በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሃይማኖታዊ ምስሎች አመጣጥ

የሃይማኖታዊ ምስሎች አመጣጥ

ሃይማኖታዊ ምስሎች አመጣጥ

‘ሃይማኖታዊ ምስሎች ወደ አምላክና ወደ ቅዱሳን ያደርሱናል።’--በአውስትራሊያ የግሪክ ኦርቶዶክስ አገረ ስብከት

ወቅቱ ሞቃታማው የበጋ ወር ነው። ከ25, 000 የሚበልጡ የግሪክ ኦርቶዶክስ ተሳላሚዎች በጠራራው ፀሐይ በኤጂያን ባሕር፣ ቲኖስ ደሴት ላይ ወደሚገኘው “ቅድስት ማርያም” ገዳም ይጓዛሉ። የፀሐዩ ትኩሳት በኢየሱስ እናት ምስል ፊት ለመስገድ እያዘገሙ የሚጓዙትን እነዚህን ቀናተኛ ተሳላሚዎች ፈጽሞ አልበገራቸውም።

ፊቷ ላይ ስቃይ የሚነበብባት አንዲት የአካል ጉዳተኛ ልጃገረድ ደሟን እያዘራች በጉልበቷ ትድሃለች። ከእርሷ ትንሽ እልፍ ብሎ በድካም የዛሉ አንዲት አዛውንት እግራቸውን እንደምንም እየጎተቱ ይጓዛሉ። ላብ ያጠመቀው አንድ ጠና ያለ ሰው በሕዝቡ መሃል እየተሽሎከለከ ይጓዛል። እነዚህ ሁሉ እንዲህ ያለውን አድካሚ ጉዞ የሚያደርጉት በማርያም ምስል ፊት ለመስገድና ለመሳለም ነው።

እነዚህ ቀናተኛ ሃይማኖተኞች በቅን ልቦና ተነሳስተው አምላክን እንደሚያመልኩ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ሃይማኖታዊ ምስሎችን ማምለክ ከክርስትና ዘመን በፊት በርካታ መቶ ዓመታት ያስቆጠረ ልማድ እንደሆነ የሚያውቁት ምን ያህሉ ናቸው?

የሃይማኖታዊ ምስሎች መበራከት

በኦርቶዶክስ እምነት ሃይማኖታዊ ምስሎች በብዛት ይገኛሉ። በቤተ ክርስቲያን ሕንፃዎች በዋና ዋና ቦታዎች ላይ የኢየሱስ፣ የማርያምና የበርካታ “ቅዱሳን” ምስሎች ተሰቅለው ይታያሉ። አማኞች በመሳለም፣ ዕጣን በማጨስና ጧፍ በማብራት ለእነዚህ ምስሎች ያላቸውን አክብሮት ያሳያሉ። በተጨማሪም ብዙዎቹ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አባላት በቤታቸው ግድግዳ ላይ ሃይማኖታዊ ሥዕሎችን የሚሰቅሉ ከመሆኑም በላይ ወደ እነርሱ ጸሎት ያቀርባሉ። የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ምስሎቹን ማምለካቸው ወደ አምላክ እንዲቀርቡ እንደሚረዳቸው ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው። ሃይማኖታዊ ምስሎች በአምላክ ጸጋ የተሞሉና ተአምር የመፈጸም ኃይል እንዳላቸው ተደርጎ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል።

እነዚህ አማኞች የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ ምስሎችን ለአምልኮ የመጠቀምን ልማድ ይደግፉ እንዳልነበር ቢያውቁ መደነቃቸው አይቀርም። ባይዛንታይም የተባለ አንድ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ከአይሁድ እምነት የመጡት የጥንት ክርስቲያኖች ለጣዖት አምልኮ ከፍተኛ ጥላቻ ነበራቸው። ቅዱሳን ለሚባሉ ሰዎች ምስል የሚቀርበውን ማንኛውንም ዓይነት አምልኮ ይቃወሙ ነበር።” ይኸው መጽሐፍ በመቀጠል ‘ሃይማኖታዊ ምስሎችን በየአብያተ ክርስቲያናቱም ሆነ በግል የማምለክ ልማድ ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ የመጣው . . . ከአምስተኛው መቶ ዘመን ወዲህ ነው’ በማለት ተናግሯል። ታዲያ የጥንቱ ክርስትና ምስሎችን ለአምልኮ የማይጠቀም ከነበረ ይህ ዓይነቱ ልማድ የጀመረው መቼ ነው?

ሃይማኖታዊ ምስሎችን ማምለክ የተጀመረው መቼ ነው?

ቪታሊ ኢቫኖይች ፔትሬንኮ የተባሉ አንድ የሃይማኖት ተመራማሪ “ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምና ከዚህ ጋር የተያያዙ ልማዶች የጀመሩት ከክርስትና ዘመን በፊት ሲሆን ‘አመጣጣቸውም ከአረማዊ አምልኮ ነው’” በማለት ጽፈዋል። ብዙዎቹ የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚስማሙበት ምስልን ማምለክ የተጀመረው በጥንቷ ባቢሎን፣ ግብፅና ግሪክ ከነበሩ ሃይማኖቶች ነው። ለምሳሌ ያህል በጥንቷ ግሪክ በአብዛኛው ይመለክ የነበረው ሃይማኖታዊ ሥዕል ሳይሆን የተቀረጹ ምስሎች ነበሩ። እነዚህ የተቀረጹ ምስሎች መለኮታዊ ኃይል እንዳላቸው ተደርጎ ይታመን ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ ምስሎች በሰው እጅ የተሠሩ ሳይሆኑ ከሰማይ የወረዱ እንደሆኑ አድርገው ያስቡ ነበር። በአንዳንድ ልዩ ክብረ በዓላት ወቅት ምስሎቹ ታጅበው በከተማ ውስጥ የሚዞሩ ሲሆን መሥዋዕትም ይቀርብላቸው ነበር። ፔትሬንኮ “የሚመለከው አካልና ምስሉ ሁለት የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን ለማስረዳት ጥረት የተደረገ ቢሆንም . . . አማኞች ምስሉ ራሱ አምላክ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩት ነበር” በማለት ተናግረዋል።

