በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ሞት የሚነገሩ አንዳንድ አፈ ታሪኮችን ጠለቅ ብሎ መመርመር

ስለ ሞት የሚነገሩ አንዳንድ አፈ ታሪኮችን ጠለቅ ብሎ መመርመር

ስለ ሞት የሚነገሩ አንዳንድ አፈ ታሪኮችን ጠለቅ ብሎ መመርመር

የሰው ልጅ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ከፊቱ አፍጥጦ የሚጠብቀውን የሞት ጽልመት በተመለከተ በግራ መጋባትና በስጋት ስሜት ተውጦ ኖሯል። ከዚህም በተጨማሪ የተሳሳቱ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች፣ በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተሩ ልማዶችና ሥር የሰደዱ የግል አመለካከቶች አንድ ላይ ተዳምረው ሞትን ይበልጥ አስፈሪ አድርገውታል። አንድ ሰው ሞትን መፍራቱ ከሕይወት ሊያገኝ የሚችለውን ደስታ ሊያጠፋበትና ሕይወት ትርጉም እንደሌለው ሆኖ እንዲሰማው ሊያደርገው ይችላል።

በተለይ ሞትን አስመልክተው የሚነገሩ አንዳንድ የታወቁ አፈ ታሪኮችን በማስፋፋት ረገድ ግንባር ቀደም ተወቃሽ የሆኑት ዋና ዋናዎቹ ሃይማኖቶች ናቸው። የአምላክን ቃል ተጠቅመህ አንዳንዶቹን አፈ ታሪኮች በመመርመር ስለ ሞት ያለህ ግንዛቤ ይጠራ እንደሆነ ተመልከት።

አፈ ታሪክ 1:- ሞት ተፈጥሮአዊ የሕይወት ፍጻሜ ነው።

ዴዝ​—⁠ዘ ፋይናል ስቴጅ ኦቭ ግሮውዝ የተባለው መጽሐፍ “ሞት . . . የሕይወታችን ዓይነተኛ ክፍል ነው” በማለት ይናገራል። እንደዚህ ያሉት አስተያየቶች ሞት የተለመደና ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ ተፈጥሮአዊ ፍጻሜ ነው የሚለውን እምነት ያንጸባርቃሉ። እንዲህ ያለው እምነት ደግሞ ሁሉ ነገር ከንቱና ትርጉም የለሽ ነው የሚል ፍልስፍና እንዲስፋፋና አብዛኞቹ ሰዎች የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ፈላጊዎች እንዲሆኑ አድርጓል።

ይሁን እንጂ ሞት በእርግጥ ተፈጥሮአዊ የሕይወት ፍጻሜ ነው? አንዳንድ ተመራማሪዎች በዚህ አይስማሙም። ለምሳሌ ያህል ካልቪን ሃርሌይ የተባሉ የሰውን እርጅና የሚያጠኑ የሥነ ሕይወት ተመራማሪ በአንድ ቃለ ምልልስ ላይ ሰዎች “እንዲሞቱ ተደርገው ተፈጥረዋል” በሚለው አባባል እንደማያምኑ ተናግረዋል። ዊልያም ክላርክ የተባሉ የሰውነትን በሽታ የመከላከል ችሎታ የሚያጠኑ ኢሚዩኖሎጂስት ደግሞ “ሞት ለሕይወት የሚሰጠው ትርጉም አንድ ገጽታ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ አይገባውም” ብለዋል። እንዲሁም ሲሞር ቤንዘር የተባሉት የካሊፎርኒያ የቴክኖሎጂ ተቋም ባልደረባ “እርጅና ሰዓቱን ጠብቆ የሚመጣ ነገር ሳይሆን ደረጃ በደረጃ የሚከናወንና ልንለውጠው እንችላለን ብለን ተስፋ የምናደርገው ሂደት ተደርጎ መገለጹ የተሻለ ሊሆን ይችላል” በማለት ተናግረዋል።

