በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

አንድ ክርስቲያን የራሱን ሕይወት ባጠፋ ሰው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ማቅረብ ይችላልን?

የራሱን ሕይወት እንዳጠፋ በሚታወቅ ሰው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ በንጹህ ሕሊና ንግግር መስጠት ይችል እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን የእያንዳንዱ ክርስቲያን ኃላፊነት ነው። ይህንን ውሳኔ ሲያደርግ ግን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ሊያስብባቸው ይገባል:- ይሖዋ የራስን ሕይወት ስለ ማጥፋት ያለው አመለካከት ምንድን ነው? በእርግጥ ግለሰቡ ሕይወቱን ያጠፋው በራሱ እጅ ነውን? ለዚህ ነገር ምክንያት የሆነው የአእምሮ ወይም የስሜት ቀውስ ነውን? የራስን ሕይወት ማጥፋት በአካባቢው ኅብረተሰብ ዘንድ እንዴት ይታያል?

ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን ይሖዋ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አመለካከት ማወቅ እንፈልጋለን። የሰው ሕይወት በይሖዋ ዘንድ ትልቅ ዋጋ ያለውና የተቀደሰ ነው። (ዘፍጥረት 9:5፤ መዝሙር 36:9) ሆን ብሎ የራስን ሕይወት ማጥፋት እንደ ነፍስ ግድያ ይቆጠራል። ይህ ደግሞ አምላክን የሚያሳዝን ድርጊት ነው። (ዘጸአት 20:13፤ 1 ዮሐንስ 3:15) ታዲያ ይህ ሲባል የራሳቸውን ሕይወት ላጠፉ ሁሉ የቀብር ንግግር ማድረግ አይቻልም ማለት ነውን?

የእስራኤል ንጉሥ የነበረውን የሳኦልን ሁኔታ ተመልከት። ከፍልስጤማውያን ጋር ካደረገው የመጨረሻ ጦርነት በሕይወት እንደማይተርፍ ሲረዳ በጠላቶቹ እጅ ወድቆ እንዳያሰቃዩት ሲል “ሰይፉን ወስዶ በላዩ ወደቀ።” ፍልስጤማውያን አስከሬኑን ሲያገኙት በቤትሳን ከተማ ቅጥር ላይ አንጠለጠሉት። የኢያቢስ ገለዓድ ነዋሪዎች ፍልስጤማውያን ያደረጉትን ሲሰሙ የሳኦልን አስከሬን ከተንጠለጠለበት አወረዱና አቃጠሉት። ከዚያም አጥንቶቹን ቀበሩ። እንዲያውም በእስራኤላውያን የለቅሶ ልማድ መሠረት ለሰባት ቀን ጾመዋል። (1 ሳሙኤል 31:4, 8-13፤ ዘፍጥረት 50:10) ይሖዋ የቀባው ዳዊት የኢያቢስ ገለዓድ ነዋሪዎች ያደረጉትን ሲሰማ “እናንተ ለጌታችሁ ለሳኦል ይህን ቸርነት አድርጋችኋልና፣ ቀብራችሁትማልና በእግዚአብሔር የተባረካችሁ ሁኑ። አሁንም እግዚአብሔር ቸርነትንና እውነትን ያድርግላችሁ” ብሏቸዋል። (2 ሳሙኤል 2:5, 6) መለኮታዊው ዘገባ የኢያቢስ ገለዓድ ነዋሪዎች ለንጉሥ ሳኦል የቀብር ሥነ ሥርዓት ማድረጋቸው እንዳስወገዛቸው አይናገርም። ይህን ታሪክ በክፉ ድርጊታቸው ምክንያት እንደማይቀበሩ ከተነገረላቸው ሰዎች ሁኔታ ጋር አወዳድር። (ኤርምያስ 25:32, 33) አንድ ክርስቲያን የራሱን ሕይወት ላጠፋ ሰው የቀብር ንግግር ማድረግ ይችል እንደሆነና እንዳልሆነ ከመወሰኑ በፊት የሳኦልን ታሪክ ከግምት ውስጥ ሊያስገባ ይችላል።

ከዚህም ሌላ የቀብር ሥነ ሥርዓት የሚደረግበትን ዓላማም ማሰብ ያስፈልገው ይሆናል። የይሖዋ ምሥክሮች የቀብር ሥነ ሥርዓቶችን የሚያደርጉት ነፍስ አትሞትም ብለው እንደሚያምኑት ሰዎች ሟቹን ወደ ሌላ ዓለም ለመሸኘት በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ አይደለም። የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ዋነኛ ዓላማ ሟቹን መጥቀም ሳይሆን ሐዘን የደረሰባቸውን ማጽናናትና በቀብሩ ላይ ለተገኙት ሰዎች ሙታን ያሉበትን ሁኔታ በሚመለከት ምሥክርነት መስጠት ነው። (መክብብ 9:5, 10፤ 2 ቆሮንቶስ 1:3-5) የቀብር ንግግር የሚደረግበት ሌላው ምክንያት በቀብሩ ላይ የተገኙት ሁሉ ሕይወት አላፊ መሆኑን እንዲያስተውሉ ለመርዳት ነው። (መክብብ 7:2) የራሱን ሕይወት ላጠፋ ሰው የቀብር ንግግር ቢደረግ እነዚህን ዓላማዎች ማሳካት ይቻላል?

አንዳንዶች ግለሰቡ ሕይወቱን ያጠፋው ሆን ብሎና በይሖዋ ላይ የሚፈጸም ኃጢአት መሆኑን እያወቀ ነው ብለው ሊያስቡ እንደሚችሉ የታወቀ ነው። ነገር ግን ሁልጊዜ እንደዚያ ብሎ ለመደምደም የሚያስደፍር ሁኔታ ይኖራልን? በጊዜያዊ ስሜት ተነድቶ ያደረገው ሊሆን አይችልም? ሕይወታቸውን ለማጥፋት የሚሞክሩ አንዳንዶች ሐሳባቸውን ለውጠው ከድርጊቱ ይታቀባሉ። አንድ ሰው ሕይወቱን ካጠፋ በኋላ በድርጊቱ የመጸጸት አጋጣሚ አይኖረውም።

ሊታሰብበት የሚገባ ሌላው ትልቁ ጉዳይ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉት አብዛኞቹ ሰዎች የአእምሮና የስሜት ቀውስ ያለባቸው መሆኑ ነው። የእንደዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ሁኔታ በእርግጥም የተለየ ነው። አንድ ጥናት እንዳረጋገጠው ሕይወታቸውን ከሚያጠፉ ሰዎች ውስጥ 90 በመቶዎቹ ዓይነቱ ይለያይ እንጂ የአእምሮ፣ የስሜት ወይም ከሱስ ጋር የተያያዘ ችግር አለባቸው። ሰዎች እንዲህ ባለ አእምሯዊ ሁኔታ ውስጥ እያሉ የራሳቸውን ሕይወት ቢያጠፉ ይሖዋ ይቅር ይላቸዋል? ሟቹ በይሖዋ ፊት ይቅርታ የማይደረግለት ኃጢአት ፈጽሟል ብለን የመፍረድ ሥልጣን የለንም። አንድ ክርስቲያን የራሱን ሕይወት ላጠፋ ሰው የቀብር ንግግር ስለ ማድረግ ሲያስብ ሟቹ የነበረበትን ሁኔታና የሕክምና መረጃዎቹን ግምት ውስጥ ሊያስገባ ይችላል።

ትኩረት የሚያሻው አንድ ሌላ ጉዳይ አለ። በአካባቢው ያሉ ሰዎች የራስን ሕይወት ማጥፋትን እንዲሁም የዚህን ግለሰብ ሞት በተመለከተ ምን ይሰማቸዋል? ይህ በተለይ በአካባቢው ያለውን የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ መልካም ስም የመጠበቅ ኃላፊነት የተጣለባቸውን ሽማግሌዎች ያሳስባቸዋል። ሽማግሌዎች የአካባቢው ኅብረተሰብ የራስን ሕይወት ስለ ማጥፋትና በተለይ ስለዚህ ግለሰብ ሞት ካለው አመለካከት በመነሳት የቀብር ሥነ ሥርዓቱን በግልጽ ላለመደገፍ ወይም በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ንግግር እንዲሰጥ ላለመፍቀድ ሊወስኑ ይችላሉ።

ያም ሆኖ ግን አንድ ክርስቲያን የቀብር ሥነ ሥርዓቱን እንዲመራ ጥያቄ ሲቀርብለት በግሉ ጥያቄውን መቀበል እንደሚችል ይሰማው ይሆናል። የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ለመምራት ከወሰነ ሟቹ ትንሣኤ ያገኛል አያገኝም የሚለውን ነጥብ በተመለከተ ቁርጥ ያለ ነገር ከመናገር መቆጠብ ይኖርበታል። የሙታን የወደፊት ተስፋ ያለው በይሖዋ እጅ ስለሆነ ማንም ሰው ሟቹ የትንሣኤ ተስፋ አለው ወይም የለውም ብሎ የመናገር ሥልጣን የለውም። ንግግሩን የሚሰጠው ወንድም ስለ ሞት በሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ላይ በማተኮር ሐዘን የደረሰባቸውን ማጽናናቱ የተሻለ ይሆናል።