቄዎች ይብራራሉ?

19 በእርግጥም የይሖዋ ሕዝቦች በመሆናችን ልዩ ሞገስ አግኝተናል! ይሖዋ በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ከገለጸው ፍቅር ጥቅም ከማግኘታችንም በተጨማሪ ከሰማያዊ አባታችን ፍቅራዊ ደግነት ወይም ታማኝ ፍቅር ልዩ በረከቶች አግኝተናል። (ዮሐንስ 3:​16) በተለይ ችግር በሚያጋጥመን ጊዜ ከዚህ ድንቅ የይሖዋ ባሕርይ እንጠቀማለን። (መዝሙር 36:​7) ሆኖም የይሖዋ አምላክን ፍቅራዊ ደግነት መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? በግለሰብ ደረጃ ይህን ድንቅ ባሕርይ እያሳየን ነው? እነዚህና ሌሎች ተዛማጅ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በዚህና ቀጥሎ ባለው የጥናት ርዕስ ላይ በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ምሕረት፣ ቸርነትና ሞገስ የሚሉት ቃላት የሚገኙባቸው ጥቅሶች በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ፍቅራዊ ደግነት ተብለዋል።

ታስታውሳለህ?

• “ፍቅራዊ ደግነት” የሚለው ሐረግ ምን ተብሎም ሊተረጎም ይችላል?

• ፍቅራዊ ደግነት ከፍቅርና ከታማኝነት የሚለየው እንዴት ነው?

• ይሖዋ ለሎጥ፣ ለአብርሃምና ለዮሴፍ ፍቅራዊ ደግነት ያሳየው በምን መንገዶች ነው?

• ይሖዋ በጥንት ዘመን ካሳየው ፍቅራዊ ደግነት ምን ማረጋገጫ ማግኘት እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ ለሎጥ ፍቅራዊ ደግነት ያሳየው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ በፍቅራዊ ደግነቱ ለአብርሃም ሎሌ አመራር ሰጥቶታል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ለዮሴፍ ጥበቃ በማድረግ ፍቅራዊ ደግነት አሳይቷል