የአንባብያን ጥያቄዎች
የአንባብያን ጥያቄዎች
አንድ ሰው ለመጠመቅ ቢፈልግና ውኃ ውስጥ እንዳይጠልቅ እንቅፋት የሚሆን ከባድ የአካል ጉዳት ወይም የጤና እክል ቢኖርበት የግድ ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ መጥለቅ ያስፈልገዋልን?
“ማጥመቅ” የሚለው ቃል ማጥለቅ የሚል ፍቺ ካለው ቫፕቶ ከሚለው የግሪክኛ ግስ የተተረጎመ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ማጥመቅ” ማለት ማጥለቅ እንደ ማለት ነው። በሮተርሃም የተዘጋጀው ዚ ኢምፋሳይስድ ባይብል ፊሊጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ እንዴት እንዳጠመቀው ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ፊሊጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃው ወረዱ፣ ፊሊጶስም ጃንደረባውን ውኃው ውስጥ አጠለቀው።” (ሥራ 8:38) ስለዚህ የሚጠመቀው ሰው ቃል በቃል ውኃው ውስጥ ይጠልቃል።—ማቴዎስ 3:16፤ ማርቆስ 1:10
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . እያጠመቃችኋቸው፣ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል አዟቸዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) በዚህ መሠረት የይሖዋ ምሥክሮች የጥምቀት ሥነ ሥርዓቶችን የሚያከናውኑት በመዋኛ ገንዳዎች፣ ሐይቆች፣ ወንዞች ወይም ሙሉ በሙሉ ለማጥለቅ የሚያስችል ውኃ ባለባቸው ሌሎች ቦታዎች ነው። ሙሉ በሙሉ ውኃው ውስጥ ጠልቆ መጠመቅ መሟላት ያለበት ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃት በመሆኑ ሰዎች አንድን ግለሰብ ከጥምቀት ነፃ የማድረግ ሥልጣን የላቸውም። ስለሆነም አንድ ሰው ባለበት ሁኔታ ምክንያት ለየት ያሉ ዝግጅቶች ማድረግ ቢያስፈልግ እንኳን መጠመቅ ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል በዕድሜ የገፉ ወይም ለየት ያለ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎችን ለማጥመቅ በትላልቅ የገላ መታጠቢያ ገንዳዎች መጠቀም ተችሏል። የገንዳውን ውኃ አሙቆ ተጠማቂውን በርጋታና ቀስ በቀስ ውኃው ውስጥ በማስገባት ከውኃው ጋር ሲለማመድ ጥምቀቱን ማከናወን ይችላል።
በጣም ከባድ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች እንኳን ተጠምቀዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንገታቸው አካባቢ በሚገኝ የመተንፈሻ ቱቦ ላይ ቀዶ ሕክምና የተደረገላቸውና በዚህም ምክንያት በጉሮሯቸው ላይ ቋሚ የሆነ ቀዳዳ ያላቸው ሰዎች ወይም የመተንፈሻ መሣሪያ ተገጥሞላቸው የሚተነፍሱ ሰዎች በውኃ ውስጥ እንዲጠልቁ ተደርጓል። እርግጥ ነው፣ እንደዚህ ዓይነት ጥምቀቶች ሲከናወኑ የተሟላ ዝግጅት መደረግ ይኖርበታል። የሰለጠነች ነርስ ወይም ከተቻለ የሕክምና ዶክተር እንዲኖር ማድረጉ የጥበብ እርምጃ ነው። ይሁን እንጂ የተለየ ጥንቃቄ ወይም ቅድመ ዝግጅት ከተደረገ በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ሥር ማለት ይቻላል፣ የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ሊከናወን ይችላል። በመሆኑም አንድ ሰው ለመጠመቅ ልባዊ ፍላጎት ካለውና ከዚህ ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ የሚችሉትን አደጋዎች ለመቀበል ፈቃደኛ ከሆነ በውኃ እንዲጠመቅ ለማድረግ ማንኛውም ዓይነት ምክንያታዊ የሆነ ጥረት ሊደረግ ይገባል።