በይሖዋ ጽድቅ ደስ ይበላችሁ
በይሖዋ ጽድቅ ደስ ይበላችሁ
“ጽድቅንና ምሕረትን የሚከተል ሕይወትንና ጽድቅን ክብርንም ያገኛል።”—ምሳሌ 21:21
1. ዛሬ ሰዎችን ለውድቀት የዳረጋቸው የትኛውን አካሄድ መከተላቸው ነው?
“ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው።” (ምሳሌ 16:25) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ዛሬ አብዛኛው ሕዝብ የሚከተለውን አካሄድ ምንኛ በትክክል ይገልጸዋል! በጥቅሉ ሲታይ ሰዎች በራሳቸው ዓይን ትክክል የመሰላቸውን ከማድረግ በስተቀር በጣም መሠረታዊ ለሚባለው የሌሎች ሰዎች ፍላጎት እንኳን ደንታ የላቸውም። (ምሳሌ 21:2) ለአገሩ ሕግና ደንብ እንደሚገዙ በአፋቸው ቢናገሩም ማምለጫ ቀዳዳ ለማግኘት የማያደርጉት ጥረት የለም። ይህም አሁን ያለውን እርስ በርሱ የተከፋፈለና ግራ የተጋባ ኅብረተሰብ አስገኝቷል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
2. የሰው ዘር በአጣዳፊ ምን ማግኘት ያስፈልገዋል?
2 ለራሳችን ጥቅም እንዲሁም ለመላው የሰው ዘር ቤተሰብ ሰላምና ደኅንነት ሲባል ሰዎች ሁሉ ወድደው የሚቀበሉትና የሚታዘዙት ፍጹምና ትክክለኛ ሕግ ወይም መሥፈርት ማግኘታችን በጣም አጣዳፊ ጉዳይ ነው። የትኛውም ሰው ምንም ያህል አስተዋይ ወይም ቅን ቢሆን እንዲህ ያለውን ሕግ ወይም መሥፈርት ማውጣት እንደማይችል የታወቀ ነው። (ኤርምያስ 10:23፤ ሮሜ 3:10, 23) እንዲህ ዓይነት መሥፈርት ካለ የት ይገኛል? ደግሞስ ምን ዓይነት ይሆናል? ከዚህ ይበልጥ መልስ የሚያሻው ጥያቄ ደግሞ እንደዚህ ያለ መሥፈርት ካለ ደስ ብሎህ ትቀበለዋለህ? የሚለው ነው።
የጽድቅ መሥፈርት ማግኘት
3. ሰዎች ሁሉ የሚቀበሉትንና የሚጠቅማቸውን መሥፈርት ለማውጣት ከማንም በላይ ብቃቱ ያለው ማን ነው? ለምንስ?
3 በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለውና ሁሉንም የሚጠቅም መሥፈርት ለማግኘት ከዘር፣ ከባሕልና ከፖለቲካ ልዩነቶች እንዲሁም ከሰው ልጅ የአቅም ውሱንነትና ድክመቶች ሁሉ ነፃ ወደሆነ አካል ፊታችንን መመለሳችን ግድ ይሆናል። ይህን መሥፈርት ሊያሟላ የሚችለው ብቸኛው አካል “ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው” በማለት የተናገረው ሁሉን ቻይ የሆነው ፈጣሪ ይሖዋ አምላክ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። (ኢሳይያስ 55:9) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን “የታመነ አምላክ፣ ክፋትም የሌለበት፣ እርሱ እውነተኛና [“ጻድቅና፣” NW ] ቅን ነው” በማለት ይገልጸዋል። (ዘዳግም 32:4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “እግዚአብሔር ጻድቅ ነው” የሚለውን መግለጫ በተደጋጋሚ እናገኛለን። (ዘጸአት 9:27፤ 2 ዜና መዋዕል 12:6፤ መዝሙር 11:7፤ 129:4፤ ሰቆቃወ ኤርምያስ 1:18) አዎን፣ ይሖዋ የታመነ፣ ትክክለኛና ጻድቅ ስለሆነ ከሁሉ የላቀውን መሥፈርት ከእርሱ ማግኘት እንችላለን።
4. “ጻድቅ” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው?
