በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለመልካም ሥራ የተዘጋጀ ንጹሕ ሕዝብ

ለመልካም ሥራ የተዘጋጀ ንጹሕ ሕዝብ

ለመልካም ሥራ የተዘጋጀ ንጹሕ ሕዝብ

“በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።”​2 ቆሮንቶስ 7:​1

1. ይሖዋ ከአምላኪዎቹ ምን ይጠብቅባቸዋል?

 “ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ይወጣል? በቅድስናውስ ስፍራ ማን ይቆማል?” በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አምልኮ በሚመለከት አእምሮን የሚያመራምር ይህን ጥያቄ ያነሳው የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ነው። ከዚያም “እጆቹ የነጹ፣ ልቡም ንጹሕ የሆነ፣ ነፍሱን ለከንቱ ያላነሣ፣ ለባልንጀራውም በሽንገላ ያልማለ” በማለት መልሱን ሰጥቷል። (መዝሙር 24:​3, 4) አንድ ሰው ሁለመናው ቅዱስ በሆነው በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ከፈለገ ንጹሕና ቅዱስ መሆን ይኖርበታል። ቀደም ሲል ይሖዋ ለመላው የእስራኤል ጉባኤ “ሰውነታችሁን ቀድሱ፣ ቅዱሳንም ሁኑ፣ እኔ ቅዱስ ነኝና” በማለት አሳስቧቸው ነበር።​—⁠ዘሌዋውያን 11:​44, 45፤ 19:​2

2. ጳውሎስና ያዕቆብ ንጽሕና በእውነተኛ አምልኮ ውስጥ ያለውን ቦታ ጎላ አድርገው የገለጹት እንዴት ነው?

2 ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ወራዳ ሥነ ምግባር በነገሠባት በቆሮንቶስ ከተማ ይኖሩ ለነበሩ የእምነት ባልንጀሮቹ “ወዳጆች ሆይ፣ የዚህ ተስፋ ቃል ካለን፣ በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” በማለት ጽፎላቸው ነበር። (2 ቆሮንቶስ 7:​1) ይህም ከአምላክ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረትና እርሱ ቃል የገባውን በረከት ለማግኘት የሚፈልግ ሰው አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ርኩሰትና ብክለት የሌለበትና ንጹሕ መሆን እንደሚኖርበት በድጋሚ ይጠቁማል። በተመሳሳይም ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አምልኮ በሚመለከት ሲጽፍ “ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፣ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው” ብሏል።​—⁠ያዕቆብ 1:​27

3. አምልኮታችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያገኝ በቁም ነገር ልናስብበት የሚገባው ጉዳይ ምንድን ነው?

3 ንጹሕ፣ ቅዱስና ያልረከሱ መሆን ለእውነተኛው አምልኮ በጣም አስፈላጊ ባሕርያት በመሆናቸው የአምላክን ሞገስ ማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በዚህ ረገድ የሚፈለግበትን ብቃት ለማሟላት በቁም ነገር ሊያስብበት ይገባል። ይሁን እንጂ ዛሬ ሰዎች ስለ ንጽሕና ያላቸው አመለካከትና የሚያወጡት መሥፈርት ወጥነት ስለሚጎድለው በይሖዋ ፊት ንጹሕና ተቀባይነት ያለውን መሥፈርት ማወቅና ራሳችንን ከዚያ ጋር ማስማማት ይኖርብናል። አምላክ በዚህ ረገድ ከአምላኪዎቹ ምን እንደሚጠብቅባቸው እንዲሁም ንጹሕና በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሕዝቦች ሆነው እንዲገኙ ብሎም ይህንን ባሕርይ ጠብቀው እንዲኖሩ ለመርዳት ምን እንዳደረገላቸው ማወቅ ይኖርብናል።​—⁠መዝሙር 119:​9፤ ዳንኤል 12:​10

ለእውነተኛው አምልኮ እንደሚገባ ንጹሕ መሆን

4. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ንጽሕና የያዘውን ሐሳብ ግለጽ።

4 ለብዙ ሰዎች ንጽሕና ከቆሻሻ ወይም ከብክለት ነጻ ከመሆን ያለፈ ትርጉም የለውም። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አካላዊ ንጽሕናን ለማመልከት ብቻ ሳይሆን አብዛኛውን ጊዜ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናን ለማመልከት የተሠራባቸው ንጹሕ የመሆንን ሐሳብ የሚያስተላልፉ በርካታ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት ይገኛሉ። ስለሆነም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “‘ንጹሕ’ እና ‘ንጹሕ ያልሆነ’ የሚሉት ቃላት አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ከንጽሕና አጠባበቅ ጋር ግንኙነት የላቸውም። ከዚህ ይልቅ በአመዛኙ ሃይማኖታዊ ሐሳብ የሚያስተላልፉ ናቸው። እዚህ ላይ በተሰጠው ፍቺ መሠረት ‘የንጽሕና’ መሠረታዊ ሥርዓት ሁሉንም የሕይወት ገጽታ ይነካል ለማለት ይቻላል።”

