በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በይሖዋ መንገድ መመላለስ የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል

በይሖዋ መንገድ መመላለስ የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል

በይሖዋ መንገድ መመላለስ የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል

ተራራ ወጥተህ ታውቃለህ? የምታውቅ ከሆነ ዓለምን የተቆጣጠርክ ሆኖ ተሰምቶህ ይሆናል። ንጹሑን አየር መተንፈስ፣ በርቀት አሻግሮ እየተመለከቱ የተፈጥሮ ውበትን ማድነቅ ምንኛ የሚያስደስት ነው! ለጊዜውም ቢሆን የዓለምን ጭንቀት ረስተህ እፎይ ብለህ ይሆናል።

ብዙ ሰዎች ተራራ የመውጣት አጋጣሚያቸው አነስተኛ ነው። አንተ ግን ራስህን ለአምላክ የወሰንክ ክርስቲያን ከሆንክ በመንፈሳዊ ሁኔታ በተራራ ላይ መሄድ ከጀመርክ ቆይተሃል ማለት ነው። እንደ ጥንቱ መዝሙራዊ “አቤቱ፣ መንገድህን አመልክተኝ፣ ፍለጋህንም አስተምረኝ” ብለህ እንደጸለይህ ምንም አያጠራጥርም። (መዝሙር 25:4) ወደ ይሖዋ ቤት ተራራ ለመጀመሪያ ጊዜ ስትወጣና በከፍታ ላይ መሄድ ስትጀምር የተሰማህን ስሜት ታስታውሳለህ? (ሚክያስ 4:2፤ ዕንባቆም 3:19) በዚህ ከፍ ያለ የንጹሕ አምልኮ ጎዳና ላይ መጓዝ ጥበቃና ደስታ እንደሚያስገኝ ወዲያው ሳትገነዘብ አልቀረህም። “እልልታ የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው፤ አቤቱ፣ በፊትህ ብርሃን ይሄዳሉ” ብሎ እንደተናገረው እንደ መዝሙራዊው ዓይነት ስሜት ተሰምቶህ ይሆናል።​—⁠መዝሙር 89:15

አንዳንድ ጊዜ ግን ተራራማ በሆነ ቦታ ላይ በእግር የሚጓዙ ሰዎች ረጅምና አስቸጋሪ የሆኑ አቀበቶችን መውጣት ይኖርባቸዋል። እግራቸውን ያምማቸዋል፣ እንዲሁም ይዝላሉ። እኛም በተመሳሳይ ለአምላክ በምናቀርበው አገልግሎት ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኃይላችን ተሟጥጦ መራመድ አቅቶን ይሆናል። ታዲያ ኃይላችንንና ደስታችንን ማደስ የምንችለው እንዴት ነው? የመጀመሪያው እርምጃ የይሖዋ መንገዶች ከሁሉ የላቁ መሆናቸውን መገንዘብ ነው።

ከፍ ያለ ደረጃ ያላቸው የይሖዋ ሕጎች

የይሖዋ መንገድ ‘ከሰው መንገድ ከፍ ያለ’ ሲሆን አምልኮቱም ‘በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ቆሟል፣ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ብሏል።’ (ኢሳይያስ 55:9፤ ሚክያስ 4:1) የይሖዋ ጥበብ “ላይኛይቱ ጥበብ” ተብሎ ተገልጿል። (ያዕቆብ 3:17) ሕጎቹ ከሌሎች ሕጎች ሁሉ የላቁ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ከነዓናውያን ልጆቻቸውን በጭከና መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ በነበረበት ጊዜ ይሖዋ ለእስራኤላውያን የርኅራኄ ስሜት የተንጸባረቀባቸውና የላቀ የሥነ ምግባር ደረጃ ያላቸው ሕጎች ሰጥቷቸው ነበር። እንዲህ አላቸው:- “ለድሀ አታድላ፣ ባለ ጠጋውንም አታክብር፤ . . . ከእናንተ ጋር የሚቀመጥ እንግዳ እንደ አገር ልጅ ይሁንላችሁ፣ እርሱንም እንደ ራስህ ውደድ።”​—⁠ዘሌዋውያን 19:15, 34

ከ1, 500 ዓመት በኋላ ኢየሱስ የይሖዋ ‘ሕግ ታላቅ’ መሆኑን የሚያሳዩ ተጨማሪ ምሳሌዎችን ሰጥቷል። (ኢሳይያስ 42:21) በተራራ ስብከቱ ላይ ለደቀ መዛሙርቱ:- “በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ . . . ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 5:44, 45) እንዲሁም “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና” ብሏል።​—⁠ማቴዎስ 7:12

እነዚህ ከፍ ያለ ደረጃ ያላቸው ሕጎች ቀና ምላሽ የሚሰጡ ሰዎችን ልብ በመንካት የአምላካቸውን ምሳሌ እንዲከተሉ ያነሳሷቸዋል። (ኤፌሶን 5:1፤ 1 ተሰሎንቄ 2:13) ጳውሎስ ያደረገውን ለውጥ ተመልከት። ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ የምናገኘው በእስጢፋኖስ ‘መገደል እንደተስማማና’ ‘ቤተ ክርስቲያንን ያፈርስ እንደነበር’ በሚገልጸው ታሪክ ውስጥ ነው። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን በተሰሎንቄ የነበሩ ክርስቲያኖችን “ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ” በየዋህነት ይንከባከባቸው እንደ ነበር ተጠቅሷል። መለኮታዊ ትምህርት አሳዳጅ የነበረው ጳውሎስ ሩኅሩኅ ክርስቲያን እንዲሆን አድርጎታል። (ሥራ 8:1, 3፤ 1 ተሰሎንቄ 2:7) በክርስቶስ ትምህርት ባሕርይው በመለወጡ ምክንያት አመስጋኝ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 1:12, 13) አመስጋኝ መሆን ከፍ ባሉት የይሖዋ መንገዶች ላይ መጓዛችንን እንድንቀጥል እኛንም የሚረዳን እንዴት ነው?

በአመስጋኝነት ስሜት መጓዝ

ተራራ የሚወጡ ሰዎች በከፍታ ቦታዎች ላይ ሆነው በሚያዩት ውብ የተፈጥሮ ትዕይንት ይደሰታሉ። እንዲሁም እንደ አለት፣ አበባ ወይም የዱር እንስሳ የመሰሉ ነገሮችን በመንገዳቸው ላይ ሲመለከቱ በአድናቆት ይሞላሉ። በመንፈሳዊ ሁኔታም ከአምላክ ጋር መጓዝ የሚያስገኛቸውን በረከቶች (ትላልቅም ሆኑ ትናንሽ) በንቃት መከታተል አለብን። እንደዚህ ማድረጋችን ኃይላችንን ሊያድስልንና አድካሚውን ጉዞ በከፍተኛ ብርታት እንድንጓዝ ሊረዳን ይችላል። “አንተን ታምኛለሁና በማለዳ ምሕረትህን አሰማኝ፤ አቤቱ፣ ነፍሴን ወደ አንተ አንሥቻለሁና የምሄድበትን መንገድ አስታውቀኝ” የሚሉትን የዳዊትን ቃላት እናስተጋባለን።​—⁠መዝሙር 143:8

በይሖዋ መንገድ ለበርካታ ዓመታት ስትመላለስ የኖረችው ሜሪ እንዲህ ትላለች:- “የይሖዋን ፍጥረት ቆም ብዬ ስመለከት የተፈጥሮውን ውበት ብቻ ሳይሆን በዚያ ላይ የተንጸባረቀውን የአምላክንም ፍቅር ለመገንዘብ እሞክራለሁ። እንስሳም ሆነ ወፍ ወይም ትንንሽ ነፍሳት ሁሉም ማራኪ የሆኑ ልዩ ፍጥረታት ናቸው። ባለፉት ዓመታት ይበልጥ ግልጽ እየሆኑ ከመጡት መንፈሳዊ እውነቶችም ተመሳሳይ የሆነ ደስታ አገኛለሁ።”