4 እርግጥ ነው፣ ዛሬ “ጻድቅ” የሚለው ቃል እምብዛም ተወዳጅ አይደለም። እንዲያውም አብዛኞቹ ሰዎች አጉል ከመመጻደቅ ወይም ግብዝ ሃይማኖተኛ ከመሆን ጋር ስለሚያያይዙት ለቃሉ ያላቸው አመለካከት አሉታዊ ነው። አልፎ ተርፎም ሌሎችን ለማንቋሸሽ እንደሚያገለግል ቃል አድርገው ይመለከቱታል። ይሁን እንጂ አንድ መዝገበ ቃላት በሰጠው ፍቺ መሠረት “ጻድቅ” ሲባል “ትክክል፣ ቅን፣ በጎ፣ ነቀፋ የሌለበት፣ ኃጢአት የሌለበት፣ መለኮታዊው ሕግ ወይም ተቀባይነት ያለው የሥነ ምግባር መሥፈርት ከሚጠይቀው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር የሚስማማ፣ ትክክል የሆነውን የሚያደርግ” ማለት ነው። እነዚህን ግሩም ባሕርያት አቅፎ በሚይዝ ሕግ ወይም መሥፈርት ብትመራ ደስ አይልህም?
5. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው መሠረት ጽድቅ ምን ዓይነት ባሕርይ እንደሆነ ግለጽ።
5 ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ ጽድቅ የተባለውን ባሕርይ አስመልክቶ “ጽድቅ በፅንሰ ሐሳብ መልክ የሚገኝ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ግንኙነት ትክክልና ቀና የሆነውን በማድረግ ላይ የተመሠረተ ባሕርይ ነው” ሲል ገልጿል። ለምሳሌ ያህል የአምላክ ጽድቅ እንደ ቅድስናው ውስጣዊ ወይም ግላዊ የሆነ ባሕርይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ትክክልና ቅን በሆኑ መንገዶች ባሕርይው የሚገለጽበት ሁኔታ ነው። ይሖዋ ቅዱስና ንጹሕ ስለሆነ የሚያደርገውም ሆነ ከእርሱ የሚወጣው ማንኛውም ነገር ጽድቅ የተሞላ ነው ሊባል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ሁሉ ቸር ነው።”—መዝሙር 145:17
6. ጳውሎስ በዘመኑ ስለነበሩ አንዳንድ አማኝ ያልሆኑ አይሁዳውያን ምን ብሎ ተናግሯል? ለምንስ?
6 ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይህን ነጥብ ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። አማኝ ያልሆኑ አንዳንድ አይሁዳውያንን በሚመለከት “የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፣ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም” በማለት ጽፏል። (ሮሜ 10:3) ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች ‘የአምላክን ጽድቅ እንደማያውቁ’ የገለጸው ለምን ነበር? በሕጉ ውስጥ የሰፈረውን የአምላክን የጽድቅ መሥፈርቶች ተምረው አልነበረምን? በእርግጥ ተምረው ነበር። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ጽድቅን ይመለከቱ የነበረው ከሌሎች ሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ መመሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል መሥፈርት ሳይሆን ሃይማኖታዊ ደንቦችን ዝንፍ ሳይሉ በጥንቃቄ በመጠበቅ የሚንጸባረቅ ግላዊ የሆነ በጎ ባሕርይ አድርገው ነው። በኢየሱስ ዘመን እንደነበሩት የሃይማኖት መሪዎች እነርሱም ስለ ፍትሕና ስለ ጽድቅ ማወቅ የሚገባቸውን ዋነኛ ነጥብ ሳይረዱ ቀርተዋል።—ማቴዎስ 23:23-28
7. የይሖዋ ጽድቅ የተገለጸው እንዴት ነው?
7 በአንጻሩ ግን የይሖዋ ጽድቅ በሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ በግልጽ ተንጸባርቆ ይታያል። ምንም እንኳን የጽድቅ ባሕርይው ሆን ብለው ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎችን በቸልታ እንዳያልፋቸው ቢያስገድደውም ይህ ባሕርይው የሚፈራ፣ የማይቀረብ፣ ለሌሎች የማያስብ እንዲሁም ጥብቅ እንደሆነ አድርጎ አያስቆጥረውም። ከዚህ በተቃራኒ የጽድቅ እርምጃዎቹ ሰዎች እንዲቀርቡትና ኃጢአት ከሚያስከትለው መዘዝ እንዲድኑ መሠረት ጥሎላቸዋል። በመሆኑም ይሖዋ “ጻድቅ አምላክና መድኃኒት” ተብሎ መገለጹ ሙሉ በሙሉ የተገባ ነው።—ኢሳይያስ 45:21
ጽድቅ እና መዳን
8, 9. ሕጉ የአምላክን ጽድቅ የገለጸው በምን መንገዶች ነው?
