በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን መማርና ማስተማር

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን መማርና ማስተማር

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን መማርና ማስተማር

“እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን?”​​—⁠⁠ሮሜ 2:​21

1, 2. መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና የሚገፋፉ ምን ምክንያቶች አሉ?

 የአምላክን ቃል እንድታጠና የሚገፋፉ ብዙ ምክንያቶች አሉ። መጽሐፉ ስለተለያዩ ሕዝቦች፣ ክንውኖች፣ ቦታዎችና ሌሎች ነገሮች የያዛቸውን መረጃዎች ማወቅ ትፈልግ ይሆናል። ሥላሴን ወይም እሳታማ ሲኦልን ከመሳሰሉ የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶች በተቃራኒ እውነተኛውን መሠረተ ትምህርት ማወቅ ትፈልግ ይሆናል። (ዮሐንስ 8:​32) በተጨማሪም ይሖዋን በይበልጥ ለመምሰልና በፊቱ በቅንነት ለመመላለስ እርሱን በተሻለ ሁኔታ የማወቅ ፍላጎት ሊያድርብህ ይገባል።​​—⁠⁠1 ነገሥት 15:​4, 5

2 የአምላክን ቃል እንድታጠና የሚገፋፋህ ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያለው ጉልህ ምክንያት ደግሞ ሌሎችን ይኸውም የምትወዳቸው ዘመዶችህን፣ በቅርብ የምታውቃቸውንም ሆነ የማታውቃቸውን ሰዎች የማስተማር ብቃት እንዲኖርህ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲህ ማድረጋቸው አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ብሏቸዋል።​​—⁠⁠ማቴዎስ 28:​19, 20

3, 4. ኢየሱስ እንድናስተምር የሰጠን ትእዛዝ የተቀደሰ ተግባር የሆነው በምን ምክንያት ነው?

3 ሌሎችን የማስተማር ፍላጎት ይዞ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የተቀደሰ ተግባር ከመሆኑም በላይ ዘላቂ እርካታ ሊያስገኝ ይችላል። ከረጅም ጊዜ አንስቶ ማስተማር የተከበረ ሙያ ተደርጎ ሲታይ ቆይቷል። ኢንካርታ የተባለው ኢንሳይክሎፒዲያ “ብዙ አይሁዳውያን በዘመኑ የነበሩትን አስተማሪዎች ወደ ሕይወት ጎዳና የሚመሩ ሰዎች አድርገው ይመለከቷቸው ስለነበር ልጆቻቸው አስተማሪዎቻቸውን ከእነሱ አስበልጠው እንዲያከብሩ ያበረታቷቸው ነበር” በማለት ጠቅሷል። በተለይ ደግሞ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ራሳቸውን አስተምረው ከዚያም ሌሎችን ማስተማራቸው የተቀደሰ ተግባር ነው።

4 ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “በማስተማር ሙያ የተሰማሩ ሰዎች ቁጥር በሌላ በየትኛውም ሙያ ከተሰማሩ ሰዎች ቁጥር ይበልጣል። በመላው ዓለም 48 ሚልዮን የሚያክሉ ወንድና ሴት አስተማሪዎች አሉ።” አንድ መምህር የልጆችን አእምሮ የመቅረጽ አደራ የተጣለበት ሲሆን በተማሪዎቹም ላይ ለዓመታት የሚዘልቅ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል። ኢየሱስ ሌሎችን እንድናስተምር የሰጠውን ትእዛዝ ማክበርህ የሚያስገኘው ውጤት ከዚህ በእጅጉ የሚልቅ ሲሆን የምትሰጠው ትምህርት ዘላለማዊ ሕይወታቸውን ሊነካ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ለራስህና ለትምህርትህ [“ለማስተማር ሥራህ፣” የ1980 ትርጉም ] ተጠንቀቅ፣ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና” ብሎ ጢሞቴዎስን ባሳሰበው ጊዜ ይህን ጠበቅ አድርጎ ተናግሯል። (1 ጢሞቴዎስ 4:​16 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አዎን፣ የማስተማር ሥራህ ከመዳን ጋር የተያያዘ ነው።

5. ክርስቲያኖች የሚያከናውኑትን የማስተማር ሥራ የላቀ የሚያደርገው ምንድን ነው?

