በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰው ልጅ ችግሮች በቅርቡ ይወገዳሉ!

የሰው ልጅ ችግሮች በቅርቡ ይወገዳሉ!

የሰው ልጅ ችግሮች በቅርቡ ይወገዳሉ!

“የበጎ አድራጎት ተግባራት የግጭቶችን ዋነኛ መንሥኤ ለማስወገድ ተብሎ በተነደፈ ሰፊ ዕቅድ ካልታቀፉና ፖለቲካዊ ድጋፍ ካላገኙ በቀር የሚያስገኙት ጥቅም ውስን ነው። በተደጋጋሚ ከተሞክሮ እንደታየው የበጎ አድራጎት ተግባር በራሱ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ችግሮች ሊፈታ አይችልም።”​​—⁠ዘ ስቴት ኦቭ ዘ ዎርልድስ ሪፊውጂስ 2000

ከፍተኛ የሆነ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ ቢካሄድም የሰው ልጅ ችግሮች እየጨመሩ በመሄድ ላይ ናቸው። ዘላቂ የሆነ ፖለቲካዊ መፍትሔ ይገኝ ይሆን? እውነቱን ለመናገር ሁኔታው ብዙም ተስፋ የሚጣልበት አይደለም። ታዲያ ተስፋችንን በማን ላይ ልንጥል እንችላለን? ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ መግቢያ ላይ ባሰፈረው ጠቃሚ መልእክት አምላክ የሰው ልጅ ችግሮችን በሙሉ ስለሚያስወግድበት መንገድ አብራርቷል። እንዲያውም አምላክ ይህንን ለማድረግ መሣሪያ አድርጎ ስለሚጠቀምበት አካል ተናግሯል። ይህ አካል ዛሬ የሚያሠቃዩንን ችግሮች ከሥራቸው ነቅሎ የሚያስወግድ ነው። ጳውሎስ ምን እንዳለ ለምን አትመረምርም? መልእክቱ የሚገኘው በኤፌሶን 1:​3-10 ላይ ነው።

“እንደገና በክርስቶስ ለመጠቅለል”

ሐዋርያው የአምላክ ዓላማ “በተወሰኑት ዘመናት ፍጻሜ ላይ ለማስተዳደር ” እንደሆነ ተናግሯል። ይህ ምን ማለት ነው? ይህ ማለት አምላክ “በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ [“እንደገና፣” NW ] በክርስቶስ ለመጠቅለል” እርምጃ የሚወስድበት የተወሰነ ጊዜ አለው ማለት ነው። (ኤፌሶን 1:10) አዎን፣ አምላክ እንደገና በሰማይና በምድር ያለውን ነገር ሁሉ ሙሉ በሙሉ በእሱ ቁጥጥር ሥር አንድ ለማድረግ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ጄ ኤች ቴየር እዚህ ላይ ‘እንደገና አንድ ላይ ለመጠቅለል’ ተብሎ ስለተገለጸው ሐረግ የሚከተለውን ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ሰንዝረዋል:- “ሁሉንም ነገሮችና (በኃጢአት ምክንያት ተለይተው የቆዩትን) ፍጡራን . . . በክርስቶስ ከራሱ ጋር አንድ ያደርጋቸዋል።”

አምላክ ይህንን ዝግጅት ማድረግ ያስፈለገው የሰው ልጅ ከአምላክ በመራቁ ነው። በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ከሰይጣን ዲያብሎስ ጋር በመተባበር በአምላክ ላይ ዓመፁ። ምን ነገር መልካም፣ ምን ነገር መጥፎ እንደሆነ ራሳቸው በመወሰን በራሳቸው ፈቃድ መመራት ፈልገው ነበር። (ዘፍጥረት 3:1-5) መለኮታዊው ፍትሕ በሚያዝዘው መሠረት ከአምላክ ቤተሰብ ተባረሩ እንዲሁም ከእርሱ ጋር የነበራቸውን ወዳጅነት አጡ። ሰብዓዊው ኅብረተሰብም ፍጽምና የጎደለው እንዲሆንና በዚህም ሳቢያ በዛሬው ጊዜ እየደረሱብን ላሉት አስከፊ መዘዞች እንዲጋለጥ አደረጉት።​​—⁠⁠ሮሜ 5:12