8 በአምላክ ጽድቅና ሌሎችን ለማዳን በወሰደው ፍቅራዊ እርምጃ መካከል ያለውን ግንኙነት ለመረዳት በሙሴ በኩል ለእስራኤል ብሔር የሰጠውን ሕግ ተመልከት። ሕጉ ጽድቅ የተንጸባረቀበት እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። ሙሴ በመሰነባበቻ ንግግሩ ላይ እስራኤላውያንን “በዓይናችሁ ፊት ዛሬ እንደማኖራት እንደዚህች ሕግ ሁሉ ጽድቅ የሆነች ሥርዓትና ፍርድ ያለው ታላቅ ሕዝብ ማን ነው?” በማለት አስታውሷቸው ነበር። (ዘዳግም 4:8) የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ “የእግዚአብሔር ፍርድ እውነትና ቅንነት [“ጽድቅ፣” NW ] በአንድነት ነው” በማለት ተናግሯል።—መዝሙር 19:9
9 ይሖዋ በሕጉ አማካኝነት ትክክልና ስህተት የሆነውን በሚመለከት ያወጣውን ፍጹም መሥፈርት በግልጽ አስቀምጧል። ሕጉ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን እስራኤላውያን በንግድ እንቅስቃሴዎች፣ በጋብቻ ጥምረቶች፣ በአመጋገብ ሥርዓት፣ በንጽሕና አጠባበቅ አልፎ ተርፎም በፍርድ ጉዳዮች ረገድ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚገልጹ ዝርዝር መመሪያዎችን ይዟል። በተጨማሪም ሕጉን በሚተላለፉ ሰዎች ላይ አንዳንድ ጊዜ የሚበየነውን የሞት ቅጣት ጨምሮ ሌሎች ከባድ ቅጣቶችንም አካትቶ ይዟል። a ይሁን እንጂ ዛሬ ብዙ ሰዎች እንደሚሉት በሕጉ ላይ የተገለጹት የአምላክ የጽድቅ ብቃቶች የሕዝቡን ነፃነትና ደስታ የሚያሳጡ ከባድና አድካሚ ሸክም ነበሩን?
10. ይሖዋን የሚወድዱ ሰዎች ስለ ሕግጋቱ ምን ይሰማቸዋል?
10 ይሖዋን የሚወድዱ ሰዎች በጽድቅ ሕግጋቱና በድንጋጌዎቹ እጅግ ይደሰታሉ። ለምሳሌ ያህል ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ንጉሥ ዳዊት የይሖዋ ሥርዓት እውነትና ጽድቅ መሆኑን አምኖ ከመቀበሉ ባሻገር ለሕጉና ለሥርዓቱ ከልብ የመነጨ ፍቅርና አድናቆት ነበረው። የይሖዋን ሕግና ሥርዓት በሚመለከት “ከወርቅና ከክቡር ዕንቁ ይልቅ ይወደዳል፤ ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል። ባሪያህ ደግሞ ይጠብቀዋል፤ በመጠበቁም እጅግ ይጠቀማል” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 19:7, 10, 11
11. ሕጉ ‘ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚት’ ሆኖ ያገለገለው እንዴት ነው?
11 ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ጳውሎስ ሕጉ የያዘውን የላቀ ጠቀሜታ ገልጿል። ለገላትያ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል” ብሏል። (ገላትያ 3:24) ጳውሎስ በኖረበት ዘመን ሞግዚት (መምህር፣ ኪንግደም ኢንተርሊኒየር) የአንድ ትልቅ ቤተሰብ አገልጋይ ወይም ባሪያ ነበር። ልጆቹን መጠበቅና ወደ ትምህርት ቤት ማመላለስ የእርሱ ኃላፊነት ነበር። በተመሳሳይም ሕጉ እስራኤላውያንን በዙሪያቸው የሚኖሩ አሕዛብ ከሚከተሉት ወራዳ ሥነ ምግባርና ሃይማኖታዊ ልማድ ጠብቋቸዋል። (ዘዳግም 18:9-13፤ ገላትያ 3:23) ከዚህም በላይ ሕጉ እስራኤላውያን ኃጢአተኛ መሆናቸውን እንዲሁም ምሕረትና መዳን ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸው አስገንዝቧቸዋል። (ገላትያ 3:19) በወቅቱ ይቀርብ የነበረው የእንስሳት መሥዋዕት፣ ቤዛዊ መሥዋዕት እንደሚያስፈልግ የጠቆመ ከመሆኑም በላይ እውነተኛው መሲሕ ተለይቶ የሚታወቅበት ትንቢታዊ ጥላ በመሆን አገልግሏል። (ዕብራውያን 10:1, 11, 12) ስለሆነም ይሖዋ በሕጉ አማካኝነት ጽድቁን ሲገልጽ የሰዎችን ደኅንነትና ዘላለማዊ መዳንም ግምት ውስጥ አስገብቷል።
በአምላክ ፊት ጻድቅ ሆነው የተቆጠሩ ሰዎች
12. እስራኤላውያን ሕጉን በጥንቃቄ በመጠበቅ ምን ማግኘት ይችሉ ነበር?
