‘አንቺ ምግባረ መልካም ሴት ነሽ’
‘አንቺ ምግባረ መልካም ሴት ነሽ’
እነዚህ ስለ አንዲት ሞዓባዊት ወጣት የተነገሩ የአድናቆት ቃላት ናቸው። ይህች ወጣት መበለት ሩት ትባላለች። ኑኃሚን የተባለች የአንዲት እስራኤላዊት ምራት ናት። መሳፍንት በሚገዙበት ዘመን ማለትም ከዛሬ 3000 ዓመታት በፊት እስራኤል ውስጥ ትኖር የነበረችው ሩት በመልካም ምግባሯ ጥሩ ስም አትርፋ ነበር። (ሩት 3:11) ይህን ስም ለማትረፍ የበቃችው እንዴት ነው? ከእሷስ ምሳሌ እነማን ሊጠቀሙ ይችላሉ?
‘የሀኬትንም እንጀራ’ መብላት የማትፈልገው ሩት በማሳው ላይ ለቃርሚያ ተሠማርታ ረጅም ሰዓት በትጋት ትሠራ ነበር። እንዲህ ዓይነት ትጋት ማሳየቷ አድናቆት አትርፎላታል። ድካሟን የሚቀንስ ነገር ቢደረግላትም እንኳ እስከ መጨረሻ በትጋት ከመሥራት ወደኋላ አላለችም። የሩት ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ልባምና ታታሪ ስለሆነች የምትመሰገን ሚስት ከሚሰጠው መግለጫ ጋር ፍጹም ተስማሚ ነው።—ምሳሌ 31:10-31፤ ሩት 2:7, 15-17
ሩት በሰዎች ፊት ላተረፈችው መልካም ስም ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱት እንደ ትህትና፣ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስና ታማኝ ፍቅር ያሉት መንፈሳዊ ባሕርይዎቿ ነበሩ። የተረጋጋ ትዳር ይዛ የመኖር ተስፋዋ የሚደበዝዝ ቢሆንም እንኳ ወላጆቿንና የትውልድ ሀገሯን ትታ ከኑኃሚን ጋር የሙጥኝ ብላለች። በዚሁ ወቅት ሩት የአማትዋን አምላክ ይሖዋን ለማምለክ ያላትን ጠንካራ ፍላጎት ገልጻለች። ቅዱስ ጽሑፋዊው ዘገባ ለኑኃሚን ‘ከሰባት ወንዶች ልጆች ይልቅ’ እንደምትሻል በመናገር ያወድሳታል።—ሩት 1:16, 17፤ 2:11, 12፤ 4:15
ሩት በመልካም ምግባሯ በሰዎች ዘንድ ምስጋና ማትረፏ ትልቅ ነገር ቢሆንም ከሁሉ የላቀ ግምት የሚሰጠው ግን በአምላክ ፊት ያገኘችው ሞገስና የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት የመሆን መብቷ ነው። (ማቴዎስ 1:5፤ 1 ጴጥሮስ 3:4) ሩት ለክርስቲያን ሴቶች ብቻ ሳይሆን ይሖዋን እናመልካለን ለሚሉ ሁሉ እንዴት ያለች ግሩም ምሳሌ ነች!