ጽኑ አቋም ቅኖችን ይመራቸዋል
ጽኑ አቋም ቅኖችን ይመራቸዋል
መጽሐፍ ቅዱስ “ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው፣ መከራም ይሞላዋል” ሲል ይናገራል። (ኢዮብ 14:1) ሥቃይና መከራ የሰው ልጅ ሕይወት የማይቀሩ ገጽታዎች የሆኑ ይመስላል። ሌላው ቢቀር የዕለት ተዕለት ሕይወት እንኳን በስጋትና በሁከት የተሞላ ሊሆን ይችላል። ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ በተሳካ መንገድ ሊመራንና በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም ይዘን እንድንኖር ሊረዳን የሚችለው ነገር ምንድን ነው?
ከዛሬ 3, 500 ዓመታት በፊት በዛሬው ጊዜ አረቢያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይኖር የነበረን ኢዮብ የተባለ አንድ ባለጠጋ ሰው ምሳሌ ተመልከት። ሰይጣን ፈሪሃ አምላክ ባለው በዚህ ሰው ላይ ያመጣበት መከራ ምንኛ አሰቃቂ ነበር! ከብቶቹን በሙሉ ከማጣቱም ሌላ በጣም የሚወዳቸውን ልጆቹን በሞት ተነጠቀ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሰይጣን ኢዮብን ከራስ ጠጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ በአሰቃቂ ቁስል መታው። (ኢዮብ ምዕራፍ 1, 2) ኢዮብ መከራ እየደረሰበት ያለው ለምን እንደሆነ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ሆኖም “ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም።” (ኢዮብ 2:10) “እስክሞት ድረስ ፍጹምነቴን ከእኔ አላርቅም [“ጽኑ አቋሜን አላላላም፣” NW ]” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 27:5) አዎን፣ ጽኑ አቋም ኢዮብን በመከራው ወቅት መርቶታል።
ጽኑ አቋም ሲባል ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና ወይም ምሉዕነት ማለት ሲሆን በአምላክ ፊት ከነቀፋ ነፃ መሆንን እንዲሁም እንከን የለሽ ሆኖ መገኘትን ይጨምራል። እንዲህ ሲባል ግን የአምላክን የአቋም ደረጃዎች ሙሉ በሙሉ መጠበቅ የማይችሉ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች በአነጋገርም ሆነ በድርጊት ፍጹም ይሆናሉ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሰዎች የሚያሳዩት ጽኑ አቋም በሙሉ ልብ ወይም በፍጹም ልብ ለይሖዋ፣ ለፈቃዱና ለዓላማው ያደሩ መሆንን ያመለክታል። እንዲህ ያለው ለአምላክ የማደር ባሕርይ ቅኖችን በማንኛውም ሁኔታ ሥርና በማንኛውም ጊዜ ይመራቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ 11ኛ ምዕራፍ የመጀመሪያ ክፍል ጽኑ አቋም በተለያዩ የሕይወታችን ዘርፎች እንዴት ሊመራን እንደሚችልና በዚህም ምክንያት ስለምናገኘው በረከት ይገልጽልናል። እንግዲያው በውስጡ የሰፈረውን ከልብ ትኩረት ሰጥተን እንመርምር።
ጽኑ አቋም በንግድ ሥራ ሐቀኛ ወደመሆን ይመራል
የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን ውስጠ ወይራ በሆነ አነጋገር የሐቀኝነትን መሠረታዊ ሥርዓት ጠበቅ አድርጎ ሲናገር “አባይ ሚዛን በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው፤ እውነተኛ ሚዛን ግን ደስ ያሰኘዋል” ይላል። (ምሳሌ 11:1) ይሖዋ አገልጋዮቹ በንግድ ነክ ጉዳዮች ረገድ ሐቀኛ እንዲሆኑ እንደሚፈልግ ለማሳየት በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ሚዛን የሚለውን ቃል ከተጠቀመባቸው አራት ቦታዎች መካከል ይህ የመጀመሪያው ነው።—ምሳሌ 16:11፤ 20:10, 23
በአባይ ሚዛን መጠቀምን ወይም ማጭበርበርን የመረጡ ሰዎች የሚያገኙት ብልጽግና ሊያጓጓ ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ሐቀኝነት በጎደለው የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ በመካፈል አምላክ መልካምና ክፉ የሆነውን በተመለከተ ያወጣውን የአቋም ደረጃ ችላ ማለት እንፈልጋለን? ጽኑ አቋም ያለን ከሆንን እንዲህ አናደርግም። ይሖዋ ሐቀኝነትን በሚያመለክተው እውነተኛ ወይም ትክክለኛ ሚዛን ደስ ስለሚሰኝ ከማጭበርበር ድርጊት እንርቃለን።
“በትሑታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች”
ንጉሥ ሰሎሞን ቀጥሎ “ትዕቢት ከመጣች ውርደት ትመጣለች፤ በትሑታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች” ይላል። (ምሳሌ 11:2) ትዕቢት የሚገለጠው በኩራትም ይሁን በአለመታዘዝ ወይም በቅናት ውርደት ማስከተሉ አይቀርም። በሌላ በኩል ያለብንን የአቅም ገደብ በትሕትና መቀበላችን የጥበብ መንገድ ነው። በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ የተመዘገቡ ምሳሌዎች የዚህን አነጋገር እውነተኛነት ምንኛ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው!
