በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን “በመንፈስ” አምልክ

አምላክን “በመንፈስ” አምልክ

አምላክን “በመንፈስ” አምልክ

“እንግዲህ፣ እግዚአብሔርን ከማን ጋር ታወዳድሩታላችሁ? ከየትኛውስ ምስል ጋር ታነጻጽሩታላችሁ?”--ኢሳይያስ 40:​18 አ.መ.ት

ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አለው ብለህ ታምን ይሆናል። ምስሎች ወደማይታየውና ወደማይዳሰሰው ጸሎት ሰሚ አምላክ እንደሚያቀርቡህ ይሰማህ ይሆናል።

አምላክን እኛ በፈለግነው መንገድ መቅረብ እንችላለን ማለት ነው? በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ያለውንና የሌለውን የመወሰን ሥልጣን ያለው አምላክ ራሱ መሆን አይገባውምን? ኢየሱስ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት አምላክ በዚህ ረገድ ያለውን አመለካከት ገልጿል። (ዮሐንስ 14:6) ይህ ጥቅስ ብቻ እንኳ ምስሎችንም ሆነ እንደ ቅዱስ የሚታዩ ነገሮችን ለአምልኮ መጠቀም ተገቢ አለመሆኑን ጥሩ አድርጎ ያሳያል።

አዎን፣ ይሖዋ አምላክ የሚቀበለው አንድ አምልኮ አለ። ይህ አምልኮ የትኛው ነው? በአንድ ወቅት ኢየሱስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።”​—⁠ዮሐንስ 4:​23, 24

ታዲያ አምላክ “መንፈስ” ሆኖ ሳለ ይህን ይመስላል ብሎ በምስል መግለጽ ይቻላልን? በፍጹም። ምስሉ ምንም ያህል ማራኪና ውብ ቢሆን ከአምላክ ክብር ጋር ፈጽሞ ሊስተካከል አይችልም። ስለሆነም አምላክ ይህን ይመስላል ተብሎ የሚሳለው ሥዕል አምላክን በትክክል ሊወክል አይችልም። (ሮሜ 1:​22, 23) አንድ ሰው በምስል አማካኝነት ወደ አምላክ ለመቅረብ ጥረት ቢያደርግ አምላክን ‘በእውነት አምልኳል’ ሊባል ይቻላልን?

ግልጽ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት

የአምላክ ቃል ለአምልኮ ሲባል ምስል መሥራትን ይከለክላል። የአሥርቱ ትእዛዛት ሁለተኛ ሕግ “በላይ በሰማይ ካለው፣ በታችም በምድር ካለው፣ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፣ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ” ይላል። (ዘጸአት 20:​4, 5) በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎችም “ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ” በማለት ያዝዛሉ።​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:​14

እርግጥ ነው፣ ብዙ ሰዎች ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀማቸው ጣዖት ከማምለክ እንደማይቆጠር ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የምንሰግደውና የምንጸልየው ለምስሎቹ አይደለም ብለው ይከራከራሉ። አንድ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄስ “ለምስሎች አክብሮት የምንሰጠው ቅዱስ ስለሆኑና ምስሎቹ የሚወክሏቸውን ስለምናከብራቸው ነው” በማለት ጽፈዋል።

አሁንም አንድ የሚነሳ ጥያቄ አለ። አምላክ በምስል አማካኝነት የሚቀርብለትን አምልኮ ይቀበላልን? አምላክ እንዲህ ያለውን አምልኮ እንደሚቀበል የሚናገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድም ቦታ የለም። እስራኤላውያን ይሖዋን ለማምለክ በሚል የጥጃ ምስል በሠሩ ጊዜ የክህደት ድርጊት እንደፈጸሙ አድርጎ በመናገር ድርጊቱን በጥብቅ ተቃውሟል።​—⁠ዘጸአት 32:​4-7

ስውር አደጋ

ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም አደገኛ ነው። ሰዎች ምስሉ የተሠራለትን አምላክ ከማምለክ ይልቅ በቀላሉ ግዑዙን ምስል ወደ ማምለክ ዞር ሊሉ ይችላሉ። በሌላ አነጋገር ምስሉ ራሱ ጣዖት ይሆንባቸዋል።

እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ጊዜያት እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። ለምሳሌ ያህል እስራኤላውያን በምድረ በዳ ይጓዙ በነበረበት ወቅት ሙሴ የነሐስ እባብ ሠርቶ ነበር። በመሠረቱ እባብ ሠርቶ በእንጨት ላይ መስቀል ያስፈለገው ሕዝቡን ከሞት ለማዳን ነበር። በሠሩት ጥፋት ምክንያት በእባብ የተነደፉት ሰዎች የነሐሱን እባብ በመመልከት የአምላክን እርዳታ ማግኘት ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ ሕዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገባ በኋላ ይህ የነሐስ እባብ በራሱ የመፈወስ ኃይል እንዳለው አድርገው በማሰብ እንደ ጣዖት ማምለክ የጀመሩ ይመስላል። ዕጣን ያጥኑለት የነበረ ከመሆኑም በላይ ኑሑሽታን የሚል ስም አውጥተውለት ነበር።​—⁠ዘኁልቊ 21:​8, 9፤ 2 ነገሥት 18:​4 አ.መ.ት

ከዚህም በተጨማሪ እስራኤላውያን የቃል ኪዳኑ ታቦት ጠላቶቻቸውን ጠራርጎ የማጥፋት ኃይል እንዳለው አድርገው እስከማመን ደርሰው ነበር። (1 ሳሙኤል 4:​3, 4፤ 5:​11) እንዲሁም በኤርምያስ ዘመን የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ለአምላክ ከሚያቀርቡት አምልኮ ይልቅ ግዑዝ ለሆነው ቤተ መቅደስ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ ነበር።​—⁠ኤርምያስ 7:​12-15

ከአምላክ ይልቅ ሌሎች ነገሮችን የማምለክ ዝንባሌ አሁንም ቢሆን ተስፋፍቶ ይገኛል። ቪታሊ ኢቫኖይች ፔትሬንኮ የተባሉ ተመራማሪ ‘ብዙ ሰዎች ምሥሎችን . . . ለአምልኮ ስለሚጠቀሙባቸው ጣዖት ይሆናሉ ብዬ እፈራለሁ። . . . የምስል አምልኮ ታዋቂ በሆኑ እምነቶች አማካኝነት ቀስ በቀስ ወደ ጣዖት አምልኮ የተሸጋገረ አረማዊ አስተሳሰብ እንደሆነ ሁሉም ማወቅ ይኖርበታል’ ብለዋል። በተመሳሳይም ደሚትሪዎስ ኮንስታንቴሎስ የተባሉ አንድ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቄስ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ማወቅ (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “አንድ ክርስቲያን ምስሎችን እስከተጠቀመ ድረስ ለማምለክ ያለው አጋጣሚ ሰፊ ነው” በማለት ተናግረዋል።

ምስሎችን ለአምልኮ እንጠቀምባቸዋለን እንጂ አናመልካቸውም የሚለው አባባል አጠያያቂ ነው። ለምን? ምክንያቱም ማርያምን ወይም “ቅዱሳትን” ያመለክታሉ ተብለው ከሚታመንባቸው የተለያዩ ምስሎች መካከል አንዱ ብቻ ተመርጦ ልዩ ክብር ሲሰጠውና ከሌሎቹ ምስሎች የሚበልጥ ኃይል እንዳለው ተደርጎ ሲታይ እንመለከት የለምን? ለምሳሌ ያህል በግሪክ ቲኖስ ደሴት ላይ የሚገኘውን የማርያም ምስል ከምንም በላይ ከፍ አድርገው የሚመለከቱ የግሪክ ኦርቶዶክስ አማኞች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በሰሜን ግሪክ ሱሜላ ገዳም ውስጥ ለሚገኘው የማርያም ምስል የማይተናነስ ክብር የሚሰጡ የኦርቶዶክስ አማኞች አሉ። ምንም እንኳን ሁለቱም ምስሎች የማርያም እንደሆኑ ቢታመንም ሁለቱም ቡድኖች እነርሱ የመረጡት ምስል እንደሚበልጥና ከሌላው የሚልቅ ኃይል እንዳለው ይሰማቸዋል። በተግባር እንደምንመለከተው ሰዎች አንዳንድ ምስሎች የተለየ ኃይል እንዳላቸው አድርገው በማመን ያመልኳቸዋል።

ወደ “ቅዱሳት” ወይም ወደ ማርያም መጸለይ ተገቢ ነውን?