5 ራስህን አስተምረህ ሌሎችን እንድታስተምር ያዘዘውም ሆነ ለሥራው አመራር የሚሰጠው የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ የሆነው የመጨረሻው ባለሥልጣን ነው። ይህ እውነታ በራሱ ይህን የማስተማር ሥራ ከማንኛውም የቀለም ትምህርት ማለትም ከመደበኛ ትምህርት፣ በሙያ ማሠልጠኛዎች ወይም በከፍተኛ ደረጃ ከሚሰጠው የሕክምና ትምህርት እንኳን እጅግ የላቀ ያደርገዋል። ክርስቲያኖች አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እሱ ራሱ የአምላክን ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ እንዲከተል ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ እንዲረዳ ያስተምሩታል።​​—⁠⁠ዮሐንስ 15:​10

ራስን ማስተማር ለምን አስፈለገ?

6, 7. (ሀ) በመጀመሪያ ራሳችንን ማስተማር የሚገባን ለምንድን ነው? (ለ) የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዳውያን አስተማሪዎች መሆን ያልቻሉት ከምን አንጻር ነው?

6 በመጀመሪያ ራሳችንን ማስተማር ይገባናል የሚባለው ለምንድን ነው? ራሳችንን ካላስተማርን ሌሎችን በሚገባ ማስተማር ስለማንችል ነው። ጳውሎስ በዘመኑ የነበሩት አይሁዳውያን ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ አንድ ሐሳብ በመሰንዘር ይህን ሐቅ ጎላ አድርጎ የገለጸ ሲሆን ይህ ዛሬ ላሉት ክርስቲያኖችም ትልቅ መልእክት ይዟል። እንዲህ ሲል ጠየቀ:- “እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን? በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን?”​​—⁠⁠ሮሜ 2:​21-23

7 ጳውሎስ በእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ አሥርቱ ትእዛዛት በቀጥታ ከሚያወግዛቸው ኃጢአቶች መካከል ሁለቱን ማለትም አትስረቅ እና አታመንዝር የሚሉትን ጠቅሷል። (ዘጸአት 20:​14, 15) በጳውሎስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ አይሁዳውያን የአምላክን ሕግ በመቀበላቸው በጣም ይኩራሩ ነበር። ‘ሕጉን ስለተማሩ የዕውሮች መሪ፣ በጨለማ ላሉ ብርሃን እንዲሁም የሕፃናት መምህር እንደሆኑ አድርገው’ ራሳቸውን ይቆጥሩ ነበር። (ሮሜ 2:​17-20) ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ በስውር ይሰርቁ ወይም ያመነዝሩ ስለነበር ግብዞች ሆነዋል። ይህ ደግሞ ሕጉንም ሆነ በሰማይ የሚኖረውን ሕግ አውጪ የሚያስነቅፍ ነበር። ጳውሎስ የተናገራቸው ቃላት በዘመኑ የነበሩ አንዳንድ አይሁዳውያን ሕጉንና ይሖዋ አምላክን እንዳሰደቡ ያሳያል። ሌላውን ለማስተማር ብቁ መሆን ይቅርና ራሳቸውን ማስተማር እንዳልቻሉ ከዚህ መረዳት ትችላለህ።

8. በጳውሎስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ አይሁዳውያን ‘ቤተ መቅደስ የዘረፉት’ እንዴት ሊሆን ይችላል?

8 ጳውሎስ ቤተ መቅደስን ስለ መዝረፍ ጠቅሷል። አንዳንድ አይሁዳውያን ቃል በቃል እንዲህ አድርገዋል? ጳውሎስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? ጥቅሱ ዝርዝር ሐሳብ ስለማይሰጥ አንዳንድ አይሁዳውያን እንዴት ‘ቤተ መቅደስ ይዘርፉ’ እንደነበረ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። የኤፌሶን ከተማ ጸሐፊ ቀደም ሲል የጳውሎስ ጓደኞች ‘የቤተ መቅደስ ዕቃ’ አለመስረቃቸውን መናገሩ አይሁዳውያንን በዚህ ድርጊት የሚወነጅሉ አንዳንድ ሰዎች እንደነበሩ ያሳያል። (ሥራ 19:​29-37) ድል አድራጊዎች ወይም ቀናኢ ሃይማኖተኞች ከአረማዊ ቤተ መቅደሶች ዘርፈው ያመጧቸውን ውድ ዕቃዎች አይሁዳውያኑ ለግል ጥቅማቸው ያውሉ ወይም ለሽያጭ ያቀርቡ ነበር? የአምላክ ሕግ በሚያዘው መሠረት በወርቅም ሆነ በብር የተሠሩ ጣዖታት በእሳት መቃጠል እንጂ ለግል ጥቅም መዋል የለባቸውም። (ዘዳግም 7:​25) a ስለሆነም ጳውሎስ፣ የአምላክን ትእዛዝ በመጣስ ከአረማዊ ቤተ መቅደሶች የተወሰዱ ዕቃዎችን ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ ወይም የሸጡ አይሁዳውያን መኖራቸውን በተዘዋዋሪ መጥቀሱ ሊሆን ይችላል።

9. ኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ እንደ መዝረፍ ሊቆጠሩ የሚችሉ ምን መጥፎ ድርጊቶች ተፈጽመዋል?

9 በሌላ በኩል ጆሴፈስ ሮም ውስጥ አራት አይሁዳውያን ስለፈጸሙት የዝርፊያ ቅሌት ተናግሯል። የቡድኑ መሪ የሕጉ አስተማሪ የነበረ ሰው ነው። እነዚህ አራት ሰዎች ወደ ይሁዲነት የተለወጠች አንዲት ሮማዊት ሴት በኢየሩሳሌም ለሚገኘው ቤተ መቅደስ ወርቅና ሌሎች ውድ ዕቃዎች በስጦታ መልክ እንድትሰጥ አግባብተው ተቀበሏት። ዕቃዎቹን እጃቸው ካስገቡ በኋላ ለግል ጥቅማቸው አዋሉት። ይህ ደግሞ ቤተ መቅደሱን ከመዝረፍ ተለይቶ የሚታይ አይደለም። b ሌሎች ደግሞ እንከን ያለባቸውን መሥዋዕቶች በማቅረብ እንዲሁም በአምላክ ቤተ መቅደስ አደባባይ ውስጥ ስግብግብነት የተሞላበት ንግድ በማካሄድ ቦታውን “የወንበዴዎች ዋሻ” በማድረጋቸው የአምላክን ቤት ዘርፈዋል ሊባል ይችላል።​​—⁠⁠ማቴዎስ 21:​12, 13፤ ሚልክያስ 1:​12-14፤ 3:​8, 9

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን አስተምሩ

10. ጳውሎስ በሮሜ 2:​21-23 ላይ የጠቀሰው መርሳት የሌለብን ዋነኛው ቁም ነገር ምንድን ነው?

10 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጳውሎስ ከጠቀሳቸው እንደ ስርቆት፣ ምንዝርና የቤተ መቅደስ ዝርፊያ ያሉ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ ይፈጸሙ የነበሩት ነገሮች ምንም ይሁኑ ምን ይህን ሐሳብ ለመጥቀስ የተነሳሳበትን ዋነኛ ምክንያት መዘንጋት አይኖርብንም። “እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን?” ሲል ጠይቋል። ጳውሎስ በምሳሌነት የጠቀሳቸው ድርጊቶች ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዙ መሆናቸው ሊስተዋል ይገባል። ሐዋርያው እዚህ ላይ ትኩረት ያደረገው በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶች ወይም ታሪክ ላይ አይደለም። ጳውሎስ ራስን አስተምሮ ሌሎችን ስለማስተማር የተናገረው ሐሳብ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን የሚመለከት ነው።

11. የአምላክን ቃል በምታጠናበት ጊዜ ለክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ትኩረት መስጠት የሚገባህ ለምንድን ነው?

