በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰዎች ስለ ሲኦል ያላቸው እምነት ተለውጧልን?

ሰዎች ስለ ሲኦል ያላቸው እምነት ተለውጧልን?

ሰዎች ስለ ሲኦል ያላቸው እምነት ተለውጧልን?

“ሲኦል” የሚለውን ቃል ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ሲኦል ሲባል ወደ አእምሮህ የሚመጣው ዘላለማዊ የመሠቃያ ቦታ ነው? ወይስ ከአምላክ መራቅን የሚያመለክት ምሳሌያዊ መግለጫ?

ለብዙ መቶ ዘመናት የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች ሲኦልን የኃጢአተኞች ዕጣ ፈንታ እንደሆነ አድርገው ሲመለከቱት ቆይተዋል። ሌሎች ብዙ ሃይማኖቶችም የዚህ ዓይነት እምነት አላቸው። ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት እንደዘገበው ‘ሲኦል የሚለውን ቃል በስፋት ያስተዋወቁት ክርስቲያኖች ቢሆኑም በዚህ መሠረተ ትምህርት የሚያምኑት እነርሱ ብቻ አይደሉም።’ ‘አንዳንድ አነስተኛ ሃይማኖታዊ ቡድኖችን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ያሉ ታላላቅ ሃይማኖቶች በሙሉ ማለት ይቻላል ከሞት በኋላ ቅጣት አለ የሚል እምነት አላቸው።’ ሂንዱዎች፣ ቡዲስቶች፣ ሙስሊሞችና ሌሎች በሩቅ ምሥራቅ የሚገኙ ሃይማኖቶችም በሲኦል እሳት ያምናሉ።

ሆኖም በዛሬው ጊዜ ሰዎች ስለ ሲኦል ያላቸው አመለካከት በመለወጥ ላይ ነው። ከላይ የተጠቀሰው መጽሔት እንደገለጸው “ዛሬም በእሳታማ ሲኦል የሚያምኑ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም ሲኦል አንድ ሰው ለብቻው ተገልሎ የሚታሠርበት ቦታ ነው የሚል አመለካከት ያላቸው ሰዎች ብቅ ማለት ጀምረዋል። ይህም ሲኦል ቀድሞ ይታመንበት እንደነበረው የሥቃይ ቦታ አይደለም ማለት ነው።”

ላ ሲቪልታ ካቶሊካ የተባለ አንድ የካቶሊኮች መጽሔት እንደገለጸው “አምላክ አጋንንትን ተጠቅሞ ኃጢአተኞችን በእሳት ያቃጥላል ብሎ ማሰብ . . . ስህተት ነው።” አክሎም “ሲኦል የሚያመለክተው ቦታን ሳይሆን ግለሰቡ ከአምላክ በመለየቱ ምክንያት በአእምሮው ላይ የሚደርስበትን ሥቃይ ነው።” በ1999 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዳግማዊ ጆን ፖል እንደሚከተለው ብለው ነበር:- “ሲኦል የሚያመለክተው ቦታን ሳይሆን ራሳቸውን የሕይወትና የደስታ ምንጭ ከሆነው አምላክ ሙሉ በሙሉ የለዩ ሰዎች የሚገኙበትን ሁኔታ ነው።” ሲኦል እሳታማ ቦታ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ያለውን እምነት በማስመልከት ሲገልጹ “ከአምላክ ውጪ የሆነ ሕይወት ምን ያህል ባዶና ትርጉም የለሽ መሆኑን ያሳያል” ብለዋል። ጳጳሱ ሲኦልን “ኃጢአተኞች መንሽ በያዘ ዲያብሎስ የሚጠበሱበት ቦታ እንደሆነ” አድርገው ቢገልጹት ኖሮ “አንድም ሰው አያምንበትም ነበር” በማለት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ማርቲን ማርቲ ተናግረዋል።

ሌሎች ሃይማኖቶችም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አስተሳሰብ ማዳበር ጀምረዋል። የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ባቀረበው አንድ ሪፖርት መሠረት ‘ሲኦል ዘላለማዊ መቃጠያ ሳይሆን አንድ ሰው ከአምላክ በመራቅ የሚመርጠው የሕይወት መንገድ ነው።’

የዩናይትድ ስቴትስ ኤፔስኮፓል ቤተ ክርስቲያን ማስተማሪያ መጽሐፍ ሲኦልን “ከአምላክ በመራቃችን ምክንያት የሚደርስብን ዘላለማዊ ሞት” በማለት ይፈታዋል። ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት እንደዘገበው ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ብዙ ሰዎች “የኃጢአተኞች ዕጣ ፈንታ ጥፋት እንጂ ዘላለማዊ ሥቃይ አይደለም” የሚል አመለካከት አላቸው። “አምላክን ችላ የሚሉ ሁሉ በሲኦል ‘አጥፊ እሳት’ ሙሉ በሙሉ ይጠፋሉ በማለት ይከራከራሉ።”

