በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተጠያቂው ማን ነው? አንተ ወይስ ጂንህ

ተጠያቂው ማን ነው? አንተ ወይስ ጂንህ

ተጠያቂው ማን ነው? አንተ ወይስ ጂንህ

ሳይንቲስቶች ለመጠጥ ሱሰኛነት፣ ለግብረ ሰዶማዊነት፣ ለሴሰኝነት ለጠበኝነትና እንግዳ ለሆኑ ሌሎች ባሕርያት ሌላው ቀርቶ ለሞት እንኳን መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ ከጅን ጋር የተያያዙ ምክንያቶችን ለማግኘት ከፍተኛ ምርምር በማድረግ ላይ ናቸው። ለምናደርጋቸው ነገሮች ተጠያቂዎቹ እኛው ራሳችን ሳንሆን አፈጣጠራችን የዚህ ሰለባ እንዳደረገን ብናውቅ እፎይታ አይሰጠንም? ሰዎች ስንባል ጥፋታችንን በሌላ ሰው ወይም በሌላ ነገር ላይ ማሳበብ ልማዳችን ነው።

ለምናደርጋቸው ነገሮች ተጠያቂው ጂኖቻችን ከሆኑ ሳይንቲስቶች በጀነቲካዊ ምህንድስና አማካኝነት የማይፈለጉ ባሕርያትን አስወግደው በሌላ የመተካት አማራጭ እንዳለ ይናገራሉ። መላውን የሰው ልጅ ጄኖም በካርታ ለማስቀመጥ የተደረገው ጥረት ስኬታማ መሆኑ ይህን ተስፋ ይበልጥ አጠናክሮላቸዋል።

ይሁን እንጂ ይህ አማራጭ የተመሠረተው ለምንሠራቸው ኃጢአቶችና ስህተቶች በሙሉ ዋነኛው ተጠያቂ በዘር ያገኘነው ውርስ ነው በሚለው ሐሳብ ላይ ነው። በሳይንሱ መስክ እየተደረገ ያለው የምርመራ ውጤት ጂኖቻችንን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል በቂ መረጃ አስገኝቶ ይሆን? በግልጽ እንደምንረዳው ለዚህ ጥያቄ የምናገኘው መልስ ለራሳችንም ሆነ ለወደፊቱ ሕይወታችን የሚኖረንን አመለካከት በእጅጉ ይነካል። ማስረጃውን ከመመርመራችን በፊት ግን ስለ ሰው ዘር አፈጣጠር መመልከታችን እውቀታችንን ሊያሰፋልን ይችላል።

ኃጢአት እንዴት ጀመረ?

ብዙ ሰዎች የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት አዳምና ሔዋን በዔድን ገነት ውስጥ ስለ ሠሩት ኃጢአት የሚናገረውን ታሪክ በደንብ ያውቃሉ፤ ወይም ቢያንስ ሲነገር ሰምተዋል። አዳምና ሔዋን የተፈጠሩት በጂኖቻቸው ንድፍ ላይ ኃጢአት እንዲሠሩ ወይም እንዳይታዘዙ የሚያደርግ ጉድለት ወይም እንከን እንዲኖርባቸው ተደርጎ ነውን?

ሥራው ሁሉ ፍጹም የሆነው ፈጣሪያቸው ይሖዋ አምላክ ለምድራዊ ፍጥረቱ የመጨረሻ ሥራው “እጅግ መልካም” እንደነበረ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 1:​31፤ ዘዳግም 32:​4) የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት መባረኩና በዝተው ተባዝተው ምድርን በሰው ልጆች እንዲሞሏት እንዲሁም ምድራዊ ፍጥረታቱን እንዲገዙ መናገሩ በሥራው መርካቱን የሚያሳይ ሌላ ማስረጃ ነው። በእጁ ሥራ የማይተማመን ሰው እንዲህ እንደማያደርግ የታወቀ ነው።​—⁠ዘፍጥረት 1:​28

መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ባልና ሚስት አፈጣጠር አስመልክቶ ሲናገር “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ይለናል። (ዘፍጥረት 1:​27) ይህ ሲባል ግን ሰዎች በመልክ አምላክን ይመስላሉ ማለት አይደለም። ምክንያቱም “እግዚአብሔር መንፈስ ነው።” (ዮሐንስ 4:​24) ከዚህ ይልቅ የሰው ዘሮች የሥነ ምግባር ስሜት ማለትም ሕሊናና አምላካዊ ባሕርያት ተሰጥቷቸው ተፈጥረዋል ማለት ነው። (ሮሜ 2:​14, 15) እንዲሁም አንድን ነገር አመዛዝነው ተገቢውን እርምጃ መውሰድ የሚችሉ የመምረጥ ነጻነት ያላቸው ሰዎች ነበሩ።

ይሁን እንጂ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ያለ አንዳች መመሪያ አልተተዉም። ከዚህ ይልቅ መጥፎ ተግባር መፈጸም ምን መዘዝ እንደሚያስከትል ተነግሯቸዋል። (ዘፍጥረት 2:​17) ስለሆነም ማስረጃው እንደሚያሳየው አዳም የተሰጠውን ትእዛዝ በማክበርና ባለማክበር መካከል አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ጊዜ ይበጀኛል ወይም ይጠቅመኛል ብሎ ያሰበውን የመምረጥ ነጻነት ነበረው። ከፈጣሪው ጋር ያለውን ዝምድና ወይም የሚወስደው እርምጃ ከረጅም ጊዜ በኋላ የሚያስከትልበትን ውጤት በማመዛዘን ፋንታ በኃጢአት ድርጊት ከሚስቱ ጋር ተባበረ። አልፎ ተርፎም ይሖዋ የሰጠው ሚስት እንዳሳሳተችው በመናገር ጥፋቱን በይሖዋ ላይ ለማመካኘት ሞከረ።​—⁠ዘፍጥረት 3:​6, 12፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:​14

አዳምና ሔዋን ለፈጸሙት ኃጢአት አምላክ የሰጠው ምላሽ እውቀት ሰጭ ሆኖ እናገኘዋለን። በጂኖቻቸው ንድፍ ላይ ያለውን ‘ጉድለት’ ለማስተካከል አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ አታድርጉ ያላቸውን ቢያደርጉ እንደሚደርስባቸው አስቀድሞ የነገራቸውን ውጤት አመጣባቸው፤ ይህም ከጊዜ በኋላ ወደ ሞት አድርሷቸዋል። (ዘፍጥረት 3:⁠17-19) ጥንት የተፈጸመው ይህ ታሪክ የሰውን ባሕ​ርይ ለመረዳት የሚያስችል ተጨማሪ ብርሃን ይፈነጥቅልናል። a

ጂናችን ተጠያቂ እንዳልሆነ የሚያሳይ ማስረጃ

ሳይንቲስቶች ለረጅም ጊዜ ለሰው ልጅ በሽታና ባሕርይ መንስኤም ሆነ መፍትሔ የሚሆኑ ጀነቲካዊ ምክንያቶች ለማወቅ እልህ አስጨራሽ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል። በስድስት ቡድን የተከፈሉ ተመራማሪዎች ለአሥር ዓመታት ጥናት ካደረጉ በኋላ ጂኑ በሽታውን የሚያመጣው እንዴት እንደሆነ አይወቁ እንጂ ሃንቲንግተንስ ዲዚዝ ለተባለው በሽታ መንስዔ የሚሆነውን ጂን ለይተው ለማወቅ ችለዋል። ይሁን እንጂ ሳይንቲፊክ አሜሪካን “ለባሕርይ ችግር መንስዔ የሚሆኑትን ጂኖች ለይቶ ማወቅ ፈጽሞ የሚቻል አይመስልም” በማለት የተናገሩትን የሃርቫርዱን የሥነ ሕይወት ተመራማሪ ኢቫን ባላባንን ጠቅሶ በዚህ ጥናት ውጤት ላይ ሪፖርት አድርጓል።

እንዲያውም የተወሰኑ ጂኖችን ከሰው ልጅ ባሕርይ ጋር ለማያያዝ ታስቦ የተደረገው ምርምር ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል። አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ሳይኮሎጂ ቱዴይ ለጭንቀት መንስዔ ሊሆን የሚችለውን ጂን ለማግኘት የተደረገውን ጥረት በሚመለከት “በከባድ የአእምሮ ሕመሞች ላይ የተደረገው ጥናት ውጤት እንዳመለከተው የእንዲህ ዓይነቶቹ የጤና እክሎች መንስዔ ጂን ብቻ ነው ሊባል አይቻልም” በማለት ዘግቧል። ዘገባው አንድ ምሳሌ ጠቅሷል:- “ከ1905 በፊት የተወለዱ አሜሪካውያን በ75 ዓመት ዕድሜያቸው የመንፈስ ጭንቀት የነበረባቸው 1 በመቶ ብቻ ነበሩ። ከግማሽ መቶ ዓመት በኋላ ከተወለዱ አሜሪካውያን መካከል 6 በመቶ የሚያክሉት የመንፈስ ጭንቀት የያዛቸው ገና በ24 ዓመት ዕድሜያቸው ሳሉ ነበር!” በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ለውጥ ሊያስከትሉ የሚችሉት ውጪያዊ ወይም ማኅበራዊ ሁኔታዎች ብቻ ናቸው የሚል መደምደሚያ ላይ ተደርሷል።

እነዚህና ሌሎቹ ብዙ የምርምር ውጤቶች ምን ያስገነዝቡናል? ጂኖች ባሕርያችንን በመቅረጽ ረገድ የሚጫወቱት ሚና ሊኖር ቢችልም ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ሌሎች ሁኔታዎችም እንደሚኖሩ ግልጽ ነው። በዋነኛነት የሚጠቀሰው በተለይ በዚህ ዘመን ፈጣን ለውጥ እያሳየ የመጣው አካባቢያችን የሚያሳድረው ተጽዕኖ ነው። ቦይስ ዊል ቢ ቦይስ የተባለው መጽሐፍ የዛሬ ወጣቶች በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነት ባተረፉ መዝናኛዎች ሳቢያ ለምን ነገር እየተጋለጡ እንዳለ ሲናገር ልጆች “ሰዎች ሲደበደቡ፣ በሽጉጥ ሲገደሉ፣ በጩቤ ሲወጉ፣ ሆዳቸው ሲዘረገፍ፣ አካላቸው በስለት ሲከተፍ፣ ቆዳቸው ሲገፈፍ ወይም አካላቸው ሲቆራረጥ የሚያሳዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችንና ፊልሞችን ለብዙ ሺህ ሰዓታት እየተመለከቱና አስገድዶ መድፈርን፣ ራስን መግደልን፣ ዕፅ መውሰድን፣ አልኮል መጠጣትንና ጥላቻን የሚያበረታቱ ሙዚቃዎችን እየሰሙ አድገው” ጥሩ ሥነ ምግባር ይኖራቸዋል ብሎ መጠበቁ ዘበት እንደሆነ ተናግሯል።

“የዚህ ዓለም ገዥ” የሆነው ሰይጣን የሰውን ርኩስ ምኞቶች የሚያረካ አካባቢ እንደፈጠረ ግልጽ ነው። እንዲህ ያለው ሁኔታ በሁላችንም ላይ ከፍተኛ ጫና ሊፈጥር አይችልም ብሎ ማን ሊከራከር ይችላል?።​—⁠ዮሐንስ 12:​31፤ ኤፌሶን 6:​12፤ ራእይ 12:​9, 12

የሰው ልጅ ችግሮች መንስዔ

ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የሰው ልጆች ችግሮች የጀመሩት የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ኃጢአት በሠሩ ጊዜ ነበር። ይህስ ምን ውጤት አስከተለ? የአዳም ዝርያዎች አዳም ለሠራው ኃጢአት ተጠያቂ ባይሆኑም እንኳ ሁሉም ኃጢአትን፣ አለፍጽምናንና ሞትን ወርሰው ተወልደዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” በማለት ይናገራል።​—⁠ሮሜ 5:​12

የሰው ልጅ አለፍጽምና ከፍተኛ ጉዳት አስከትሎበታል። ሆኖም ይህ መሆኑ ከየትኛውም ዓይነት የሞራል ግዴታ ነፃ አያደርገውም። ይሖዋ ለሕይወት ባደረገው ዝግጅት ላይ እምነት የሚጥሉና ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር ሕይወታቸውን አስማምተው የሚኖሩ ሁሉ ሞገሱን እንደሚያገኙ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይሖዋ በፍቅራዊ ደግነቱ ተነሳስቶ የሰውን ዘር ለመቤዠት ማለትም አዳም ያጣውን መልሶ ለማምጣት የምሕረት እጁን ዘርግቶላቸዋል። ይህ ዝግጅት “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” በማለት የተናገረው ፍጹም ልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው።​—⁠ዮሐንስ 3:​16፤ 1 ቆሮንቶስ 15:​21, 22

ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ ዝግጅት የተሰማውን ጥልቅ አድናቆት ገልጿል። “እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 7:​24, 25) ጳውሎስ በድክመት ምክንያት ኃጢአት ቢሠራ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት አምላክን ይቅርታ መጠየቅ እንደሚችል ያውቅ ነበር። b

እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ በአሁኑ ጊዜም ቀደም ሲል ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት ይመሩ የነበሩ ሰዎች ወይም ተስፋ አስቆራጭ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ይመላለሱ የነበሩ ሰዎች ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አውቀው አስፈላጊውን ለውጥ በማድረግ የአምላክን ሞገስ ወደሚያስገኝ ደረጃ ላይ መድረስ ችለዋል። ያደረጓቸው ለውጦች ቀላል የሚባሉ ባይሆኑም ብዙዎቹ አሁንም እንኳን ጎጂ ከሆኑ ዝንባሌዎች ጋር መታገል አስፈልጓቸዋል። ይሁን እንጂ በአምላክ እርዳታ ጽኑ አቋማቸውን ጠብቀው መመላለስና እርሱን በማገልገል ደስታ ማግኘት ችለዋል። (ፊልጵስዩስ 4:​13) አምላክን ለማስደሰት ሲል ከፍተኛ ለውጥ ያደረገን ቢያንስ የአንድ ሰው ምሳሌ ተመልከት።

አበረታች ተሞክሮ

“ገና በልጅነቴ በአዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ሳለሁ ምንም እንኳን ራሴን እንደ ግብረ ሰዶም ፈጻሚ አድርጌ ባልቆጥረውም እንዲህ በመሰለው ድርጊት መካፈል ጀመርኩ። ወላጆቼ ተፋትተው ስለነበር በሕይወቴ አግኝቼው የማላውቀውን የወላጅ ፍቅር ለማግኘት እጓጓ ነበር። ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ የውትድርና አገልግሎት ግዴታዬን ተወጣሁ። እዚያም እኔ ከምኖርበት ቀጥሎ በሚገኘው ሕንፃ ውስጥ ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ሰዎች ነበሩ። ነገረ ሥራቸው ያስቀናኝ ስለነበር ከእነርሱ ጋር መቀራረብ ጀመርኩ። ግብረ ሰዶም ፈጻሚ እንደሆንኩ ማሰብ የጀመርኩት ከእነርሱ ጋር በጓደኝነት አንድ ዓመት ካሳለፍኩ በኋላ ነበር። ሆኖም ‘አንድ ጊዜ ገብቼበታለሁ ከዚህ በኋላ ልለውጠው አልችልም’ ብዬ አሰብኩ።

“አነጋገራቸውን ከመልመዴም በተጨማሪ አደገኛ ዕፆችና የአልኮል መጠጥ እንደልብ ወደሚገኝባቸው የግብረ ሰዶማውያን ክበቦች መሄድ ጀመርኩ። ላይ ላዩን ሲታይ ሁሉም ነገር አስደሳችና ማራኪ ቢመስልም እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በጣም አስቀያሚ ነበር። እንዲህ ያለው ግንኙነት ተፈጥሯዊ እንዳልሆነና ዘላቂነት እንደሌለው ልቤ ይነግረኝ ነበር።

“በአንዲት አነስተኛ ከተማ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰበሰቡበትን የመንግሥት አዳራሽ አገኘሁ። እዚያም ስደርስ ስብሰባ ላይ ነበሩ። ወደ ውስጥ ገባሁና ይቀርብ የነበረውን ወደፊት ስለምትመጣዋ ገነት የሚገልጽ ንግግር አዳመጥኩ። ከስብሰባው በኋላ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች አነጋገሩኝና በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጋበዙኝ። እዚያም የተገኘሁ ሲሆን አምልኳቸውን አንድ ላይ የሚያካሂዱ ደስተኛ ቤተሰቦች ስመለከት በሕልም ዓለም ውስጥ እንዳለሁ ሆኖ ተሰማኝ። ከምሥክሮቹ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ።