5. የሙሴ ሕግ በእስራኤላውያን ሕይወት ሊንጸባረቅ ስለሚገባው ንጽሕና የሚናገረው እስከ ምን ድረስ ነው?

5 እርግጥ ነው፣ የሙሴ ሕግ ንጹሕ የሆነውንና ያልሆነውን ተቀባይነት የነበረውንና ያልነበረውን እያንዳንዱን ጉዳይ በመግለጽ የእስራኤላውያንን ሕይወት የሚዳስስ ደንብና መመሪያ አካትቶ ይዟል። ለምሳሌ ያህል ከዘሌዋውያን ምዕራፍ 11 እስከ 15 ድረስ የሚያረክሱና የማያረክሱ ነገሮችን በሚመለከት ዝርዝር መመሪያዎች ሰፍረው እናገኛለን። አንዳንድ እንስሳት ርኩስ በመሆናቸው ምክንያት እስራኤላውያን እነዚያን እንዳይበሉ ታዘዋል። ልጅ መውለድ አንዲትን ሴት ለተወሰነ ጊዜ እንድትረክስ ያደርጋታል። በተመሳሳይ አንዳንድ የቆዳ በሽታዎች በተለይ ደግሞ ሥጋ ደዌ እንዲሁም ከወንድና ከሴት ብልት የሚወጡ ፈሳሾች ሰውን ያረክሳሉ። በተጨማሪም ሕጉ ከርኩሰት ለመንጻት ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል ዘኁልቊ 5:​2 ላይ “የእስራኤል ልጆች ለምጻሙን ሁሉ፣ ፈሳሽ ነገርም ያለበትን ሁሉ፣ በሬሳም የረከሰውን ሁሉ ከሰፈሩ እንዲያወጡ እዘዛቸው” የሚል እናነብባለን።

6. ንጽሕናን የሚመለከተው ሕግ የተሰጠበት ዓላማ ምን ነበር?

6 እነዚህና ይሖዋ የሰጣቸው ሌሎች ሕጎች ከዘመኑ ጥበብ እጅግ የመጠቁ ለሕክምናም ሆነ ለጤና የሚበጁ ሐሳቦችን የያዙ በመሆናቸው ሰዎች ሕጎቹን በማክበር ጥቅም ያገኙ እንደነበር አያጠራጥርም። ሆኖም እነዚህ ሕጎች የተሰጡት የጤና ወይም የሕክምና መመሪያ እንዲሆኑ ብቻ ታስቦ አልነበረም። የእውነተኛው አምልኮ ክፍል ነበሩ። እነዚህ ሕጎች የአመጋገብ ልማድን፣ ልጅ መውለድን፣ ጋብቻንና የመሳሰሉትን የሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች የሚመለከቱ ሲሆን ይሖዋ አምላካቸው እንደመሆኑ መጠን ያለ ምንም ገደብ ለእርሱ የተወሰኑ በመሆናቸው በማንኛውም የሕይወታቸው ዘርፍ ተገቢ የሆነውንና ያልሆነውን ነገር የመወሰን መብት እንዳለው የሚያመለክት ነው።​—⁠ዘዳግም 7:​6፤ መዝሙር 135:​4

7. የእስራኤል ብሔር ሕጉን በመጠበቅ ምን በረከት ሊያገኝ ይችል ነበር?