ቅንዓት ያንገበገበው ሌዋዊው ቆሬ ይሖዋ በሾማቸው አገልጋዮቹ በሙሴና በአሮን ሥልጣን ላይ ዓመፅ አነሳስቶ ነበር። ይህ ትዕቢት የተሞላበት ድርጊት ምን ውጤት አስከተለ? ‘ምድሪቱ አፍዋን ከፍታ ከዓመፀኞቹ መካከል አንዳንዶቹን የዋጠቻቸው’ ሲሆን ቆሬን ጨምሮ ሌሎቹ ደግሞ በእሳት ተበሉ። (ዘኁልቊ 16:1-3, 16-35፤ 26:10፤ ዘዳግም 11:6) እንዴት ያለ ውርደት ነው! በተጨማሪም በትዕቢት ተነሳስቶ የይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦት እንዳይወድቅ ለመደገፍ እጁን ዘርግቶ የያዘውን ዖዛን ተመልከት። እሱም ቢሆን ወዲያውኑ ተቀስፏል። (2 ሳሙኤል 6:3-8) እኛም ከትዕቢት መንፈስ መራቃችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!
ትሑትና ልኩን የሚያውቅ ሰው ስህተት በሚሠራበት ጊዜም እንኳን ቢሆን ውርደት አይደርስበትም። ኢዮብ በብዙ መንገዶች ምሳሌ ሊሆን ቢችልም ፍጹም አልነበረም። የደረሱበት ፈተናዎች በአስተሳሰቡ ረገድ አንዳንድ ከባድ ጉድለቶች እንደነበሩበት ይፋ አውጥተዋል። ኢዮብ ለከሳሾቹ መልስ በሚሰጥበት ጊዜ ሚዛኑን ስቶ ነበር ማለት ይቻላል። ሌላው ቀርቶ ራሱን ከአምላክ ይበልጥ ጻድቅ እንደሆነ አድርጎ አቅርቦ ነበር። (ኢዮብ 35:2, 3) ኢዮብ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል ይሖዋ የረዳው እንዴት ነበር?
ይሖዋ ለኢዮብ ስለ ምድር፣ ስለ ባሕር፣ በከዋክብት ስለተሞላው ሰማይ፣ ስለ አንዳንድ እንስሳት እንዲሁም ስለ ሌሎች አስደናቂ ፍጥረታት በመንገር ከአምላክ ታላቅነት አንጻር ሲታይ ሰው ኢምንት መሆኑን የሚገልጽ ትምህርት ሰጠው። (ኢዮብ ምዕራፍ 38-41) ይሖዋ በንግግሩ ውስጥ ኢዮብ መከራ የደረሰበት ለምን እንደሆነ አንድም ቦታ አልጠቀሰም። መጥቀስም አላስፈለገውም። ኢዮብ ልኩን የሚያውቅ ሰው ነበር። በእርሱና በአምላክ፣ በእርሱ አለፍጽምናና በይሖዋ ጽድቅ እንዲሁም በእርሱ ድክመትና በይሖዋ ኃይል መካከል ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ በትሕትና ተገንዝቧል። “ራሴን እንቃለሁ፤ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ” ብሏል። (ኢዮብ 42:6) ኢዮብ ያሳየው ጽኑ አቋም የተሰጠውን ወቀሳ ሳያንገራግር እንዲቀበል አድርጎታል። እኛስ እንዴት ነን? ጽኑ አቋማችን እንዲመራን በመፍቀድ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሚሰጠንን እርማትና ማስተካከያ ለመቀበል ዝግጁዎች ነን?