ክፋት ለጊዜው ተፈቀደ

አንዳንዶች ‘አምላክ ለምን እንደዚያ እንዲያደርጉ ፈቀደላቸው? ታላቅ ኃይሉን ተጠቅሞ ፈቃዱን እንዲያደርጉ በማስገደድ ዛሬ የሚደርስብን ሥቃይና መከራ እንዲቀር ለምን አላደረገም?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። እንደዚያ ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ይመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለው የኃይል ድርጊት ምን የሚያረጋግጠው ነገር ይኖራል? ኃይል ስላለው ብቻ ገና ተቃውሞ ሲነሳ በተቃዋሚዎቹ ላይ የኃይል እርምጃ የሚወስድን ግለሰብ ታደንቃለህ ወይም በሚወስደው እርምጃ ትስማማለህን? እንደማትስማማ የታወቀ ነው።

እነዚያ ዓመፀኞች የተገዳደሩት ሁሉን ማድረግ የሚችለውን የአምላክ ኃይል አልነበረም። የተገዳደሩት የአምላክን የመግዛት መብትና የአገዛዙን ትክክለኛነት ነበር። ይሖዋ ለተነሱት አከራካሪ ጉዳዮች የማያዳግም ምላሽ ለመስጠት ሲል ፍጡሮቹ ያለ እሱ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ለተወሰነ ጊዜ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ፈቅዶላቸዋል። (መክብብ 3:1፤ ሉቃስ 21:24) ያ ጊዜ ሲያበቃ ምድርን እንደገና ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ጣልቃ ይገባል። በዚያን ጊዜ ለምድር ነዋሪዎች ዘላቂ ሰላም፣ ደስታ እንዲሁም ብልጽግና የሚያመጣው የእሱ አገዛዝ ብቻ መሆኑ ግልጽ ይሆናል። ከዚያም ምድርን የሚያስተዳድሯት ጨቋኝ ገዥዎች በሙሉ ለዘላለም ይወገዳሉ።​​—⁠⁠መዝሙር 72:12-14፤ ዳንኤል 2:44

“ዓለም ሳይፈጠር”

ይሖዋ ይህንን ሁሉ ለማድረግ ዓላማ ያወጣው ከረዥም ጊዜ በፊት ነው። ጳውሎስ “ዓለም ሳይፈጠር” ሲል ገልጾታል። (ኤፌሶን 1:4፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ይህ ማለት ምድር ሳትፈጠር ወይም አዳምና ሔዋን ሳይፈጠሩ ማለት አይደለም። ያን ጊዜ የነበረው ዓለም “እጅግ መልካም” ከመሆኑም በላይ ዓመፅም አልተቀሰቀሰም ነበር። (ዘፍጥረት 1:31) ታዲያ ሐዋርያው ጳውሎስ የትኛውን “ዓለም” ማለቱ ነበር? ሊዋጅ የሚችለውን ኃጢአተኛና ፍጽምና የጎደለው የአዳምና የሔዋን ልጆች ዓለም ማለቱ ነበር። ይሖዋ ገና ምንም ልጆች ሳይወለዱ በፊት፣ ሊዋጁ የሚችሉትን የአዳም ዘሮች ነፃ የሚያወጣበትን መንገድ አስቀድሞ ያውቅ ነበር።​​—⁠⁠ሮሜ 8:20

እርግጥ ነው፣ ይህ ማለት የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ነገሮችን ሰዎች በሚያከናውኑበት መንገድ ያከናውናል ማለት አይደለም። ሰዎች ድንገተኛ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ በመገንዘብ ያንን ለመቋቋም የሚያስችሏቸው ብዙ ዝርዝር እቅዶች ያወጣሉ። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ግን ዓላማ አለው፤ ዓላማውንም ይፈጽማል። ያም ሆኖ ይሖዋ ለሰው ዘር ዘላቂ እረፍት ለማስገኘት ነገሮችን እንዴት ሊያከናውን እንዳሰበ ጳውሎስ አብራርቷል። እነዚህ እርምጃዎች ምንድን ናቸው?

እረፍት የሚያመጣው ማን ነው?