11 በሮሜ 2:​21-23 ላይ የሚገኘውን ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ የአምላክ ቃል የሚያስተምረውን ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መማር፣ በተማርነው መሠረት መመላለስ ከዚያም ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ ማስተማር ይኖርብናል። ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስን በምታጠናበት ጊዜ ለክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መሠረት የሆኑትን ይሖዋ ያወጣቸውን የአቋም ደረጃዎች ለመረዳት ንቁ ሁን። ከመጽሐፍ ቅዱስ በምታገኘው ምክርና ትምህርት ላይ አሰላስል። ከዚያም የተማርከውን ተግባራዊ ከማድረግ ወደ ኋላ አትበል። በእርግጥም ይህ ድፍረትና ቆራጥነት ይጠይቃል። ሰዎች ስንባል ፍጹማን ባለመሆናችን ለሠራነው ስህተት ሰበብ ማቅረብ እንዲሁም ክርስቲያናዊውን ሥነ ምግባር ለመጣስ የተገደድንበትን ምክንያት መደርደር ይቀናናል። ጳውሎስ የጠቀሳቸው አይሁዳውያን እንዲህ ዓይነት የረቀቀ ሰበብ አስባብ የማቅረብ ወይም ሰዎች የተሳሳተ ግምት ላይ እንዲደርሱ የማድረግ ችሎታ የነበራቸው ይመስላል። ይሁን እንጂ የጳውሎስ ቃላት ክርስቲያናዊው የሥነ ምግባር አቋም በግለሰቦች ምርጫ ዝቅ ሊደረግ ወይም ችላ ሊባል እንደማይገባው ያሳያሉ።

12. የሥነ ምግባር አቋማችን በጥሩም ሆነ በመጥፎ ጎኑ የይሖዋ አምላክን ስም ሊነካው የሚችለው እንዴት ነው? ይህን ሐቅ መገንዘብ ጠቃሚ የሆነውስ ለምንድን ነው?

12 ሐዋርያው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ሥነ ምግባር መማርና ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ የሆነበትን ዋነኛ ምክንያት አስረግጦ ተናግሯል። አይሁዳውያን ያሳዩት ተገቢ ያልሆነ ባሕርይ ይሖዋን አስነቅፎታል:- “በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን? በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና።” (ሮሜ 2:​23, 24) ዛሬም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ ክርስቲያናዊውን ሥነ ምግባር ችላ የምንል ከሆነ አምላክን እናስነቅፋለን። አምላክ ያወጣውን የሥነ ምግባር መሥፈርት በጥብቅ የምንከተል ከሆነ ግን እርሱን እናስከብረዋለን። (ኢሳይያስ 52:​5፤ ሕዝቅኤል 36:​20) ይህን መገንዘብህ የሚያጋጥምህን ፈተና ለማለፍ ቀላሉ ወይም አመቺው መንገድ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን ችላ ማለት እንደሆነ እንዲሰማህ በሚያደርግ ሁኔታ ውስጥ በምትገባበት ጊዜም እንኳ አቋምህን እንዳታላላ ይረዳሃል። ከዚህም በላይ ጳውሎስ ከተናገራቸው ቃላት ሌላም የምንማረው ነገር አለ። የምታሳየው ባሕርይ የአምላክን ስም እንደሚነካ በግል ከመገንዘብህ በተጨማሪ ሌሎችን በምታስተምርበት ጊዜ እየተማሩት ያለውን የሥነ ምግባር መሥፈርት ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የሚኖራቸው አቋም የይሖዋን ስም ሊነካ እንደሚችል እንዲገነዘቡ እርዳቸው። ክርስቲያናዊው ሥነ ምግባር እርካታና ጥሩ ጤንነት ሊያስገኝ የሚችል ከመሆኑም በላይ የሥነ ምግባር መሥፈርቱን ያወጣውንና ተግባራዊ እንዲሆን ያዘዘውን አካልም ይነካል።​​—⁠⁠መዝሙር 74:​10፤ ያዕቆብ 3:​17

13. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ምግባርን በሚመለከት የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) በ1 ተሰሎንቄ 4:​3-7 ላይ የሚገኘው ምክር ፍሬ ነገር ምንድን ነው?

13 ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን መጠበቅ ወይም አለመጠበቅ ሌሎች ሰዎችንም ይነካል። ይህንን ለመረዳት እርሱ ያወጣውን የሥነ ምግባር መሥፈርት ተግባራዊ ማድረግ የሚያስገኘውን ጥቅምና ችላ ማለት የሚያስከትለውን ውጤት በተመለከተ ከአምላክ ቃል ውስጥ አንዳንድ ምሳሌዎችን መመልከት ትችላለህ። (ዘፍጥረት 39:​1-9, 21፤ ኢያሱ 7:​1-25) እንዲሁም ሥነ ምግባርን አስመልክቶ የሚከተለውን ግልጽ ምክር ታገኛለህ:- “ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤ ከዝሙት እንድትርቁ፣ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፣ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ . . . ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ ወንድሙንም አያታልል [“የወንድሙን መብት አይጋፋ፣” NW ]። ለርኩሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና።”​​—⁠⁠1 ተሰሎንቄ 4:​3-7

14. በአንደኛ ተሰሎንቄ 4:​3-7 ላይ የሚገኘውን ምክር በሚመለከት ራስህን ምን ብለህ መጠየቅ ትችላለህ?