ሳይንቲስቶች የሰው ልጆችን ንድፍ ሲያጠኑ ግራ ይገባቸዋል። ከ70 እስከ 80 ዓመት በሚደርሰው የእድሜ ዘመናችን ልንጠቀምበት ከምንችለው በላይ የሆነ ችሎታና ተሰጥኦ ተሰጥቶን እንደተሠራን ይገነዘባሉ። ለምሳሌ ያህል ሳይንቲስቶች የሰው አእምሮ ከፍተኛ የማስታወስ ችሎታ እንዳለው ተገንዝበዋል። አንድ ተመራማሪ አእምሮአችን “ወደ ሃያ ሚልዮን የሚጠጉ ጥራዞች የሚወጣው” መረጃ ሊይዝ እንደሚችል የገለጹ ሲሆን ይህም “በዓለም ታላላቅ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙት ጥራዞች ብዛት ጋር እንደሚተካከል” ተናግረዋል። አንድ ሰው በአማካይ የሕይወት ዘመኑ ከአንጎሉ የመሥራት አቅም ውስጥ ጥቅም ላይ የሚያውለው አንድ አሥር ሺህኛውን ወይም የአንድ መቶኛውን አንድ መቶኛ ብቻ እንደሆነ አንዳንድ የነርቭ ሳይንቲስቶች ይናገራሉ። ስለዚህ ‘በአማካይ የሕይወት ዘመናችን ከአንጎላችን የመሥራት አቅም ውስጥ ጥቅም ላይ የምናውለው በጣም ትንሹን ሆኖ ሳለ ይህን የመሰለ ከፍተኛ ችሎታ ያለው አእምሮ የተሰጠን ለምንድን ነው?’ ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው።

በተጨማሪም የሰው ልጆች ለሞት የሚሰጡትን ያልተለመደ ምላሽ ተመልከት! ለአብዛኛው ሰው የሚስት፣ የባል ወይም የልጅ ሞት በሕይወት ዘመን ከሚያጋጥሙ ሁኔታዎች ሁሉ እጅግ አሳዛኝ ክስተት ሊሆን ይችላል። ሰዎች አንድ የሚወዱትን ሰው በሞት ሲያጡ አብዛኛውን ጊዜ ስሜታዊ ሚዛናቸው ለረዥም ጊዜ ተዛብቶ ይቆያል። እንዲያውም ሞት የተለመደ ነገር ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ የራሳቸው ሞት የሁሉም ነገር ፍጻሜ ማለት እንደሆነ አምኖ መቀበሉ ይከብዳቸዋል። ብሪቲሽ ሜዲካል ጆርናል “እያንዳንዱ ሰው በተቻለ መጠን ለረዥም ዘመን መኖር ይፈልጋል በማለት ብዙዎቹ ጠበብት የሚሰጡትን አስተያየት” ጠቅሷል።

የሰው ዘር ባጠቃላይ ለሞት ከሚሰጠው ምላሽ፣ በማስታወስም ሆነ በመማር ረገድ ካለው አስደናቂ ችሎታ እንዲሁም ለዘላለም ለመኖር ካለው ውስጣዊ ፍላጎት አንጻር ሲታይ የተሠራው ለዘላለም እንዲኖር ታስቦ ነው ቢባል አትስማማም? በእርግጥም አምላክ የሰው ልጆችን የፈጠረው እንዲሞቱ ሳይሆን ለዘላለም እንዲኖሩ ብሎ ነው። አምላክ በሁለቱ ሰብዓዊ ጥንዶች ፊት ያስቀመጠውን ተስፋ ልብ በል:- “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።” (ዘፍጥረት 1:​28) ይህ ምንኛ አስደናቂ የሆነ ዘላለማዊ ተስፋ ነው!