የአመስጋኝነት መንፈሳችንን ከፍ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ ይሖዋ የሚያደርግልንን ነገር አቅልለን ባለመመልከት ነው። ጳውሎስ “ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ” በማለት ጽፏል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 5:17, 18፤ መዝሙር 119:62

የግል ጥናት የአመስጋኝነት መንፈሳችንን ለማዳበር ይረዳል። ጳውሎስ የቆላስይስ ክርስቲያኖችን “በእርሱ [በኢየሱስ ክርስቶስ] ተመላለሱ፤ . . . በሃይማኖት ጽኑ፣ ምስጋናም ይብዛላችሁ” ሲል አሳስቧቸዋል። (ቆላስይስ 2:6, 7) መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ባነበብነው ላይ ማሰላሰል እምነታችንን ያጠነክርልናል፤ እንዲሁም ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ ይበልጥ እንድንቀርብ ያደርገናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ምስጋና እንዲበዛልን’ የሚያነሳሱ ውድ ሃብቶችን እናገኛለን።

ከዚህ በተጨማሪም ከወንድሞቻችን ጋር ሆኖ ይሖዋን ማገልገል ጎዞውን ያቀልልናል። መዝሙራዊው ስለራሱ ሲናገር “እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፣ . . . ባልንጀራ ነኝ” ብሏል። (መዝሙር 119:63) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ወይም በሌሎች ቦታዎች ከወንድሞቻችን ጋር አብረን የምናሳልፈው ጊዜም ደስታ የምናገኝባቸው ወቅቶች ናቸው። ውድ የሆነው ዓለም አቀፋዊ የክርስቲያን ቤተሰባችን ሊገኝ የቻለው በይሖዋና ከፍ ያለ ደረጃ ባለው መንገዱ እንደሆነ እንገነዘባለን።​—⁠መዝሙር 144:15ለ

ከአመስጋኝነት መንፈስ በተጨማሪ የኃላፊነት ስሜት ከፍ ባሉት የይሖዋ ጎዳናዎች ላይ መጓዛችንን እንድንቀጥል የሚያስችል ጥንካሬ ይሰጠናል።

የኃላፊነት ስሜት እንዲሰማን ያስፈልጋል

ጠንቃቃ የሆኑ ተራራ ወጪዎች አቅጣጫቸውን እንዳይስቱ ወይም ከተራራው ላይ ተንሸራተው እንዳይወድቁ በንቃት መጓዝ እንዳለባቸው ያውቃሉ። የመምረጥ ነጻነት ያለን ፍጡራን እንደመሆናችን መጠን ይሖዋ አንጻራዊ የሆነ ነጻነትና በራሳችን ተነሳስተን ነገሮችን የማከናወን ችሎታ ሰጥቶናል። ይሁን እንጂ ክርስቲያናዊ ግዴታችንን በምንወጣበት ጊዜ የኃላፊነት ስሜት ሊሰማን ይገባል።

ለምሳሌ ያህል ይሖዋ አገልጋዮቹ ግዴታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ ይተማመንባቸዋል። በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ምን ያህል ጊዜና ጉልበት ማዋል እንዳለብን ወይም በገንዘብ ወይም በሌሎች መንገዶች ምን ያህል አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለብን አይነግረንም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጻፋቸው “እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ” የሚሉት ቃላት ለእኛም ይሠራሉ።​—⁠2 ቆሮንቶስ 9:7፤ ዕብራውያን 13:15, 16

ኃላፊነት ተሰምቶን የምናደርገው ልግስና ምሥራቹን ለሌሎች ማካፈልንም ይጨምራል። በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ ለሚደረገው የመንግሥቱ ሥራ የገንዘብ አስተዋጽኦ እናደርጋለን። ጌርሃርት የተባለ አንድ ሽማግሌ እሱና ባለቤቱ በምሥራቅ አውሮፓ በአንድ ስብሰባ ላይ ከተገኙ በኋላ የሚያደርጉትን የገንዘብ መዋጮ ከፍ እንዳደረጉ ሲናገር እንዲህ አለ:- “በዚያ ያሉት ወንድሞቻችን ኑሯቸው ዝቅተኛ እንደሆነ ተመለከትን፤ ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን ግን ከፍተኛ አድናቆት አላቸው። ስለዚህ በሌሎች አገሮች ላሉ የተቸገሩ ወንድሞቻችን የሚቻለንን ያህል እርዳታ ለመስጠት ወሰንን።”