14 ይህን ጥቅስ ያነበበ ማንኛውም ሰው የጾታ ብልግና መፈጸም ክርስቲያናዊውን የሥነ ምግባር ሕግ እንደሚያስጥስ በቀላሉ መገንዘብ ይችላል። ሆኖም ጥቅሱን ይበልጥ ሰፋ አድርገህ መገንዘብ ትችላለህ። አንዳንዶቹ ቁጥሮች ተጨማሪ ምርምር ለማድረግና ይበልጥ ለማሰላሰል ስለሚያስችሉ ጥልቅ ማስተዋል ያስገኛሉ። ለምሳሌ ያህል እንዲህ እያልክ መጠየቅ ትችላለህ:- ጳውሎስ አንድ ሰው ዝሙት መፈጸሙ ‘ወንድሙን ማታለሉና የወንድሙንም መብት መጋፋቱ’ እንደሆነ ሲናገር ምን ማለቱ ነው? እዚህ ላይ የተጠቀሰው መብት ምን ነገሮችን ያጠቃልላል? ይህን ጉዳይ በሚገባ መረዳትህ ክርስቲያናዊ የሥነ ምግባር አቋምህን ጠብቀህ እንድትኖር ተጨማሪ ጥንካሬ የሚሰጥህ እንዴት ነው? እንዲህ ያለ ምርምር ማድረግህ ሌሎችን ለማስተማር የተሻለ ብቃት እንዲኖርህና አምላክን እንዲያከብሩ እንድትረዳቸው የሚያስችልህ እንዴት ነው?

ሌሎችን ለማስተማር ጥሩ ምርምር ማድረግ

15. በግል ጥናትህ ራስህን ለማስተማር በየትኞቹ መሣሪያዎች መጠቀም ትችላለህ?

15 የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ለማስተማር ሲያጠኑ በሚፈጠሩባቸው ጥያቄዎች ላይ ምርምር ለማድረግ የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ መሣሪያዎች አሏቸው። በብዙ ቋንቋዎች የሚገኘው አንደኛው መሣሪያ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ ነው። ይህ መጽሐፍ ካለህ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ በሚያዘጋጁአቸው ጽሑፎች ላይ የምትፈልገውን ማብራሪያ በአርዕስት ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ዝርዝር አማካኝነት በቀላሉ ማግኘት ትችላለህ። የይሖዋ ምሥክሮች በብዙ ዋና ዋና ቋንቋዎች ማግኘት የሚችሉት ሌላው መሣሪያ በኮምፒውተር የተዘጋጀው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ቤተ መጻሕፍት ነው። በሲዲ የተዘጋጀው ይህ የኮምፒውተር ፕሮግራም ብዙ ቁጥር ያላቸው ጽሑፎችን አንድ ላይ አጠቃልሎ ይዟል። ፕሮግራሙ አንድ ሰው በአርዕስቶችና ማብራሪያ በተሰጠባቸው ጥቅሶች ላይ ምርምር እንዲያደርግ ያስችለዋል። ከእነዚህ መሣሪያዎች መካከል አንዱን ወይም ሁለቱንም የማግኘት አጋጣሚ ካለህ ሌሎችን ለማስተማር የአምላክን ቃል በምታጠናበት ጊዜ አዘውትረህ ተጠቀምባቸው።

16, 17. (ሀ) በ1 ተሰሎንቄ 4:​6 ላይ የተጠቀሰውን መብት በሚመለከት ተጨማሪ እውቀት ማግኘት የምትችለው ከየት ነው? (ለ) ዝሙት የሚፈጽም ሰው የሌሎችን መብት የሚጋፋው እንዴት ነው?