ሙሴም እንዲሁ ልኩን የሚያውቅና ትሑት ሰው ነበር። አማቱ ዮቶር ሙሴ የሌሎችን ችግር ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት ራሱን እየጎዳ እንዳለ ሲገነዘብ አንዳንድ ኃላፊነቶችን ብቃት ላላቸው ሌሎች ወንዶች ዘጸአት 18:17-26፤ ዘኁልቊ 12:3) ልኩን የሚያውቅ ሰው ለሌሎች ሥልጣን ለመስጠት ወደኋላ አይልም፤ ወይም ተገቢ የሆኑ የኃላፊነት ቦታዎችን ብቃት ላላቸው ሌሎች ወንዶች ቢሰጥ ሁሉ ነገር ከቁጥጥሩ ውጪ እንደሚሆን አድርጎ አያስብም። (ዘኁልቊ 11:16, 17, 26-29) ከዚህ ይልቅ ሌሎች በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት ዝግጁ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:15) እኛስ እንዲህ መሆን አይገባንም?
እንዲያካፍል መከረው። ሙሴም ያለበትን የአቅም ገደብ ተገንዝቦ የተሰጠውን ሐሳብ በእሺታ ተቀበለ። (‘ነቀፋ የሌለበት ሰው መንገዱ የቀና ነው’
ጽኑ አቋም ቅን የሆነን ሰው ሁልጊዜ ከአደጋ ወይም ከመከራ እንደማይጠብቀው በመገንዘብ ሰሎሞን “ቅኖችን ቅንነታቸው [“ጽኑ አቋማቸው፣” NW ] ትመራቸዋለች፤ ወስላቶችን ግን ጠማማነታቸው ታጠፋቸዋለች” ይላል። (ምሳሌ 11:3) በእርግጥም ጽኑ አቋም ቅን ሰው ያለበት ሁኔታ አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳን በአምላክ ፊት ትክክል የሆነውን እንዲያደርግ ይመራዋል፤ ይህም በመጨረሻ በረከት ያስገኝለታል። ኢዮብ ጽኑ አቋሙን ለማላላት ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ ይሖዋ ‘ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ባርኮለታል።’ (ኢዮብ 42:12) አታላዮች በሌላው ሰው ጉዳት ራሳቸውን እንዳሻሻሉ ሊሰማቸውና አልፎ ተርፎም ለጊዜውም ቢሆን ባለጸጎች የሆኑ ሊመስላቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ውሎ አድሮ አታላይነታቸው መልሶ ያጠፋቸዋል።
ጠቢቡ ንጉሥ “በቁጣ ቀን ሀብት አትረባም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ታድናለች” ይላል። (ምሳሌ 11:4) ራስን ለቁሳዊ ጥቅም ማስገዛትና ለአምላክ ያለንን ፍቅር የሚያሳድጉትንና ለእርሱ የማደር ባሕርያችንን የሚያጠናክሩትን እንደ ግል ጥናት፣ ጸሎት፣ ስብሰባና የመስክ አገልግሎት የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎችን ችላ ማለት እንዴት ያለ ሞኝነት ነው! የትኛውም መጠን ያለው ሃብት ቢሆን ከመጪው ታላቅ መከራ አያድንም። (ማቴዎስ 24:21) ከታላቁ መከራ የሚያድነው የጻድቃን ጽድቅ ብቻ ነው። (ራእይ 7:9, 14) እንግዲያው ሶፎንያስ “የእግዚአብሔርም ቁጣ ቀን ሳይደርስባችሁ . . . እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም ፈልጉ” በማለት ያቀረበውን ልመና መስማታችን የጥበብ እርምጃ ነው። (ሶፎንያስ 2:2, 3) እስከዚያው ድረስ ግን ‘ይሖዋን በሃብታችን የማክበር’ ግብ ይኑረን።—ምሳሌ 3:9