12 ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግ በሁሉም አቅጣጫ ጽድቅ የተንጸባረቀበት ስለሆነ ሕጉን በመታዘዝ በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም አግኝተው መኖር ይችሉ ነበር። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገቡ ተቃርበው በነበረበት ወቅት ሙሴ “እርሱም እንዳዘዘን በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት እናደርጋት ዘንድ ይህችን ትእዛዝ ሁሉ ብንጠብቅ ለእኛ ጽድቅ ይሆንልናል” በማለት አሳስቧቸዋል። (ዘዳግም ) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ “የሚሠራቸው ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራልና ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ” በማለት ቃል ገብቶላቸው ነበር።— 6:25ዘሌዋውያን 18:5፤ ሮሜ 10:5
13. ይሖዋ ሕዝቦቹ የጽድቅ ሕጉን እንዲጠብቁ መጠየቁ ፍትህ የጎደለው ነውን? አብራራ።
13 የሚያሳዝነው ግን እስራኤላውያን በብሔር ደረጃ ‘ይህችን ትእዛዝ ሁሉ በይሖዋ ፊት መጠበቅ’ ባለመቻላቸው ምክንያት ቃል የተገባላቸውን በረከቶች ሳያገኙ ቀርተዋል። የአምላክን ትእዛዛት ሁሉ መጠበቅ ያልቻሉት የአምላክ ሕግ ፍጹም ሲሆን እነርሱ ፍጹም ባለመሆናቸው ምክንያት ነበር። ታዲያ ይህ አምላክን ፍርደ ገምድል ወይም ዓመፀኛ ያሰኘዋል? በፍጹም አያሰኘውም። ጳውሎስ “እንግዲህ ምን እንላለን? በእግዚአብሔር ዘንድ ዓመፃ አለ ወይ? አይደለም” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 9:14) ሕጉ ከመሰጠቱ በፊትም ሆነ ከተሰጠ በኋላ የነበሩ ሰዎች ፍጽምና የጎደላቸውና ኃጢአተኞች ቢሆኑም በአምላክ ፊት ጻድቃን ሆነው ተቆጥረዋል። እንዲህ ከተባለላቸው ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች መካከል ኖኅ፣ አብርሃም፣ ኢዮብ፣ ረዓብና ዳንኤል ይገኙበታል። (ዘፍጥረት 7:1፤ 15:6፤ ኢዮብ 1:1፤ ሕዝቅኤል 14:14፤ ያዕቆብ 2:25) እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ይነሳል:- እነዚህ ግለሰቦች በአምላክ ፊት ጻድቃን ሆነው የተቆጠሩት ከምን አንጻር ነው?
14. መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው “ጻድቅ” እንደሆነ ሲናገር ምን ማለቱ ነው?
14 መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ሰው “ጻድቅ” እንደሆነ ሲናገር ከኃጢአት ነፃ መሆኑን ወይም ፍጹም እንደሆነ ማመልከቱ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአምላክና በሰዎች ፊት ያለበትን ግዴታ እንደተወጣ መግለጹ ነው። ለምሳሌ ያህል ኖኅ ‘እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ በማድረጉ’ ምክንያት “በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው” ተብሎ ተጠርቷል። (ዘፍጥረት 6:9, 22፤ ሚልክያስ 3:18) የመጥምቁ ዮሐንስ ወላጆች የሆኑት ዘካርያስና ኤልሳቤጥ “በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ።” (ሉቃስ 1:6) እንዲሁም እስራኤላዊ ያልሆነው ቆርኔሌዎስ የተባለ ኢጣሊያዊ የጦር መኮንን “ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርንም የሚፈራ” ተብሎ ተጠርቷል።—ሥራ 10:22
15. ጽድቅ የቅርብ ዝምድና ያለው ከምን ጋር ነው?