16 እስቲ ከላይ የተጠቀሰውን የ1 ተሰሎንቄ 4:​3-7 ጥቅስ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። መብትን በተመለከተ ጥያቄ ተነስቷል። ስለ ማን መብት? ይህ መብት ሊጣስ የሚችለው እንዴት ነው? ከላይ በተጠቀሱት የማጥኛ መሣሪያዎች አማካኝነት በእነዚህ ቁጥሮች ሌላው ቀርቶ ጳውሎስ በጠቀሰው የመብት ጉዳይ ላይ እውቀት የሚጨምሩ በርካታ ማብራሪያዎችን ማግኘት ትችላለህ። እነዚህን ማብራሪያዎች ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል ጥራዝ 1፣ ገጽ 863-4፤ እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት​​⁠⁠እንዴት ማግኘት ትችላለህ? ገጽ 145 እና ከኅዳር 15, 1989 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 31 ላይ ማንበብ ትችላለህ። (በእንግሊዝኛ የሚገኙ ናቸው።)

17 ጥናትህን ስትቀጥል ጳውሎስ የተናገራቸው ቃላት ምን ያህል ትክክል መሆናቸውን ከእነዚያ ጽሑፎች ትገነዘባለህ። ዝሙት የሚፈጽም ሰው በአምላክ ላይ ኃጢአት ከመሥራቱም በላይ ራሱን ለበሽታ ያጋልጣል። (1 ቆሮንቶስ 6:​18, 19፤ ዕብራውያን 13:​4) አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ዝሙት ሲፈጽም የተለያዩ መብቶችን እንደሚያሳጣት መገንዘብ አለበት። ንጹሕ የሥነ ምግባር አቋምና በጎ ሕሊና እንድታጣ ያደርጋታል። ያላገባች ከሆነ ክብረ ንጽሕናዋን ጠብቃ ትዳር ለመመሥረት ያላትን መብት የሚያሳጣት ከመሆኑም በላይ ወደፊት ባልዋ የሚሆነው ሰው ንጽሕናዋን እንደጠበቀች የማግኘት መብቱንም ይጋፋዋል። ባለ ትዳር ከሆነች ደግሞ የሴትዮዋን ወላጆችና የባለቤትዋን ስሜት ይጎዳል። የጾታ ብልግና የፈጸመው ሰው የቤተሰቡን መልካም ስም ያጎድፋል። የክርስቲያን ጉባኤ አባል ከሆነ ደግሞ የጉባኤውን ስም በማጥፋት ነቀፋ ያስከትልበታል።​​—⁠⁠1 ቆሮንቶስ 5:​1

18. ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን በሚመለከት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

18 መብትን አስመልክቶ የተሰጡት እነዚህ ማብራሪያዎች ስለ 1 ተሰሎንቄ 4:​3-7 ያለህን ማስተዋል ይበልጥ አላሰፋልህም? እንዲህ ያለው ጥናት ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝ ምንም ጥርጥር የለውም። በጥናቱ በገፋህ መጠን ራስህን እያስተማርህ ትሄዳለህ። የአምላክ ቃል እውነት እንደሆነና ኃይል እንዳለው ያለህ ግንዛቤ ያድጋል። ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥምህ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን ለመጠበቅ ያደረግኸውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልሃል። እንዲሁም በአስተማሪነትህ ምን ያህል ውጤታማ ልትሆን እንደምትችል አስብ! ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን እውነት ለሌሎች በምታስተምርበት ጊዜ 1 ተሰሎንቄ 4:​3-7ን በደንብ ልታብራራላቸውና ለክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ያላቸው ማስተዋልና አድናቆት እንዲጨምር ልትረዳቸው ትችላለህ። ስለሆነም የምታደርገው ጥናት አንተም ሆንክ ሌሎች ሰዎች አምላክን እንድታከብሩ ሊረዳችሁ ይችላል። ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ከጻፈው ደብዳቤ ላይ እዚህ ላይ የጠቀስነው አንድ ምሳሌ ብቻ ነው። ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ሌሎች ብዙ ገጽታዎችም አሉት። ምርምር ልታደርግባቸው፣ በሥራ ልታውላቸውና ለሌሎች ልታስተምራቸው የምትችላቸው ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ሌሎች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችና ምክሮች አሉ።

19. ክርስቲያናዊውን ሥነ ምግባር አጥብቀህ መያዝ ያለብህ ለምንድን ነው?

