በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተገኘው አስደናቂ ጭማሪ አጣዳፊ የግንባታ ሥራ እንዲከናወን አስገድዷል

የተገኘው አስደናቂ ጭማሪ አጣዳፊ የግንባታ ሥራ እንዲከናወን አስገድዷል

“ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ”

የተገኘው አስደናቂ ጭማሪ አጣዳፊ የግንባታ ሥራ እንዲከናወን አስገድዷል

ኢየሱስ ክርስቶስ “ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” ብሏል። (ማቴዎስ 11:28) የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ከሆነው አካል የቀረበ እንዴት ያለ አስደሳች ግብዣ ነው! (ኤፌሶን 5:23) በእነዚህ ቃላት ላይ ስናሰላስል ትልቅ የእረፍት ምንጭ ስለሚሆንልን ነገር ይኸውም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ስለምናሳልፈው አስደሳች ወቅት አመስጋኝ መሆናችን አይቀርም። “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፣ እነሆ፣ መልካም ነው፣ እነሆም፣ ያማረ ነው” በማለት ከዘመረው መዝሙራዊ ጋር እንደምንስማማ ምንም ጥርጥር የለውም።​—⁠መዝሙር 133:1

በእርግጥም በእነዚህ የአምልኮ ስብሰባዎች ላይ በየትም ስፍራ የማይገኙ ከሁሉ የተሻሉ ወዳጆች ከማግኘታችንም በላይ እዚያ ያለው መንፈሳዊ ሁኔታ አስተማማኝና አስደሳች ነው። አንዲት ወጣት ክርስቲያን እንደሚከተለው ብላ መናገሯ ትክክል ነው:- “ሙሉ ቀን ትምህርት ቤት ውዬ ስመጣ እዝላለሁ። ስብሰባዎች ግን ልክ በበረሃ መካከል እንዳለ ገነት ለሚቀጥለው ቀን የትምህርት ቤት ውሎዬ መንፈሴን ያድሱልኛል።” አንዲት ሌላ ናይጄሪያዊ ወጣትም “ይሖዋን ከሚወድዱ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረቴ ከይሖዋ ጋር ተጣብቄ እንድኖር እንደሚረዳኝ ተገንዝቤያለሁ” ብላለች።

የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በማኅበረሰቡ ውስጥ የእውነተኛ አምልኮ ማዕከል በመሆን ትልቅ አገልግሎት ይሰጣል። በብዙ ቦታዎች ቢያንስ በሳምንት ሁለት ጊዜ በመንግሥት አዳራሾች ውስጥ ስብሰባዎች የሚከናወኑ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም በስብሰባዎች ላይ ከሚገኘው እረፍት የሚሰጥ ወዳጅነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተቻለ መጠን ወዲያው መሰብሰብ እንዲጀምሩ ይበረታታሉ።​—⁠ዕብራውያን 10:24, 25

የመንግሥት አዳራሾች በአስቸኳይ ያስፈልጋሉ

ይሁን እንጂ ተስማሚ በሆኑ የመንግሥት አዳራሾች የመሰብሰብ አጋጣሚ ያላቸው ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች አለመሆናቸው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው። በዓለም ዙሪያ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር አስደናቂ በሆነ ፍጥነት መጨመሩ የመንግሥት አዳራሾች በአስቸኳይ እንዲያስፈልጉ አድርጓል። አሁንም ቢሆን፣ በተለይ በታዳጊ አገሮች በሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ።​—⁠ኢሳይያስ 54:2፤ 60:22

በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ ውስጥ 290 ጉባኤዎች ሲኖሩ የነበሩት የመንግሥት አዳራሾች ግን አሥር ብቻ ናቸው። ይህቺ አገር አጣዳፊ በሆነ ሁኔታ በርካታ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጓት ነበር። በአንጎላ የመንግሥት አዳራሾች ቁጥር ውስን በመሆኑ አብዛኞቹ ጉባኤዎች የሚሰበሰቡት ሜዳ ላይ ነው። በሌሎች ብዙ አገሮችም በተመሳሳይ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ።

በመሆኑም አቅማቸው ውስን በሆነ አገሮች ውስጥ ያለውን የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ለማገዝ ከ1999 ወዲህ የተቀናጀ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። በእነዚህ አገሮች እየተከናወኑ ላሉት የግንባታ ፕሮጀክቶች እገዛ ለማድረግ ልምድ ያላቸው ምሥክሮች ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል። ከእነዚህ ጥረቶች ጎን ለጎን የአካባቢው ወንድሞች የፈቃደኝነት መንፈስ ማሳየታቸውና ራሳቸውን ለሥራ ማቅረባቸው አበረታች ውጤቶች እያስገኘ ነው። የአካባቢው ወንድሞችም ልምድ እያገኙ በመሆኑ ይጠቀማሉ። ይህ ሁሉ የመንግሥት አዳራሽ በሚያስፈልግባቸው አገሮች ያለውን ፍላጎት ለማሟላት አስተዋጽኦ ያደርጋል።

