በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለአምላክ የማደር ባሕርይ በመኮትኮቴ ተክሼአለሁ

ለአምላክ የማደር ባሕርይ በመኮትኮቴ ተክሼአለሁ

የሕይወት ታሪክ

ለአምላክ የማደር ባሕርይ በመኮትኮቴ ተክሼአለሁ

ዊልያም አይሂኖሪያ እንደተናገረው

አባቴ እንደተለመደው እኩለ ሌሊት ላይ ሲያቃስት ባንኜ ተነሳሁ። ሆዱን ይዞ በወለሉ ላይ ይንከባለል ነበር። እናቴ፣ ታላቅ እህቴና እኔ ዙሪያውን ከብበነው ቆምን። ሕመሙ ትንሽ ጋብ ሲልለት ቀና ብሎ ተቀመጠና በረዥሙ ከተነፈሰ በኋላ “በዚህች ምድር ላይ ሰላም ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው” በማለት ተናገረ። አባባሉ ግራ የሚያጋባ ነበር። ከዚህ ቀደም ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሰምቼ ስለማላውቅ ይህ አባባሉ በጣም አስገረመኝ። ምን ማለቱ ይሆን ብዬ አሰብኩ።

ይህ የሆነው በ1953 የስድስት ዓመት ልጅ ሳለሁ ነበር። ኢዎሳ በተባለ በመካከለኛው ምዕራብ ናይጄሪያ በሚገኝ አንድ የእርሻ መንደር ውስጥ ከአንድ በላይ ሚስቶች የማግባት ልማድ በነበረው ቤተሰብ ውስጥ ተወለድኩ። ሁለተኛ ልጅ ብሆንም የአባቴን 3 ሚስቶችና 13 ልጆች ላቀፈው ቤተሰብ የመጀመሪያው ወንድ ልጅ ነበርኩ። በወንድ አያቴ ባለ አራት ክፍል የሣር ክዳን ጭቃ ቤት ውስጥ አንድ ላይ ሆነን እንኖር ነበር። ቤተሰቡ የሴት አያቴን እንዲሁም የአባቴን ሦስት ወንድሞችና ቤተሰቦቻቸውን ጭምር ያቀፈ ነበር።

የልጅነት ሕይወቴ አስደሳች አልነበረም። ለዚህ በዋነኛነት አስተዋጽኦ ያደረገው የአባቴ የጤና መታወክ ነበር። ሥር በሰደደ የሆድ ዕቃ ችግር ለብዙ ዓመታት ተሠቃይቷል። ተለይቶ ሊታወቅ ያልቻለው በሽታው በግብርና የሚተዳደር የአንድ ድሃ አፍሪካዊ ቤተሰብ አቅም ሊፈቅድ ለሚችለው ለማንኛውም ዓይነት ባሕላዊ ሕክምና የሚበገር አልሆነም። አባታችን ሲያምመው ሌሊቱን ሙሉ መሬት ላይ ይንከባለል ነበር። እኛም ጎሕ እስኪቀድድ ድረስ ከእርሱ ጋር አብረን በማልቀስ በርካታ ሌሊቶች አሳልፈናል። ለሕመሙ ፈውስ ለማግኘት ሲል እኔንና ሌሎቹን ልጆች ለአያቴ ትቶ ብዙውን ጊዜ ከእናቴ ጋር ይጓዝ ነበር።

ቤተሰባችን የስኳር ድንች፣ ካሳቫና የኮላ ፍሬ በማምረትና በመሸጥ ይተዳደር ነበር። በተጨማሪም ከጎማ ዛፍ የሚገኘውን ፈሳሽ በማውጣት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ገቢያችንን እንደጉም ነበር። ዋነኛው ምግባችን ስኳር ድንች ሲሆን ቁርስ ስኳር ድንች፣ ምሳ የተፈጨ ስኳር ድንች ማታም ስኳር ድንች እንመገብ ነበር። አልፎ አልፎ ፕላንቴይን ከተባለው ዛፍ የሚገኘውን እንደ ሙዝ ያለ ፍሬ ቀቅለን እንበላ ነበር። ትንሽ የተለየ ነገር የምናገኘው በዚህ ጊዜ ብቻ ነበር።

