በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ሞት ያለህ አመለካከት ምንድን ነው?

ስለ ሞት ያለህ አመለካከት ምንድን ነው?

ስለ ሞት ያለህ አመለካከት ምንድን ነው?

የቱንም ያህል ጤናሞች ወይም ሃብታሞች እንሁን በማንኛውም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ላይ ሞት ጥላውን እንዳጠላብን ነው። መንገድ ስናቋርጥ ወይም እንቅልፍ ላይ እንዳለን ልንሞት እንችላለን። መስከረም 11, 2001 በኒው ዮርክ ከተማና በዋሽንግተን ዲ ሲ የደረሰውን የአሸባሪዎች ጥቃት የመሳሰሉ አደጋዎች “የኋለኛው ጠላት” ሞት እገሌ ከእገሌ ሳይል በሁሉም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ሰዎች እንደሚያጭድ አንዳንድ ጊዜም በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ብቻ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እንደሚቀጥፍ ቆም ብለን እንድናስብ ያደርጉናል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​26

ያም ሆኖ የሞት ዜና የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ይመስላል። ስለ ሞት በተለይም አሰቃቂ በሆነ መንገድ ሕይወታቸውን ስላጡ ሰዎች እልቂት ከሚናገሩ ሪፖርቶች ይበልጥ የጋዜጦች ገበያ እንዲደራ የሚያደርግ ወይም ብዙዎችን ቴሌቪዥን ፊት የሚደቅን ዜና የለም። ሰዎች በጦርነት ምክንያትም ይሁን በተፈጥሮ አደጋ፣ በወንጀልም ይሁን በሕመም ምክንያት ስለሞቱ ሰዎች የሚገልጹ ዜናዎችን መስማት አይታክታቸውም። ይህ የሞት ዜና አባዜ በኅብረተሰቡ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያላቸውና ታዋቂ የሆኑ ሰዎች ሲሞቱ በሚታየው ፈንቅሎ የሚወጣ የሕዝብ ስሜት እንግዳ በሆነ መንገድ ሲንጸባረቅ ይታያል።

ይህ የማይካድ ነው። ወደፊትም ቢሆን የሌሎች ሞት የብዙዎችን ቀልብ መሳቡ አይቀርም። ይሁን እንጂ ሰዎች ስለ ራሳቸው ሞት ማሰብ አይፈልጉም። አብዛኞቻችን ስለ ራሳችን ሞት ማሰብ በጣም ይከብደናል።

ሞትን መፍራት?

ስለ ራሳችን ሞት ማሰብ መቼም ቢሆን አያስደስትም። ወደፊትም ቢሆን የሚያስደስት አይሆንም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አምላክ በውስጣችን ከፍተኛ የሆነ ለዘላለም የመኖር ፍላጎት ስላስቀመጠ ነው። መክብብ 3:​11 “ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው” በማለት ይናገራል። ስለዚህ ሞት የማይቀር መሆኑ የሰው ልጆች ከራሳቸው ጋር የማያቋርጥ ሙግት እንዲገጥሙ አድርጓቸዋል። ከራሳቸው ጋር የገጠሙትን ሙግት እልባት ላይ ለማድረስና የመኖርን ተፈጥሯዊ ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ ነፍስ አትሞትም ከሚለው አንስቶ እንደገና መወለድ እስከሚለው እምነት ድረስ ያሉትን በርካታ መሠረተ ትምህርቶች ፈጥረዋል።

ያም ሆነ ይህ ሞት አስፈሪ ክስተት ነው። የሞት ፍርሃት የማይዳስሰው የኅብረተሰብ ክፍል የለም። በመሆኑም መላው የሰው ዘር ሞትን አሳዛኝ ክስተት አድርጎ መመልከቱ ሊያስደንቀን አይገባም። አንደኛ ነገር ሞት ሃብትንና ሥልጣንን በማሳደድ ላይ የተመሠረተ ሕይወት መጨረሻው ከንቱ መሆኑን ያረጋግጣል።

ከሰው ተገልሎ መሞት?

