በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰው ልጅ ችግሮች የሚወገዱበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

የሰው ልጅ ችግሮች የሚወገዱበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

የሰው ልጅ ችግሮች የሚወገዱበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

የዓለምን ሁኔታ አስመልክቶ በአየርላንድ የወጣ አንድ ዘገባ “ከዓለም ሕዝብ መካከል ሩብ ያህሉ በድህነት ይማቅቃል፣ 1.3 ቢልዮን የሚያክሉት በቀን ከ1 የአሜሪካ ዶላር [8 ብር ገደማ] ባነሰ ገቢ ኑሯቸውን ይገፋሉ፣ 1 ቢልዮን የሚያክሉት መሃይማን ናቸው፣ 1.3 ቢልዮን ያህሉ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ አያገኙም እንዲሁም በየቀኑ 1 ቢልዮን የሚያክሉ ሰዎች የሚቀምሱት አጥተው ይራባሉ” ይላል።

የሰው ልጅ ለዓለም ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት እንደተሳነው የሚያሳይ እንዴት ያለ አሳዛኝ እውነታ ነው! በዘገባው ላይ ከተገለጹት ሰዎች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸው የችግሩን አስከፊነት ይበልጥ የሚያጎላ ነው። በዚህ በ21ኛው መቶ ዘመንም እንኳን ‘ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሰዎች በየዕለቱ ሰብዓዊ መብታቸው እየተረገጠ’ መሆኑ የሚያሳዝን አይደለምን?​​—⁠ዘ ስቴት ኦቭ ዘ ዎርልድስ ቺልድረን 2000

“በአንድ ትውልድ ዕድሜ ውስጥ አዲስ ዓለም ማምጣት”

የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት “በእነዚህ ችግሮች ምክንያት . . . በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሰዎች ላይ ያጠላው የተስፋ መቁረጥ ደመና እንደሚገፈፍ” ያለውን ትምክህት ገልጿል። ይህ ድርጅት እነዚህ በቢልዮን የሚቆጠሩ ምስኪን ሰዎች ዛሬ እየታገሏቸው ያሉት ችግሮች “ሊወገዱ ወይም ሊለወጡ የማይችሉ” አይደሉም ይላል። እንዲያውም “በአንድ ትውልድ ዕድሜ ውስጥ አዲስ ዓለም ለማምጣት ሁሉም ሰው የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ” ጥሪ ያቀረበ ሲሆን ይህ አዲስ ዓለም ሁሉም የሰው ልጅ “ከድህነትና ከመድልዎ፣ ከዓመፅና ከበሽታ የሚገላገልበት” ዓለም እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋል።

እንደዚህ ዓይነት አስተያየት የሚሰነዝሩት ሰዎች ዛሬም እንኳን አሳቢ የሆኑ ግለሰቦች “መቋጫ ያላቸው የማይመስሉት ግጭቶችና ብጥብጦች” ያስከተሏቸውን አሳዛኝ ውጤቶች ለመቅረፍ እያከናወኑ ያሉት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ የቼርኖቤል ቺልድረንስ ፕሮጀክት “በኑክሌር ፍንዳታ ምክንያት በካንሰር የተጠቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕፃናትን ሥቃይ በመቀነስ በኩል ትልቅ እርዳታ አበርክቷል።” (ዚ አይሪሽ ኤግዛማይነር፣ ሚያዝያ 4, 2000) ትላልቅም ሆኑ ትናንሽ የእርዳታ ድርጅቶች በጦርነትም ሆነ በሌሎች አደጋዎች ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች ሕይወት በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንዳለ አይካድም።

ያም ሆኖ በእንደዚህ ዓይነት የበጎ አድራጎት ሥራ የተሰማሩ ሰዎች እውነታውን አይሸሽጉም። ከፊታቸው የተጋረጡት ችግሮች “ሌላው ቢቀር ከአሥር ዓመት በፊት ከነበረው እንኳን የበለጠ እንደተስፋፉና ሥር እንደሰደዱ” ያውቃሉ። አይሪሽ ቻሪቲ ኮንሰርን የተባለው ድርጅት ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት ዴቪድ ቤግ ሞዛምቢክ አውዳሚ የሆነ የጎርፍ መጥለቅለቅ ሲደርስባት “የድርጅቱ ሠራተኞች፣ ደጋፊዎችና እርዳታ ሰጪዎች አስደናቂ በሆነ መንገድ ምላሽ እንደሰጡ” ተናግረዋል። “ሆኖም እንደዚህ ዓይነት መጠነ ሰፊ አደጋዎችን ብቻችንን ልንቋቋማቸው አንችልም” ሲሉ አክለው ገልጸዋል። በአፍሪካ እርዳታ ለመስጠት እየተደረጉ ስላሉት ጥረቶች ሲናገሩ “ያሉን ጥቂት የተስፋ ጭላንጭሎችም ሊጠፉ ተቃርበዋል” በማለት ሐቁን ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። ብዙዎች ይህ አባባል በዓለም ዙሪያ ያለውን ሁኔታ በትክክል እንደሚገልጸው ይሰማቸዋል።

“በአንድ ትውልድ ዕድሜ ውስጥ አዲስ ዓለም” ለማምጣት የታለመው ግብ በእርግጥ እውን ይሆናል ብለን መጠበቅ እንችላለንን? ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ያለው የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ የሚያስመሰግን ቢሆንም ፍትሕ የሰፈነበት አዲስ ሰላማዊ ዓለም ለማግኘት ወደ ሌላ የተሻለ አማራጭ ዞር ማለት እንደሚያስፈልግ ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የተሻለ አማራጭ አስመልክቶ የሚሰጠውን ሐሳብ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ገጽ 3፣ ልጆቹ:- UN/DPI Photo by James Bu