የቀድሞ አባቶች አምልኮ በሕይወታችን ውስጥ ጉልህ ሥፍራ ነበረው። ቤተሰባችን የተለያየ የባሕር እንስሳት ቅርፊት በተሰካባቸው እንጨቶች ፊት ምግብ በማስቀመጥ ለሞቱ አባቶች መሥዋዕት ያቀርብ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ አባቴ ከክፉ መናፍስትና ከዛር ለመጠበቅ ሲል ጣዖት ያመልክ ነበር።

አምስት ዓመት ሲሞላኝ አሥራ አንድ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ወደሚገኝ አንድ የእርሻ ካምፕ በጊዜያዊነት ተዛወርን። እዚያም አባቴ ከሆድ ዕቃ ሕመሙ በተጨማሪ ጊኒ ዎርም በተባለ ጥገኛ ተውሳክ የሚመጣ በሽታ ያዘው። ቀን ሥራ መሥራት አይችልም። ማታ ማታ የሆድ ሕመሙ ያሠቃየዋል። እኔ ደግሞ በሙጃሌ አማካኝነት የሚመጣ እንደ ተስቦ ያለ በሽታ ያዘኝ። ከዚህም የተነሣ ከዘመድ አዝማዶቻችን በምናገኛት ምጽዋት ኑሮአችንን ለመግፋት ተገደድን። ብቻችንን በችግር ተቆራምደን ከምንሞት በማለት ኢዎሳ ወደሚገኘው መንደራችን ተመለስን። አባቴ የመጀመሪያ ልጁ እንደመሆኔ መጠን ከዕለት ጉርስ ያለፈ ነገር በማያስገኝ የግብርና ሥራ ተወስኜ እንድቀር አልፈለገም። የቤተሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እንዲሁም ወንድሞቼንና እህቶቼን ለማሳደግ የምችለው ጥሩ ትምህርት ካገኘሁ ብቻ እንደሆነ ተሰማው።

ከተለያዩ ሃይማኖቶች ጋር መተዋወቅ

እዚያው መንደራችን ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት ገባሁ። ይህም ከሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ጋር እንድተዋወቅ አደረገኝ። በ1950ዎቹ ዓመታት የምዕራባውያኑን ትምህርት ከቅኝ ገዥዎቹ ሃይማኖት ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነበር። እማር የነበረው በአንድ የካቶሊክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በመሆኑ የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ መሆን ነበረብኝ።

በ1966 አሥራ ዘጠኝ ዓመት ሲሞላኝ ከኢዎሳ 8 ኪሎ ሜትሮች ርቆ በኢዎሂንሚ ከተማ ወደሚገኘው የፒልግሪም ባፕቲስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዛወርኩ። እዚያም ሃይማኖታዊ ትምህርቴ ተለወጠ። አሁን በፕሮቴስታንት ትምህርት ቤት ውስጥ የምማር በመሆኔ የካቶሊክ ቄሶች እሁድ በሚደረገው የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳልገኝ ከለከሉኝ።

ለመጀመሪያ ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የተዋወቅሁት በዚህ የባፕቲስት ትምህርት ቤት ውስጥ ሳለሁ ነበር። ወደ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሄዴን ብቀጥልም ሁልጊዜ እሁድ እሁድ ከቤተ ክርስቲያን ስመለስ መጽሐፍ ቅዱሴን አነብብ ነበር። የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች በጣም የነኩኝ ሲሆን በውስጤ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ በመኮትኮት ትርጉም ያለው ሕይወት የመኖር ፍላጎትን ቀስቅሰውብኛል። መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ እያነበብኩ በሄድኩ መጠን የአንዳንድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ግብዝነትና የአብዛኞቹ ምዕመናን ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ አኗኗር ይበልጥ እያስጸየፈኝ መጣ። ክርስቲያን ነን በሚሉት መካከል ያየሁት ነገር ኢየሱስና ተከታዮቹ ካስተማሩትና ካደረጉት ፈጽሞ የተለየ ነው።