ባለፉት ጊዜያት ቀሳፊ በሆነ በሽታ የተያዘ አሊያም ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ የደረሰበት ሰው አብዛኛውን ጊዜ በሚያውቀውና በሚወደው ቤቱ ውስጥ እንዳለ እንዲሞት ይደረግ ነበር። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የተለመደ ነበር። አሁንም ቢሆን በአንዳንድ ባሕሎች የተለመደ ነው። (ዘፍጥረት 49:​1, 2, 33) እነዚህን በመሳሰሉ ሁኔታዎች ቤተሰቡ አንድ ላይ የሚሰበሰብ ሲሆን ልጆችም በውይይቱ እንዲካፈሉ ይደረጋል። ይህም እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሐዘኑ የደረሰው በእርሱ ወይም በእርሷ ላይ ብቻ እንዳልሆነ እንዲሰማቸው ያደርጋል። በተጨማሪም ኃላፊነቱንም ሆነ ሐዘኑን በጋራ መወጣታቸው መጽናናትን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።

ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ስለ ሞት መወያየት ጭንቀት እንደሚፈጥር ተደርጎ በሚታይበትና ክልክል በሆነበት እንዲሁም ይህን የመሰለው ወሬ ለሕፃናት “በጣም ይከብዳቸዋል” በሚል ከውይይቱ እንዲገለሉ በሚደረግበት ኅብረተሰብ ውስጥ ካለው ሁኔታ ፈጽሞ የተለየ ነው። ዛሬ ዛሬ የሰዎች አሟሟት በብዙ መንገዶች ለየት ያለ መልክ እየያዘ መጥቷል። አብዛኛውን ጊዜ ለሞት ሲቃረቡ ከሌሎች እንዲገለሉ ይደረጋል። ብዙዎች በቤተሰቦቻቸው ፍቅራዊ እንክብካቤ ሥር ሆነው መሞትን ቢመርጡም የሚያሳዝነው ግን ከሌሎች ተገልለው በሕመም እየተሰቃዩና ዘመኑ ባፈራቸው አስፈሪ የሕክምና መሣሪያዎች ተከብበው ሆስፒታል ውስጥ ይሞታሉ። በሌላው በኩል ደግሞ ማንነታቸው እንኳ በውል የማይታወቅ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዘር ማጥፋት፣ በረሃብ፣ በኤድስ፣ በእርስ በርስ ጦርነት አሊያም በአሰቃቂ ድህነት ሳቢያ ይሞታሉ።

ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሞት አታስቡ አይልም። እንዲያውም መክብብ 7:​2 “ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፤ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና” በማለት ይናገራል። ከሞት እውነታ ጋር ስንጋፈጥ ቆም ብለን ስለ ሕይወት አጭርነት ማሰብ እንጀምራለን። ይህም ዓላማ የሌለው ሕይወት ከመምራት ይልቅ ይበልጥ ትርጉም ያለው ሕይወት እንድንመራ ሊያነሳሳን ይችላል።

ስለ ሞት ያለህ አመለካከት ምንድን ነው? ስለ ሕይወትህ ፍጻሜ ስታስብ የሚሰማህ ስሜት እንዲሁም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ያለህ እምነት፣ ተስፋና ስጋት ምንድን ነው?

እንደ ሕይወት ምንነት ሁሉ የሞትም ምንነት ከሰው የመረዳትም ሆነ የማስረዳት ችሎታ በላይ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ አስተማማኝ ማብራሪያ ሊሰጠን የሚችለው ፈጣሪያችን ብቻ ነው። “የሕይወት ምንጭ” ከእርሱ ዘንድ ነው። “ከሞት መውጣት” የሚቻለውም በእርሱ ነው። (መዝሙር 36:​9፤ 68:​20) አስገራሚ ሊመስል ቢችልም ሞትን በተመለከተ በሰፊው የሚታወቁትን አንዳንድ እምነቶች በአምላክ ቃል ብርሃን መመርመር አበረታችና አጽናኝ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ማድረጉ ሞት የሁሉም ነገር ፍጻሜ ነው ማለት እንዳልሆነ ለመገንዘብ ይረዳል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በማንኛውም ጊዜ ልንሞት እንደምንችል ማወቃችን ይበልጥ ትርጉም ያለው ሕይወት እንድንመራ ሊያነሳሳን ይችላል