በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሮማ ታሪክ የሚገኝ ትምህርት

ከሮማ ታሪክ የሚገኝ ትምህርት

ከሮማ ታሪክ የሚገኝ ትምህርት

“እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር [ታገልሁ።]” አንዳንዶች በ1 ቆሮንቶስ 15:​32 ላይ የሚገኙት እነዚህ የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ጳውሎስ በሮማ የትግል ሜዳ ውስጥ እንዲታገል ተፈርዶበት እንደነበር ያሳያሉ በማለት ይናገራሉ። ጳውሎስ ቃል በቃል ይህ ፍርድ ተበይኖበት ይሁን አይሁን ምንም የሚታወቅ ነገር ባይኖርም በወቅቱ እንዲህ በመሰሉ የመወዳደሪያ ሥፍራዎች ውስጥ እስከሞት ድረስ መፋለም የተለመደ ነበር። ስለ መወዳደሪያ ሥፍራውና በዚያ ይከናወኑ ስለነበሩት ነገሮች ታሪክ ምን ይነግረናል?

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን አስተሳሰባችን ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር እንዲስማማ ማድረግ እንፈልጋለን። ይህም በዘመናዊ መዝናኛ ረገድ ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል “በግፈኛ ሰው አትቅና፣ መንገዱንም ሁሉ አትምረጥ” በሚሉት ቃላት ላይ የተንጸባረቀውን አምላክ ስለ ዓመፅ ያለውን አመለካከት ተመልከት። (ምሳሌ 3:​31) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በዙሪያቸው ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች ደም አፍሳሽ በሆኑት የሮማውያን የግላዲያተር ውድድሮች ሲደሰቱ ይህ ምክር እንደ መመሪያ ሆኖ አገልግሏቸዋል። በእነዚህ ጊዜያት የተፈጸሙትን ክንውኖች በመመርመር በዛሬው ጊዜ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ምን ትምህርት እንደያዙ እንመልከት።

በአንድ የሮማ የመወዳደሪያ ሥፍራ ሁለት የታጠቁ ግላዲያተሮች እርስ በርስ ይፋለማሉ። ግጥሚያው እንደተጀመረ ሰይፍ ሲሰናዘሩና በጋሻቸው ሲመክቱ በስሜት ያበደው ተመልካች ድጋፉን በጩኸት ይገልጻል። ውድድሩ የሞት ሽረት ትግል የሚካሄድበት ነው። ብዙም ሳይቆይ የቆሰለውና ውድድሩን መቀጠል ያልቻለው ግለሰብ መሸነፉን በማመን መሣሪያውን ጥሎና ተንበርክኮ ምህረት ይጠይቃል። ተመልካቹ የሚያሰማው ጩኸት እየተጋጋለ ይሄዳል። አንዳንዶች ምህረት እንዲደረግለት ሲጠይቁ ሌሎች ደግሞ እንዲገደል ይጠይቃሉ። የሁሉም ሰው ዓይን በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ተተክሏል። ንጉሠ ነገሥቱ የብዙኃኑን ፍላጎት በማየት የተሸነፈውን ተወዳዳሪ ነጻ መልቀቅም ሆነ ምልክት በመስጠት እንዲገደል ማድረግ ይችላል።

ሮማውያን ለግላዲያተር ውድድሮች ከፍተኛ ፍቅር ነበራቸው። ውድድሮቹን ማካሄድ የተጀመረው በታወቁ ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ እንደሆነ ስታውቅ ትገረም ይሆናል። ይህ ውድድር በመካከለኛው ኢጣሊያ ይኖሩ የነበሩት የኦስካን ወይም የሳምናይት ሰዎች ያቀርቡት ከነበረው የሰው መሥዋዕት ጋር የተያያዘ አመጣጥ እንዳለው ይነገራል። መሥዋዕቱ የሚቀርበው የሙታንን መንፈስ ለማስደሰት በሚል ነበር። ይህ ፍልሚያ ሙኑስ ወይም “ስጦታ” (በብዙ ቁጥር ሙኔራ) በመባል ይታወቃል። በሮም ከተካሄዱት በታሪክ ተመዝግበው የሚገኙ ውድድሮች መካከል የመጀመሪያው በ264 ከዘአበ የተካሄደ ሲሆን ሦስት ጥንድ ግላዲያተሮች በአንድ የበሬ ገበያ ውስጥ ተፋልመዋል። በማርከስ ኤሚሊየስ ሌፒደስ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ 22 ፍልሚያዎች ተካሂደዋል። በፑብሊየስ ሊሲኒየስ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ 60 ጥንዶች ተፋልመዋል። በ65 ከዘአበ ጁሊየስ ቄሣር 320 ጥንድ ተፋላሚዎችን ወደ መወዳደሪያ ሥፍራው ልኳል።