አፈ ታሪክ 2:- አምላክ ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ ለማድረግ ሲል ሰዎችን በሞት ይነጥቃል።

ሦስት ልጆቿን ጥላ ለመሞት እያጣጣረች የነበረች አንዲት የ27 ዓመት እናት ለአንዲት የካቶሊክ መነኩሲት የሚከተለውን ብላታለች:- “እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ ነው አትበይኝ። . . . እንዲህ ሲሉኝ በጣም ያበሳጨኛል።” ይሁን እንጂ ብዙ ሃይማኖቶች ሞትን አስመልክተው የሚያስተምሩት ይህንኑ ነው። አምላክ ሰዎች ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ ይወስዳቸዋል ይላሉ።

ፈጣሪ ሞት ልባችንን በሐዘን እንደሚሰብረው እያወቀ ያላንዳች ርኅራኄ እንድንሞት ያደርጋል? በፍጹም፣ የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ እንዲህ አያደርግም። አንደኛ ዮሐንስ 4:​8 በሚለው መሠረት “እግዚአብሔር ፍቅር ነው።” ጥቅሱ አምላክ ፍቅር አለው ወይም አምላክ አፍቃሪ ነው እንደማይል ልብ በል። ከዚህ ይልቅ አምላክ ፍቅር ነው ይላል። የአምላክ ፍቅር እጅግ ጥልቅ፣ ፈጽሞ እንከን የማይወጣለትና እጅግ ፍጹም በመሆኑ እንዲሁም በስብዕናው ብሎም በተግባሩ ላይ ሙሉ በሙሉ የሚንጸባረቅ በመሆኑ አምላክ የፍቅር ተምሳሌት ነው ሊባል ይችላል። ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ ለማድረግ ሲል ሰዎችን በሞት የሚነጥቅ አምላክ አይደለም።

የሃሰት ሃይማኖት ብዙዎች ሙታን ስለሚገኙበት ቦታና ሁኔታ ግራ እንዲጋቡ አድርጓል። ሰማይ፣ ሲኦል፣ መንጽሔና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ብዙ ቦታዎች ለመረዳት አስቸጋሪና አንዳንዶቹም ጨርሶ አስፈሪ ናቸው። በሌላው በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን አንዳች እንደማያውቁና ከእንቅልፍ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ይነግረናል። (መክብብ 9:​5, 10፤ ዮሐንስ 11:​11-14) ስለዚህ ድብን ያለ እንቅልፍ የወሰደውን ሰው ስናይ እንደማንጨነቅ ሁሉ ከሞትን በኋላ ስለሚደርስብን ሁኔታም መጨነቅ አያስፈልገንም። ኢየሱስ “በመቃብር ያሉት ሁሉ” ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለመኖር ‘ስለሚወጡበት’ ሰዓት ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 5:​28, 29፤ ሉቃስ 23:​43

አፈ ታሪክ 3:- አምላክ ሕፃናትን መላእክት እንዲሆኑ ይወስዳቸዋል።

ለሞት በሚያደርስ ሕመም በተያዙ ሰዎች ላይ ጥናት ያካሄዱት ኤልሳቤት ኩብለር ሮዝ በሃይማኖታዊ ሰዎች ዘንድ ስለተለመደ አንድ ሌላ አስተሳሰብ ገልጸዋል። በአንድ ወቅት ያጋጠማቸውን እውነተኛ ታሪክ በመጥቀስ “ወንድሟን በሞት ላጣች ለአንዲት ትንሽ ልጅ አምላክ ትንንሽ ልጆችን በጣም ስለሚወድድ ትንሹን ጆኒን ወደ ሰማይ ወስዶታል ብሎ መናገሩ ጥበብ እንዳልሆነ” ገልጸዋል። እንደዚህ ያሉት አባባሎች ስለ አምላክ የተሳሳተ ግምት የሚያሳድሩ ሲሆን ትክክለኛ ማንነቱም ሆነ ስብዕናው እንዲሸፈን ያደርጋሉ። ዶክተር ኩብለር ሮዝ በመቀጠል “ይህች ትንሽ ልጅ በአምላክ ላይ ያደረባትን ቁጣ በውስጥዋ እንደያዘች አደገች። ከሦስት አሥርተ ዓመታት በኋላ የራስዋን ልጅ በሞት ስታጣ ለከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ተዳረገች” በማለት ተናግረዋል።

አምላክ ከልጁ ወላጆች ይበልጥ ይፈልገው ይመስል ሌላ መልአክ ለማግኘት ልጁን ነጥቆ የሚወስድበት ምን ምክንያት ይኖራል? አምላክ ሕፃናትን ይወስዳል የሚለው አባባል እውነት ከሆነ ይህ ፈጣሪን ጨካኝና ራስ ወዳድ አያሰኘውምን? ከዚህ ሁሉ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ፍቅር ከእግዚአብሔር ነው’ በማለት ይናገራል። (1 ዮሐንስ 4:​7) ታዲያ የፍቅር አምላክ ጥሩ አስተሳሰብ ላለው ለማንኛውም ሰው አእምሮ በሚከብድ መንገድ የሰዎችን ሕይወት ይቀጥፋልን?