በተለይ አንዳንድ የገጠሙኝ ሁኔታዎች በጣም አስደነገጡኝ። በአንድ ወቅት መቁጠሪያ ለመግዛት ወደ አንድ ሃይማኖታዊ አስተማሪ መደብር ስሄድ በሩ ላይ ጁጁ የተባለው የምዕራብ አፍሪካውያን ክታብ ተሰቅሎ አየሁ። በሌላ ጊዜ ደግሞ የባፕቲስት ትምህርት ቤቱ ዲሬክተር በጾታ ሊያስነውረኝ ሞከረ። ከጊዜ በኋላ ሰውዬው ግብረ ሰዶም ፈጻሚ እንደሆነና ያስነወራቸው ሰዎች እንዳሉ ተረዳሁ። ‘አምላክ ለፈጸሙት ከባድ ኃጢአት በኃላፊነት የማይጠየቁ አባሎች ብሎም መሪዎች ያሉትን ሃይማኖት ይቀበላል?’ በማለት አሰብኩ።

ሃይማኖቴን ለወጥኩ

ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያነበብኩት ነገር ስላስደሰተኝ ንባቤን ለመቀጠል ወሰንኩ። አባቴ ከ15 ዓመታት በፊት “በዚህች ምድር ላይ ሰላም ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው” በማለት የተናገራቸውን ቃላት መለስ ብዬ ማሰብ የጀመርኩት በዚህ ጊዜ ነበር። ሆኖም በምማርበት ትምህርት ቤት የነበሩ የይሖዋ ምሥክር ወጣቶች ይፌዝባቸውና አንዳንዴም ጠዋት ጠዋት በምናደርገው የአምልኮ ሥርዓት ላይ ባለመገኘታቸው ብቻ ቅጣት ይደርስባቸው ስለነበር ስጋት አደረብኝ። አንዳንድ እምነቶቻቸውም ቢሆኑ ለእኔ እንግዳ ነበሩ። ለምሳሌ ያህል ወደ ሰማይ የሚሄዱት 144,000 ሰዎች ብቻ ናቸው የሚለውን መቀበል ከብዶኝ ነበር። (ራእይ 14:⁠3) ወደ ሰማይ መሄድ እፈልግ ስለነበር ምናልባት ቁጥሩ ከመወለዴ በፊት ሞልቶ ይሆን? በማለት አሰብኩ።

ምሥክሮቹ በጠባያቸውና በዝንባሌዎቻቸው ከሌሎች የተለዩ እንደሆኑ በግልጽ ማየት ይቻል ነበር። ሌሎቹ ተማሪዎች በሚፈጽሙት ዓመፅና ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ድርጊት አይካፈሉም ነበር። እውነተኛውን እምነት የያዙ ሰዎች ምን ዓይነት ባሕርይ ማሳየት እንዳለባቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንብቤ ስለነበር ለእኔ በእርግጥ ከዓለም የተለዩ ነበሩ።​—⁠ዮሐንስ 17:​14-​16፤ ያዕቆብ 1:​27

ስለዚህ ሃይማኖቱን ይበልጥ ለመመርመር ወሰንኩ። መስከረም 1969 “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውነት” የተባለውን መጽሐፍ አገኘሁ። በተከታዩ ወር ከአንድ አቅኚ (የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። በመጀመሪያው ጥናቴ በጣም ስለተደሰትኩ እውነት የተባለውን መጽሐፍ ቅዳሜ ማታ ማንበብ ጀመርኩና እሁድ ከሰዓት በኋላ ጨረስኩት። ወዲያው ያነበብኳቸውን አስደናቂ ነገሮች ለክፍል ጓደኞቼ ማካፈል ጀመርኩ። ተማሪዎቹና አስተማሪዎቹ አዲሱ እምነቴ እንዳሳበደኝ ተሰምቷቸው ነበር። ሆኖም እንዳላበድኩ እርግጠኛ ነበርኩ።​—⁠ሥራ 26:​24