ታሪክ ጸሐፊው ኪዝ ሆፕኪንስ “የባላባቶች የቀብር ሥነ ሥርዓት ፖለቲካዊ ዓላማን ለማራመድ አገልግሏል” በማለት ጽፈዋል። “በተጨማሪም በቀብር ሥነ ሥርዓቶቹ ላይ የሚካሄዱት ውድድሮች . . . የአገሩ ዜጋ በሆኑ መራጮች ዘንድ ተወዳጅ ከመሆናቸው የተነሳ ፖለቲካዊ አንድምታ ነበራቸው። እንዲያውም ውድድሩን ይበልጥ አስደሳች ያደረገው የሥልጣን ጥም በተጠናወታቸው ባላባቶች መካከል የሚደረገው ፖለቲካዊ ሹክቻ ነው።” እነዚህ ውድድሮች በአውግስጦስ (ከ27 ከዘአበ እስከ 14 እዘአ) የግዛት ዘመን ሃብታም ባለ ሥልጣናት ብዙኃኑን ለማዝናናት በሚል ሰበብ ፖለቲካዊ ውጥናቸውን ለማሳካት የሚጠቀሙባቸው በገፍ የሚቀርቡ ስጦታዎች ሆነው ነበር።

ተወዳዳሪዎቹና የሚወስዱት ሥልጠና

‘ግላዲያተሮቹ እነማን ነበሩ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ግላዲያተሮቹ ባሮች፣ የሞት ፍርድ የተበየነባቸው ወንጀለኞች፣ የጦር እስረኞች ወይም በፍላጎት አሊያም ዝና እና ሃብት እናገኛለን በሚል የመጡ ነጻ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ሁሉም እስር ቤት በመሰሉ ማሠልጠኛዎች ውስጥ ይሰለጥናሉ። ጆኪ ኤ ስፔታኮሊ (ጨዋታዎችና ትርኢቶች) የተባለው መጽሐፍ እንደዘገበው በሥልጠና ላይ ያሉት ግላዲያተሮች “ሁልጊዜ በጠባቂዎቹ እይታ ሥር ናቸው። ጥብቅ ለሆነ ዲሲፕሊንና መመሪያ መገዛት የነበረባቸው ሲሆን ስህተት ከሠሩ ከባድ ቅጣት ይደርስባቸው ነበር። . . . እንዲህ ያለው ሁኔታ ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን እንዲገድሉና ረብሻና ዓመፅ እንዲያነሳሱ ያደርጋቸው ነበር።” በሮም የሚገኘው ትልቁ የግላዲያተር ማሰልጠኛ ቢያንስ ለአንድ ሺህ ሰልጣኞች የሚሆኑ ክፍሎች ነበሩት። እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ ችሎታ ነበረው። አንዳንዶች ከብረት የተሠራ መከላከያ አጥልቀውና ጋሻና ጎራዴ ታጥቀው ሲፋለሙ ሌሎቹ መረብና ሦስት አንጓ ያለው መንሽ የመሰለ ጦር ይዘው ይፋለማሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ በሆነው የአደን ትርዒት ከዱር አውሬዎች ጋር ለመፋለም የሚያስችላቸውን ሥልጠና ይወስዳሉ። ጳውሎስ የተናገረው ይህንን ውድድር አስመልክቶ ይሆን?

የውድድሩ አዘጋጂዎች የ17 ወይም የ18 ዓመት ልጆች መልምለው በግላዲያተርነት የሚያሰለጥኑ ድርጅቶችን እርዳታ ማግኘት ይችላሉ። በሰው ሕይወት ላይ የሚካሄደው ንግድ ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኝ ሥራ ነበር። ትራጃን አንድን ወታደራዊ ድል ለማክበር ባዘጋጀው ልዩ ትርዒት ላይ 10, 000 ግላዲያተሮችና 11, 000 እንስሳት ቀርበው ነበር።

የፍልሚያ ሜዳው ውሎ

በፍልሚያ ሜዳው ውስጥ የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ለአደን የተመደበ ነው። የተለያየ ዓይነት ዝርያ ያላቸው የዱር እንስሳት ወደ ፍልሚያ ሜዳው እንዲገቡ ይደረጋል። አብዛኛው ተመልካች በተለይ በጎሽና በድብ መካከል የሚደረገውን ፍልሚያ መመልከት ያስደስተዋል። ብዙውን ጊዜ ሁለቱም አንድ ላይ ይታሠሩና አንደኛው ወገን እስኪሞት ድረስ እንዲፋለሙ ይደረጋል። በመጨረሻም በሕይወት የተረፈው በአዳኝ ይገደላል። ከሌሎች ታዋቂ ግጥሚያዎች መካከል በአንበሳና በነብር ወይም በዝሆንና በድብ መካከል የሚደረጉት ይገኙበታል። አዳኞች ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸውም ቢሆን ከሁሉም የአገሪቱ ግዛቶች የመጡትን እንደ ነብር፣ አውራሪስ፣ ጉማሬ፣ ቀጭኔ፣ ጅብ፣ ግመል፣ ተኩላ፣ ከርከሮና ድኩላ የመሳሰሉ ብርቅዬ እንስሳት በመግደል የአዳኝነት ችሎታቸውን ያሳያሉ።

አካባቢውን ከጫካ ጋር ለማመሳሰል ሲባል በፍልሚያ ሜዳው አለቶች፣ ኩሬዎችና ዛፎች እንዲኖሩ መደረጉ ትርኢቱ በተመልካቾቹ ላይ የማይረሳ ትዝታ ጥሎ እንዲያልፍ አድርጓል። በአንዳንድ የፍልሚያ ሜዳዎች የዱር አራዊቱ መሬት ውስጥ በተሠሩ አሳንሰሮች አማካኝነት ከያሉበት ብቅ ሲሉ በአንድ ምትሃታዊ ኃይል ሜዳው ውስጥ የገቡ ይመስላል። እንስሳቱ የሚያሳዩት እንግዳ የሆነ ባሕርይም ለውድድሩ ድምቀት ሰጥቶታል። ይሁን እንጂ ተመልካቹን ይበልጥ የሚያስደስተው በትርኢቱ ላይ የሚንጸባረቀው ጭካኔ ነበር።

በፕሮግራሙ ቀጣይ ክፍል ነፍስ ግድያ የሚፈጸምባቸው ትርኢቶች የሚቀርቡ ሲሆን ይህንንም በተቻለ መጠን የሚስብ ለማድረግ የተለያዩ መንገዶች ይጠቀማሉ። ተዋንያኑ ቃል በቃል ሲገደሉ የሚያሳዩ አፈ ታሪካዊ ድራማዎች ይቀርቡ ነበር።

በከሰዓት በኋላው ክፍለ ጊዜ በተለያዩ መንገዶች የታጠቁና የተለያየ ዓይነት ሥልጠና የወሰዱ ግላዲያተሮች ይፋለማሉ። የሞተውን ሰው ሬሳ ጎትተው ከሚያወጡት መካከል አንዳንዶቹ የሙታን ዓለም አምላክ ዓይነት አለባበስ ነበራቸው።

በተመልካቹ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ

ተመልካቹ ፍልሚያውን ለማየት ያለው ጉጉት ይህ ነው አይባልም። በመሆኑም ሸሸት ሸሸት የሚሉ ግላዲያተሮች በጅራፍ እንዲመቱና በጋለ ብረት እንዲተኮሱ ይደረግ ነበር። ተመልካቹ ‘ምን ይንቦቀቦቃል? ምን ለኮፍ ለኮፍ ያደርገዋል? መሞቱ ካልቀረ ለምን የፈሪ ሞት ይሞታል? ወደ ኋላ እንዳያፈገፍግ ደህና አድርገህ በጅራፍ ለምጥጠው! ደረታቸውን ሰጥተው በደንብ ይጨፋጨፉ!’ እያለ ይጮኻል። ሮማዊው ባለሥልጣን ሴኔካ በእረፍት ሰዓት “ውድድሩ እስኪጀመር የአንዳንድ ሰዎች አንገት ሲሰየፍ ትመለከታላችሁ!” የሚል ማስታወቂያ እንደሚነገር ጽፏል።

ሴኔካ “ይበልጥ ጨካኝና አረመኔ” ሆኖ ወደ ቤቱ እንደሚመለስ ሳይሸሽግ መናገሩ አያስደንቅም። ይህ ተመልካች የሰጠውን ግልጽ አስተያየት ስንመለከት በጉዳዩ ላይ በቁም ነገር ለማሰብ እንገፋፋለን። በዛሬው ጊዜ ያሉትን አንዳንድ ስፖርቶች የሚከታተሉ ሰዎችስ በተመሳሳይ “ይበልጥ ጨካኝና አረመኔ” እየሆኑ ይሆን?

አንዳንዶች ወደ ቤት በሰላም በመመለሳቸው ራሳቸውን እድለኛ አድርገው ቆጥረው ይሆናል። አንድ ተመልካች በንጉሠ ነገሥት ዶሚሽያን ላይ በመቀለዱ ንጉሠ ነገሥቱ ከመቀመጫው አስጎትተው ካስነሱት በኋላ ለውሾች እንዲሰጥ አድርገውታል። ካሊጉላ ለግድያ የሚሆኑ ወንጀለኞች ሲጠፉ የተወሰነው ተመልካች እንዲያዝና ለአውሬዎች እንዲሰጥ አድርጓል። በተጨማሪም ቀላውዲዎስ የመድረኩ መሣሪያዎች ስላላስደሰቱት የመሣሪያዎቹ ባለሙያዎች በፍልሚያ ሜዳው ውስጥ እንዲፋለሙ አዟል።

በተጨማሪም ተመልካቾች ያስነሱት ረብሻ ከፍተኛ አደጋና ብጥብጥ አስከትሏል። ከሮም በስተሰሜን የሚገኝ አንድ አምፊቲያትር የተደረመሰ ሲሆን በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው ሪፖርት ተደርጓል። በ59 እዘአ ፖምፒ ውስጥ በቀረበ አንድ ትርኢት ላይ ከፍተኛ ረብሻ ተነስቶ ነበር። ታሲተስ እንደዘገበው ከሆነ በከተማይቱ ነዋሪዎችና በአቅራቢያ ከምትገኝ ከተማ በመጡ ሰዎች መካከል የተነሳው ግጭት ድንጋይ እስከ መወራወር ብሎም ጎራዴ እስከ መማዘዝ አድርሷል። ብዙዎች ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በርካታ ሰዎችም ተገድለዋል።

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት

በቅርቡ ሮም ውስጥ በሚገኝ አንድ ጥንታዊ አምፊቲያትር ውስጥ የተደረገ ኤግዚቢሽን (ሳንጉ ኤ አሪና፣ “ደምና አሸዋ”) ከጥንቶቹ ፍልሚያዎች ጋር የሚመሳሰሉ ዘመናዊ ውድድሮችን አሳይቷል። የሚያስገርመው በኤግዚቢሽኑ ላይ የኮርማ ትግል፣ ፕሮፌሽናል የቦክስ ውድድር፣ በመኪናና በሞተር ብስክሌት ውድድሮች ወቅት የሚከሰቱ አሰቃቂ አደጋዎች፣ በተለያዩ ውድድሮች ላይ በስፖርተኞች መካከል የሚካሄድ ድብድብና በተመልካቾች መካከል በሚፈጠር ግጭት ሳቢያ የሚከሰተውን ድብድብ የሚያሳዩ የቪዲዮ ፊልሞች ቀርበዋል። ኤግዚቢሽኑ ያበቃው ከአየር ላይ የተነሣውን የአምፊቲያትሩን ፎቶግራፍ በማሳየት ነበር። ጎብኚዎቹ ምን ዓይነት መደምደሚያ ላይ የሚደርሱ ይመስልሃል? ምን ያህሎቹስ ትምህርት ያገኙ ይሆን?

ዛሬም በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ውሻ ከውሻ ጋርና ዶሮ ከዶሮ ጋር የሚፋለሙባቸውን ውድድሮች መመልከት እንዲሁም ሰዎች ከኮርማዎች ጋር የሚያካሂዷቸውን ግጥሚያዎችና የኃይል ድርጊት የሚፈጸምባቸውን ስፖርቶች ማየት የተለመደ ነው። ብዙኃኑን ለማስደሰት ሲባል የብዙዎችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ የመኪና እና የሞተር ብስክሌት ውድድሮች ይደረጋሉ። በተጨማሪም በየቀኑ የሚቀርቡትን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች አስብ። በአንድ ምዕራባዊ አገር ውስጥ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቴሌቪዥን የሚመለከት አንድ ልጅ እስከ አሥር ዓመት እድሜው ድረስ 10, 000 ነፍስ ግድያዎችንና 100, 000 የኃይል ድርጊቶችን ይመለከታል።

የሦስተኛው መቶ ዘመን ጸሐፊ ተርቱልያን የተመልካቾቹ ፈንጠዝያ “ከእውነተኛው ሃይማኖት ጋርም ሆነ ከእውነተኛው አምላክ መመሪያና ትእዛዝ ጋር የሚጋጭ ነው” በማለት ተናግሯል። የውድድሩን ተመልካቾች የግድያው ግብረ አበሮች አድርጎ ተመልክቷቸዋል። በዛሬው ጊዜ ስላለው ሁኔታስ ምን ለማለት ይቻላል? አንድ ሰው ራሱን እንደሚከተለው በማለት ሊጠይቅ ይችላል:- ‘ለመዝናኛነት የምመርጠው ደም ማፍሰስ፣ ግድያና ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸውን የቴሌቪዥንና የኢንተርኔት ፕሮግራሞች ነው?’ መዝሙር 11:​5 “እግዚአብሔር ጻድቅንና ኀጥእን ይመረምራል፤ ዓመፃን የወደዳት ግን ነፍሱን ጠልቶአል” እንደሚል ማስታወሱ ተገቢ ነው።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ሙታንን ለማስደሰት” የሚደረጉ ፍልሚያዎች

የግላዲያተርን ፍልሚያ አመጣጥ በተመለከተ የሦስተኛው መቶ ዘመን ጸሐፊ ተርቱልያን የሚከተለውን ብሏል:- “የጥንት ሰዎች ትዕይንቱ ይበልጥ ዘመናዊነትን እንዲላበስ በማድረግ ሙታንን እያገለገሉ እንዳለ አድርገው ያስቡ ነበር። ቀደም ባሉት ጊዜያት የሰው ደም የሙታንን ነፍስ ያስደስታል የሚል እምነት ስለነበር ሰዎች ምርኮኞችን ወይም በዝቅተኛ ዋጋ የገዟቸውን ባሪያዎች በቀብር ሥነ ሥርዓቶች ላይ ለመሥዋዕትነት ያቀርቧቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ የዚህ ልማድ አራማጆች ልማዱን ወደ መዝናኛነት በመለወጥ አምላካዊ ፍርሃት የጎደለውን ድርጊታቸውን ለመሸፋፈን ሞክረዋል። ለዚህ ዓላማ የተመለመሉት ሰዎች ዘመኑ ባፈራቸው መሣሪያዎች ተጠቅመው አቅማቸውና ችሎታቸው የፈቀደላቸውን ያህል ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ በተወሰነው የቀብር ሥነ ሥርዓት ቀን እንዲሠዉ ይደረጋል። የሚወስዱት ሥልጠና የገዛ መቃብራቸውን የሚያስቆፍራቸው ነበር! በጊዜው የነበሩት ሰዎች ነፍስ በማጥፋት መጽናናትን ያገኙ ነበር። የሙኑስ አመጣጥ ይህን ይመስላል። ሆኖም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ውድድሩና በውድድሩ መካከል የሚንጸባረቀው ጭከና እኩል ደረጃ ላይ ደረሰ። ምክንያቱም የዱር አውሬዎች የሰዎችን አካል ካልቆራረጡ በቀር በዓሉ አንዳች የጎደለው ነገር እንዳለ ተደርጎ ይቆጠራል። ሙታንን ለማስደሰት በሚል የሚቀርበው መሥዋዕት ቋሚ የቀብር ሥነ ሥርዓት ልማድ ተደርጎ ይታይ ነበር።”

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥንታዊ የግላዲያተር ራስ ቁርና የቅልጥም መከላከያ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ዓመፅ የሞላባቸውን መዝናኛዎች ተጸይፈዋል። አንተስ?

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቦክስ ውድድር:- Dave Kingdon/Index Stock Photography; የመኪና ግጭት:- AP Photo/Martin Seppala

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Phoenix Art Museum, Arizona/Bridgeman Art Library