በዚህ መንገድ የየአካባቢውን የግንባታ ዘዴና ቁሳቁስ በመጠቀምና እንደየሁኔታው የተለያዩ የመንግሥት አዳራሾችን በመገንባት ተግባራዊ እገዛ ተደርጓል። ይህም ሲደረግ ዓላማው ከፍተኛ የሆነውን የመንግሥት አዳራሽ ፍላጎት ማሟላት ብቻ ሳይሆን ከአካባቢው ሁኔታ ጋር የሚስማማ የእድሳት ፕሮግራም ማዘጋጀትንም የሚጨምር ነው።​—⁠2 ቆሮንቶስ 8:14, 15

አበረታች ውጤቶች

የአምልኮ ቦታ ለማዘጋጀት የሚደረጉት እነዚህ ጥረቶች ምን ውጤት አስገኝተዋል? በ2001 መጀመሪያ ላይ ከማላዊ የተላከ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “በዚህ አገር የተከናወነው ሥራ በጣም የሚደነቅ ነው። በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾችን ሠርተን እንጨርሳለን።” (ፎቶ 1 እና 2) በቶጎ ፈቃደኛ ሠራተኞች በቅርብ ወራት ውስጥ በርካታ ቀለል ያሉ የመንግሥት አዳራሾችን ሠርተዋል። (ፎቶ 3) ፈቃደኛ ሠራተኞች በሜክሲኮ፣ በብራዚል እና በሌሎችም ቦታዎች ተስማሚ የመንግሥት አዳራሾች እንዲገነቡ በመርዳት በኩል አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

ብዙ ጉባኤዎች እንዳስተዋሉት የመንግሥት አዳራሾች መገንባት የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢው በደንብ መደራጀታቸውን ለነዋሪዎቹ ያስገነዝባል። ብዙዎች ተስማሚ የመሰብሰቢያ ቦታ እስኪገኝ ድረስ ከምሥክሮቹ ጋር ለመሰብሰብ ያመነቱ ነበር። በማላዊ የሚገኘው የናፊሴ ጉባኤ እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “ተስማሚ የመንግሥት አዳራሽ ማግኘታችን ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት አጋጣሚ ከፍቷል። በዚህም ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ማስጀመር ቀላል እየሆነ ነው።”

በቤኒን የክራክ ጉባኤ አባላት ቀደም ሲል የነበራቸው የመንግሥት አዳራሽ በአካባቢው ካሉ አንዳንድ ቤተ ክርስቲያኖች ጋር ሲወዳደር ኋላ ቀር ስለነበር ብዙ ፌዝ ይደርስባቸው ነበር። (ፎቶ 4) አሁን ጉባኤው ልከኛና እውነተኛውን አምልኮ የሚያስከብር የሚያምር አዲስ የመንግሥት አዳራሽ አለው። (ፎቶ 5) ይህ ጉባኤ 34 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ሲኖሩት በእሁዱ ስብሰባ ላይ አማካይ የተሰብሳቢዎች ቁጥር 73 ነው፤ ሆኖም በመንግሥት አዳራሹ ውሰና እለት 651 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር። ከእነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ ምሥክሮቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ አዳራሽ መገንባት በመቻላቸው አድናቆት ያደረባቸው የከተማው ሰዎች ነበሩ። በዚህ ረገድ ስለተገኙት ውጤቶች የዚምባብዌ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አዲስ የመንግሥት አዳራሽ በሠራን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ባብዛኛው በእጥፍ ይጨምራል።”​—ፎቶ 6 እና 7

አዲስ የተሠሩት በርካታ የመንግሥት አዳራሾች ራሳቸውን ለወሰኑ ክርስቲያኖችም ሆነ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች መንፈሳዊ ማበረታቻ የሚያስገኙ ቦታዎች እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። በዩክሬይን በአካባቢው ያለው ጉባኤ በአዲሱ የመንግሥት አዳራሽ መጠቀም ከጀመረ በኋላ አንዲት ምሥክር “በጣም ተደስተናል። ይሖዋ ሕዝቦቹን እንዴት እንደሚረዳ በገዛ ዓይናችን ተመልክተናል።” ብላለች።

[በገጽ 10, 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በልግስና የሚደረገው ድጋፍ ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ነው

የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ በአስቸኳይ የሚያስፈልጉትን አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች በመገንባት ረገድ እየተገኘ ያለውን ፈጣን እድገት መመልከት ያስደስታቸዋል። በበርካታ አገሮች የይሖዋ አምላኪዎች የሚያደርጉት ያልተቋረጠ እድገት በቀጣዮቹ ዓመታት ብዙ አዲስ የመንግሥት አዳራሾች መገንባት እንደሚያስፈልግ ያሳያል። በ2001 የአገልግሎት ዓመት በእያንዳንዱ ሳምንት በአማካይ 32 አዳዲስ ጉባኤዎች ተቋቁመዋል! እነዚህ ጉባኤዎች አንድ ላይ ተሰብስበው አምልኳቸውን የሚያካሂዱበት ቦታ ይፈልጋሉ።

‘በተለይ የወንድሞች የገንዘብ አቅም ውስን በሆነባቸው አገሮች ውስጥ እንደ መንግሥት አዳራሽ ግንባታ የመሳሰሉ ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የምናገኘው ከየት ነው?’ የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል። መልሱ በመለኮታዊ ድጋፍና በሰብዓዊ ልግስና የሚል ነው።

ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት በአገልጋዮቹ ላይ መንፈስ ቅዱሱን በማፍሰስ “መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፣ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ” አስችሏቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:18) የአምላክ መንፈስ የይሖዋ ምሥክሮች ጊዜያቸውን፣ ኃይላቸውን፣ ጉልበታቸውን እንዲሁም ሌሎች ንብረቶቻቸውን በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በማዋል የመንግሥቱን ስብከት ሥራ በማንኛውም መንገድ እንዲደግፉ ያነሳሳቸዋል።

የይሖዋ ምሥክሮችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች የግንባታውን ሥራ በገንዘብ እንዲደግፉ የሚያነሳሳቸው የለጋስነት መንፈስ ነው። የጉባኤያቸውን መደበኛ ወጪዎች ከመሸፈን በተጨማሪ በሌሎች የምድር ክፍሎች ለሚደረገው የግንባታ ሥራ የገንዘብ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

በየጉባኤው “ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚውል መዋጮ​—ማቴዎስ 24:​14” የሚል ጽሑፍ በጉልህ የተጻፈባቸው ሳጥኖች አሉ። ግለሰቦች ልባቸው ሲያነሳሳቸው በፈቃደኝነት የሚያደርጉትን መዋጮ በእነዚህ ሳጥኖች ውስጥ መክተት ይችላሉ። (2 ነገሥት 12:​10) ትልቅም ይሁን ትንሽ ማንኛውም መዋጮ ከፍ ተደርጎ ይታያል። (ማርቆስ 12:42-44) እነዚህ መዋጮዎች የመንግሥት አዳራሽ ግንባታን ጨምሮ እንደ አስፈላጊነቱ በተለያዩ መንገዶች ይሠራባቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በደመወዝ የሚሠሩ ባለ ሥልጣናት ስለሌሏቸው እነዚህ መዋጮዎች ደመወዝ ለመክፈል አይውሉም።

ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚደረጉ መዋጮዎች ለተመደቡበት ዓላማ ይውላሉን? አዎን፣ ይውላሉ። በእርስ በርስ ጦርነት በፈራረሰችው በላይቤሪያ ያለው ቅርንጫፍ ቢሮ ሪፖርት እንዳደረገው በዚያች አገር የሚኖሩት አብዛኞቹ ወንድሞች ሥራ አጥ ከመሆናቸውም በላይ ከባድ የገንዘብ ችግር አለባቸው። በዚህች አገር የሚገኙት የይሖዋ ሕዝቦች ተስማሚ የአምልኮ ቦታ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው? ቅርንጫፍ ቢሮው እንዲህ ይላል:- “በሌሎች አገሮች ያሉ ወንድሞች በለጋስነት ያደረጉት መዋጮ እዚህ የሚካሄደውን ሥራ በገንዘብ ለመደገፍ ይውላል። እንዴት ያለ ጥበብ የተንጸባረቀበት ፍቅራዊ ዝግጅት ነው!”

የአካባቢው ወንድሞች አቅማቸው ውስን ቢሆንም መዋጮ ያደርጋሉ። ሴራሊዮን ከተባለች የአፍሪካ አገር የተላከው ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “የአገሩ ወንድሞች ለሥራው በሚደረጉት ጥረቶች እገዛ ከማድረጋቸውም በላይ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታውን በጉልበታቸውና አቅማቸው የፈቀደውን ያህል በገንዘባቸው ለመደገፍ ፈቃደኞች ናቸው።”

ዞሮ ዞሮ የዚህ ዓይነት የግንባታ ሥራዎች የሚያስከብሩት ይሖዋን ነው። የላይቤሪያ ወንድሞች በደስታ ስሜት እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ተስማሚ የአምልኮ ቦታዎች በመላው አገሪቱ መሠራታቸው በአካባቢው እውነተኛው አምልኮ በደንብ መደራጀቱን ለሰዎች ያሳያል፤ ይህ ደግሞ የአምላካችንን ታላቅ ስም የሚያስከብርና የሚያስውብ ነው።”