ታዲያ ሕፃናት የሚሞቱት ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው አንዱ መልስ በመክብብ 9:​11 ላይ ይገኛል:- “ጊዜና እድል [“አጋጣሚ፣” NW ] ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል።” በተጨማሪም መዝሙር 51:​5 ሁላችንም ፍጹማን አለመሆናችንን፣ ከተፀነስንበት ጊዜ አንስቶ ኃጢአተኞች መሆናችንንና ምክንያቱ ይለያይ እንጂ ሁላችንም ሟቾች መሆናችንን ይነግረናል። አንዳንድ ጊዜም ሕፃናት ገና በማኅፀን ሳሉ ይሞታሉ። ሌሎች ደግሞ መጥፎ ሁኔታዎች ወይም ድንገተኛ አደጋ አጋጥሟቸው ይሞታሉ። አምላክ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ አይደለም።

አፈ ታሪክ 4:- አንዳንድ ሰዎች ከሞቱ በኋላ በእሳታማ ሲኦል ውስጥ ለዘላለም ይቃጠላሉ።

ብዙ ሃይማኖቶች ክፉዎች በእሳታማ ሲኦል ውስጥ ለዘላለም እንደሚቃጠሉ ያስተምራሉ። ይህ ትምህርት ምክንያታዊና ቅዱስ ጽሑፋዊ ነው? የሰው ልጅ እድሜ ከ70 አሊያም ከ80 ዓመት አይበልጥም። አንድ ሰው በጠቅላላው የሕይወት ዘመኑ ብዙ ኃጢአት ቢሠራ እንኳ ዘላለማዊ የሲኦል እሳት ተገቢ ቅጣት ይሆናልን? በፍጹም። አንድን ሰው በአጭር የሕይወት ዘመኑ ለሠራው ኃጢአት ለዘላለም ማቃጠል ፈጽሞ ተገቢ አይሆንም።

ሰዎች ከሞቱ በኋላ ምን እንደሚሆኑ ሊነግረን የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። ይህንንም በተጻፈው ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ይናገራል:- “[እንስሳ] እንደሚሞት [ሰውም] እንዲሁ ይሞታል፤ የሁሉም እስትንፋስ አንድ ነው፤ . . . ሁሉ ወደ አንድ ቦታ ይሄዳል፤ ሁሉ ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል።” (መክብብ 3:​19, 20) እዚህ ላይ ስለ እሳታማ ሲኦል የተገለጸ አንዳችም ነገር የለም። ሰዎች ሲሞቱ ወደ አፈር ይመለሳሉ ወይም በሌላ አባባል ከሕልውና ውጪ ይሆናሉ።

አንድ ሰው ሊሠቃይ የሚችለው የሚሰማው ከሆነ ብቻ ነው። ሙታን የሚሰማቸው ነገር አለ? አሁንም መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን ይሰጠናል:- “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም።” (መክብብ 9:​5) ‘አንዳች የማያውቁት’ ሙታን በየትኛውም ቦታ ሥቃይ ሊሰማቸው አይችልም።

አፈ ታሪክ 5:- አንድ ሰው ሲሞት ሙሉ በሙሉ አበቃለት ማለት ነው።

ስንሞት ከሕልውና ውጪ የምንሆን ቢሆንም ይህ ማለት ሁሉም ነገር አከተመለት ማለት አይደለም። ታማኙ ኢዮብ ሲሞት ወደ መቃብር ማለትም ወደ ሲኦል እንደሚሄድ ያውቅ ነበር። ሆኖም እስቲ ለአምላክ ያቀረበውን ጸሎት አዳምጥ:- “በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! ቁጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግኸኝ ኖሮ! ቀጠሮም አድርገህ ምነው ባሰብኸኝ ኖሮ! በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን? . . . በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር።”​—⁠ኢዮብ 14:​13-15