7 በተጨማሪም የሕጉ ቃል ኪዳን እስራኤላውያን በዙሪያቸው የሚኖሩ ሕዝቦች ከሚከተሏቸው ርኩስ ድርጊቶች ጠብቋቸዋል። እስራኤላውያን በይሖዋ ፊት ንጹሕ ሆነው እንዲመላለሱ የሚረዷቸውን መመሪያዎች ጨምሮ ሕጉን በታማኝነት ቢጠብቁ አምላካቸውን ለማገልገልና በረከቱን ለማግኘት ብቁ ይሆናሉ። በዚህ ረገድ ይሖዋ የእስራኤልን ብሔር “አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፣ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤ እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ” ብሏቸው ነበር።​—⁠ዘጸአት 19:​5, 6፤ ዘዳግም 26:​19

8. ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች ሕጉ ስለ ንጽሕና ለሚናገረው ነገር ትኩረት መስጠት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

8 ይሖዋ እስራኤላውያን ንጹሕ፣ ቅዱስና በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሕዝቦች ሆነው መኖር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ለማስተማር በሕጉ ውስጥ ዝርዝር መመሪያ እንዲሰፍር ካደረገ ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች እነዚህን ብቃቶች እንዴት ማሟላት እንደሚችሉ በጥንቃቄ መመርመራቸው ተገቢ አይሆንም? ክርስቲያኖች በሕጉ ሥር ባይሆኑም ጳውሎስ እንደተናገረው በሕጉ ውስጥ የሰፈሩት ነገሮች በሙሉ ‘ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ሲሆኑ አካሉ ግን የክርስቶስ መሆኑን’ መዘንጋት አይኖርባቸውም። (ቆላስይስ 2:​17፤ ዕብራውያን 10:​1) “አልለወጥም” በማለት የተናገረው ይሖዋ አምላክ በዚያ ዘመን በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ንጹሕ መሆንንና ከርኩሰት መራቅን ይህን ያህል ከፍ አድርጎ ተመልክቶት ከነበረ እኛም የእርሱን ሞገስና በረከት ለማግኘት ከፈለግን በአካል፣ በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ንጹሕ ሆኖ የመገኘትን አስፈላጊነት አክብደን ልንመለከተው ይገባናል።​—⁠ሚልክያስ 3:​6፤ ሮሜ 15:​4፤ 1 ቆሮንቶስ 10:​11, 31

አካላዊ ንጽሕና ያስመሰግነናል

9, 10. (ሀ) አካላዊ ንጽሕና ለአንድ ክርስቲያን ያን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያደርጓቸው የአውራጃ ስብሰባዎች ብዙውን ጊዜ ምን አስተያየቶች ይሰነዘራሉ?

9 አካላዊ ንጽሕና አሁንም የእውነተኛው አምልኮ ዐቢይ ክፍል ነውን? አንድ ሰው አካላዊ ንጽሕናውን መጠበቁ ብቻውን እውነተኛ አምላኪ ባያሰኘውም አንድ እውነተኛ አምላኪ ሁኔታው እስከፈቀደለት ድረስ አካላዊ ንጽሕናውን መጠበቁ የተገባ ነው። በተለይ ብዙ ሰዎች ለራሳቸው፣ ለልብሳቸው ወይም ለአካባቢያቸው ንጽሕና እምብዛም ትኩረት በማይሰጡበት በዚህ ጊዜ እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች በአብዛኛው ከሌሎች ተለይተው ይታወቃሉ። ይህ ደግሞ ጳውሎስ “አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ፣ ለማንም ዕንቅፋት መሆን አንፈልግም። ይሁን እንጂ በምናደርገው ነገር ሁሉ ራሳችንን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች እናቀርባለን” በማለት በቆሮንቶስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች እንደተናገረው ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 6:​3, 4 አ.መ.ት

10 የይሖዋ ምሥክሮች በተለይ በትላልቅ ስብሰባዎቻቸው ላይ በሚያሳዩት ንጹሕ፣ ሥርዓታማና የተከበረ ባሕርይ ምክንያት ብዙ ጊዜ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ምስጋና ይቸራቸዋል። ለምሳሌ ያህል ላ ስታምፓ የተባለው ጋዜጣ የኢጣሊያ ግዛት በሆነችው በሳቮና ስለተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ “አንድ ሰው ስብሰባው በሚካሄድበት ቦታ ወዲያ ወዲህ ሲዘዋወር ወዲያው ዓይኑን የሚስበው የተሰብሳቢዎቹ ንጽሕናና ሥርዓታማነት ነው” የሚል አስተያየት ሰጥቷል። የይሖዋ ምሥክሮች በብራዚል ሳኦ ፖውሎ በአንድ ስታዲዮም ውስጥ የአውራጃ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ አንድ የስታዲዮሙ ባለሥልጣን ለጽዳት ክፍሉ ኃላፊ “ከዛሬ ጀምሮ ስታዲዮሙን የይሖዋ ምሥክሮች በሚያጸዱበት መንገድ እንዲጸዳ እንፈልጋለን” በማለት ነገሩት። የስታዲዮሙ አንድ ሌላ ባለሥልጣን ደግሞ “የይሖዋ ምሥክሮች ስታዲዮሙን መከራየት ሲፈልጉ የሚያሳስበን ነገር ቢኖር ቀኑ ብቻ ነው። ከዚያ ውጪ ምንም የሚያስጨንቀን ነገር የለም” ብለዋል።

11, 12. (ሀ) የግል ንጽሕና አጠባበቅን በሚመለከት የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ማስታወስ ይገባናል? (ለ) የግል ልማዶቻችንንና አኗኗራችንን በሚመለከት የትኞቹ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ?