እንዲህ ያለው ምስሎችን የማምለክ ሐሳብና ልማድ ወደ ክርስትና ሰርጎ የገባው እንዴት ነው? ከላይ የተጠቀሱት ተመራማሪ እንዳሉት የክርስቶስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት በተለይ ግብፅ ውስጥ “የክርስትና እምነት ከግብፅ፣ ከግሪክ፣ ከአይሁድ፣ ከሩቅ ምሥራቅና ከሮም በመነጩ ‘አረማዊ እምነቶች’ የመበረዝ አደጋ ገጥሞት ነበር።” በውጤቱም “ክርስቲያን ቅርጻ ቅርጽ ሠሪዎች የአረማዊ ሃይማኖታዊ ምልክቶችን በመኮረጅ ለክርስትና እምነት አዳዲስ ምስሎችን አስተዋወቁ። እነዚህ አዳዲስ ሃይማኖታዊ ምስሎች አረማውያን እንደሚያደርጉት የተለየ ትኩረት ይሰጣቸው ነበር።”

ብዙም ሳይቆይ ሃይማኖታዊ ምስሎች በአብያተ ክርስቲያናትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ከፍ ያለ ቦታ ይሰጣቸው ጀመር። ዚ ኤጅ ኦቭ ፌይዝ በተባለው መጽሐፍ ላይ ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት ይህን ሁኔታ በማስመልከት እንዲህ ብለዋል:- “አምልኮ የሚሰጣቸው ቅዱሳን ቁጥር እየተበራከተ ሲመጣ አንዱን ከሌላው መለየትና ማስታወስ የሚያስችል ዘዴ መፍጠር የግድ አስፈላጊ ሆነ። የቅዱሳንና የማርያም ምስሎች በብዛት ይዘጋጁ ጀመር። ክርስቶስን በሚመለከት የእርሱ ምስል እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰበው ሥዕል ብቻ ሳይሆን መስቀሉም ጭምር ለአምልኮ መዋል ጀመረ። እንዲያውም አንዳንዶች ከክፉ ይጠብቀናል ብለው እስከማመን ደረሱ። ሕዝቡ ለሃይማኖታዊ ምስሎች ከፍተኛ ግምት ከመስጠታቸው የተነሳ ይሰግዱላቸው፣ ይሳለሟቸው፣ ጧፍ ያበሩላቸው፣ ዕጣን ያጨሱላቸው፣ በአበባ ያስጌጧቸውና ከእነርሱ አንድ ዓይነት ተዓምር ይጠብቁ ጀመር። . . . የቤተ ክርስቲያን አባቶች ምስሎቹ አማልክት ሳይሆኑ እነርሱን ለማሰብ የሚረዱ መሣሪያዎች እንደሆኑ አድርገው በተደጋጋሚ ቢናገሩም ሰሚ ጆሮ አላገኙም።”

ዛሬም ሃይማኖታዊ ምስሎችን ለአምልኮ የሚጠቀሙ ሰዎች ለምስሎቹ አክብሮት እንሰጣቸዋለን እንጂ አናመልካቸውም በማለት በተመሳሳይ ይከራከሩ ይሆናል። ከዚህም በላይ በሃይማኖታዊ ምስሎች አማካኝነት ወደ አምላክ መቅረብ ምንም ስህተት እንደሌለው እንዲያውም አስፈላጊ እንደሆነ አድርገው ይናገሩ ይሆናል። ምናልባት አንተም እንዲሁ ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጥያቄ አምላክ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማዋል? የሚለው ነው። ለሃይማኖታዊ ምስሎች አክብሮት መስጠት እንደ ማምለክ ተደርጎ ይቆጠራል? እንዲህ ያለው ልማድ ስውር አደጋዎች ይኖሩት ይሆን?

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ምስል ምንድን ነው?

የካቶሊክ እምነት አብዛኛውን ጊዜ የተቀረጹ ሐውልቶችን ለአምልኮ ይጠቀማል። የኦርቶዶክስ እምነት ግን በእንጨት ወይም በወረቀት ላይ የተሳሉ የክርስቶስ፣ የማርያም፣ “የቅዱሳን፣” የመላእክት ምስሎችን እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ወይም በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ውስጥ የጎላ ስፍራ የሚሰጣቸው ሰዎችንና ክንውኖችን የሚያሳዩ ምስሎችን ለአምልኮ ይጠቀማሉ።

የኦርቶዶክስ አማኞች እንደሚሉት ሃይማኖታዊ ምስሎቹ ከተለመዱት የሥዕል ዓይነቶች በእጅጉ የተለዩ ናቸው። በተጨማሪም ምስሎቹ የተሠሩባቸው እንጨቶችና ወረቀቶች “በአምላክ ጸጋ የተሞሉ” እንደሆነ ተደርጎ ይታመናል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምስሎችን ለአምልኮ የመጠቀም ልማድ የጀመረው ከአረማዊ እምነቶች ነው

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© AFP/CORBIS