በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ብርታት ሆኖኛል

ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ብርታት ሆኖኛል

የሕይወት ታሪክ

ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ብርታት ሆኖኛል

ቶምሰን ካንጋሌ እንደተናገረው

ሚያዝያ 24, 1993 አዲስ የተገነባውና አሥራ ሦስት ሕንፃዎችን ያቀፈው የዛምቢያ ቅርንጫፍ ቢሮ ለአምላክ አገልግሎት ሲወሰን በፕሮግራሙ ላይ እንድገኝ ተጋበዝኩ። የመራመድ ችግር ስለነበረብኝ ሕንፃዎቹን ታስጎበኘን የነበረችው እህት በደግነት:- “አልፎ አልፎ አረፍ የምትልባት ወንበር ልያዝልህ?” በማለት ጠየቀችኝ። እርሷ ነጭ እኔ ጥቁር ብሆንም የቀለም ልዩነታችን አሳቢነት እንዳታሳየኝ አላገዳትም። ከልብ በመነጨ ስሜት አመሰገንኳት። ያሳየችኝ ደግነት ሁሉንም ሕንፃዎች ያለ ችግር እንድጎበኝ አስችሎኛል።

ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙኝ እነዚህን የመሳሰሉት ተሞክሮዎች እጅግ ያስደሰቱኝ ከመሆኑም በላይ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮቹን ለይቶ እንደሚያሳውቅ የተናገረለት ፍቅር በይሖዋ ምሥክሮች መካከል መኖሩን በተደጋጋሚ ጊዜያት አስገንዝበውኛል። (ዮሐንስ 13:​35፤ 1 ጴጥሮስ 2:​17) ከእነዚህ ክርስቲያኖች ጋር እንዴት ልተዋወቅ እንደቻልኩ ልንገራችሁ። ይህ የሆነው የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስም መጠራት እንደሚፈልጉ በገለጹበት ዓመት ማለትም በ1931 ነው።​—⁠ኢሳይያስ 43:​12

በቀድሞዎቹ ዓመታት በአፍሪካ ማገልገል

ኅዳር 1931 የ22 ዓመት ወጣት ሳለሁ በሰሜን ሮዴዥያ (አሁን ዛምቢያ) ኮፐር ቤልት ግዛት በምትገኘው ኬትዌ እኖር ነበር። አብሮኝ እግር ኳስ ይጫወት የነበረ አንድ ጓደኛዬ ከምሥክሮቹ ጋር አስተዋወቀኝ። በአንዳንድ ስብሰባዎቻቸው ላይ ከተገኘሁ በኋላ የአምላክ በገና! a የተባለ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ መጽሐፍ እንዲላክልኝ ደቡብ አፍሪካ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ጻፍኩ። መጽሐፉ የተዘጋጀው በእንግሊዝኛ ስለነበር አንብቤ መረዳት አቃተኝ።

እኔ ካደግሁበት ከባንግዌሉ ሐይቅ ደቡብ ምዕራብ 240 ኪሎ ሜትር ሮቆ በሚገኘው የኮፐርቤልት ግዛት ከሌሎች ከተሞች የመጡ በርካታ የመዳብ ማውጫ ሠራተኞች ነበሩ። በቡድን በቡድን የተደራጁ በርካታ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በዚህ ቦታ ይሰባሰቡ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከኪትዌ አቅራቢያ ወደሚገኘው ንዶላ ከተማ ተዛወርኩ። እዚያም ከአንድ የምሥክሮች ቡድን ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። በወቅቱ ፕሪንስ ኦቭ ዌልስ የተባለ የአንድ እግር ኳስ ቡድን አምበል ሆኜ እጫወት ነበር። የአፍሪካ ሐይቆች ኮርፖሬሽን ኃላፊ ለሆነ ነጭ ግለሰብም በቤት ሠራተኛነት አገልግያለሁ። ይህ ኩባንያ በመካከለኛው አፍሪካ አገሮች የተለያዩ መደብሮች ነበሩት።