11 በአምልኮ ቦታችን የምናሳየው ንጽሕናና ሥርዓታማነት ለምናመልከው አምላክ ይህን የመሰለ ውዳሴ የሚያመጣለት ከሆነ እነዚህን ባሕርያት በግል ሕይወታችን ውስጥ ማንጸባረቃችን የዚያኑ ያህል አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ቤታችን ውስጥ ብቻችንን በምንሆንበት ጊዜ እንደልባችን የመሆን መብት እንዳለን ተሰምቶን ደስ እንዳለን ማድረግ እንጀምር ይሆናል። አለባበስንና አጋጌጥን በሚመለከት ይስማማኛል እንዲሁም እወድደዋለሁ የምንለውን የመምረጥ ነፃነት ያለን መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም! ይሁን እንጂ በአመዛኙ ይህ ዓይነቱ ነፃነት አንጻራዊ ነው። ጳውሎስ አንድ ሰው አንዳንድ የምግብ ዓይነቶችን ለመመገብ ያለውን ምርጫ አስመልክቶ ሲናገር “ዳሩ ግን ይህ መብታችሁ ለደካሞች ዕንቅፋት እንዳይሆንባቸው ተጠንቀቁ” በማለት ክርስቲያን ባልንጀሮቹን አሳስቦ እንደነበረ ልብ በል። ከዚያም “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም” የሚል ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓት ሰጥቷል። (1 ቆሮንቶስ 8:​9፤ 10:​23) ጳውሎስ የሰጠው ምክር በንጽሕና አጠባበቅ ረገድ በእኛ ላይ ሊሠራ የሚችለው እንዴት ነው?

12 ሰዎች አንድ የአምላክ አገልጋይ በአኗኗሩ ንጹሕና ሥርዓታማ እንዲሆን መጠበቃቸው ምክንያታዊ ነው። ስለሆነም ቤታችንንና አካባቢውን የምንይዝበት መንገድ በአምላክ ቃል አገልጋይነታችን ላይ ነቀፋ የሚያስከትል እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። ቤታችን ስለ እኛና ስለ እምነታችን ምን ዓይነት ምሥክርነት ይሰጣል? ለሌሎች ደጋግመን እንደምንናገረው ንጹሕና ሥርዓታማ በሆነ ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ከልብ እንደምንጓጓ የሚያሳይ ነውን? (2 ጴጥሮስ 3:​13) በተመሳሳይም በምንዝናናበትም ሆነ አገልግሎት ላይ በምንሆንበት ጊዜ የሰውነት አያያዛችን የምንሰብከውን መልእክት ማራኪነት ሊጨምር ወይም ሊቀንስ ይችላል። ለምሳሌ ያህል በሜክሲኮ የሚገኝ አንድ የጋዜጣ ዘጋቢ የሰጠውን አስተያየት ተመልከት:- “እንደ እውነቱ ከሆነ ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል አብዛኞቹ ወጣቶች ሲሆኑ የፀጉር አያያዛቸው፣ ንጽሕናቸውና ተገቢ የሆነው አለባበሳቸው የሰውን ቀልብ ይስባል።” እንደዚህ ያሉ ወጣቶች በመካከላችን መኖራቸው ምንኛ ያስደስታል!

13. የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴያችን በአጠቃላይ ንጹሕና ሥርዓታማ እንዲሆን ምን ልናደርግ እንችላለን?