15 ከዚህም በተጨማሪ የሰዎች የጽድቅ አቋም አንድ ሰው አምላክ የሚፈልግበትን ከማድረጉ ጋር ብቻ ሳይሆን በልቡ ውስጥ ካለው ነገር ጋር ይኸውም በይሖዋና በተስፋዎቹ ላይ ካለው እምነት እንዲሁም ለይሖዋም ሆነ ለተስፋዎቹ ካለው አድናቆትና ፍቅር ጋር በጥብቅ የተዛመደ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች አብርሃም “በእግዚአብሔር አመነ፣ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት” ይላሉ። (ዘፍጥረት 15:6) አብርሃም አምላክ መኖሩን ብቻ ሳይሆን ‘ዘሩን’ አስመልክቶ በሰጠው ተስፋም ላይ እምነት ነበረው። (ዘፍጥረት 3:15፤ 12:2፤ 15:5፤ 22:18) ይሖዋ አብርሃምም ሆነ ሌሎቹ የታመኑ ሰዎች ፍጹማን ባይሆኑም ከእነርሱ ጋር ግንኙነት እንዲፈጥርና እንዲባርካቸው መሠረት የሆነው እንዲህ ያለው እምነትና የእምነት መግለጫ ተግባር ነበር።—መዝሙር 36:10፤ ሮሜ 4:20-22
16. በቤዛው ማመን የሚያስገኘው ጥቅም ምንድን ነው?
16 በመጨረሻም ሰዎች የሚያሳዩት ጽድቅ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ባላቸው እምነት የተመካ ነው። ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለነበሩ ክርስቲያኖች ‘በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በአምላክ ጸጋ ይጸድቃሉ’ በማለት ጽፏል። (ሮሜ 3:24) እዚህ ላይ ጳውሎስ በሰማያዊው መንግሥት ከክርስቶስ ጋር አብረው እንዲገዙ የተመረጡትን አስመልክቶ መናገሩ ነበር። ሆኖም የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም እንዲያገኙ የሚያስችል በር ከፍቶላቸዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ ባየው ራእይ ላይ ‘አንድ እንኳ ሊቈጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሰዎች፣ ነጭ ልብስ ለብሰው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው’ ተመልክቷል። የለበሱት ነጭ ልብስ ‘ልብሳቸውን አጥበው በበጉ ደም በማንጻታቸው’ ምክንያት በአምላክ ፊት ንጹሕና ጻድቅ መሆናቸውን የሚያመለክት ነው።—ራእይ 7:9, 14
በይሖዋ ጽድቅ ደስ ይበላችሁ
17. ጽድቅን በመከታተል ረገድ የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ይኖርብናል?
17 ይሖዋ ሰዎች በፊቱ የጽድቅ አቋም እንዲያገኙ ለማስቻል በፍቅር ተነሳስቶ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ቢሰጣቸውም የጽድቅ አቋም እንዲሁ በራሱ ይገኛል ማለት አይደለም። አንድ ሰው በቤዛው ማመን፣ ሕይወቱን ከአምላክ ፈቃድ ጋር ማስማማት፣ ራሱን ለይሖዋ መወሰንና ይህንንም በውኃ ጥምቀት ማሳየት ይኖርበታል። ከዚያም ጽድቅን መከታተሉንም ሆነ ሌሎች መንፈሳዊ ባሕርያት ማዳበሩን መቀጠል ይገባዋል። ጳውሎስ፣ የሰማያዊ ጥሪ ተካፋይና የተጠመቀ ክርስቲያን የነበረውን ጢሞቴዎስን “ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል” በማለት በጥብቅ አሳስቦታል። (1 ጢሞቴዎስ 6:11፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:22) እንዲሁም ኢየሱስ “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ [“መፈለጋችሁን አታቋርጡ፣” NW ]” ብሎ በተናገረ ጊዜ የማያቋርጥ ጥረት የማድረግን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸውን በረከቶች ለማግኘት ጠንክረን እንሠራ ይሆናል፤ ሆኖም የይሖዋን የጽድቅ መንገድ ለመከታተል ከዚያ የማይተናነስ ጥረት እናደርጋለን?—ማቴዎስ 6:33
18. (ሀ) ጽድቅን መከታተል ቀላል ያልሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ከሎጥ ምሳሌ ምን መማር እንችላለን?
