ሲኦል ምንድን ነው?
ሲኦል ምንድን ነው?
“ሲኦል” የሚለውን ቃል ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንም ይሁን ምን ብዙ ሰዎች ሲኦል ኃጢአተኞች የሚቀጡበት ቦታ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአትንና እርሱ የሚያስከትለውን መዘዝ አስመልክቶ ሲናገር “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” ይላል። (ሮሜ 5:12) በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎች “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው” በማለት ይናገራሉ። (ሮሜ 6:23) ለኃጢአት የሚከፈለው ቅጣት ሞት እንደመሆኑ መጠን የሲኦልን ትርጉም ለመረዳት መነሳት ያለበት መሠረታዊ ጥያቄ ስንሞት ምን እንሆናለን? የሚለው ነው።
ሕይወት ከሞት በኋላ በአንድ ዓይነት መልክ መኖሩን ይቀጥላል? ሲኦል ምንድን ነው? ወደዚያስ የሚሄዱት እነማን ናቸው? በሲኦል ያሉት ወደፊት ተስፋ ይኖራቸው ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች እውነተኛና አጥጋቢ መልስ ይሰጣል።
ከሞት በኋላ ሕይወት አለን?
ስንሞት በውስጣችን እንደ ነፍስ ወይም መንፈስ ያለ አንድ ነገር ከሥጋችን ተለይቶ በሕይወት መኖሩን ይቀጥላልን? የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕይወት ያገኘው እንዴት እንደሆነ ተመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 2:7) አዳም በሕይወት መኖሩን ለመቀጠል መተንፈስ ቢኖርበትም በአፍንጫው ‘እፍ የተባለበት የሕይወት እስትንፋስ’ በሳንባዎቹ ውስጥ አየር ከማስገባት የበለጠ ነገርን ይጨምራል። አምላክ በአዳም በድን አካል ውስጥ በሁሉም ምድራዊ ፍጥረታት ላይ የሚሠራውን “የሕይወት እስትንፋስ” ማለትም ‘የሕይወት ኃይል’ አስገብቷል ማለት ነው። (ዘፍጥረት 6:17 አ.መ.ት፤ 7:22 NW ) መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ኃይል “መንፈስ” በማለት ይጠራዋል። (ያዕቆብ 2:26 አ.መ.ት ) ይህ መንፈስ አንድን መሣሪያ ወይም ማሽን ከሚያንቀሳቅስና ሥራውን እንዲሠራ ከሚያደርግ ኤሌክትሪክ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ኤሌክትሪኩ የሚያንቀሳቅሰውን መሣሪያ ቅርጽና ባሕርይ ሊወስድ እንደማይችል ሁሉ የሕይወት ኃይልም ሕያው አድርጎ የሚያንቀሳቅሰውን ፍጥረት ባሕርይ ወይም ቅርጽ ሊወስድ አይችልም። ስብዕናም ሆነ የማሰብ ችሎታ የለውም።
ታዲያ አንድ ሰው ሲሞት መንፈሱ ምን ይሆናል? መዝሙር 146:4 [አ.መ.ት ] “መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል” በማለት ይናገራል። አንድ ሰው ሲሞት መንፈሱ መንፈሳዊ ፍጥረት ሆኖ በሌላ ዓለም ውስጥ መኖሩን አይቀጥልም። ከዚህ ይልቅ ‘ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ይመለሳል።’ (መክብብ 12:7 አ.መ.ት ) ይህም የዚያ ግለሰብ የወደፊት ተስፋ የተመካው ሙሉ በሙሉ በአምላክ ላይ ነው ማለት ነው።
ሶቅራጥስ እና ፕላቶ የተባሉት የጥንት ግሪካውያን ዘፍጥረት 2:7 [አ.መ.ት ] አዳም “ሕያው ነፍስ ሆነ” በማለት ይናገራል። አዳም ነፍስ አልተሰጠውም። ከዚህ ይልቅ ራሱ ነፍስ ማለትም ሙሉ ሰው ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎች ነፍስ ልትወለድ፣ ልትጾም፣ ልትጠግብ ወይም ልትራብ፣ ልትደክምና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ሊደርሱባት እንደሚችሉ ያሳያሉ። (ዘፍጥረት 46:18፤ መዝሙር 35:13፤ ምሳሌ 27:7፤ ዮናስ 2:8) አዎን፣ ሰው ራሱ ነፍስ ነው። አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱም ይሞታል።—ሕዝቅኤል 18:4
ፈላስፎች በሰው ውስጥ ያለችው ነፍስ ከሞት ተርፋ በሕይወት መኖሯን ትቀጥላለች የሚል አምነት ነበራቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ ምን ይላል?ታዲያ ሙታን በምን ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ? ይሖዋ በአዳም ላይ ሲፈርድ “አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህ” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 3:19) አምላክ አዳምን ከምድር አፈር አበጅቶ ሕይወት ከመስጠቱ በፊት አዳም የት ይኖር ነበር? አዳም በሕይወት አልነበረም! ስለዚህ አዳም ሲሞት ቀድሞ ወደነበረበት ሕይወት አልባነት ተመልሷል። ሙታን የሚገኙበት ሁኔታ መክብብ 9:5, 10 ላይ በግልጽ ሰፍሯል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ሙታን ግን አንዳች አያውቁም . . . አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙም።” በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሞት የሕይወት ተቃራኒ ነው። ሙታን አንዳች አያውቁም፣ አያስቡም፣ ምንም አይሰማቸውም።
ሲኦል ዘላለማዊ መቃጠያ ነው ወይስ መቃብር?