የትምህርት ደረጃዬ ዝቅተኛ ሲሆን ያወቅኳትን ትንሽ እንግሊዝኛ የተማርኩት ከአውሮፓውያን አሠሪዎቼ ነበር። ትምህርቴን የመቀጠል ፍላጎት ስለነበረኝ ደቡብ ሮዴዥያ (አሁን ዛምቢያ) በሚገኘው ፕለምትሪ ትምህርት ቤት ተመዘገብኩ። ሆኖም በዚሁ ጊዜ የአምላክ በገና የተባለው መጽሐፍ እንደደረሰኝና ይሖዋን ሙሉ ጊዜ ማገልገል እንደምፈልግ በመግለጽ ደቡብ አፍሪካ ለሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ጻፍኩ።

ይሁን እንጂ የሰጡኝ ምላሽ በጣም አስገረመኝ። እንደሚከተለው ይነበባል:- “ይሖዋን የማገልገል ፍላጎት እንዳለህ በማወቃችን ደስ ብሎናል። ሆኖም በጉዳዩ ላይ እንድትጸልይበት እናበረታታሃለን። ይሖዋ እውነትን በተሻለ መንገድ እንድታውቅ እንደሚረዳህና በአገልግሎቱ ለአንተ የሚሆን ቦታ እንደሚሰጥህ እርግጠኞች ነን።” ደብዳቤውን ደግሜ ደጋግሜ ካነበብኩት በኋላ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ለማወቅ አንዳንድ ምሥክሮች አማከርኩ። “በእርግጥ ይሖዋን ማገልገል የምትፈልግ ከሆነ አትዘግይ፣ አሁኑኑ አገልግሎት ጀምር” በማለት መለሱልኝ።

በጉዳዩ ላይ አንድ ሳምንት ሙሉ ከጸለይኩ በኋላ በመጨረሻ ትምህርቴን ለማቆምና ከምሥክሮቹ ጋር የጀመርኩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመቀጠል ወሰንኩ። በተከታዩ ዓመት ማለትም ጥር 1932 ራሴን ለይሖዋ አምላክ ወሰንኩና ተጠመቅሁ። ከኑዶላ አቅራቢያ ወደሚገኘው የሉዋንሻ ከተማ ከተዛወርኩ በኋላ ጃኔት ከምትባል ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር ተዋወቅሁ። ከዚያም መስከረም 1934 ተጋባን። ስንጋባ ጃኔት አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ ነበሯት።

ቀስ በቀስ መንፈሳዊ እድገት አደረግሁና በ1937 የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ተጓዥ አገልጋይ (በአሁኑ ጊዜ የወረዳ የበላይ ተመልካች ማለት ነው) ሆኜ ተሾምኩ። ተጓዥ አገልጋዮች ጉባኤዎችን በመጎብኘት በመንፈሳዊ ያጠናክሯቸዋል።

በቀድሞዎቹ ዓመታት መስበክ

ጥር 1938 ሶኮንትዌ የተባለ አንድን አፍሪካዊ የመንደር አለቃ እንድጎበኝ ተነገረኝ። ሰውዬው የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው እንዲያነጋግሩት ጠይቆ ነበር። ለሦስት ቀናት በብስክሌት ከተጓዝኩ በኋላ ቤቱ ደረስኩ። የመጣሁት ለኬፕ ታውን ቢሮ በጻፈው ደብዳቤ መሠረት እንደሆነ ስነግረው በጣም ደስ አለው።

ከአንዱ ጎጆ ወደ ሌላኛው ጎጆ እየሄድኩ በኢንሳካ (የሕዝብ መሰብሰቢያ ዳስ) እንዲገኙ ጋበዝኳቸው። ከዚያም አንድ ላይ ሲሰባሰቡ ንግግር አደረግሁ። በውጤቱም ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። የመንደሩ አለቃና ጸሐፊው በአካባቢው የመጀመሪያዎቹ የጉባኤ ሽማግሌዎች ለመሆን በቁ። ዛሬ በዚያ አካባቢ ከ50 የሚበልጡ ጉባኤዎች ያሉ ሲሆን ወረዳው ሳምፋያ በመባል ይታወቃል።

ከ1942 እስከ 1947 ባሉት ዓመታት ከባንግዌሉ ሐይቅ ዙሪያ ባሉት አካባቢዎች አገልግያለሁ። በእያንዳንዱ ጉባኤ አሥር ቀናት እቆይ ነበር። በወቅቱ በመንፈሳዊው መከር የተሠማሩት ሠራተኞች ቁጥር አነስተኛ ስለነበር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰማው ዓይነት ስሜት ተሰምቶናል:- “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።” (ማቴዎስ 9:​36-38) በእነዚያ የቀድሞ ዓመታት ከአንዱ ወደ ሌላው አካባቢ መጓዝ በጣም አስቸጋሪ ነበር። በመሆኑም እኔ ጉባኤዎችን ስጎበኝ ጃኔት ደግሞ ከልጆቹ ጋር በሉዋንሻ ትቆይ ነበር። በወቅቱ ጃኔትና እኔ ሁለት ተጨማሪ ልጆች ነበሩን። ሆኖም አንደኛው ልጅ ገና በአሥር ወሩ ሞተ።

በወቅቱ መኪና እንደልብ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። መንገዶችም ቢሆኑ ውስን ነበሩ። አንድ ቀን የጃኔትን ብስክሌት እየነዳሁ ከ200 ኪሎ ሜትር የሚበልጥ ጉዞ ጀመርኩ። ትንሽ ወንዝ ሲያጋጥመኝ ብስክሌቴን ትከሻዬ ላይ እሸከምና በአንድ እጄ ደግፌ ይዤ በሌላኛው እጄ እየዋኘሁ እሻገራለሁ። የሚያስገርመው በሉዋንሻ የምሥክሮቹ ቁጥር በሚያስደንቅ ሁኔታ አድጎ በ1946 1, 850 የሚያክሉ ሰዎች በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተዋል።

ሥራችን የገጠመውን ተቃውሞ መጋፈጥ

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በመካሄድ ላይ እንዳለ አንድ የካዋምቡዋ አውራጃ አስተዳዳሪ ጠራኝና “የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ስለታገዱ ከአሁን በኋላ በእነርሱ መጠቀምህን አቁም። ሆኖም ሌሎች ጽሑፎች ለማዘጋጀት የሚረዷችሁ የምርምር ጽሑፎች ልሰጣችሁ እችላለሁ።”

“ያሉን ጽሑፎች ይበቁናል። ምንም አያስፈልገንም” በማለት መለስኩ።

“አሜሪካውያንን አታውቃቸውም። ያታልሉሃል” ሲል ተናገረ። (በወቅቱ ጽሑፎቻችን የሚታተሙት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ነበር።)

“የለም፣ እኔ የማውቃቸው እንዲህ አያደርጉም” በማለት መለስኩለት።

ከዚያም “እንደ ሌሎቹ ሃይማኖቶች ሁሉ የእናንተም ሰዎች ጦርነቱን ለመደገፍ የሚያስችል የገንዘብ መዋጮ እንዲያደርጉ ለምን አታበረታታቸውም?” ሲል ጠየቀኝ።

“ይህን የማድረግ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው” በማለት መለስኩለት።

“ለምን ቤትህ ሄደህ በጉዳዩ ላይ አታስብበትም” አለኝ።

“መጽሐፍ ቅዱስ በዘጸአት 20:​13 እና በ2 ጢሞቴዎስ 2:​24 ላይ እንዳንገልና እንዳንዋጋ አዝዞናል” በማለት መለስኩ።

እንድሄድ ቢፈቀድልኝም ብዙም ሳይቆይ አሁን ማንሳ የተባለችው የፎርት ሮዝቤሪ አውራጃ አስተዳዳሪ ጠራኝና “እዚህ የጠራሁህ መንግሥት ጽሑፎቻችሁን እንዳገደባችሁ ልነግርህ ነው” አለኝ።

“አዎን፣ ስለዚህ ጉዳይ ሰምቻለሁ” በማለት መለስኩለት።

“የአምልኮ አጋሮችህ በሙሉ ጽሑፎቻቸውን ይዘው ወደዚህ እንዲመጡ ንገራቸው። ገባህ?” አለኝ።

“ይህ የእኔ ሥራ ሳይሆን የመንግሥት ኃላፊነት ነው” በማለት መለስኩለት።

በአጋጣሚ የተደረገ ምሥክርነት ፍሬ አስገኘ

ጦርነቱ ሲያበቃ ወዲያው ስብከታችንን ቀጠልን። በ1947 ምዋንዛ በተባለው መንደር የሚገኝ አንድ ጉባኤ ጎብኝቼ ስጨርስ ሻይ መጠጣት ፈለግሁ። በአካባቢው ሻይ ቤት ይኖር እንደሆነ ስጠይቅ የሚስተር ንኮንዴን ሻይ ቤት አመለከቱኝ። ሚስተር ንኮንዴና ባለቤቱ ሞቅ ባለ ሰላምታ ተቀበሉኝ። ሻይውን እየጠጣሁ “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” ከሚለው መጽሐፍ ላይ “ሲኦል​—⁠ተስፋ ያለው የማረፊያ ቦታ” የሚለውን ምዕራፍ እንዲያነብብ ሚስተር ንኮንዴን ጠየቅኩት።

ሻይውን ጠጥቼ ስጨርስ “ታዲያ ሲኦል ምን ዓይነት ቦታ መሆኑን ተረዳኽ?” በማለት ጠየቅኩት። ባነበበው ነገር በመነካቱ ከምሥክሮቹ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከባለቤቱ ጋር ተጠመቀ። ሚስተር ንኮንዴ ምሥክር ሆኖ ባይቀጥልም ባለቤቱና አንዳንድ ልጆቹ በእውነት ውስጥ ጸንተዋል። እንዲያውም ፕሌኔ የተባለችው ልጁ አሁንም ዛምቢያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በማገልገል ላይ ትገኛለች። የፕሌኔ እናት እርጅና ቢጫጫናትም አሁንም ታማኝ ምሥክር ናት።

በምሥራቅ አፍሪካ የተደረገ ጥቂት ቆይታ

በ1948 መጀመሪያ ላይ ሉሳካ ውስጥ የተቋቋመውና ሰሜናዊ ሮዴዥያ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮአችን ታንጋኒካ (አሁን ታንዛኒያ) መደበኝ። እኔና ባለቤቴ ተራራማውን ክልል በእግራችን ስናቋርጥ አንድ ሌላ ምሥክር አብሮን ተጉዟል። ጉዞው ሦስት ቀን የፈጀና በጣም አድካሚ ነበር። እኔ በካርቶን የታጨቁ መጻሕፍት ስሸከም ባለቤቴ ደግሞ ልብሳችንን ያዘች። ሌላኛው ምሥክር ደግሞ አልጋችንን ተሸከመልን።

መጋቢት 1948 እምቤያ ስንደርስ ወንድሞች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታቸው ውስጥ ይበልጥ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሏቸውን አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ ነበረባቸው። ስለዚህም ብዙ የሚሠራ ነበር። በአንደኛ ደረጃ የአካባቢው ሰዎች የሚያውቁን የመጠበቂያ ግንብ ሰዎች በሚለው ስም ነበር። ወንድሞች የይሖዋ ምሥክር የሚለውን ስም የተቀበሉ ቢሆንም በሰዎች ዘንድ በስፋት አይታወቅም ነበር። በተጨማሪም አንዳንድ ምሥክሮች ሙታንን ከማክበር ጋር የተያያዙ አንዳንድ ልማዶችን መተው ነበረባቸው። ሆኖም ብዙ ወንድሞች ከሁሉ ይበልጥ ከባድ ሆኖ ያገኙት ጋብቻቸውን ሕጋዊ ማድረጉ ነበር። ይህ ትዳራቸው በሌሎች ዘንድ አክብሮትን እንዲያተርፍ ያስችላቸዋል።​—⁠ዕብራውያን 13:​4

በኋላም ኡጋንዳን ጨምሮ በተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የማገልገል መብት አግኝቻለሁ። በኢንተቤና በካምፓላ ለስድስት ሳምንታት የቆየሁ ሲሆን እዚያም ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያውቁ የመርዳት አጋጣሚ አግኝቻለሁ።

ወደ ኒው ዮርክ ከተማ መጓዝ

ለጥቂት ጊዜ በኡጋንዳ ካገለገልኩ በኋላ በ1956 መግቢያ ላይ የታንጋኒካ ዋና ከተማ ወደሆነችው ዳሬ ሰላም ተጓዝኩ። እዚያም ከይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የተላከ ደብዳቤ ደረሰኝ። ደብዳቤው ከሐምሌ 27 እስከ ነሐሴ 3, 1958 ኒው ዮርክ በሚደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት የሚያስችለኝን ዝግጅት እንዳደርግ የሚያሳስብ ነበር። ምን ያህል በደስታ እንደፈነጠዝኩ መገመት ትችላላችሁ።

ጊዜው ሲደርስ ሉካ ሙዋንጎ ከተባለ አንድ ሌላ የወረዳ የበላይ ተመልካች ጋር ከንዶላ ተነስተን ደቡብ ሮዴዥያ ወደምትገኘው ሳልስቤሪ (አሁን ሃራሬ) ተጓዝን። ከዚያም ወደ ናይሮቢ ኬንያ አቀናን። በኋላም ወደ ለንደን እንግሊዝ ተጓዝን። እዚያም ሞቅ ያለ አቀባበል ተደረገልን። በእንግሊዝ ባሳለፍነው የመጀመሪያ ምሽት በጣም ከመደሰታችን የተነሳ ሌሊቱን ሁሉ ነጮቹ ለእኛ ለአፍሪካውያን ስላሳዩን ደግነት ስናወራ አደርን። በዝግጅቱ ከመጠን በላይ ተበረታተን ነበር።

በመጨረሻም ስብሰባው በሚደረግበት ኒው ዮርክ ደረስን። በአንደኛው የስብሰባ ቀን በሰሜናዊ ሮዴዥያ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሪፖርት አቀረብኩ። በዚያ ቀን በኒው ዮርክ ከተማ በፖሎ ግራውንድስና በያንኪ ስታዲየም በተደረገው ስብሰባ ላይ ወደ 200, 000 የሚጠጉ ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር። በዚያ ምሽት ስላገኘሁት አስደሳች መብት ሳስብ ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ ባይኔ ሳይዞር አደረ።

ብዙም ሳይቆይ ስብሰባው አለቀና ወደ ቤታችን ተመለስን። በዚህም ጊዜ ቢሆን የእንግሊዝ ወንድሞችና እህቶች የተለመደውን ፍቅራዊ አቀባበል አደረጉልን። የይሖዋ ምሥክሮች የተለያየ ዘር ቢኖራቸውም እንኳ በዚህ ጉዞ ወቅት በመካከላቸው ያለውን አንድነት በማይረሳ ሁኔታ ለማየት ችለናል!

ፈተናዎች ቢኖሩም በአገልግሎቱ መቀጠል

በ1967 የአውራጃ አገልጋይ በመሆን ከወረዳ ወደ ወረዳ እየሄድኩ ማገልገል ጀመርኩ። በወቅቱ በዛምቢያ የምሥክሮቹ ቁጥር 35, 000 ደርሶ ነበር። በኋላም ጤናዬ በማሽቆልቆሉ በኮፐርቤልት የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ በድጋሚ ተመደብኩ። ከጊዜ በኋላ ጃኔት በጠና ታመመችና ታኅሣሥ 1984 ለይሖዋ ታማኝ እንደሆነች አንቀላፋች።

እርሷ ከሞተች በኋላ አንዳንድ የማያምኑ ዘመዶቿ አስጠንቁለህ የገደልካት አንተ ነህ በማለት ሲናገሩ በጣም አዘንኩ። ይሁን እንጂ የጃኔትን ሕመም የሚያውቁና ከሐኪሟ ጋር የተነጋገሩ አንዳንዶች ለእነዚህ ዘመዶች የሞተችበትን ምክንያት ነገሯቸው። አሁን ደግሞ ሌላ ፈተና ተደቀነብኝ። አንዳንድ ዘመዶቿ ኡኩፕያኒካ የተባለውን የአካባቢውን ልማድ እንድከተል ፈለጉ። እኔ ባደግኩበት አካባቢ ባል ወይም ሚስት ሲሞት በሕይወት ያለው የትዳር ጓደኛ ከሟቹ የቅርብ ዘመድ ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸም ይኖርበታል። ፈቃደኛ እንደማልሆን የታወቀ ነው።