አዲስ እምነት እየሰበክሁ እንዳለሁ የሚገልጽ ወሬ ወደ ወላጆቼ ጆሮ ደረሰ። ችግሬ ምን እንደሆነ ለማወቅ በፍጥነት ወደ ቤት እንድመለስ ጠየቁኝ። ምሥክሮቹ በጠቅላላ በኢሌሻ ከተማ ወደሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ሄደው ስለነበር ምክር የምጠይቀው ሰው አጣሁ። ወደ ቤት ስመለስ እናቴና ሌሎች ዘመዶቼ የጥያቄና የትችት ናዳ አወረዱብኝ። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩትን ነገር ለመከላከል የቻልኩትን ያህል ጥረት አደረግሁ።​—⁠1 ጴጥሮስ 3:​15

አጎቴ የይሖዋ ምሥክሮች ሐሰተኛ አስተማሪዎች መሆናቸውን ለማሳመን ብዙ ጥረት ካደረገ በኋላ ሌላ ለየት ያለ ዘዴ ተጠቀመ። “ትምህርት ቤት የሄድከው ለመማር እንደሆነ አትዘንጋ። ትምህርትህን ትተህ ስብከት ከጀመርክ ትምህርትህን ፈጽሞ አትጨርስም። ታዲያ ለምን ይህንን አዲስ ሃይማኖት ከመያዝህ በፊት ትምህርትህን አትጨርስም?” ሲል ተማጸነኝ። በጊዜው ይህ ሐሳብ ምክንያታዊ መስሎ ስለታየኝ ከምሥክሮቹ ጋር የማደርገውን ጥናት አቋረጥኩ።

ከዚያም ታኅሣሥ 1970 ትምህርቴን ስጨርስ ቀጥታ ወደ መንግሥት አዳራሹ ሄድኩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ ስገኝ ቆይቻለሁ። ነሐሴ 30, 1971 ለአምላክ ያደረግሁትን ውሳኔ በውኃ ጥምቀት አሳየሁ። ይህም ወላጆቼን ብቻ ሳይሆን መላውን የመንደሩን ነዋሪ አስደነገጠ። በኢዎሳም ሆነ በአካባቢዋ መንግሥት የሚሰጠውን የነፃ ትምህርት እድል ያገኘሁት የመጀመሪያው ሰው እኔ ስለነበርኩ የመንደሩ ነዋሪዎች ምን ያህል እንዳዘኑብኝ ተናገሩ። ብዙዎች የት ይደርሳል ብለው ያስቡ ነበር። ትምህርቱን የመንደሩን ሕይወት ለማሻሻል ይጠቀምበታል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር።

ሃይማኖት መለወጤ ያስከተላቸው ውጤቶች

ቤተሰቤና የመንደሩ ሽማግሌዎች እምነቴን ለማስለወጥ መልእክተኞች ላኩ። ያደረጉት ጥረት እርግማንን ያካተተ ነበር። “ይህንን ሃይማኖት ካልተውክ የወደፊት ዕጣህ ይጨልማል። ሥራ አታገኝም። የራስህ የሆነ ቤት መሥራት አትችልም። ማግባትም ሆነ ቤተሰብ መመሥረት አትችልም” በማለት ተናገሩ።

ሆኖም እነሱ እንዳሉት አልሆነም። ትምህርቴን ከጨረስኩ ከአሥር ወራት በኋላ በአስተማሪነት ተቀጠርኩ። ከዚያም ጥቅምት 1972 ቬሮኒካ የተባለችውን ተወዳጅ ባለቤቴን አገባሁ። በኋላም መንግሥት የግብርና ኤክስቴንሽን ወኪል ሆኜ ለመሥራት የሚያስችል ሥልጠና ሰጠኝ። የመጀመሪያ መኪናዬን ገዛሁና ቤታችንን መሥራት ጀመርኩ። ኅዳር 5, 1973 የመጀመሪያ ልጃችን ቪክትሪ ተወለደች። ከዚያም በተከታዮቹ ዓመታት ሊዲያ፣ ዊልፍሬድና ጆአን የተባሉት ልጆቻችን ተወለዱ። በ1986 ማይካ የተባለው የመጨረሻ ልጃችን ተወለደ። ሁሉም ልጆች ከይሖዋ ያገኘናቸው ውድ ስጦታዎች ሆነውልናል።​—⁠መዝሙር 127:​3

