‘ለሰው ሁሉ መልካም እናድርግ’
“ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ”
‘ለሰው ሁሉ መልካም እናድርግ’
የኢየሱስ ተቀዳሚ ተግባር የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክና ማስተማር ነበር። (ማርቆስ 1:14፤ ሉቃስ 8:1) ተከታዮቹ የእሱን ምሳሌ መኮረጅ ስለሚፈልጉ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የማስተማሩን ሥራ የሕይወታቸው ዋነኛ ክፍል አድርገውታል። (ሉቃስ 6:40) ኢየሱስ ምድር በነበረበት ጊዜ እንደሆነው ሁሉ ዛሬም የመንግሥቱን መልእክት የተቀበሉ ሰዎች ዘላቂ የሆነ እረፍት እንዳገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ሲመለከቱ በጣም ይደሰታሉ።—ማቴዎስ 11:28-30
ኢየሱስ የአምላክን ቃል ከማስተማሩም በላይ የታመሙትን ፈውሷል፣ የተራቡትን መግቧል እንዲሁም ሌሎች መልካም ሥራዎችን አከናውኗል። (ማቴዎስ 14:14-21) በተመሳሳይም የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ከማስተማር ሥራቸው በተጨማሪ ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን ይረዳሉ። ደግሞም ቅዱሳን ጽሑፎች ክርስቲያኖች ‘ለበጎ ሥራ ሁሉ ’ የተዘጋጁ እንዲሆኑ በማስታጠቅ ‘ለሰው ሁሉ መልካም እንዲያደርጉ’ ያሳስቧቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17፤ ገላትያ 6:10
“ወንድሞቻችን ደርሰውልናል”
መስከረም 1999 ታይዋን አውዳሚ በሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ተመታች። ከጥቂት ወራት በኋላ በኃይለኛ ዝናብና በመሬት ናዳ ምክንያት በቬንዙዌላ ታሪክ ውስጥ በአጥፊነቱ ተወዳዳሪ የሌለው አደጋ ተከሰተ። ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ሞዛምቢክ ኃይለኛ በሆነ ጎርፍ ተጥለቀለቀች። በሦስቱም ጊዜያት የይሖዋ ምሥክሮች ለአደጋው ሰለባዎች ምግብ፣ ውኃ፣ መድኃኒት፣ ልብስ፣ ድንኳኖችና የምግብ ማብሰያ ቁሳቁሶችን ይዘው በአደጋው ቦታ በፍጥነት ደርሰዋል። የህክምና ሙያ ያላቸው ፈቃደኛ ሠራተኞች ጉዳት የደረሰባቸውን ለማከም ጊዜያዊ ክሊኒኮችን ያቋቋሙ ሲሆን ፈቃደኛ የግንባታ ሠራተኞች ደግሞ ቤታቸው ለፈረሰባቸው ሰዎች አዳዲስ ቤቶችን ገንብተዋል።
የአደጋው ተጠቂዎች በተደረገላቸው ፈጣን እርዳታ ልባቸው በጥልቅ ተነክቷል። በቬንዙዌላ በተከሰተው የመሬት ናዳ ቤቷ የወደመባት ማልዮሪ “ተስፋ በቆረጥንበት ሰዓት ወንድሞቻችን ደርሰውልናል” ብላለች። ፈቃደኛ ሠራተኞች ለቤተሰቧ አዲስ ቤት ከገነቡላት በኋላ ማልዮሪ የተሰማትን ደስታ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “ላደረገልን ሁሉ ይሖዋን ለማመስገን ቃላት ያጥረናል!” a
በሞዛምቢክ የጎርፉ አደጋ ተጠቂዎች የአዲሱን ቤታቸውን ቁልፍ ሲረከቡ ሁሉም በድንገት “ይሖዋ መጠጊያችን ነው” የሚለውን የመንግሥቱን መዝሙር መዘመር ጀመሩ።ፈቃደኛ ሠራተኞቹም የተቸገሩ ወንድሞቻቸውን በመርዳታቸው የመንፈስ እርካታ አግኝተዋል። ሞዛምቢክ በሚገኝ አንድ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ነርስ ሆኖ ያገለገለው ማርሴሎ “ይህን ያህል ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ለእነዚህ ወንድሞች አንድ ዓይነት አስተዋጽዖ ማድረግ መቻሌ አስደስቶኛል” በማለት ተናግሯል። በታይዋን ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆኖ ያገለገለው ሁዋንግ እንዲህ ብሏል:- “በችግር ላይ ለሚገኙት ወንድሞቻችን ምግብና ድንኳን በማቅረቡ ሥራ መካፈል ትልቅ ደስታ የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ እምነት የሚያጠነክር ነበር።”
ውጤታማ የሆነ በፈቃደኝነት የሚደረግ የማስተማር ሥራ
በፈቃደኝነት የሚደረግ የማስተማር ሥራም በዓለም ዙሪያ በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ እስረኞች መንፈሳዊ እረፍት አምጥቶላቸዋል። እንዴት? በቅርብ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ 4,000 በሚሆኑ ወኅኒ ቤቶች ውስጥ ለሚገኙ ከ30, 000 ለሚበልጡ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አሰራጭተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ምሥክሮቹ በወኅኒ ቤቶች ውስጥ በአካል ተገኝተው እስረኞቹን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናሉ፤ እንዲሁም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ያደርጋሉ። እስረኞቹ ከዚህ ዝግጅት ጥቅም አግኝተዋል?
መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያጠኑት እስረኞች መካከል አንዳንዶቹ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን እረፍት የሚሰጡ ትምህርቶች ለሌሎች እስረኞች ማካፈል ጀምረዋል። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ በብዙ ወኅኒ ቤቶች ውስጥ አንድ ላይ ሆነው ይሖዋን የሚያመልኩ የእስረኞች ቡድኖች ሊኖሩ ችለዋል። በ2001 አንድ በኦሪገን ዩ ኤስ ኤ የሚገኝ እስረኛ እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “ቡድናችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው። ሰባት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ያሉን ሲሆን 38 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እንመራለን። በሕዝብ ንግግርና በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ከ25 የሚበልጡ ሰዎች ይገኛሉ። [በኢየሱስ ሞት] መታሰቢያ በዓል ላይ ደግሞ 39 የሚያህሉ ተሰብሳቢዎች ነበሩን። በቅርቡ ሦስት ሰዎች ይጠመቃሉ!”
የተገኘው ጥቅምና ደስታ
ይህ በፈቃደኝነት የሚደረግ የማስተማር ሥራ ውጤታማ መሆኑን የወኅኒ ቤት ባለ ሥልጣናት አስተውለዋል። ባለ ሥልጣኖችን ይበልጥ ያስገረማቸው ግን ይህ በፈቃደኝነት የሚደረግ የትምህርት መርኃ ግብር የሚያስገኘው ጥቅም ዘላቂ መሆኑ ነው። አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “ይህ መርኃ ግብር ተግባራዊ በሆነባቸው ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ወኅኒ ቤት ተጠምቀው ከተፈቱት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንድም እስረኛ በድጋሚ አልታሰረም። በተቃራኒው ግን ከሌሎች እስረኞች መካከል ከ50-60 በመቶ የሚሆኑት ከእስር ከተፈቱ በኋላ ሌላ ወንጀል ፈጽመው ዳግመኛ ይታሰራሉ።” በኢዳሆ የሚገኙ አንድ የወኅኒ ቤት ቄስ ምሥክሮቹ የሚያከናውኑት የፈቃደኝነት ሥራ ባስገኘው ውጤት ስለ ተነኩ ለይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በጻፉት ደብዳቤ ላይ “በሃይማኖታዊ እምነታችሁ የማልስማማ ብሆንም እንኳ ድርጅታችሁ ግን በጣም ያስደንቀኛል” ብለዋል።
ፈቃደኛ ሠራተኞቹም እስረኞችን መርዳት እርካታ የሚሰጥ ሥራ ሆኖ አግኝተውታል። ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግሥቱን መዝሙር የመዘመር አጋጣሚ ያገኙ እስረኞች የተገኙበትን ስብሰባ ከመራ በኋላ አንድ ፈቃደኛ ሠራተኛ እንዲህ ሲል ጻፈ:- “ሃያ ስምንት እስረኞች በአንድነት ለይሖዋ ውዳሴ ሲዘምሩ መመልከት መንፈስን የሚያድስ ነው። የዘመሩትም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ነበር! እንዲህ ባለ አጋጣሚ ላይ መገኘት ምንኛ ልዩ መብት ነው!” በአሪዞና የሚገኙ ወኅኒ ቤቶችን የሚጎበኝ አንድ ፈቃደኛ ሠራተኛ “በዚህ ልዩ ሥራ መካፈል እንዴት ያለ ግሩም በረከት ነው!” ብሏል።
በዓለም ዙሪያ በፈቃደኛ አገልግሎት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ምሥክሮች ‘ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ደስተኛ ነው’ በሚለው የኢየሱስ አባባል ይስማማሉ። (ሥራ 20:35) እንዲሁም ለሰው ሁሉ መልካም ማድረግን አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር መከተል በእርግጥም መንፈስን እንደሚያድስ በራሳቸው ሕይወት ተመልክተውታል።—ምሳሌ 11:25
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች በታተመው ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ በተባለው ቡክሌት ውስጥ መዝሙር ቁጥር 38 (85)ን ተመልከት።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቬንዙዌላ
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታይዋን
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሞዛምቢክ