ቴትራግራማተን በሴፕቱጀንት ትርጉም ውስጥ ይገኛሉ
ቴትራግራማተን በሴፕቱጀንት ትርጉም ውስጥ ይገኛሉ
ቴትራግራማተን በመባል የሚታወቁትና יהוה (የሐወሐ) የሚሉት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት ይሖዋ የተባለውን መለኮታዊ ስም ይወክላሉ። ቀደም ባሉት ዓመታት ቴትራግራማተን፣ በግሪክኛ በተዘጋጀው ሴፕቱጀንት ተብሎ የሚጠራ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የመጀመሪያ ትርጉም ቅጂዎች ውስጥ አይገኙም ተብሎ ይታመን ነበር። በመሆኑም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን የጻፉት ሰዎች ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጠቅሰው ሲጽፉ መለኮታዊውን ስም አልተጠቀሙበትም የሚል ሐሳብ ተሰንዝሯል።
ባለፉት ወደ መቶ የሚጠጉ ዓመታት ውስጥ የተደረሰባቸው ግኝቶች እንዳመለከቱት የአምላክ ስም በሴፕቱጀንት ትርጉም ውስጥ ይገኛል። አንድ መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “የግሪክ አይሁዶች የአምላክን ቅዱስ ስም በትክክል ጠብቀው ለማቆየት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው የዕብራይስጡን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ግሪክኛ ሲተረጉሙ የቴትራግራማተን ን ፊደላት በግሪክኛው ጽሑፍ ውስጥ እንዳሉ አስቀምጠዋቸዋል።”
በግራ በኩል የሚታየው የፓፒረስ ቁራጭ በእጅ ከሚገኙት በርከት ያሉ ምሳሌዎች አንዱ ነው። በኦክሲሪንኩስ ግብጽ የተገኘውና 3522 የሚል ቁጥር የተሰጠው ይህ ቁራጭ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከዘአበ የተጻፈ ነው። a ቁራጩ 7 ሴንቲ ሜትር በ10.5 ሴንቲ ሜትር ስፋት ሲኖረው ከኢዮብ 42:11, 12 ላይ የተወሰደ ሐሳብ ይዟል። በክብ የተሰመረባቸው ቴትራግራማተን የተጻፉት በጥንታዊ ዕብራይስጥ ፊደላት ነው። b
ታዲያ መለኮታዊው ስም በመጀመሪያዎቹ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች ውስጥ ይገኛል ማለት ነው? ጆርጅ ሀዋርድ የተባሉ ምሁር እንዲህ ይላሉ:- “ቴትራግራማተን የጥንትዋ ቤተ ክርስቲያን ትጠቀምባቸው በነበሩት የግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች [የሴፕቱጀንት ትርጉም] ውስጥ ተጽፎ የሚገኝ በመሆኑ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ከቅዱሳን ጽሑፎች ሲጠቅሱ ቴትራግራማተን ን እንዳሉ አስቀምጠዋቸዋል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው።” ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ገልባጮቹ መለኮታዊውን ስም እንደ ኪሪዮስ (ጌታ) እና ቴኦስ (አምላክ) ባሉት ቃላት የተኩት ይመስላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በኦክሲሪንኩስ ስለተገኙ የፓፒረስ ጽሑፎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የየካቲት 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 26-8 ተመልከት።
b በጥንታዊ ግሪክኛ ትርጉሞች ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የመለኮታዊው ስም ምሳሌዎች ለማግኘት ባለ ማጣቀሻውን የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም አፔንዲክስ 1C ተመልከት።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Courtesy of the Egypt Exploration Society