ኢዮብ እስከሞት ድረስ ታማኝ ከሆነ አምላክ እንደሚያስታውሰውና ጊዜው ሲደርስ ከሞት እንደሚያስነሳው ያውቅ ነበር። ይህ በጥንት ጊዜ የነበሩ የሁሉም የአምላክ አገልጋዮች እምነት ነበር። ኢየሱስ ራሱ ይህንን ተስፋ ያረጋገጠ ሲሆን አምላክ ሙታንን ለማስነሳት በእርሱ እንደሚጠቀምም አሳይቷል። ክርስቶስ ራሱ የተናገራቸው ቃላት ለዚህ ማረጋገጫ ይሆኑናል:- “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን [“የኢየሱስን ድምፅ፣” NW ] የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።”​—⁠ዮሐንስ 5:​28, 29

በቅርቡ አምላክ ክፋትን ሁሉ ጠራርጎ በማስወገድ በሰማያዊ መንግሥት የሚተዳደር አዲስ ዓለም ያቋቁማል። (መዝሙር 37:​10, 11፤ ዳንኤል 2:​44፤ ራእይ 16:​14, 16) በውጤቱም መላዋ ምድር አምላክን በሚያገለግሉ ሰዎች የተሞላች ገነት ትሆናለች። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚከተለውን እናነብባለን:- “ታላቅም ድምፅ ከሰማይ:- እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”​—⁠ራእይ 21:​3, 4

ከፍርሃት ነጻ መሆን

ስለ ትንሣኤ ተስፋና የዚህ ዝግጅት ምንጭ ስለሆነው አካል ማወቅህ ሊያጽናናህ ይችላል። ኢየሱስ “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” በማለት ቃል ገብቷል። (ዮሐንስ 8:​32) ይህ ደግሞ ከሞት ፍርሃት ነጻ መውጣትንም ይጨምራል። የማርጀትንና የመሞትን ሂደት ሊያስቆምና የዘላለም ሕይወት ሊሰጠን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ማመን ትችላለህ? አዎን፣ ትችላለህ። ምክንያቱም የአምላክ ቃል ሁልጊዜ ይፈጸማል። (ኢሳይያስ 55:​11) አምላክ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ ተጨማሪ እውቀት እንድታገኝ እናበረታታሃለን። የይሖዋ ምሥክሮች አንተን ለመርዳት ዝግጁዎች ናቸው።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አንድ ሰው ሞትን መፍራቱ ከሕይወት ሊያገኝ የሚችለውን ደስታ ሊያጠፋበት ይችላል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ግራፍ]

ስለ ሞት የሚነገሩ አንዳንድ አፈ ታሪኮች ቅዱሳን ጽሑፎች ምን ይላሉ?

● ሞት ተፈጥሮአዊ የሕይወት ፍጻሜ ነው ዘፍጥረት 1:​28፤ 2:​17፤ ሮሜ 5:​12

● አምላክ ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ ለማድረግ ኢዮብ 34:15; መዝሙር 37:11, 29፤ 115:16

ሲል ሰዎችን በሞት ይነጥቃል

● አምላክ ሕፃናትን መላእክት እንዲሆኑ መዝሙር 51:5፤ 104:1, 4፤ ዕብራውያን 1:7, 14

ይወስዳቸዋል

● አንዳንድ ሰዎች ከሞቱ በኋላ መዝሙር 146:4፤ መክብብ 9:5, 10፤ ሮሜ 6:23

በእሳታማ ሲኦል ለዘላለም ይቃጠላሉ

● አንድ ሰው ሲሞት ኢዮብ 14:14, 15፤ ዮሐንስ 3:16; 17:3፤ ሥራ 24:15

ሙሉ በሙሉ አበቃለት ማለት ነው

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ ሞት እውነቱን ማወቃችን ከፍርሃት ነጻ ያደርገናል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Barrators​—Giampolo/The Doré Illustrations For Dante’s Divine Comedy/Dover Publications Inc.