ሰሎሞን ጽድቅን መፈለግ ያለውን ጥቅም ጎላ አድርጎ ለመናገር በማሰብ ከነቀፋ ነፃ የሆነን ሰው መጨረሻ ከክፉ ሰው መጨረሻ ጋር እንዲህ በማለት አወዳድሯል:- “የፍጹም [“ከነቀፋ ነፃ የሆነ፣” NW ] ሰው ጽድቁ መንገዱን ያቀናለታል፤ ኀጥእ ግን በኃጢአቱ ይወድቃል። ቅኖችን ጽድቃቸው ይታደጋቸዋል፤ ወስላቶች ግን በምኞታቸው ይጠመዳሉ። ኀጥእ በሞተ ጊዜ ተስፋው ይቈረጣል፣ የኃያል አለኝታም ይጠፋል። ጻድቅ ከጭንቀት ይድናል፣ ኀጥእም በእርሱ ፋንታ ይመጣል።” (ምሳሌ 11:5-8) ከነቀፋ ነፃ የሆነ ሰው የሚከተለው መንገድ ለውድቀት አይዳርገውም ወይም ሥራው ወጥመድ አይሆንበትም። መንገዱ የቀና ነው። በመጨረሻ ጻድቅ ከጭንቀት ይድናል። ክፉዎች ብርቱዎች መስለው ይታዩ ይሆናል፤ ሆኖም ፈጽሞ እንዲህ ያለ መዳን አያገኙም።
“ከተማ ደስ ይላታል”
በተጨማሪም ቅን ሰው የሚያሳየው ጽኑ አቋምና የክፉ አድራጊዎች ክፋት በሌሎች ሰዎች ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም። የእስራኤል ንጉሥ “ዝንጉ ሰው በአፉ ባልንጀራውን ያጠፋል፤ ጻድቃን ግን በእውቀት ይድናሉ” ይላል። (ምሳሌ 11:9) ስም ማጥፋት፣ ጎጂ ሐሜት፣ ጸያፍ አነጋገርና ከንቱ ልፍለፋ ሌሎችን እንደሚጎዳ ማን ይክዳል? በሌላ በኩል ግን የጻድቅ ሰው አነጋገር ንጹሕ፣ የታሰበበትና አሳቢነት የሚንጸባረቅበት ነው። እንዲህ ያለ ሰው ያለው ጽኑ አቋም ከሳሾቹ እየዋሹ እንደሆነ ለማሳየት የሚያስችለውን የማሳመኛ ነጥብ እንዲያቀርብ ስለሚያስችለው በእውቀት ይድናል።
ንጉሡ በመቀጠል “በጻድቃን ልማት ከተማ ደስ ይላታል፣ በኀጥአንም ጥፋት እልል ትላለች” ይላል። (ምሳሌ ) ጻድቃን በአጠቃላይ ሲታይ በሌሎች ይወደዳሉ ጎረቤቶቻቸውም ደስ ይሰኙባቸዋል። ‘በኃጥእ’ የሚደሰት ሰው ግን የለም። ብዙውን ጊዜ ክፉዎች ሲሞቱ ሕዝብ አያለቅስላቸውም። ይሖዋ ‘ኃጥአንን ከምድር ላይ ሲያጠፋና ዓመፀኞችን ሲያስወግድ’ ማንም ሰው እንደማያዝን የታወቀ ነው። ( 11:10ምሳሌ 2:21, 22) ከዚህ ይልቅ ክፉዎች ዳግም ስለማይኖሩ ሁሉም ደስ ይሰኛል። ይሁን እንጂ እኛስ እንዴት ነን? የምናሳየው ጠባይ ሌሎች ደስታ እንዲያገኙ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑን ለማረጋገጥ ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል።
“ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች”
ሰሎሞን ቅኖችና ክፉዎች በማኅበረሰቡ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽእኖ በተጨማሪ ሲያወዳድር “በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፤ በኀጥአን አፍ ግን ትገለበጣለች ” ይላል።—ምሳሌ 11:11
ቀና የሆነውን መንገድ የሚከተሉ የከተማ ሰዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ለሚኖሩ ሌሎች ሰዎች ሰላምና ደህንነት ያስገኛሉ። በዚህም ምክንያት ከተማዋ ከፍ ከፍ ትላለች ወይም ትበለጽጋለች። ስም የሚያጠፉ፣ ጎጂና የተሳሳቱ ነገሮችን የሚናገሩ ሰዎች አለመረጋጋት፣ ሐዘን፣ ክፍፍልና ችግር ይፈጥራሉ። በተለይ ደግሞ እነዚህ ሰዎች በሌሎች ዘንድ ተደማጭነት ካላቸው እንዲህ ያለው ነገር መከሰቱ የማይቀር ነው። እንዲህ ያለች ከተማ ረብሻ፣ ምግባረ ብልሹነትና የሥነ ምግባር ምናልባትም የኢኮኖሚ ውድቀት አያጣትም።
በምሳሌ 11:11 ላይ የተገለጸው መሠረታዊ ሥርዓት ከተማ መሰል በሆነው ጉባኤያቸው ውስጥ እርስ በርስ በሚቀራረቡ የይሖዋ ሕዝቦች ላይም በእኩል ደረጃ ይሠራል። መንፈሳዊ ሰዎች በሌላ አነጋገር በጽኑ አቋማቸው የሚመሩ ቅን ሰዎች በጎ ተጽእኖ የሚያሳድሩበት ጉባኤ ለአምላክ ክብር የሚያመጡ ደስተኛ፣ ንቁና እርዳታ ለማበርከት ዝግጁ የሆኑ ሰዎችን ያቀፈ ጉባኤ ይሆናል። ይሖዋ ጉባኤውን ስለሚባርክ በመንፈሳዊ ይበለጽጋል። አልፎ አልፎ፣ አንዳንድ ነገሮች የሚከናወኑበት መንገድ ቅር ያሰኛቸውና በሁኔታው ያልተደሰቱ፣ የሚተቹና በምሬት የሚናገሩ ጥቂት ሰዎች ብቅ ብቅ በማለት ቀስ በቀስ ሊዛመትና ጤነኛ የነበሩትን ሊመርዝ የሚችል “መራራ ሥር” ይሆናሉ። (ዕብራውያን 12:15) እንዲህ ያሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ፍላጎታቸው ተጨማሪ ሥልጣንና ክብር ማግኘት ነው። በጉባኤው ውስጥ ወይም በሽማግሌዎች ላይ አድሏዊነት፣ ዘረኝነት ወይም ይህን የመሰለ ችግር እንደሚታይ የሚገልጽ ወሬ ከወዲያ ወዲህ ያናፍሳሉ። በእርግጥም አፋቸው በጉባኤው ውስጥ መከፋፈልን ሊፈጥር ይችላል። ለወሬያቸው ጆሮ ባለመስጠት ለጉባኤው ሰላምና አንድነት የበኩላችንን አስተዋጽኦ የምናበረክት መንፈሳዊ ሰዎች ለመሆን መጣር አይኖርብንም?
ሰሎሞን ቀጥሎ እንዲህ ይላል:- “ወዳጁን የሚንቅ እርሱ አእምሮ የጐደለው ነው፤ አስተዋይ ግን ዝም ይላል። ለሐሜት የሚሄድ ምሥጢሩን ይገልጣል፤ በመንፈስ የታመነ ግን ነገሩን ይሰውራል።”—ምሳሌ 11:12, 13
ማስተዋል ወይም “አእምሮ የጎደለው” ሰው የሚፈጥረው ጉዳት ምንኛ የከፋ ነው! ለአንደበቱ ገደብ ስለማያበጅ ስም እስከማጥፋት ወይም እስከመሳደብ ይደርሳል። የተሾሙ ሽማግሌዎች እንዲህ ያለ ሰው የሚያሳድረውን መጥፎ ተጽእኖ ለማስቆም ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል። አስተዋይ ሰው ‘አእምሮ ከጎደለው’ ሰው በተቃራኒ መቼ ዝም ማለት እንዳለበት ያውቃል። የሌላውን ምስጢር ከማውጣት ይቆጠባል። አስተዋይ ሰው እንዳመጣለት የሚናገር ምላስ ብዙ ጉዳት እንደሚያስከትል በመገንዘብ “በመንፈስ የታመነ” ይሆናል። ለእምነት ባልንጀሮቹ ታማኝ ሲሆን አደጋ ላይ ሊጥላቸው የሚችለውን ምስጢር አያወጣባቸውም። እንዲህ ያሉ ጽኑ አቋማቸውን የሚጠብቁ ሰዎች ለአንድ ጉባኤ ምንኛ በረከት ናቸው!
ይሖዋ ከነቀፋ ነፃ በሆኑ ሰዎች መንገድ ላይ እንድንጓዝ እኛን ለመርዳት ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አመራር ሥር የሚዘጋጅ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርብልናል። ማቴዎስ 24:45) በተጨማሪም ከተማ መሰል በሆኑት ጉባኤዎቻችን ውስጥ በሚገኙ ክርስቲያን ሽማግሌዎች አማካኝነት በግለሰብ ደረጃ ብዙ እርዳታ እናገኛለን። (ኤፌሶን 4:11-13) ለዚህ ሁሉ አመስጋኞች ነን፤ ምክንያቱም “መልካም ምክር ከሌለ ዘንድ ሕዝብ ይወድቃል፤ በመካሮች ብዛት ግን ደኅንነት ይሆናል።” (ምሳሌ 11:14) ምንም ይምጣ ምን ‘በጽኑ አቋማችን ለመሄድ’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—መዝሙር 26:1 NW
([በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ኢዮብ በጽኑ አቋሙ የተመራ ሲሆን ይሖዋም ባርኮታል
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዖዛ ባሳየው ትዕቢት ምክንያት ሕይወቱን አጥቷል
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለቁሳዊ ጥቅም በማደር ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችን ችላ ማለት እንዴት ያለ ሞኝነት ነው!