በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማስተማር ችሎታህ ውጤታማ ነውን?

የማስተማር ችሎታህ ውጤታማ ነውን?

የማስተማር ችሎታህ ውጤታማ ነውን?

ወላጆችም ሆኑ ሽማግሌዎች እንዲሁም የምሥራቹ ሰባኪዎች ሁሉም የማስተማር ኃላፊነት አለባቸው። ወላጆች ልጆቻቸውን ያስተምራሉ፣ ሽማግሌዎች የክርስቲያን ጉባኤን አባላት ያስተምራሉ፣ የምሥራቹ ሰባኪዎች ደግሞ ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎችን ያስተምራሉ። (ዘዳግም 6:6, 7፤ ማቴዎስ 28:19, 20፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:13, 16) የማስተማር ችሎታህን ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ በአምላክ ቃል ውስጥ የተጠቀሱት ብቃት ያላቸው አስተማሪዎች የተዉትን ምሳሌና የሚያስተምሩበትን መንገድ በመኮረጅ ነው። ዕዝራ እንደዚህ ያለ አስተማሪ ነበር።

ከዕዝራ ምሳሌ መማር

ዕዝራ ከአሮን ወገን የተወለደ ካህን ሲሆን ከ2,500 ዓመታት ገደማ በፊት በባቢሎን ይኖር ነበር። በ468 ከዘአበ በኢየሩሳሌም በሚኖሩት አይሁዳውያን መካከል ንጹሕ አምልኮን ለማስፋፋት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። (ዕዝራ 7:1, 6, 12, 13) ይህ ኃላፊነት ለሕዝቡ የአምላክን ሕግ ማስተማር ይጠይቅበት ነበር። ዕዝራ ውጤታማ የማስተማር ችሎታ ለማዳበር ምን አደረገ? በርካታ አስፈላጊ እርምጃዎች ወስዷል። በዕዝራ 7:​10 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን እነዚህን እርምጃዎች ተመልከት:-

“ዕዝራም የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግ ና ያደርግ ዘንድ፣ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እስቲ እነዚህን እርምጃዎች አንድ በአንድ እንመርምርና ምን ትምህርት ልናገኝ እንደምንችል እንመልከት።

‘ዕዝራም ልቡን አዘጋጅቶ ነበር’

አንድ ገበሬ ዘር ከመዝራቱ በፊት መሬቱን በማረስ አፈሩን እንደሚያዘጋጀው ሁሉ ዕዝራም የአምላክን ቃል ለመቀበል በጸሎት አማካኝነት ልቡን አዘጋጅቶ ነበር። (ዕዝራ 10:​1) በሌላ አባባል ልቡን ወደ ይሖዋ ትምህርት ‘አዘንብሎ’ ነበር።​—⁠ምሳሌ 2:​2

በተመሳሳይ ንጉሥ ኢዮሣፍጥም ‘እግዚአብሔርን ለመፈለግ ልቡን እንዳዘጋጀ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ዜና መዋዕል 19:​3) ከዚህ በተቃራኒ ግን “ልቡን ያላዘጋጀ[ው]” የእስራኤል ሕዝብ “እልከኛና ዓመፀኛ” ተብሏል። (መዝሙር 78:​8 NW ) ይሖዋ “የተሰወረው[ን] የልብ ሰው” ይመለከታል። (1 ጴጥሮስ 3:​4) አዎን፣ “ለትሑታን መንገዱን ያስተምራቸዋል።” (መዝሙር 25:​9 አ.መ.ት ) እንግዲያው ዛሬ ያሉት አስተማሪዎችም የዕዝራን ምሳሌ በመከተል በጸሎት አማካኝነት በቅድሚያ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ማዳበራቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው!