በዛሬው ጊዜ የእሳታማ ሲኦል መሠረተ ትምህርት የቀድሞ ተቀባይነቱን ቢያጣም ብዙዎች ሲኦል ቃል በቃል መቃጠያ ቦታ ነው በሚለው እምነታቸው ጸንተዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ኬንታኪ ሉዊቨል የሚገኘው የሳውዘርን ባፕቲስት ቲኦሎጂካል ሴሚናሪ ባልደረባ የሆኑት አልበርት ሞህለር “ቅዱስ ጽሑፉ ሲኦል ቃል በቃል የመቃጠያ ቦታ እንደሆነ አድርጎ ይገልጻል” በማለት ተናግረዋል። እንዲሁም ዘ ኔቸር ኦቭ ሄል በሚል ርዕስ ኢቫንጀሊካል አሊያንስ ኮሚሽን ያዘጋጀው አንድ ሪፖርት “ሲኦል የሚያመለክተው ሆነ ብሎ ከአምላክ መራቅንና በዚህም ምክንያት የሚደርስን ሥቃይ ነው” ብሏል። አክሎም “በምድር ላይ በተሠራው ኃጢአት መጠን ቅጣቱና ሥቃዩም የዚያኑ ያህል ይለያያል” ሲል ገልጿል።

ስለዚህ አሁንም በድጋሚ የሚነሳው ጥያቄ ሲኦል የሚያመለክተው ዘላለማዊ መቃጠያ ቦታን ነው ወይስ ጨርሶ መጥፋትን? ወይስ ከአምላክ መለየትን? በእርግጥ ሲኦል ምንድን ነው?

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የእሳታማ ሲኦል እምነት ታሪካዊ አመጣጥ በአጭሩ

ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች በእሳታማ ሲኦል ማመን የጀመሩት መቼ ነው? ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ ከሞቱ ከረዥም ጊዜ በኋላ ነው። በፈረንሳይኛ የተዘጋጀው ኢንሳይክሎፒዲያ ዩኒቨርሳሊስ “ኃጢአተኞች በሲኦል እንደሚቀጡና እንደሚሠቃዩ ለመጀመሪያ ጊዜ የገለጸው የጴጥሮስ ራእይ (2ኛው መቶ ዘመን እዘአ) የተባለው [አዋልድ] መጽሐፍ ነው” በማለት ገልጿል።

ሲኦልን በተመለከተ በቀድሞዎቹ የክርስቲያን አባቶች መካከል የነበረው እምነት የተለያየ ነበር። ሰማዕቱ ጀስቲን፣ የእስክንድርያው ክሌመንት፣ ተርቱልያን እና ሲፕሪያን ሲኦል የመቃጠያ ሥፍራ ነው ብለው ያምኑ ነበር። ኦሪጀንና የኒሳው የሃይማኖት ምሁር ግሪጎሪ ሲኦል ከአምላክ በመለየታችን ምክንያት የሚደርስብን መንፈሳዊ ሥቃይ ነው የሚል አመለካከት ነበራቸው። በሌላው በኩል ደግሞ የሂፖው አውግስቲን የሲኦል ሥቃይ መንፈሳዊና ሥጋዊ ነው የሚል እምነት ነበረው። ይህ አመለካከት በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል። ፕሮፌሰር ጄ ኤን ዲ ኬሊ እንደገለጹት ከሆነ “በአምስተኛው መቶ ዘመን አካባቢ ኃጢአተኞች ከዚህ ሕይወት በኋላ ሌላ ሁለተኛ እድል እንደማይሰጣቸውና እነርሱን ለማቃጠል የሚነድደው እሳት ፈጽሞ እንደማይጠፋ የሚገልጸው መሠረተ ትምህርት በሁሉም ቦታዎች ተስፋፍቶ ነበር።”

ማርቲን ሉተር እና ጆን ካልቪንን የመሳሰሉ በ16ኛው መቶ ዘመን የተነሱ የፕሮቴስታንት ተሃድሶ አራማጆች እሳታማ ሲኦል ምሳሌያዊ መግለጫ እንደሆነና ከአምላክ ለዘላለም መለየትን እንደሚያመለክት ያምኑ ነበር። ይሁን እንጂ በቀጣዮቹ ሁለት መቶ ዓመታት ሲኦል የመቃጠያ ቦታ ነው የሚለው እምነት እንደገና ተስፋፍቷል። የፕሮቴስታንቱ ሰባኪ ጆናታን ኤድዋርድስ በደማቅ ቀለም የተሳሉ ሥዕሎችን በመጠቀም የ18ኛውን መቶ ዘመን አሜሪካውያን ቅኝ ገዢዎች ልብ በፍርሃት ለማራድ ተጠቅሞበታል።

ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ የእሳታማ ሲኦል መሠረተ ትምህርት እየደበዘዘና እየጠፋ ሄደ። ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት እንደዘገበው “20ኛው መቶ ዘመን የሲኦል መሠረተ ትምህርት ሊጠፋ የተቃረበበት ዘመን ሆኗል።”

[ሥዕል]

ሰማዕቱ ጀስቲን ሲኦል እሳታማ ቦታ ነው የሚል እምነት ነበረው

የሂፖው አውግስቲን የሲኦል ሥቃይ መንፈሳዊና ሥጋዊ ነው የሚል አመለካከት ነበረው