ወደ ኋላ መለስ ብዬ ስመለከት የመንደሩ ኗሪ የተመኘልኝ ክፉ ነገር ሁሉ ለበረከት ሆኗል። የመጀመሪያ ልጄን ቪክትሪ (ድል) ብዬ የሰየምኳትም በዚህ ምክንያት ነው። በቅርቡ የመንደሩ ነዋሪዎች የሚከተለውን ጽፈውልኝ ነበር:- “እባክህ፣ አሁን አምላክ እየባረከህ ስለሆነ ወደ ቤት እንድትመለስና የመንደሩን ኑሮ ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ተካፋይ እንድትሆን እንፈልጋለን።”

ልጆችን በአምላክ መንገድ ማሳደግ

ባለቤቴና እኔ በአንድ በኩል ቁሳዊ ሀብት እያሳደድን በሌላ በኩል ደግሞ ከአምላክ የተሰጠንን ልጆችን የማሳደግ ኃላፊነት መወጣት እንደማንችል በመገንዘባችን ቀላል ኑሮ በመኖር መርካትን ተምረናል። የተለየ ዓይነት አኗኗር መምረጥ የሚያስከትላቸውን አስከፊ መዘዞች ከማጨድ ይልቅ በዚህ መንገድ መኖርን እንመርጣለን።

በአገራችን እንደ መታጠቢያ ቤትና ወጥ ቤት ያሉትን ክፍሎች ከሌሎች ቤተሰቦች ጋር መጋራት የተለመደ ነው። የመንግሥት ሠራተኛ ሆኜ በተዛወርኩባቸው ከተሞች ሁሉ ራሱን የቻለ መኖሪያ መከራየት በመቻላችን ተደስተን ነበር። እርግጥ እንዲህ ያሉት መኖሪያ ቤቶች ትንሽ ወደድ ቢሉም ልጆቻችንን ከመጥፎ ተጽእኖ ለመጠበቅ አስችለውናል። ባለፉት ዓመታት ልጆቻችንን በመንፈሳዊ ጤናማ በሆነ አካባቢ ማሳደግ በመቻላችን ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።

በተጨማሪም ባለቤቴ ከልጆቹ ጋር ለመሆንና እነርሱን ለመንከባከብ ስትል ቤት ትውል ነበር። ሥራዬን ስጨርስ አንዳንድ ነገሮችን በቤተሰብ መልክ ለማከናወን እንሞክራለን። ምንም እንሥራ ምን ሁሉንም ነገር አንድ ላይ ሆነን እንሠራ ነበር። ይህም የቤተሰብ ጥናት ማድረግን፣ ለጉባኤ ስብሰባዎች መዘጋጀትንና በስብሰባዎች ላይ መገኘትን፣ በክርስቲያናዊው አገልግሎት መካፈልንና በአንዳንድ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች መሳተፍን ይጨምራል።

ወላጆች ልጆቻቸውን በቤት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም አጋጣሚ እንዲያስተምሯቸው የሚያሳስበውን የዘዳግም 6:​6, 7ን ምክር ለመከተል ጥረናል። ይህም ልጆቹ ጓደኛ ፍለጋ ወደ ዓለማውያን ዞር ከማለት ይልቅ ምሥክር ጓደኞችን እንዲይዙ ረድቷቸዋል። ቬሮኒካና እኔ እምነታችንን ከማይጋሩን ጋር አላስፈላጊ ጊዜ አብረን ስለማናሳልፍ በጓደኛ ምርጫ ረገድ ጥንቃቄ ማድረግን ከእኛ ምሳሌ ተምረዋል።​—⁠ምሳሌ 13:​20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:​33

እርግጥ በልጆቻችን ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ ያሳደረው የምንሰጣቸው መመሪያና ትምህርት ብቻ አልነበረም። ቤታችን በፊትም ሆነ አሁን ለቀናተኛ ክርስቲያኖች ክፍት ነው። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ አገልጋዮች ናቸው። እነዚህ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ከቤተሰባችን ጋር ያሳለፉት ጊዜ ልጆቻችን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የተንጸባረቀበትን አኗኗራቸውን የመመልከትና ከዚህም የመማር አጋጣሚ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። ይህም ከእኛ ያገኙትን ትምህርት ይበልጥ ያጠናከረላቸው ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የራሳቸው እንዲያደርጉትም ረድቷቸዋል።