እስከ መጨረሻው መጽናት

ተራራ መውጣት ብርታት ይጠይቃል። ተራራ የሚወጡ ሰዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፤ እንዲሁም ብዙዎቹ አጭር የእግር ጉዞ በማድረግ ለዚህ ረጅም ጉዞ አስቀድመው ይዘጋጃሉ። በተመሳሳይም ጳውሎስ በመንፈሳዊ ብቁ ሆነን መኖራችንን እንድንቀጥል በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች መጠመድ እንዳለብን ተናግሯል። ‘ለይሖዋ እንደሚገባ መመላለስና’ ‘እየበረቱ’ መሄድ የሚፈልጉ ሁሉ ‘በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ ማፍራታቸውን’ መቀጠል እንዳለባቸው ጳውሎስ ተናግሯል።​—⁠ቆላስይስ 1:10-12

አንድ ተራራ የሚወጣ ሰው የተነሳበት ዓላማ በጉዞው እንዲጸና ይረዳዋል። እንዴት? ከሩቅ እንደሚታይ ተራራ ያለ ግልጽ የሆነ ግብ መኖሩ ራሱ የብርታት ምንጭ ይሆናል። ተጓዡ የተወሰነ ርቀት ተጉዞ አንድ ቦታ ከደረሰ በኋላ ግቡ ላይ ለመድረስ ምን ያህል እንደቀረው መገመት ይችላል። የተጓዘበትን ርቀት መለስ ብሎ ሲመለከት እርካታ ይሰማዋል።

በተመሳሳይም የዘላለም ሕይወት ተስፋችን ያበረታናል እንዲሁም ወደ ፊት እንድንገፋ ኃይል ይሰጠናል። (ሮሜ 12:12) እስከዚያ ድረስ በይሖዋ መንገዶች ስንመላለስ ክርስቲያናዊ ግቦችን በማውጣትና ከዚያም እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ በመጣጣር ስኬታማ እንሆናለን። በታማኝነት ያገለገልንባቸውን ብዙ ዓመታት መለስ ብለን ስናስብ ወይም በባሕርያችን ላይ ያደረግናቸውን ለውጦች ስንመለከት ምንኛ እንደሰታለን!​—⁠መዝሙር 16:11

በእግር የሚጓዙ ሰዎች ረጅም ርቀት ለመሸፈንና ኃይል ለመቆጠብ በአንድ ዓይነት ፍጥነት ይራመዳሉ። በተመሳሳይም አዘውትሮ በስብሰባ ላይ መገኘትንና በመስክ አገልግሎት መሳተፍን ጨምሮ ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ወደ ግባችን መጓዛችንን እንድንቀጥል ይረዳናል። ጳውሎስ ክርስቲያን ወንድሞቹን “በደረስንበት በዚያ እንመላለስ” በማለት አሳስቧቸዋል።​—⁠ፊልጵስዩስ 3:16

እርግጥ ነው፣ በይሖዋ መንገድ ላይ የምንጓዘው ብቻችንን አይደለም። “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ” በማለት ጳውሎስ ጽፏል። (ዕብራውያን 10:24) ጥሩ መንፈሳዊ ወዳጅነት ከእምነት አጋሮቻችን ጋር እኩል መራመዳችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።​—⁠ምሳሌ 13:20

በመጨረሻም ይሖዋ ኃይል እንደሚሰጠን ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። ይሖዋ በሚሰጠው ብርታት የሚታመኑ “ከኃይል ወደ ኃይል ይሄዳሉ።” (መዝሙር 84:5, 7) አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማለፍ ቢኖርብንም በይሖዋ እርዳታ ሊሳካልን ይችላል።