በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንዳትታለሉ ተጠንቀቁ

እንዳትታለሉ ተጠንቀቁ

እንዳትታለሉ ተጠንቀቁ

ማታለል ከሰው ልጅ ጋር አብሮ የኖረ ችግር ነው ለማለት ይቻላል። በጽሑፍ በሰፈረው ታሪክ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ከተጠቀሱት ክንውኖች መካከል አንዱ የማታለል ድርጊት ነው። ይህም የተፈጸመው ሰይጣን በኤደን ገነት ውስጥ ሔዋንን ባታለላት ጊዜ ነው።​—⁠ዘፍጥረት 3:13፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:14

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማታለል በምድር ላይ የነበረ ቢሆንም በዘመናችን ግን በእጅጉ ተስፋፍቷል። መጽሐፍ ቅዱስ የአሁኑን ጊዜ አስመልክቶ ሲያስጠነቅቅ “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ” ብሏል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:13

ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ይታለላሉ። አጭበርባሪዎች የሌሎችን ገንዘብ ለማግኘት ያታልላሉ። አንዳንድ የፖለቲካ ሰዎች በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ የመረጣቸውን ሕዝብ ያታልላሉ። ሰዎች ራሳቸውንም እንኳን ሳይቀር ያታልላሉ። ሐቁን ከመቀበል ይልቅ እንደ ማጨስ፣ አደገኛ ዕፅ መውሰድ ወይም የጾታ ብልግናን የመሰሉ አደገኛ ልማዶችን መፈጸም ምንም ጉዳት እንደሌለው ራሳቸውን ያሳምናሉ።

ከሃይማኖት ጋር በተያያዘም ማታለል ይፈጸማል። በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ሃይማኖታዊ መሪዎች ሕዝቡን ያሳስቱ ነበር። ኢየሱስ እነዚህን አታላዮች በማስመልከት “ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጕድጓድ ይወድቃሉ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 15:14) ሰዎች ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን በሚመለከት ራሳቸውንም ያታልላሉ። ምሳሌ 14:12 “ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው” በማለት ይናገራል።

በኢየሱስ ዘመን እንደሆነው ሁሉ ዛሬም ብዙዎች በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ይታለላሉ። ይህ ሊያስገርመን አይገባም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው” ሰይጣን “የማያምኑትን አሳብ አሳወረ” በማለት ተናግሯል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:4

አጭበርባሪዎች ቢያታልሉን የምናጣው ገንዘባችንን ነው። የፖለቲካ ሰዎች ቢያታልሉን ነፃነታችንን በተወሰነ ደረጃ እናጣ ይሆናል። ሰይጣን ቢያታልለንና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረውን እውነት አንቀበልም ብንል ግን የምናጣው የዘላለም ሕይወትን ነው! ስለዚህ እንዳትታለሉ ተጠንቀቁ። አእምሯችሁንና ልባችሁን ከፍታችሁ ጥርት ያለ ሃይማኖታዊ እውነት የሰፈረበትን መጽሐፍ ቅዱስን መርምሩ። እንዲህ አለማድረግ ትርፉ ኪሳራ ብቻ ነው።​—⁠ዮሐንስ 17:3