በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

አንድ እውነተኛ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን በሚፈጸም የቀብር ወይም የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘቱ ጥበብ ይሆናልን?

በማንኛውም ዓይነት የሐሰት ሃይማኖት እንቅስቃሴ ውስጥ መካፈል ይሖዋን የሚያሳዝን በመሆኑ መወገድ ይገባዋል። (2 ቆሮንቶስ 6:​14-17፤ ራእይ 18:​4) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጸም የቀብር ሥነ ሥርዓት ነፍስ አትሞትምና ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ እንደሚሉት ያሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ትምህርቶችን የሚደግፍ ስብከትን የሚያካትት ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ማማተብንና ቄሱ ወይም አገልጋዩ ጸሎት በሚያቀርብበት ጊዜ አብሮ መጸለይን የመሳሰሉ ድርጊቶችን ሊጨምር ይችላል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወይም በሌላ ቦታ የሚፈጸም ሃይማኖታዊ የሠርግ ሥነ ሥርዓትም እንዲሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የሚቃረኑ ጸሎቶችንና ሌሎች ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ሊያካትት ይችላል። አንድ ክርስቲያን በሃሰት ሃይማኖት ድርጊት ውስጥ በሚካፈሉ ሰዎች መካከል መገኘቱ እርሱም በአንድ ዓይነት ድርጊት እንዲካፈል የሚደረግበትን ግፊት መቋቋም አስቸጋሪ እንዲሆንበት ሊያደርገው ይችላል። እንደዚህ ላለው ግፊት ራስን ማጋለጥ ምንኛ ጥበብ የጎደለው ነው!

አንድ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚፈጸም የቀብር ወይም የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ የግድ መገኘት እንዳለበት ቢሰማውስ? ለምሳሌ ያህል አንድ የማያምን ባል እንዲህ ባለው ሥነ ሥርዓት ላይ ክርስቲያን ሚስቱ አብራው እንድትገኝ ይፈልግ ይሆናል። በተመልካችነት ብቻ አብራው ልትገኝ ትችላለች? ሚስትየው በማንኛውም ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ ላለመካፈል ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ ለባልዋ ፍላጎት ካላት አክብሮት የተነሳ አብራው ለመሄድ ትመርጥ ይሆናል። በሌላ በኩል ግን ሁኔታው የሚፈጥርባት የስሜት ጫና ከአቅም በላይ እንደሚሆንባትና ምናልባትም አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንድትጥስ ሊያደርጋት እንደሚችል በማሰብ ከእርሱ ጋር ላለመሄድ ትወስን ይሆናል። ውሳኔው ለእርሷ የተተወ ነው። ውስጧ ሳይረበሽ ንጹሕ ሕሊና ይዛ መቀጠል እንደምትፈልግ የታወቀ ነው።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 1:​19

ያም ሆነ ይህ በማንኛውም ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመካፈል ወይም መዝሙር አብሮ ለመዘመርም ሆነ ጸሎት በሚቀርብበት ጊዜ ከአንገትዋ ጎንበስ ለማለት ሕሊናዋ እንደማይፈቅድላት ለባለቤትዋ ብታስረዳው ትጠቀማለች። የምትሰጠውን ማብራሪያ መሠረት በማድረግ የሚስቱ በሥነ ሥርዓቱ ላይ መገኘት አላስፈላጊ የሆነ ነገር እንዲፈጠር ሊያደርግ እንደሚችል ይወስን ይሆናል። ለሚስቱ ካለው ፍቅር፣ ለእምነቷ ካለው አክብሮት ወይም ደግሞ አሳፋሪ ነገር እንዳይፈጠር ካለው ፍላጎት የተነሳ ብቻውን ለመሄድ ይመርጥ ይሆናል። አብራው እንድትሄድ የግድ የሚላት ከሆነ ግን እንደ ተመልካች ብቻ ሆና አብራው ለመሄድ ትመርጥ ይሆናል።

በአንድ ሃይማኖታዊ ሕንጻ ውስጥ በሚፈጸም ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘታችን በእምነት ባልንጀሮቻችን ላይ ሊያደርስ የሚችለውንም ተጽእኖ መዘንጋት አይኖርብንም። የአንዳንዶችን ሕሊና ይጎዳ ይሆን? በጣዖት አምልኮ ላለመካፈል ያደረጉትን ቁርጥ አቋም ያዳክምባቸው ይሆን? ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ነውር የሌለባችሁና ለሌሎች እንቅፋት የማትሆኑ ሆናችሁ እንድትገኙ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ እወቁ’ የሚል ጥብቅ ምክር ሰጥቷል።​—⁠ፊልጵስዩስ 1:​10 NW 

ሥነ ሥርዓቱን ያዘጋጀው የቅርብ ዘመድ ከሆነ የቤተሰብ ተጽዕኖው ያይልብን ይሆናል። ያም ሆነ ይህ አንድ ክርስቲያን ሁኔታዎቹን በሙሉ በሚገባ ማገናዘብ ይኖርበታል። አንዳንድ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚደረግ የቀብር ወይም የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ በተመልካችነት መገኘት ምንም ችግር እንደማይፈጠር ይሰማው ይሆናል። ይሁን እንጂ በሥነ ሥርዓቱ ላይ መገኘት በራስ ወይም በሌሎች ሕሊና ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ሊያስገኝ ከሚችለው ጥቅም ያመዝን ይሆናል። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን አንድ ክርስቲያን የሚያደርገው ውሳኔ በአምላክም ሆነ በሰዎች ፊት ያለውን በጎ ሕሊና የሚያሳጣው መሆን የለበትም።