13 እርግጥ ነው ሰውነታችንን፣ ዕቃዎቻችንንና ቤታችንን ሁልጊዜ በንጽሕናና በሥርዓት መያዝ ቀላል አይደለም። ለዚህ የሚያስፈልገው የተራቀቀና ውድ የሆነ የጽዳት ዕቃ ወይም መሣሪያ ሳይሆን ጥሩ እቅድ ማውጣትና ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ነው። ገላችንን ለመታጠብ፣ ልብሳችንን ለማጠብ፣ ቤታችንን፣ መኪናችንንና የመሳሰሉትን ነገሮች በንጽሕና ለመያዝ ጊዜ መመደብ አስፈላጊ ነው። ሌሎች የዕለት ተዕለት ኃላፊነቶቻችንን መወጣትን ጨምሮ በአገልግሎት፣ በጉባኤ ስብሰባና በግል ጥናት የተጠመድን መሆናችን በአምላክና በሰዎች ዘንድ ንጹሕና ተቀባይነት ያለን የመሆንን አስፈላጊነት አያስቀረውም። “ለሁሉ ዘመን አለው” የሚለው የታወቀ መሠረታዊ ሥርዓት በዚህ የሕይወታችን ዘርፍም በእኩል ደረጃ ይሠራል።​—⁠መክብብ 3:​1

ንጹሕ ልብ

14. ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕና ከአካላዊ ንጽሕና ይበልጥ አስፈላጊ ነው ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?

14 ለአካላዊ ንጽሕናችን ትኩረት መስጠት አስፈላጊ የሆነውን ያህል ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅም ከዚያ የበለጠ ትኩረት መስጠታችን አስፈላጊ ነው። እስራኤላውያን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያጡ ያደረጋቸው አካላዊ ንጽሕናቸውን አለመጠበቃቸው ሳይሆን በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ መቆሸሻቸው እንደሆነ ማስታወሳችን እዚህ መደምደሚያ እንድንደርስ ያስችለናል። ይሖዋ “ኃጢአተኛ ወገንና በደል የተሞላበት ሕዝብ” በመሆናቸው ምክንያት መሥዋዕቶቻቸው፣ መባቻዎቻቸውና ሰንበቶቻቸው ሌላው ቀርቶ የሚያቀርቡለት ጸሎት እንኳን ሸክም እንደሆነበት በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ነግሯቸው ነበር። የአምላክን ሞገስ መልሰው ለማግኘት ምን ማድረግ ነበረባቸው? ይሖዋ “ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግን ተዉ” ብሏቸዋል።​—⁠ኢሳይያስ 1:​4, 11-16

15, 16. ኢየሱስ ሰውን የሚያረክሰው ምን እንደሆነ ተናግሯል? ከኢየሱስ ቃላት ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

15 ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕና መጠበቅ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ይበልጥ ለመረዳት ጻፎችና ፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርቱ እጃቸውን ሳይታጠቡ ምግብ በመብላታቸው ረክሰዋል ብለው በተናገሩ ጊዜ ኢየሱስ ምን ብሎ እንደመለሰላቸው ተመልከት። ኢየሱስ “ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፣ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው” በማለት አስተሳሰባቸውን እንዲያስተካክሉ ነገራቸው። ከዚያም ኢየሱስ “ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፣ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው። ከልብ ክፉ አሳብ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በውሸት መመስከር፣ ስድብ ይወጣልና። ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው እንጂ፣ ባልታጠበ እጅ መብላትስ ሰውን አያረክሰውም” በማለት ገለጸላቸው።​—⁠ማቴዎስ 15:​11, 18-20

16 ኢየሱስ ከተናገራቸው ቃላት ምን እንማራለን? ኢየሱስ ክፉ፣ ሥነ ምግባር የጎደለውና ንጹሕ ያልሆነ የልብ ዝንባሌ ክፉ ወደሆነ፣ ሥነ ምግባር ወደጎደለውና ንጹሕ ወዳልሆነ ድርጊት እንደሚመራ መናገሩ ነበር። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንደገለጸው “እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል።” (ያዕቆብ 1:​14, 15) ስለሆነም ኢየሱስ የጠቀሰው ዓይነት ከባድ ኃጢአት ውስጥ እንዳንወድቅ ለእነዚህ ነገሮች ያለንን ማንኛውንም ዝንባሌ ከልባችን ውስጥ ነቅለን ማውጣት ይገባናል። ይህም ሲባል የምናነብበውን፣ የምንመለከተውንና የምንሰማውን ነገር በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርብናል ማለት ነው። ዛሬ የመዝናኛውና የማስታወቂያው ኢንዱስትሪ የመናገርና የመጻፍ ነፃነትን በመጠቀም የኃጢአተኛ ሥጋችንን ምኞቶች የሚቀሰቅሱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሙዚቃዎችንና ምስሎችን በገፍ እያመረተ ነው። እነዚህ ነገሮች ከሚያስተላልፉት ሐሳብ መካከል የትኛውም ቢሆን ወደ ልባችን እንዲገባ ላለመፍቀድ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። ዋናው ነጥብ አምላክን ለማስደሰትና በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ንጹሕ ወይም ያልረከሰ ልብ ይዘን መኖር እንድንችል የማያቋርጥ ትጋት ማሳየት ያስፈልገናል።​—⁠ምሳሌ 4:​23

ለመልካም ሥራ የነጹ

17. ይሖዋ ሕዝቡን ያነጻው ለምንድን ነው?