ጳውሎስ በመንፈስ የተቀቡት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በአዳማዊው ኃጢአት ምክንያት የተፈጠሩ ጉዳቶችን በማስወገድ ረገድ ልዩ ድርሻ እንደሚኖራቸው አብራርቷል። ከኢየሱስ ጋር በሰማያዊ መንግሥቱ እንድንገዛ ይሖዋ “በክርስቶስ መረጠን” ብሏል። ጳውሎስ ይህንን የበለጠ ሲያብራራው ይሖዋ “በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ልጆቹ እንድንሆን አስቀድሞ ወሰነን” ብሏል። (ኤፌሶን 1:4, 5 የ1980 ትርጉም፤ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ አልመረጣቸውም ወይም አስቀድሞ አልወሰናቸውም። ሆኖም ሰይጣን ዲያብሎስ ከአዳምና ከሔዋን ጋር በመተባበር በሰብዓዊው ቤተሰብ ላይ ያመጣውን ጉዳት በማስወገዱ ሥራ የታመኑና ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን ያቀፈ አንድ ቡድን ከክርስቶስ ጋር እንዲካፈል ይሖዋ አስቀድሞ መርጧል።​​—⁠⁠ሉቃስ 12:32፤ ዕብራውያን 2:14-18

እንዴት ያለ አስገራሚ ነገር ነው! ሰይጣን በመጀመሪያ በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ ግድድር ባስነሳ ጊዜ የአምላክ ሰብዓዊ ፍጡሮች ጉድለት እንዳለባቸውና ከባድ ስደት ከደረሰባቸው ወይም ማባበያ ካገኙ ሁሉም በአምላክ አገዛዝ ላይ እንደሚያምፁ ተናግሮ ነበር። (ኢዮብ 1:7-12፤ 2:2-5) ይሖዋ አምላክ ድንቅ በሆነ ‘የታላቅ ጸጋው ’ መግለጫ አማካኝነት ኃጢአተኛ ከሆነው የአዳም ቤተሰብ ውስጥ ጥቂቶች መንፈሳዊ ልጆቹ እንዲሆኑ በማድረግ በምድራዊ ፍጡሮቹ ላይ ትምክህት እንዳለው ከጊዜ በኋላ አሳይቷል። በዚህ አነስተኛ ቡድን ውስጥ የተጠቃለሉት በሰማይ እንዲያገለግሉ ይወሰዳሉ። የሚወሰዱት ለምን ዓላማ ነው?​​—⁠⁠ኤፌሶን 1:3-6፤ ዮሐንስ 14:2, 3፤ 1 ተሰሎንቄ 4:15-17፤ 1 ጴጥሮስ 1:3, 4

ሐዋርያው ጳውሎስ አምላክ ልጆቹ አድርጎ የተቀበላቸው እነዚህ ሰዎች በሰማያዊ መንግሥቱ “ከክርስቶስ ጋር አብረ[ው] ወራሾች” እንደሚሆኑ ተናግሯል። (ሮሜ 8:14-17) ነገሥታትና ካህናት በመሆን ሰብዓዊውን ቤተሰብ ዛሬ ከሚያጋጥመው ሥቃይና መከራ ነፃ በማውጣቱ ሥራ ይካፈላሉ። (ራእይ 5:9,10) “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩ” እውነት ነው። በቅርቡ ግን እነዚህ በልዩ ሁኔታ የተመረጡ የአምላክ ልጆች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመተባበር ታዛዥ የሆነ የሰው ልጅ በሙሉ “ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ” እንደገና “ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ” ያደርጋሉ።​​—⁠⁠ሮሜ 8:18-22

‘በቤዛው ተዋጀን’

ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው አምላክ ሊዋጅ ለሚችለው የሰው ዘር ዓለም ባሳየው በጣም ድንቅና ልብ የሚነካ የማይገባን ደግነቱ መግለጫ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ነው። ጳውሎስ “ከእግዚአብሔር ጸጋ ሙላት የተነሣ በ[ኢየሱስ ክርስቶስ ] ደም ተዋጅተን የኃጢአታችንን ይቅርታ አገኘን” ሲል ጽፏል።​​—⁠⁠ኤፌሶን 1:7 የ1980 ትርጉም፤ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክን ዓላማ በማስፈጸም በኩል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። (ዕብራውያን 2:10) የእሱ ቤዛዊ መሥዋዕት ይሖዋ ሕግጋቱንና መመሪያዎቹን ሳይጥስ ከአዳም ዘሮች መካከል ጥቂቶቹን የሰማያዊ ቤተሰቡ አባላት አድርጎ ለመቀበልና የሰውን ዘር አዳማዊው ኃጢአት ካስከተለው መዘዝ ለመገላገል የሚያስችለውን ሕጋዊ መሠረት ጥሏል። (ማቴዎስ 20:28፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:6) ይሖዋ ነገሮችን ያከናወነው ከጽድቁ ጋር በሚስማማና ፍጹም የሆነውን ፍትሑን በሚያሟላ መልኩ ነው።​​—⁠⁠ሮሜ 3:22-26