ከጊዜ በኋላ ዘመዶቿ ተቃውሞአቸውን አቆሙ። ይሖዋ በአቋሜ እንድጸና ስለረዳኝ አመሰግነዋለሁ። ባለቤቴ ከተቀበረች ከአንድ ወር በኋላ አንድ ወንድም ወደ እኔ መጣና እንዲህ አለኝ:- “ወንድም ካንጋሌ፣ ባለቤትህ ስትሞት ለየትኛውም ዓይነት ልማድ ባለመንበርከክህ ከፍተኛ የብርታት ምንጭ ሆነህልናል። በጣም እናመሰግንሃለን።”

የተትረፈረፈ በረከት

የይሖዋ ምሥክር በመሆን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከጀመርኩ 65 ዓመታት ተቆጥረዋል። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ጉባኤዎች ሲቋቋሙና በአንድ ወቅት የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ባገለገልኩባቸው ቦታዎች ብዙ የመንግሥት አዳራሾች ሲገነቡ መመልከቱ ምንኛ ያስደስታል! በ1943 በዛምቢያ 2, 800 የነበረው የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር አሁን አድጎ ከ122, 000 በላይ ሆኗል። እንዲያውም ባለፈው ዓመት ከ11 ሚልዮን የማይበልጥ የሕዝብ ብዛት ባለባት በዚህች አገር ከ514, 000 የሚበልጡ ሰዎች በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተዋል።

በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ይሖዋ በጥሩ ሁኔታ ተንከባክቦኛል። መታከም ስፈልግ አንድ ክርስቲያን ወንድም ወደ ሆስፒታል ይወስደኛል። ጉባኤዎች እየጋበዙኝ አሁንም ድረስ የሕዝብ ንግግር አቀርባለሁ። ይህም ብዙ አበረታች ጊዜያት እንዳሳልፍ ረድቶኛል። ያለሁበት ጉባኤ ክርስቲያን እህቶች ተራ ገብተው ቤቴን እንዲያጸዱልኝ ዝግጅት አድርጓል። ወንድሞች በፈቃደኝነት በየሳምንቱ ወደ ስብሰባዎች ይወስዱኛል። የይሖዋ አገልጋይ ባልሆን ኖሮ እንዲህ ያለውን ፍቅራዊ እንክብካቤ እንደማላገኝ አውቃለሁ። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አለማቋረጥ እንድካፈል ስለፈቀደልኝና የተሰጡኝን ብዙ ኃላፊነቶች እስካሁኗ ሰዓት ድረስ እንድወጣ ስለረዳኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።

በአሁኑ ጊዜ ዓይኔ ደክሟል። ወደ መንግሥት አዳራሹ ስሄድ በየመንገዱ አረፍ ማለት ይኖርብኛል። ዛሬ ዛሬ የመጽሐፍ ቦርሳዬ ስለሚከብደኝ በስብሰባው ወቅት የማልጠቀምባቸውን ጽሑፎች ቤት ትቻቸው እሄዳለሁ። አገልግሎቴ በአብዛኛው ወደ ቤቴ የሚመጡ ሰዎችን በማስጠናቱ ላይ ያተኮረ ነው። ሆኖም ያለፉትን ዓመታት መለስ ብሎ በማስታወስ በዚህ ጊዜ ስለተደረገው አስደናቂ እድገት ማሰላሰሉ ምንኛ ያስደስታል! በኢሳይያስ 60:​22 ላይ የተመዘገቡት የይሖዋ ቃላት አስደናቂ ፍጻሜያቸውን ባገኙበት መስክ አገልግያለሁ። ጥቅሱ እንዲህ ይነበባል:- “ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ።” በእርግጥም ይህ ትንቢት በዛምቢያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ሲፈጸም ተመልክቻለሁ። b

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የታተመ። አሁን ግን መታተም አቁሟል።

b የሚያሳዝነው የወንድም ቶምሰን ጤንነት በጣም ተዳክሞ ስለነበር ይህ ጽሑፍ ለኅትመት በመዘጋጀት ላይ እንዳለ በታማኝነት አንቀላፍቷል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቶምሰን እና የዛምቢያ ቅርንጫፍ ቢሮ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዛሬው የዛምቢያ ቅርንጫፍ ቢሮ