17 በይሖዋ እርዳታ በእርሱ ፊት ንጹሕ አቋም ይዘን መመላለስ መቻላችን በእርግጥ ልዩ መብት ከመሆኑም በላይ ጥበቃ ያስገኝልናል። (2 ቆሮንቶስ 6:​14-18) ሆኖም ይሖዋ ሕዝቡን ያነጻው ለአንድ የተለየ ዓላማ እንደሆነም እናምናለን። ጳውሎስ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ “ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፣ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፣ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል” በማለት ለቲቶ ነግሮታል። (ቲቶ 2:​14) ንጹሕ ሕዝብ እንደመሆናችን መጠን ቅንዓት ማሳየት የሚኖርብን ለየትኞቹ ሥራዎች ነው?

18. ለመልካም ሥራ እንደምንቀና ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

18 ከምንም ነገር በላይ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሕዝብ በማወጅ መትጋት ይኖርብናል። (ማቴዎስ 24:​14) እንዲህ በማድረግ ከማንኛውም ዓይነት ብክለት ነፃ በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንደሚችሉ የሚገልጸውን ተስፋ ለሰዎች ሁሉ እንናገራለን። (2 ጴጥሮስ 3:​13) የምናከናውነው መልካም ሥራ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ የአምላክን መንፈስ ፍሬ በማፍራት የሰማዩ አባታችንን ከፍ ከፍ ማድረግንም የሚጨምር ነው። (ገላትያ 5:​22, 23፤ 1 ጴጥሮስ 2:​12) በተፈጥሮ አደጋዎች ወይም በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ከባድ ችግር ላይ የወደቁትን በእውነት ውስጥ የሌሉትንም ሰዎች ቢሆን አንዘነጋም። “እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ” የሚለውን የጳውሎስ ማሳሰቢያ እናስታውሳለን። (ገላትያ 6:​10) በንጹሕ ልብና በትክክለኛ ውስጣዊ ግፊት የምናከናውናቸው እነዚህን የመሳሰሉ አገልግሎቶች በሙሉ አምላክን በእጅጉ ያስደስቱታል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 1:​5

19. ከፍ ያሉ የአካላዊ፣ የሥነ ምግባራዊና የመንፈሳዊ የንጽሕና ደረጃዎችን ጠብቀን የምንኖር ከሆነ ምን በረከቶች ይጠብቁናል?

19 የልዑል አምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን “ወንድሞች ሆይ፣ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፣ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው” የሚሉትን የጳውሎስ ቃላት እናከብራለን። (ሮሜ 12:​1) በይሖዋ እርዳታ ንጹሕ መሆን መቻላችን ትልቅ መብት መሆኑን በመገንዘብ በአካል፣ በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ከፍ ያሉትን የንጽሕና ደረጃዎች ለመጠበቅ የተቻለንን ሁሉ እናድርግ። እንዲህ በማድረግ በአሁኑ ጊዜ ለራሳችን አክብሮትና እርካታ ከማግኘታችንም በላይ አምላክ ‘ሁሉን አዲስ በሚያደርግበት’ ጊዜ “የቀደመው ሥርዓት” ማለትም የአሁኑ ክፉና ብልሹ ሥርዓት ሲጠፋ የማየት አጋጣሚ ልናገኝ እንችላለን።​—⁠ራእይ 21:​4, 5

ታስታውሳለህን?

• እስራኤላውያን ንጽሕናን አስመልክቶ ብዙ ሕጎች የተሰጧቸው ለምን ነበር?

• አካላዊ ንጽሕና የምንሰብከውን መልእክት ማራኪ የሚያደርገው እንዴት ነው?

• ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕና፣ ከአካላዊ ንጽሕናም ጭምር ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• ‘ለመልካም ሥራ የምንቀና’ ሕዝቦች መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አካላዊ ንጽሕናችን ለምንሰብከው መልእክት ውበት ይጨምራል

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ክፉ ሐሳብ ወደ ክፉ ድርጊት እንደሚመራ አስጠንቅቋል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች ንጹሕ ሕዝብ እንደመሆናቸው ለመልካም ሥራ ይቀናሉ