የአምላክ “ቅዱስ ምስጢር”

በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ እንዴት እንደሚፈጽም በግልጽ አልተናገረም ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ‘የፈቃዱን ቅዱስ ምሥጢር ለክርስቲያኖች አስታወቀ።’ (ኤፌሶን 1:9) ጳውሎስና ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሆኑት ባልደረቦቹ በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚጫወተውን ድንቅ ሚና በግልጽ ተገነዘቡ። ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊው መንግሥቱ ተባባሪ ወራሾች በመሆን የሚኖራቸውን ልዩ ሚናም መረዳት ጀመሩ። (ኤፌሶን 3:5, 6, 8-11) አዎን፣ አምላክ በሰማይ ብቻ ሳይሆን በምድርም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚጠቀምበት መሣሪያ በኢየሱስ ክርስቶስ እና በተባባሪ ገዢዎቹ የሚመራው ንጉሣዊ መንግሥት ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10) በዚህ መንግሥት በኩል ይሖዋ ለዚህች ምድር የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ይፈጸማል።​​—⁠⁠ኢሳይያስ 45:18፤ 65:21-23፤ ሥራ 3:21

ምድርን ከጭቆናና ከፍትሕ መጓደል ለማጽዳት ቀጥተኛ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ቀርቧል። ሆኖም ይሖዋ የተሐድሶ እርምጃ መውሰድ የጀመረው በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ቀን ነበር። እንዴት? ከክርስቶስ ጋር የሚገዙትን ‘በሰማይ ያለውን ሁሉ ’ መሰብሰብ በመጀመር ነው። ከእነዚህ መካከል የኤፌሶን ክርስቲያኖችም ይገኙበታል። (ኤፌሶን 2:4-7) አሁን በእኛ ዘመን ደግሞ ይሖዋ ‘በምድር ያለውን ሁሉ ሲሰበስብ ቆይቷል። (ኤፌሶን 1:​10 NW ) ዓለም አቀፍ በሆነ የስብከት ዘመቻ አማካኝነት በኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚመራው ንጉሣዊ መንግሥቱ ለአሕዛብ ሁሉ ምሥራች እያስነገረ ነው። ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች በዚህ ባለንበት ጊዜም እንኳ መንፈሳዊ ጥበቃና ፈውስ ወደሚገኝበት ቦታ እየተሰበሰቡ ነው። (ዮሐንስ 10:16) በቅርቡ በጸዳች ምድራዊ ገነት ውስጥ ከሁሉም ዓይነት የፍትሕ መጓደልና ሥቃይ ነጻ ይሆናሉ።​​—⁠⁠2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 11:18

የተጨቆኑ የሰው ዘሮችን ለመርዳት የሚደረጉት የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች “ብዙ ድንቅ እርምጃዎች አስመዝግበዋል።” (ዘ ስቴት ኦቭ ዘ ዎርልድስ ቺልድረን 2000 ) ሆኖም ከሁሉ የላቀው ድንቅ እርምጃ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ተባባሪ ገዢዎቹ በሰማያዊው መንግሥት መስተዳድር በኩል በቅርቡ የሚወስዱት እርምጃ ነው። ለግጭቶችም ሆነ ለሌሎቹ ችግሮች መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ በማያዳግም ሁኔታ ያስወግዳሉ። ለሰው ዘር ችግሮች በሙሉ እልባት ያስገኛሉ።​​—⁠⁠ራእይ 21:1-4

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የበጎ አድራጎት ተግባራት የሰውን ዘር ችግሮች አላስወገዱም

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሰውን ዘር ከአዳማዊ ኃጢአት ነፃ አውጥቶታል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዛሬም ቢሆን መንፈሳዊ ጥበቃና ፈውስ ማግኘት ይቻላል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቅርቡ በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት ከማንኛውም ችግር ሙሉ በሙሉ እንገላገላለን