ማርያምን ወይም “ቅዱስ” የሚባሉ ሰዎችን ስለማምለክስ ምን ለማለት ይቻላል? ኢየሱስ ሰይጣን ላቀረበለት ፈተና መልስ ሲሰጥ ዘዳግም 6:​13ን ጠቅሶ “ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:​10) ከጊዜ በኋላም እውነተኛ አምላኪዎች “ለአብ” ብቻ እንደሚሰግዱ ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:​23) ይህንን የተገነዘበ አንድ መልአክ ሐዋርያው ዮሐንስ ሊሰግድለት በሞከረ ጊዜ “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ . . . ለእግዚአብሔር ስገድ” በማለት ገስጾታል።​—⁠ራእይ 22:​9

የኢየሱስ ምድራዊ እናት ማርያም ወይም ሌሎች “ቅዱሳን” ከአምላክ ጋር እንዲያማልዱን ሲባል ወደ እነርሱ መጸለይ ተገቢ ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ “በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፣ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” በማለት ለዚህ ጥያቄ ግልጽ መልስ ይሰጣል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 2:​5

ከአምላክ ጋር የመሠረትከው ዝምድና እንዳይበላሽ ተጠንቀቅ

ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም ከመጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ትምህርት ጋር የሚቃረን በመሆኑ ሰዎች የአምላክን ሞገስ አግኝተው እንዲድኑ አይረዳቸውም። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን እውነተኛውን አንድ አምላክ በማወቃችን ላይ የተመካ መሆኑን ተናግሯል። ይህ እውቀት ወደር የማይገኝላቸውን ባሕርያቱን እንዲሁም ዓላማውንና ከሰዎች ጋር ያደረጋቸውን ግንኙነቶች መማርን ይጨምራል። (ዮሐንስ 17:​3) ማየት፣ መስማትም ሆነ መናገር የማይችሉ ምስሎች አንድ ሰው አምላክን እንዲያውቅና ተቀባይነት ባለው መንገድ እርሱን እንዲያመልክ ሊረዱት አይችሉም። (መዝሙር 115:​4-8) ስለ አምላክ ትክክል የሆነውን ማወቅ የሚቻለው የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ብቻ ነው።

የምስል አምልኮ ምንም ጥቅም የሌለው ከመሆኑም ሌላ መንፈሳዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። እንዴት? በዋነኛ ደረጃ ከአምላክ ጋር ሊያቆራርጠን ይችላል። አምላክ ‘በአስጸያፊ ጣዖቶቻቸው ያስቆጡትን’ እስራኤላውያንን በሚመለከት “ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ” በማለት ተናግሮ ነበር። (ዘዳግም 32:​16, 20 አ.መ.ት ) ከአምላክ ጋር ያላቸው ወዳጅነት እንዲሻሻል ከፈለጉ ‘ለኃጢአት የሠሯቸውን ጣዖታት መጣል’ ነበረባቸው።​—⁠ኢሳይያስ 31:​6, 7

እንግዲያው ቅዱሳን ጽሑፎች “ልጆች ሆይ፣ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ” በማለት ምክር መስጠታቸው ምንኛ ተገቢ ነው!​—⁠1 ዮሐንስ 5:​21

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አምላክን “በመንፈስ” ለማምለክ እርዳታ አገኙ