ሙታን ምንም የማይሰማቸው ከሆነ ሲኦልም ኃጢአተኞች ከሞት በኋላ የሚሰቃዩበት ቦታ ሊሆን አይችልም። ታዲያ ሲኦል ምንድን ነው? ኢየሱስ ከሞተ በኋላ የደረሰበትን ሁኔታ መመርመሩ የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ይረዳል። የመጽሐፍ ቅዱሱ ጸሐፊ ሉቃስ “ነፍሱ [ኢየሱስ] በሲኦል እንዳልቀረ ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ” ተናግሯል። a (ሥራ 2:31) ኢየሱስ እንኳ ሳይቀር የሄደው ወደየትኛው ሲኦል ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሏል:- “የተቀበልኩትን . . . አሳልፌ ሰጠኋችሁ . . . መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፣ ተቀበረም፣ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ።” (1 ቆሮንቶስ 15:3, 4) ስለዚህ ኢየሱስ በሲኦል ማለትም በመቃብር ውስጥ ነበር። ይሁን እንጂ ተነስቶ ወይም ትንሣኤ አግኝቶ ስለነበር እዚያ አልቀረም።
በተጨማሪም ከፍተኛ ሥቃይ የደረሰበትን የጻድቁን የኢዮብን ሁኔታ ተመልከት። ከሥቃዩ ለመገላገል በማሰብ “በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! ቁጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግኸኝ ኖሮ!” በማለት ተማጽኗል። b (ኢዮብ 14:13) ኢዮብ ለመሸሸግ ወደ እሳታማ ሲኦል መሄድ ፈልጎ ነበር ብሎ ማሰብ ምንኛ ስህተት ነው! ለኢዮብ “ሲኦል” ማለት ከሥቃዩ የሚገላገልበት መቃብር ማለት ነው። ስለዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ሲኦል ጥሩም ሆኑ መጥፎ ሰዎች የሚሄዱበት የሰው ልጆች የጋራ መቃብር ነው።
እሳታማ ሲኦል ሙሉ በሙሉ አጥፊ ነው?