18 እርግጥ ነው፣ ጽድቅን መከታተል ቀላል አይደለም። ይህ የሆነበት ምክንያት ሁላችንም ፍጹማን ባለመሆናችንና የተፈጥሮ ዝንባሌያችን ወደ ኃጢአት የሚያደላ በመሆኑ ነው። (ኢሳይያስ 64:6) ከዚህም በተጨማሪ የምንኖረው ለይሖዋ የጽድቅ መንገዶች ግድ በሌላቸው ሰዎች መካከል ነው። እኛ ያለንበት ሁኔታ ዓይን ያወጣ ክፋት በሚፈጸምባት በሰዶም ከተማ ይኖር ከነበረው ከሎጥ ሁኔታ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ይሖዋ ሎጥን በሰዶም ላይ አጥልቶ ከነበረው ጥፋት ለማዳን እርምጃ የወሰደበትን ምክንያት ገልጿል። ጴጥሮስ “ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና” ብሏል። (2 ጴጥሮስ 2:7, 8) ስለሆነም እያንዳንዳችን ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ ይኖርብናል:- ‘በአካባቢዬ የምመለከታቸውን ሥነ ምግባር የጎደላቸው ድርጊቶች በልቤ እስማማባቸዋለሁን? በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ሆኖም ዓመፅ የሞላባቸውን መዝናኛዎች ወይም የስፖርት ዓይነቶች የምመለከታቸው ለእኔ በግል እንደማይጥሙኝ ነገሮች ብቻ አድርጌ ነውን? ወይስ እነዚህን የመሰሉት ክፉ ምግባሮች እንዳስጨነቁት እንደ ሎጥ ይሰማኛል?’
19. በአምላክ ጽድቅ የምንደሰት ከሆነ ምን በረከቶች ልናገኝ እንችላለን?
19 በዚህ አደገኛና አስተማማኝ ያልሆነ ዘመን በይሖዋ ጽድቅ መደሰት የደኅንነት ምንጭና ከለላ ይሆንልናል። ንጉሥ ዳዊት “አቤቱ፣ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰው ተራራህ ማን ይኖራል?” ለሚለው ጥያቄ “በቅንነት የሚሄድ፣ ጽድቅንም የሚያደርግ” የሚል መልስ ሰጥቷል። (መዝሙር 15:1, 2) የአምላክን ጽድቅ በመከታተልና በዚያም በመደሰት ከእርሱ ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት እንዲሁም የእሱን ሞገስና በረከት ማግኘታችንን መቀጠል እንችላለን። በዚህ መንገድ እርካታ የተሞላበት፣ ለራሳችን ጥሩ ግምት የምንይዝበትና የአእምሮ ሰላም የምናገኝበት ሕይወት ይኖረናል። የአምላክ ቃል “ጽድቅንና ምሕረትን የሚከተል ሕይወትንና ጽድቅን ክብርንም ያገኛል” ይላል። (ምሳሌ 21:21) ከዚህም በተጨማሪ በምናደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ ትክክልና ቅን የሆነውን ለማድረግ መጣራችን ከሌሎች ጋር ደስታ የሰፈነበት ወዳጅነት እንድንመሠርትና በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ የተሻለ ሕይወት እንድንመራ ያስችለናል። መዝሙራዊው “ፍርድን የሚጠብቁ፣ ጽድቅንም ሁልጊዜ የሚያደርጉ ምስጉኖች [“ደስተኞች፣” NW ] ናቸው” በማለት ተናግሯል።—መዝሙር 106:3
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የሙሴን ሕግ ሰፋ ያለ ገጽታ በሚመለከት ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 214-20 ላይ “የሕጉ ቃል ኪዳን አንዳንድ ገጽታዎች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ልታብራራ ትችላለህ?
• ጽድቅ ምንድን ነው?
• መዳን ከአምላክ ጽድቅ ጋር ምን ዝምድና አለው?
• ሰዎች በአምላክ ፊት ጻድቃን ሆነው የሚቆጠሩት በምን መሠረት ነው?
• በይሖዋ ጽድቅ ልንደሰት የምንችለው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ንጉሥ ዳዊት የይሖዋን ሕግ ከልብ እንደሚወድ ገልጿል
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኖኅ፣ አብርሃም፣ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ እንዲሁም ቆርኔሌዎስ በአምላክ ፊት ጻድቃን ሆነው ተቆጥረዋል። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?