‘የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግ ዘንድ’

ዕዝራ ብቃት ያለው አስተማሪ ለመሆን የአምላክን ቃል ይፈልግ ነበር። ሐኪም ለማማከር ብትሄድ የሚናገረውንና የሚያዝዘውን በሙሉ በሚገባ መረዳት እንድትችል በትኩረት አታዳምጠውምን? ጤንነትህን የሚመለከት በመሆኑ እንደዚያ እንደምታደርግ ምንም ጥርጥር የለውም። እንግዲያው ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ እና በ“ታማኝና ልባም ባሪያ” አማካኝነት ለሚነግረን ወይም ለሚያዝዘን ነገሮች የበለጠ ትኩረት መስጠት ይገባናል። ምክንያቱም እሱ የሚሰጠው ምክር በቀጥታ ሕይወታችንን የሚነካ ነው! (ማቴዎስ 4:​4፤ 24:​45-47) እርግጥ ነው አንድ ሐኪም ሊሳሳት ይችል ይሆናል፤ “የእግዚአብሔር ሕግ [ግን] ፍጹም ነው።” (መዝሙር 19:​7) ትምህርቱ ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ከሌላ ሰው ምክር መጠየቅ ፈጽሞ አያስፈልገንም።

ዕዝራ በእርግጥም ትጉህ ተማሪ እንደነበረ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑት የዜና መዋዕል መጻሕፍት (ዕዝራ መጀመሪያ ላይ በአንድ ጥቅል የጻፋቸው) ያሳያሉ። እነዚህን መጻሕፍት ለመጻፍ በርካታ ጽሑፎችን አገላብጧል። a ከባቢሎን ከተመለሱ ብዙም ያልቆዩት አይሁዳውያን የሕዝባቸውን አጠቃላይ ታሪክ ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር። ስለ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶቻቸው፣ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ስለሚከናወነው አገልግሎትና ስለ ሌዋውያኑ የሥራ ድርሻ ያላቸው እውቀት ውስን ነበር። የዘር ሐረግ መዝገቦች በጣም ያስፈልጓቸው ነበር። ዕዝራ ለእነዚህ ጉዳዮች ለየት ያለ ትኩረት ሰጥቷል። መሲሑ እስኪመጣ ድረስ አይሁዳውያኑ የራሱ አገር፣ ቤተ መቅደስ፣ የክህነት አገልግሎት እንዲሁም ገዢ ያለው አንድ ሕዝብ ሆነው መቆየት ነበረባቸው። ዕዝራ አስፈላጊውን መረጃ በመሰብሰቡ አንድነታቸውና እውነተኛው አምልኮ ተጠብቆ ሊቆይ ችሏል።

የጥናት ልማድህ ከዕዝራ ጋር ሲወዳደር ምን ይመስላል? መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናትህ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተማር ይረዳሃል።

በቤተሰብ ሆናችሁ ‘የእግዚአብሔርን ሕግ ፈልጉ’

ከግል ጥናት በተጨማሪ የቤተሰብ ጥናትም የይሖዋን ሕግ ለመፈለግ የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ነው።

ያንና ዩልያ የተባሉ በኔዘርላንድስ የሚኖሩ ባልና ሚስት ለሁለቱም ወንዶች ልጆቻቸው ከተወለዱበት እለት ጀምሮ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያነብቡላቸው ነበር። ዛሬ ኢቮ 15 ዓመቱ ሲሆን ኤዶ ደግሞ 14 ዓመቱ ነው። አሁንም ቢሆን በሳምንት አንድ ጊዜ የቤተሰብ ጥናት ያደርጋሉ። ያን እንዲህ ይላል:- “ዋናው ዓላማችን በጥናቱ ወቅት ብዙ ሐሳብ መሸፈን ሳይሆን ልጆቹ የምንወያየው ነገር በደንብ እንዲገባቸው ማድረግ ነው። ልጆቹ ጥልቀት ያለው ምርምር ያደርጋሉ። እንግዳ ቃላት ሲገጥሟቸው ትርጉማቸውን ለማወቅ ይጥራሉ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች የኖሩበትን ዘመን፣ ማንነታቸውን፣ ሥራቸውንና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮችን ለማወቅ ምርምር ያደርጋሉ። ማንበብ ከተማሩበት ጊዜ አንስቶ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው መጽሐፍ፣ በመዝገበ ቃላትና በኢንሳይክሎፔድያዎች ይጠቀሙ ነበር። ይህም የቤተሰብ ጥናቱን ይበልጥ አስደሳች ያደርገዋል። ልጆቹ ሁልጊዜ የቤተሰብ ጥናታችንን በጉጉት ነው የሚጠባበቁት።” ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱም ልጆች በቋንቋ ችሎታቸው ከክፍላቸው ተማሪዎች የላቁ ናቸው።