“ከፍተኛ ትግል ማድረግ የሚጠይቅብኝ ቢሆንም ከመጽሐፍ ቅዱስ የማገኘውን እውቀት ተግባራዊ ማድረግ ጀመርኩ። አደርጋቸው የነበሩትን ንጹሕ ያልሆነ ተግባሮችን በሙሉ አቆምኩ። ለ14 ወራት ካጠናሁ በኋላ ራሴን ለይሖዋ ወስኜ ተጠመቅኩ። በሕይወቴ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ጓደኞች አገኘሁ። ሌሎች ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ መርዳት ከመቻሌም በተጨማሪ አሁን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የጉባኤ አገልጋይ ሆኜ በማገልገል ላይ እገኛለሁ። በእርግጥ ይሖዋ ባርኮኛል።”

ተጠያቂዎቹ እኛ ነን

ለምንሠራው ጥፋት ሁሉ ተጠያቂው ጂናችን እንደሆነ አድርጎ ማሰብ የሚያዋጣ አይደለም። ሳይኮሎጂ ቱዴይ እንዳመለከተው እንዲህ ማድረጋችን ችግሮቻችንን እንድንፈታ ወይም እንድንቋቋም ከመርዳት ይልቅ “አብዛኞቹን ችግሮቻችንን ዝም ብለን ከማየት በስተቀር ምንም ማድረግ እንደማንችል እንዲሰማን ሊያደርገን ይችላል። ይህ ደግሞ እነዚህ ችግሮች የሚያስከትሉትን ውጤት በመቀነስ ፋንታ ይበልጥ እንዲባባሱ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል።”

የራሳችንን የኃጢአት ዝንባሌና አምላክን እንዳንታዘዝ ለማድረግ የሚጥረውን ሰይጣንን ጨምሮ ከዋና ዋና ተቃዋሚ ኃይሎች ጋር መታገል እንደሚገባን የታወቀ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:​8) ጂኖቻችንም ቢሆኑ በተለያዩ መንገዶች ተጽዕኖ ሊያደርጉብን እንደሚችሉ እሙን ነው። ሆኖም ይህ ሁሉ ከአቅማችን በላይ እንደማይሆንብን የታወቀ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ይሖዋን፣ ኢየሱስ ክርስቶስን፣ የአምላክን ቅዱስ መንፈስ፣ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስንና የክርስቲያን ጉባኤን የመሳሰሉ ብርቱ አጋሮች አሏቸው።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​11, 12፤ 1 ዮሐንስ 2:​1

ሙሴ የእስራኤል ብሔር ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባቱ በፊት ሕዝቡ በአምላክ ፊት ስላለበት ኃላፊነት ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር:- “በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤ እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንዲሰጣቸው በማለላቸው በምድሪቱ ትቀመጥ ዘንድ፣ እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድደው ትጠባበቀውም ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ።” (ዘዳግም 30:​19, 20፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ዛሬም በተመሳሳይ ኃላፊነት መሸከም የሚችል እያንዳንዱ ግለሰብ አምላክን ለማገልገልና እርሱ የሚፈልግበትን ብቃቶች ለማሟላት የራሱን ምርጫ የማድረግ ግዴታ አለበት። ምርጫው ለአንተ የተተወ ነው።​—⁠ገላትያ 6:​7, 8

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የመስከረም 22, 1996 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 3-8ን ተመልከት።

b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 62-9 ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዳምና ሔዋን በጂኖቻቸው ውስጥ ኃጢአት እንዲሠሩ የሚያደርግ ጉድለት ነበረባቸውን?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እያንዳንዱ ግለሰብ ለሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ኃላፊነቱን ራሱ መውሰድ ይኖርበታልን?

[ምንጭ]

የአደገኛ ዕፅ ሱሰኛ:- Godo-Foto

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰዎችን ባሕርይ የሚለውጡ ጀነቲካዊ ምክንያቶችን ለማግኘት የተደረገው ጥረት ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ተግባራዊ ማድረግ ቅን የሆኑ ሰዎች እንዲለወጡ ይረዳቸዋል