ኦሊቬራ በአልባንያ የምትኖር አጥባቂ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ነበረች። በ1967 ሃይማኖትን የሚከለክል ሕግ በአገሯ በወጣ ጊዜ እምነቷን በድብቅ ማከናወን ቀጠለች። በጡረታ የምታገኛትን ጥቂት ገንዘብ ከወርቅና ከብር የተሠሩ ሃይማኖታዊ ምስሎችን እንዲሁም ዕጣንና ጧፍ ለመግዛት ትጠቀምበት ነበር። ምስሎቹን ሌላ ሰው እንዳያይባት ወይም እንዳይሰርቅባት ስትል አልጋዋ ውስጥ ትደብቅና አልጋዋ አጠገብ በሚገኝ ወንበር ላይ ትተኛ ነበር። በ1990ዎቹ መግቢያ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ቤትዋ መጥተው ሲያነጋግሯት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በራላት። እውነተኛ አምልኮ ‘በመንፈስ’ የሚከናወን እንደሆነና ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን በተመለከተ አምላክ ምን አመለካከት እንዳለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማረች። (ዮሐንስ 4:​24) መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናት የነበረችው የይሖዋ ምሥክር በኦሊቬራ ቤት የነበሩት ሃይማኖታዊ ምስሎች ከዕለት ወደ ዕለት እየቀነሱ እንደመጡ አስተዋለች። በመጨረሻም ሙሉ በሙሉ ተወገዱ። ኦሊቬራ ከተጠመቀች በኋላ እንዲህ ስትል ተናገረች:- “ዛሬ ምንም ጥቅም በሌላቸው ምስሎች ፋንታ የይሖዋ መንፈስ አለኝ። ያለ ምስሎች እርዳታ የይሖዋን መንፈስ ማግኘት በመቻሌ ተደስቻለሁ።”

ግሪክ ውስጥ ሌዝቮስ ደሴት ላይ የምትኖረው አቴና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አክራሪ ተከታይ ነበረች። የመዘምራን ቡድን አባል ከመሆኗም ሌላ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን ጨምሮ ሌሎች ሃይማኖታዊ ወጎችን አጥብቃ ትከተል ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች አቴና ከምታምንባቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ እንደሌላቸው እንድትገነዘብ ረዷት። ከእነዚህ መካከል ምስሎችንና መስቀልን ለአምልኮ መጠቀምን ይጨምራል። ምስሎችንና መስቀልን ለአምልኮ መጠቀም መቼ እንደተጀመረ ለማወቅ ከፍተኛ ምርምር አደረገች። የተለያዩ መጽሐፎች አገላብጣ ጥልቅ ምርምር ካደረገች በኋላ ይህ ዓይነቱ አምልኮ ከክርስትና እምነት እንዳልመነጨ አመነች። አምላክን ‘በመንፈስ’ ለማምለክ ያደረባት ብርቱ ፍላጎት ዋጋቸው ውድ ቢሆንም እንኳ ምስሎቹን እንድታስወግድ ገፋፋት። አቴና አምላክን ንጹሕና ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማምለክ ስትል በወሰደችው እርምጃ አልተቆጨችም።​—⁠ሥራ 19:​19

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ምስሎች እንዲያው የሥነ ጥበብ ሥራ ውጤት ብቻ ናቸውን?

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ምስሎችን እየሰበሰቡ ማስቀመጥ በዓለም ዙሪያ እየተለመደ መጥቷል። ሰብሳቢዎቹ ምስሎቹን የሚመለከቷቸው እንደ ቅዱስ ሃይማኖታዊ ዕቃዎች ሳይሆን የባይዛንታይንን ባሕል የሚያንጸባርቁ የሥነ ጥበብ ሥራ ውጤት እንደሆኑ አድርገው ነው። በአምላክ መኖር የማያምኑ ሰዎች እንኳን ሳይቀሩ በእነዚህ ሃይማኖታዊ ምስሎች ቤታቸውን ወይም ቢሯቸውን አስጊጠው መመልከት የተለመደ ነው።

ይሁን እንጂ ቅን ልብ ያላቸው ክርስቲያኖች የእነዚህ ምስሎች ቀደምት ዓላማ ምን እንደሆነ አይዘነጉም። የተሠሩት ለአምልኮ ነው። ክርስቲያኖች ሌሎች ሰዎች ሃይማኖታዊ ምስሎች እንዳይኖራቸው የማከላከል መብት ባይኖራቸውም እነርሱ ግን ሃይማኖታዊ ምስሎችን እንደ ንብረታቸው አድርገው አይዙም ወይም አያሰባስቡም። ይህ አቋም በዘዳግም 7:​26 ላይ “እንደ እርሱም ርጉም እንዳትሆን ርኩስን ነገር [ለአምልኮ የሚውል ምስል] ወደ ቤትህ አታግባ፤ ርጉም ነውና ተጸየፈው፣ ጥላውም” ከሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር የሚስማማ ነው።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ በምስሎች አማካኝነት የሚቀርብለትን አምልኮ አይቀበልም

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን መማር አምላክን በመንፈስ እንድናመልከው ይረዳናል