ጆንና ቲኔ የተባሉት በኔዘርላንድስ የሚኖሩ ሌላ ባልና ሚስትም ኤስሊ ከሚባለው ልጃቸው (አሁን 24 ዓመቱ ሲሆን በሌላ ጉባኤ አቅኚ ሆኖ ያገለግላል) እና ሊንዳ ከተባለችው ልጃቸው (አሁን 20 ዓመቷ ሲሆን አንድ ጥሩ ወንድም አግብታለች) ጋር ያጠኑ ነበር። ይሁን እንጂ አንድን ጽሑፍ በተለምዶው በሚደረገው የጥያቄና መልስ ውይይት መልክ ከመሸፈን ይልቅ የቤተሰብ ጥናቱን ከልጆቻቸው ዕድሜና ፍላጎት ጋር በሚስማማ መንገድ አስተካክለውት ነበር። ይጠቀሙበት የነበረው መንገድ ምንድን ነው?

ጆን ልጆቹ “የአንባብያን ጥያቄዎች” (ከመጠበቂያ ግንብ) እና “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት” (ከንቁ! ) ከሚሉት ርዕሶች ላይ ትኩረታቸውን የሳበውን ትምህርት ይመርጡ እንደነበር ይናገራል። ከዚያም የተዘጋጁበትን ሐሳብ ያቀርባሉ፤ ይህም ግሩም የቤተሰብ ውይይት ለማድረግ መንገድ ይከፍታል። በዚህ መንገድ ልጆቹ ምርምር የማድረግና ባጠኑት ነገር ላይ የመወያየት ልማድ አዳብረዋል። ከልጆችህ ጋር ሆነህ ‘የእግዚአብሔርን ሕግ ትፈልጋለህን?’ እንደዚህ ማድረግህ የራስህን የማስተማር ችሎታ ከማዳበሩም በላይ ልጆችህ ይበልጥ ውጤታማ አስተማሪዎች እንዲሆኑ ይረዳቸዋል።

“ያደርግ ዘንድ”

ዕዝራ የተማረውን ተግባራዊ ያደርግ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ እዚያው ባቢሎን እያለ የተመቻቸ ኑሮ መኖር ይችል ነበር። ሆኖም ከባቢሎን ውጪ የሚኖሩ ወገኖቹን ሊረዳ እንደሚችል ሲገነዘብ በባቢሎን የነበረውን ምቾት የተሞላበት ኑሮ ትቶ ርቃ በምትገኘውና ብዙ አመቺ ያልሆኑ ሁኔታዎች፣ ችግሮችና አደጋዎች ባሉባት በኢየሩሳሌም ለመኖር መረጠ። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ዕዝራ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ከመሰብሰብም ባሻገር የተማረውን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ነበር።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 3:13

በኢየሩሳሌም በሚኖርበትም ጊዜ የተማረውንና እያስተማረ ያለውን ነገር በተግባር እንደሚያውለው በድጋሚ አሳይቷል። ዕዝራ እስራኤላውያን ወንዶች አረማዊ ሴቶች ማግባታቸውን ሲሰማ ከሰጠው ምላሽ ይህንን መረዳት ይቻላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ‘ልብሱንና መጎናጸፊያውን እንደቀደደ እንዲሁም የራስና የጢሙን ጸጉር እንደነጨና እስከ ማታ ደንግጦ እንደተቀመጠ’ ይናገራል። ‘ፊቱን ወደ ይሖዋ ማንሣት እንኳን አሳፍሮት’ ነበር።​—⁠ዕዝራ 9:​1-6

በአምላክ ቃል ላይ ያደረገው ጥናት በጥልቅ ነክቶታል! ዕዝራ የሕዝቡ አለመታዘዝ የሚያስከትለውን አስከፊ ውጤት በሚገባ ተገንዝቦ ነበር። ከምርኮ የተመለሱት አይሁዳውያን ቁጥር ጥቂት ነበር። እነሱም ከሌሎች ጋር መጋባት ከጀመሩ ከጊዜ በኋላ በዙሪያቸው ካሉት አረማዊ ብሔራት ጋር ይቀላቀሉና እውነተኛው አምልኮ በቀላሉ ከምድር ገጽ ሊጠፋ ይችላል።