19 ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን መጠበቅ ጥቅም እንደሚያስገኝ ምንም ጥያቄ የለውም። ያዕቆብ 3:​17 ከይሖዋ አምላክ የምትገኘው “ላይኛይቱ ጥበብ” “በመጀመሪያ ንጽሕት ናት” ይላል። ይህ አምላክ ያወጣውን የሥነ ምግባር መሥፈርት መከተል እንዳለብን በግልጽ ያመለክታል። እንዲያውም ይሖዋ እርሱን ወክለው መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተምሩ ሰዎች ‘በንጽሕና’ ረገድ ጥሩ ምሳሌ እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 4:​11, 12) ጳውሎስንና ጢሞቴዎስን የመሳሰሉ የጥንት ደቀ መዛሙርት የተከተሉት ንጹሕ አኗኗር ለዚህ በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል። የሥነ ምግባር ብልግና ከመፈጸም ተቆጥበዋል። እንዲያውም ጳውሎስ “ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ የማይገቡ ናቸውና አይሁኑ” ሲል ጽፏል።​​—⁠⁠ኤፌሶን 5:​3, 4

20, 21. ሐዋርያው ዮሐንስ በ1 ዮሐንስ 5:​3 ላይ ከመዘገበው ሐሳብ ጋር የምትስማማው ለምንድን ነው?

20 የአምላክ ቃል የያዘው የሥነ ምግባር መሥፈርት ግልጽና የማያሻማ ከመሆኑም በላይ ሸክም አይደለም። ከሐዋርያት ሁሉ ረጅም ዕድሜ የኖረው ዮሐንስ ይህን በግልጽ ተረድቷል። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ባየው ነገር ላይ ተመሥርቶ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ጉዳት እንደሌለው ተገንዝቧል። ከዚህ ይልቅ ጥሩ፣ ጠቃሚና መልሶ የሚክስ መሆኑን ተመልክቷል። ዮሐንስ “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም” ብሎ በመጻፍ ይህን ጠበቅ አድርጎ ተናግሯል።​​—⁠⁠1 ዮሐንስ 5:​3

21 ይሁን እንጂ ዮሐንስ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን በመጠበቅ አምላክን መታዘዛችን አማራጭ እንደሌለው የተናገረው ከችግር ወይም አለመታዘዛችን ከሚያስከትለው መዘዝ ስለሚያድነን ብቻ እንዳልሆነ ልብ በል። ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን በመጠበቅ አምላክን መታዘዛችን ለይሖዋ አምላክ ያለንን ፍቅር ለማሳየት የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ እንደሆነ በመግለጽ ሊኖረን የሚገባውን ትክክለኛ አመለካከት ተናግሯል። በእርግጥም እኛ ራሳችን አምላክን መውደድ ተምረን ሌሎችም እንዲወዱት ማስተማራችን ከፍ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹን ተግባራዊ ማድረግን የሚጠይቅ ነው። አዎን፣ ይህም ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን ማስተማር ማለት ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ጆሴፈስ አይሁዳውያን ለቅዱስ ነገሮች አክብሮት እንዳላቸው አድርጎ ቢገልጽም የአምላክን ሕግ እንዲህ በማለት አስቀምጦታል:- “ማንኛውም ሰው ሌሎች ከተሞች የሚያመልኳቸውን አማልክት መስደብ ወይም ቤተ መቅደሶቻቸውን መዝረፍ ወይም ለየትኛውም አምላክ የተሰጡ ንዋየ ቅዱሳትን መውሰድ የለበትም።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።)​​—⁠⁠ጁዊሽ አንቲኩዊቲስ ጥራዝ 4፣ ምዕራፍ 8፣ አንቀጽ 10

b ጁዊሽ አንቲኩዊቲስ ጥራዝ 18፣ ምዕራፍ 3፣ አንቀጽ 5።

ታስታውሳለህን?

• ሌሎችን ለማስተማር ከመነሳታችን በፊት ራሳችንን ማስተማር ያለብን ለምንድን ነው?

• ባሕርያችን የይሖዋን ስም ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው?

• ዝሙት የሚፈጽም ሰው የእነማንን መብት ይጋፋል?

• ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን በሚመለከት ያለህ ቁርጥ አቋም ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ትእዛዛቱ ከባዶች አይደሉም’