የሲኦል እሳት ሙሉ በሙሉ መጥፋትን የሚያመለክት ምሳሌያዊ መግለጫ ይሆን? ቅዱሳን ጽሑፎች በእሳትና በሲኦል ወይም በሐዴስ መካከል ያለውን ልዩነት ሲገልጹ ራእይ 20:14
“ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ” በማለት ይናገራሉ። እዚህ ላይ የተጠቀሰው “ባሕር” ምሳሌያዊ ነው። ምክንያቱም ወደ ውስጡ የተጣሉት ሞትና ሲኦል (ሐዴስ) ቃል በቃል ሊቃጠሉ አይችሉም። “ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።” በሌላ አባባል ምንም ዓይነት ትንሣኤ የሌለው ሞት ነው።—ይህ የእሳት ባሕር ኢየሱስ ‘የገሃነመ እሳት’ ብሎ ከጠራው ጋር ተመሳሳይ ትርጉም አለው። (ማቴዎስ 5:22፤ ማርቆስ 9:47, 48) ገሃነም የሚለው ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ 12 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ የሚገኝ ሲሆን ከኢየሩሳሌም ቅጥር ውጪ ያለውን የሄኖም ሸለቆ ያመለክታል። ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ይህ ሸለቆ “የወንጀለኞች በድንና የእንስሳት ጥምብ እንዲሁም ሁሉም ዓይነት ቆሻሻ የሚጣልበት የከተማዋ ቆሻሻ መጣያ” ሆኖ ያገለግል ነበር። (ስሚዝስ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል) እሳቱ ሁልጊዜ እየነደደ ቆሻሻው እንዲቃጠል ለማድረግ በዚያ ውስጥ ድኝ ይጨመር ነበር። ኢየሱስ ዘላለማዊ ጥፋትን ለማመልከት ይህን ሸለቆ እንደ ምሳሌ አድርጎ መጠቀሙ ተገቢ ነበር።
እንደ ገሃነመ እሳት ሁሉ የእሳት ባሕርም ዘላለማዊ ጥፋትን ያመለክታል። ሞትና ሲኦል ወደ እርሱ ‘ተጥለዋል’ ሲባል የሰው ልጅ ከኃጢአትና ከሞት ኩነኔ ሲላቀቅ እነዚህ ነገሮች በሙሉ ይወገዳሉ ማለት ነው። ሆን ብለው ኃጢአት የሚሠሩና ንስሐ የማይገቡ ሰዎች “ዕድላቸው” በዚህ ባሕር መጣል ይሆናል። (ራእይ 21:8) እነርሱም ጭምር ለዘላለም ይጠፋሉ። በሌላው በኩል ግን አምላክ የሚዘክራቸው በሰው ልጆች የጋራ መቃብር ወይም በሲኦል ውስጥ ያሉት ሙታን አስደናቂ ተስፋ ይጠብቃቸዋል።
ሲኦል ባዶ ሆነ!
ራእይ 20:13 “ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፣ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ” በማለት ይናገራል። አዎን፣ የመጽሐፍ ቅዱሱ ሲኦል ባዶ ይሆናል። ኢየሱስ ቃል እንደገባው ‘በመቃብር ያሉት ሁሉ የኢየሱስን ድምፅ የሚሰሙበትና ከመቃብር የሚወጡበት ሰዓት ይመጣል።’ (ዮሐንስ 5:28, 29) በአሁኑ ጊዜ ሙታን በምንም ዓይነት መልክ በሕይወት እየኖሩ አይደሉም። ሆኖም በይሖዋ አምላክ የሚዘከሩት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሙታን ተመልሳ በምትቋቋመው ምድራዊ ገነት ውስጥ ለመኖር ትንሣኤ ያገኛሉ።—ሉቃስ 23:43፤ ሥራ 24:15
አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ከጽድቅ ሕጎቹ ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ትንሣኤ ያገኙ ሙታን እንደገና አይሞቱም። (ኢሳይያስ 25:8) ይሖዋ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።” በእርግጥም ‘የቀደመው ሥርዓት ያልፋል።’ (ራእይ 21:4) በሲኦል ማለትም “በመታሰቢያ መቃብር ያሉት” ምንኛ አስደናቂ ጊዜ ይጠብቃቸዋል! ይህ በረከት በእርግጥም ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ተጨማሪ እውቀት እንድንቀስም የሚያነሳሳን በቂ ምክንያት ነው።—ዮሐንስ 17:3
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሐዴስ የሚለው ቃል 9 ያህል ጊዜ “ሲኦል” ተብሎ በ1954ቱ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተተርጉሟል። በሉቃስ 16:19-31 ላይ የሚያሠቃይ ነበልባል ተጠቅሶ የሚገኝ ሲሆን መላው ዘገባ ምሳሌያዊ ትርጉም ያዘለ ነው። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ምዕራፍ 88 ተመልከት።
b ሺኦል የሚለው የዕብራይስጥ ቃል በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ 65 ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኝ ሲሆን በ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሲኦል፣” “መቃብር፣” እና “ጥልቅ” ተብሎ ተተርጉሟል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢዮብ በሲኦል ውስጥ መሸሸግ እንዲችል ጸልዮአል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ገሃነመ እሳት የዘላለማዊ ጥፋት ምሳሌ ነው
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉት ሁሉ ይወጣሉ’