የሚያስደስተው ዕዝራ ያሳየው ቅንዓትና ፈሪሃ አምላክ የተንጸባረቀበት ምሳሌው እስራኤላውያኑ መንገዳቸውን እንዲያስተካክሉ ገፋፍቷቸዋል። እስራኤላውያን ያልሆኑ ሚስቶቻቸውን አባረሩ። በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ሁሉም ነገር ተስተካከለ። ዕዝራ ለአምላክ ሕግ ታማኝ መሆኑ የሚያስተምረው ትምህርት ውጤታማ እንዲሆን ረድቶታል።

ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አንድ ክርስቲያን ወላጅ እንዲህ ብሏል:- “ልጆች ከምትነግሯቸው ነገር ይልቅ የምታደርጉትን ነገር ማድረግ ይቀናቸዋል!” በክርስቲያን ጉባኤም ውስጥ ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። ሽማግሌዎች ጥሩ ምሳሌ የሚተዉ ከሆነ ጉባኤውም የሚያስተምሩትን ትምህርት ተግባራዊ እንደሚያደርግ ሊጠብቁ ይችላሉ።

“ለእስራኤል ሥርዓትንና ፍትሕን ያስተምር ዘንድ”

ዕዝራ የማስተማር ችሎታው ውጤታማ እንዲሆን የረዳው አንድ ሌላ ምክንያት አለ። የሚያስተምረው የራሱን ሐሳብ ሳይሆን “ሥርዓትንና ፍርድን [“ፍትሕን፣” NW ]” ማለትም የይሖዋን ሥርዓቶች ወይም ሕግጋት ነበር። የክህነት ኃላፊነቱ ይህን ማድረግ ይጠይቅበት ነበር። (ሚልክያስ 2:​7) ዕዝራ ፍትሕን ያስተምር እንዲሁም መሥፈርቱ በሚጠይቀው መሠረት ፍትሐዊ በሆነና ከአድልዎ ነጻ በሆነ መንገድ ትክክል የሆነውን ነገር ተግባራዊ በማድረግ ምሳሌ ይሆን ነበር። በሥልጣን ላይ ያሉት ፍትሕ ሲያሳዩ የተረጋጋ ሁኔታ የሚሰፍን ከመሆኑም በላይ ዘላቂ ውጤቶችም ይገኛሉ። (ምሳሌ 29:​4 NW ) በተመሳሳይም የአምላክን ቃል ጠንቅቀው የሚያውቁ ክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ ወላጆች እና የመንግሥቱ ሰባኪዎች የይሖዋን ሥርዓትና ፍትሕ በጉባኤ ውስጥ፣ ለቤተሰባቸውና ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች በማስተማር የተረጋጋና የሰከነ መንፈሳዊ አቋም እንዲኖር ያደርጋሉ።

የታማኙን ዕዝራ ምሳሌ ሙሉ በሙሉ ከተከተልክ የማስተማር ችሎታህ ይበልጥ ውጤታማ የሚሆን አይመስልህም? እንግዲያው ‘ልብህን አዘጋጅ፣ የይሖዋን ሕግ ፈልግ፣ ሕጉን በተግባር ላይ አውለው እንዲሁም የይሖዋን ሥርዓት እና ፍርድ አስተምር።’​—⁠ዕዝራ 7:​10

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 444-5 ላይ ዕዝራ ዋቢ አድርጎ የጠቀሳቸውን 20 የሚያህሉ መዛግብት ዝርዝር ማግኘት ይቻላል።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ዕዝራ የማስተማር ችሎታው ውጤታማ እንዲሆን ያስቻለው ምንድን ነው?

1. ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ አዳብሮ ነበር

2. የይሖዋን ሕግ ይፈልግ ነበር

3. የተማረውን በሥራ በማዋል ረገድ ጥሩ ምሳሌ ነበር

4. መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ትምህርት ለማስተማር ይጥር ነበር