ለአምላክ የማደርን ባሕርይ በመኮትኮቴ ተክሻለሁ

በዛሬው ጊዜ አራቱን ልጆቻችንን ጨምሮ እኔና ባለቤቴ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ እንገኛለን። በአቅኚነት ማገልገል የጀመርኩት በ1973 ሲሆን ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት የሙሉ ጊዜ አገልግሎቴን ለማቋረጥ የተገደድኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። አልፎ አልፎ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ ተመልካቾችን በሚያሰለጥነው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት የማስተማር መብትም አግኝቻለሁ። በአሁኑ ጊዜ በኡሆንሞራ በከተማ የበላይ ተመልካችነትና በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ አባልነት የማገልገል መብት አግኝቻለሁ።

ቪክትሪና ሊዲያ የተባሉት የመጀመሪያዎቹ ሴቶች ልጆቼ ጥሩ ጥሩ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን አግብተዋል። ልጆቼ ከባሎቻቸው ጋር በመሆን ኢጌዱማ ናይጄሪያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በማገልገል ላይ ናቸው። ትልቁ ወንድ ልጃችን ዊልፍሬድ የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ ያገለግላል። የመጨረሻው ልጃችን ማይካ ደግሞ አልፎ አልፎ በረዳት አቅኚነት ያገለግላል። በ1997 ጆአን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንደጨረሰች የዘወትር አቅኚ ሆናለች።

በሕይወቴ በጣም ከሚያስደስቱኝ ነገሮች አንዱ ሌሎች የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች እንዲሆኑ መርዳት ነው። እንዲህ እንዲያደርጉ ከረዳኋቸው መካከል አንዳንድ ዘመዶቼ ይገኙበታል። አባቴ ይሖዋን ለማገልገል ጥረት ቢያደርግም ብዙ ሚስቶች ስለነበሩት ብዙም መግፋት አልቻለም። ከልጅነቴ ጀምሮ ለሰዎች ፍቅር ነበረኝ። ሌሎች ሲሰቃዩ ስመለከት የራሴን ችግር ከምንም አልቆጥረውም። ከልቤ ልረዳቸው እንደምፈልግ ስለሚያውቁ ይመስለኛል፣ እኔን ማነጋገር አይከብዳቸውም።

የአምላክን ዓላማዎች እንዲያውቁ ከረዳኋቸው ሰዎች መካከል የአልጋ ቁራኛ የሆነ አንድ ወጣት ይገኝበታል። የአንድ የኤሌክትሪክ ኩባንያ ሠራተኛ የነበረ ሲሆን በሥራው ላይ እንዳለ ኮረንቲ ያዘውና ከደረቱ በታች ሽባ ሆነ። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማና ለሚማረው ነገር ቀስ በቀስ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ጀመረ። ጥቅምት 14, 1995 ከቤታችን አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ወንዝ ውስጥ ሲጠመቅ በ15 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከአልጋው ለመጀመሪያ ጊዜ መውጣቱ ነበር። በሕይወቱ እንደዚያ ቀን ተደስቶ እንደማያውቅ ተናግሯል። በአሁኑ ጊዜ የጉባኤ አገልጋይ ነው።

ከ30 ዓመታት በፊት ይሖዋን አንድነት ካለውና ራሱን ለእርሱ ከወሰነ ሕዝቡ ጋር ሆኜ ለማገልገል በመምረጤ ምንም አልቆጭም። በመካከላቸው እውነተኛ ፍቅር በተግባር ሲገለጽ ተመልክቻለሁ። ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ባዘጋጃቸው ሽልማቶች ውስጥ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ባይካተት ኖሮ እንኳ ለአምላክ ያደርኩ ሆኜ ለመኖር መምረጤ አይቀርም ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 6:​6፤ ዕብራውያን 11:​6) ሕይወቴን ፈር በማስያዝና በማረጋጋት ለእኔም ሆነ ለቤተሰቤ ደስታና እርካታ ያስገኘልን ለአምላክ የማደር ባሕርይ ነው።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1990 ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ፣ ከልጆቼና ከልጆቼ ባሎች ጋር